በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የወጣቶች ጥያቄ

የጤና ችግር ቢኖርብኝ ምን ላድርግ? (ክፍል 1)

የጤና ችግር ቢኖርብኝ ምን ላድርግ? (ክፍል 1)

 ከከባድ የጤና ችግር ጋር የሚታገል ወጣት ታውቃለህ? አንተስ እኩዮችህ በሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች እንዳትካፈል የሚያግድ በሽታ ወይም የአካል ጉዳት አለብህ?

 ከሆነ አንዳንድ ጊዜ የተስፋ መቁረጥ ስሜት ቢሰማህ የሚያስገርም አይደለም። ይሁን እንጂ ሁለት የሚያጽናኑ ሐሳቦችን መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ማግኘት ትችላለህ።

  •   ፈጣሪህ የሆነው ይሖዋ አምላክ ያለህበትን ሁኔታ ይረዳል። ከዚህም በተጨማሪ ‘ስለ አንተ ያስባል።’​—1 ጴጥሮስ 5:7

  •   ይሖዋ አምላክ ሁሉንም በሽታዎች የማስወገድ ዓላማ አለው! አምላክ የሰጠውን ይህንን ተስፋ ኢሳይያስ 33:24 እና ራእይ 21:1-4 ላይ ማንበብ ትችላለህ።

 ከከባድ የጤና ችግር ጋር እየታገሉ የሚኖሩ በርካታ ወጣቶች በአምላክና እሱ በሰጣቸው ተስፋዎች ላይ ያላቸው እምነት እንዲጸኑ እንደረዳቸው ተገንዝበዋል። እስቲ አራት ወጣቶችን እንደ ምሳሌ እንውሰድ፦

 ዬሚ

 በ11 ዓመቴ ማንኛውንም እንቅስቃሴ ለማድረግ በተሽከርካሪ ወንበር መጠቀም ግድ ሆነብኝ። ትናንሽ ነገሮችን እንደማንሳት ያሉ ቀላል ሥራዎችን እንኳ ማከናወን አልችልም።

 በአምስት ዓመቴ መስኩላር ዲስትሮፊ በሚባል ጡንቻን የሚያዝል በሽታ እንዳለብኝ ታወቀ፤ ይህ በሽታ እየተባባሰ የሚሄድ ሲሆን ብዙ መንቀሳቀስ አልችልም። እኩዮቼ የሚያደርጉትን ማድረግ አለመቻሌ አንዳንድ ጊዜ ተስፋ ያስቆርጠኛል። ይሁን እንጂ ወላጆቼና የጉባኤያችን አባላት አካላዊ፣ ስሜታዊና መንፈሳዊ ድጋፍ ያደርጉልኛል። አሁን የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ነኝ፤ ፍላጎት ያላቸውን ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ለማስጠናት ስሄድ አብዛኛውን ጊዜ የእምነት ባልንጀሮቼ አብረውኝ ይሆናሉ።

 ኢየሱስ እያንዳንዱ ቀን የራሱ የሆኑ የሚያስጨንቁ ነገሮች እንዳሉት ተናግሯል። (ማቴዎስ 6:34) ስለዚህ የማስበው ስለ ዛሬ ብቻ ሲሆን ሊደረስበት የሚችል ግብ አውጥቼ ያን ለማሳካት እጥራለሁ። አምላክ በሚያመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ፣ አቅም ከሚያሳጣው ከዚህ በሽታ የምገላገልበትንና “እውነተኛ የሆነውን ሕይወት” የማገኝበትን ጊዜ በናፍቆት እጠባበቃለሁ።​—1 ጢሞቴዎስ 6:19

ሊታሰብበት የሚገባ ነጥብ፦ ዬሚ “ሊደረስበት የሚችል ግብ” ማውጣት ጠቃሚ እንደሆነ ተገንዝባለች። አንተስ እንዲህ ማድረግ ትችል ይሆን?​—1 ቆሮንቶስ 9:26

 ማቴኦ

 ስድስት ዓመት ሲሞላኝ ጀርባዬን ያምመኝ ጀመር፤ መጀመሪያ ላይ ሐኪሞች ሕመሙ ከዕድገት ጋር ተያይዞ የሚመጣ እንደሆነ ተሰምቷቸው ነበር። ከዓመት በኋላ ግን በአከርካሪዬ ላይ ዕጢ እንዳለ ደረሱበት።

 የቀዶ ሕክምና ያደረግኩ ቢሆንም ሐኪሞቹ ማውጣት የቻሉት 40 በመቶ የሚያህለውን የዕጢውን ክፍል ብቻ ነው። ከሁለት ወራት በኋላ ግን ዕጢው የቀድሞውን መጠን አከለ! ከዚያን ጊዜ ወዲህ ብዙ ምርመራና ብዙ ዓይነት ሕክምና ባደርግም ሁኔታው ተስፋ አስቆራጭ ሆኖብኛል።

 አንዳንድ ጊዜ ዕጢው፣ ሰውነቴን ሁሉ በስለት የተወጋሁ ያህል ሆኖ እንዲሰማኝ ያደርጋል፤ በተለይ ጀርባዬና ደረቴ አካባቢ በጣም ያምመኛል። ያም ቢሆን በችግሬ ላይ ከልክ በላይ ትኩረት አላደርግም። በተጨማሪም አስከፊ ሁኔታዎች ቢያጋጥማቸውም አዎንታዊ አመለካከት ይዘው የቀጠሉ ሰዎች እንዳሉ ለማስታወስ እሞክራለሁ። አዎንታዊ አመለካከት ይዤ እንድቀጥል የረዳኝ ዋነኛው ነገር ግን ይሖዋ አምላክ መከራን ሁሉ ለማስወገድ የገባውን ቃል አንድ ቀን እንደሚፈጽም ያለኝ እምነት ነው።​—ራእይ 21:4

ሊታሰብበት የሚገባ ነጥብ፦ አምላክ መከራን ለማስወገድ በሰጠው ተስፋ ላይ ማሰላሰል ማቴኦን እንደረዳው ሁሉ አንተንም ሊረዳህ የሚችለው እንዴት ነው?​—ኢሳይያስ 65:17

 ብሩነ

 የያዘኝ በሽታ ከውጪ የሚታይ ምልክት ስለሌለው አንዳንድ ሰዎች ሰነፍ እንደሆንኩ ይሰማቸዋል። ይሁን እንጂ የቤት ውስጥ ሥራዎች መሥራት፣ ማንበብ፣ ከአልጋ መነሳትም ሆነ ማንኛውንም ነገር ማከናወን በጣም ይከብደኛል።

 በ16 ዓመቴ መልቲፕል ስክለሮሲስ የተባለ አቅም የሚያሳጣና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የሚሄድ በሽታ እንዳለብኝ ታወቀ፤ በሽታው አንዳንድ ነገሮችን እንዳላከናውን ማገድ ብቻ ሳይሆን በክርስቲያናዊ እንቅስቃሴዎች የምፈልገውን ያህል እንዳልካፈል አድርጎኛል። አንደኛ ጴጥሮስ 5:7ን በተደጋጋሚ አነብብ ነበር፤ ጥቅሱ እንዲህ ይላል፦“የሚያስጨንቃችሁንም ነገር ሁሉ [አምላክ] ላይ ጣሉ፤ ምክንያቱም እሱ ስለ እናንተ ያስባል።” ይሖዋ ለእያንዳንዳችን በግለሰብ ደረጃ እንደሚያስብልን ማወቄ አበረታትቶኛል። ይህ ሐሳብ አሁንም ድረስ ያበረታታኛል።

ሊታሰብበት የሚገባ ነጥብ፦ ብሩነ እንዳደረገችው አንተም የሚያስጨንቁህን ነገሮች በይሖዋ ላይ መጣልህ ምን ጥቅም ያስገኝልሃል?​—መዝሙር 55:22

 አንድሬ

 አንዳንድ ሰዎች የሚያዩኝ እንደ 10 ዓመት ልጅ አድርገው ነው። ለነገሩ አይፈረድባቸውም፤ ምክንያቱም ሲያዩኝ ትንሽ ልጅ ነው የምመስለው።

 ሁለት ዓመት ሲሆነኝ፣ ከአከርካሪ ተነስቶ ወደ አንጎል የሚሄድ ብዙም ያልተለመደ የካንሰር ዓይነት እንዳለብኝ ታወቀ። ሐኪሞች የበሽታውን ስርጭት መቆጣጠር ቢችሉም የወሰድኩት መድኃኒት በዕድገቴ ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል። በአሁኑ ጊዜ ቁመቴ 1.37 ሜትር ብቻ ነው። ብዙ ሰዎች 18 ዓመቴ እንደሆነ ስነግራቸው እየዋሸሁ እንደሆነ ይሰማቸዋል።

 በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ያሉ ሰዎች የሚይዙኝ በአክብሮት ነው። አብሬያቸው የተማርኳቸው ልጆች ያደርጉ እንደነበረው ተንኮል አይሠሩብኝም። ስላለሁበት ሁኔታ አዎንታዊ አመለካከት ለመያዝ እሞክራለሁ። በጣም የሚያስደስተው አንድ ሰው በሕይወቱ ውስጥ ሊያጋጥመው የሚችለው ከሁሉ የተሻለ ነገር እኔንም አጋጥሞኛል፤ ይኸውም ይሖዋን ማወቅ ችያለሁ! ያለሁበት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን ይሖዋ እንደሚንከባከበኝ እርግጠኛ ነኝ። ይሖዋ አምላክ እንደሚያመጣው ቃል ስለገባው ውብ የሆነ አዲስ ዓለም ማሰቤ ደግሞ ብሩህ አመለካከት ይዤ እንድቀጥል ረድቶኛል።​—ኢሳይያስ 33:24

ሊታሰብበት የሚገባ ነጥብ፦ አንድሬ እንደተናገረው፣ “አንድ ሰው በሕይወቱ ውስጥ ሊያጋጥመው የሚችለው ከሁሉ የተሻለ ነገር” ይሖዋን ማወቅ ነው የምንለው ለምንድን ነው?​—ዮሐንስ 17:3