በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የወጣቶች ጥያቄ

ፍቅር ነው ጓደኝነት?—ክፍል 2፦ ምን ዓይነት መልእክት እያስተላለፍኩ ነው?

ፍቅር ነው ጓደኝነት?—ክፍል 2፦ ምን ዓይነት መልእክት እያስተላለፍኩ ነው?

 ጓደኞችሽ ማውራት ሲፈልጉ ጊዜ ሰጥተሽ ልታዋሪያቸው ትፈልጊያለሽ። a ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ከአንድ ጓደኛሽ ጋር ብዙ እያወራችሁ ነው። ችግሩ ጓደኛሽ ወንድ ነው። ‘ከጓደኝነት ያለፈ ቅርበት የለንም’ ብለሽ ታስቢ ይሆናል፤ እሱም ቢሆን እንደዚህ እንደሚሰማው ትገምቻለሽ። ታዲያ ጉዳዩ ሊያሳስብሽ ይገባል?

 ምን ሊፈጠር ይችላል?

 ከጓደኞችሽ አንዳንዶቹ ወንዶች መሆናቸው ስህተት አይደለም። ይሁንና ከሌሎቹ የበለጠ የምትቀርቢው አንድ ልጅ ቢኖርስ? እንደዚያ ከሆነ ልጁ፣ ግንኙነታችሁ ከጓደኝነት ያለፈ እንዲሆን እንደምትፈልጊ ሊሰማው ይችላል።

 አንቺ እንዲህ ዓይነት መልእክት ማስተላለፍ አትፈልጊም? ሆን ብለሽ ባይሆንም እንዲህ ዓይነት መልእክት ልታስተላልፊ የምትችዪው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

 •   ለአንድ ልጅ ከልክ ያለፈ ትኩረት ትሰጫለሽ።

   “እርግጥ የሌላውን ሰው ስሜት መቆጣጠር አትችሉም፤ ሆኖም ከአንድ ሰው ጋር ከጓደኝነት ያለፈ ቅርበት እንደሌላችሁ እየተናገራችሁ ከግለሰቡ ጋር ሁልጊዜ የምትደዋወሉ ከሆነ በእሳት ላይ ነዳጅ እንደ መጨመር ነው።”—ሲየራ

 •   አንድ ልጅ ለአንቺ ትኩረት መስጠቱ እንዳስደሰተሽ ታሳያለሽ።

   “መልእክት መላክ የጀመርኩት እኔ አይደለሁም፤ ሆኖም አንዲት ልጅ በተደጋጋሚ የጽሑፍ መልእክት ስትልክልኝ ሁልጊዜ እመልስላት ነበር። በኋላ ላይ፣ እንደ ጓደኛ ብቻ እንደማያት ማስረዳት ከባድ ሆኖብኝ ነበር።”—ሪቻርድ

 •   የአንድን ልጅ ትኩረት ለመሳብ ትሞክሪያለሽ።

   “አንዳንዶች፣ ማሽኮርመም ጨዋታ ይመስላቸዋል። የፍቅር ግንኙነት የመመሥረት ሐሳብ ሳይኖራቸው በሰው ስሜት ይጫወታሉ። በተደጋጋሚ እንዲህ ዓይነት ነገር ሲፈጠር አይቻለሁ፤ ሁሌም ቢሆን አንደኛው ወገን መጎዳቱ አይቀርም።”—ታማራ

 ዋናው ነጥብ፦ አዘውትረሽ ከአንድ ሰው ጋር የምታወሪና ለየት ያለ ትኩረት የምትሰጪው ከሆነ ለእሱ የፍቅር ስሜት እንዳለሽ የሚጠቁም መልእክት እያስተላለፍሽ ነው።

 ሊያሳስብሽ የሚገባው ለምንድን ነው?

 •   እንዲህ ማድረግ ሌላውን ሰው ይጎዳል።

   መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “የዘገየ ተስፋ ልብን ያሳምማል።” (ምሳሌ 13:12) አንድ ወንድ ለአንቺ የፍቅር ስሜት እንዳለው የሚያሳይ ነገር በተደጋጋሚ ቢያደርግ ምን ብለሽ ተስፋ ልታደርጊ ትችያለሽ?

   “ዓሣ የሚያጠምድ ሰው የያዘውን ዓሣ መንጠቆው ላይ አንጠልጥሎ አይተወውም፤ ወይ ከመንጠቆው አላቆ ይወስደዋል አሊያም ውኃ ውስጥ ይለቀዋል። ከጓደኝነት ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ከአንድ ሰው ጋር የፍቅር ጓደኝነት የመጀመር ሐሳብ ሳይኖራችሁ ‘ልቡን አንጠልጥሎ ማቆየት’ ግለሰቡን በጣም ይጎዳዋል።”—ጄሲካ

 •   ጥሩ ስም እንዳይኖርሽ ያደርጋል።

   መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “ስለ ራሳችሁ ፍላጎት ብቻ ከማሰብ ይልቅ እያንዳንዳችሁ ለሌሎች ሰዎች ፍላጎትም ትኩረት ስጡ።” (ፊልጵስዩስ 2:4) ስለ ራሱ ፍላጎት ብቻ ለሚያስብ ሰው ምን አመለካከት አለሽ? እንዲህ ዓይነቱ ሰው በሌሎች ዘንድ ምን ዓይነት ስም አለው?

   “ሴቶችን የሚያሽኮረምም ወንድ አይማርከኝም። ደግሞም ይህ ድርጊቱ፣ ካገባ በኋላም ቢሆን ታማኝ እንደማይሆን የሚያሳይ ምልክት ሊሆን ይችላል። ስለ ራስህ ጥሩ ስሜት እንዲኖርህ ስትል ሌሎችን ማሽኮርመም ራስ ወዳድነት ነው።”—ጁልያ

 ዋናው ነጥብ፦ የፍቅር ግንኙነት የመመሥረት ሐሳብ ሳይኖራቸው ለሌሎች የፍቅር ስሜት የሚያሳዩ ሰዎች ሌሎችንም ራሳቸውንም ይጎዳሉ።

 ምን ማድረግ ትችያለሽ?

 •   መጽሐፍ ቅዱስ “ወጣት ወንዶችን እንደ ወንድሞች፣ . . . ወጣት ሴቶችን ደግሞ እንደ እህቶች” አድርገን “በፍጹም ንጽሕና” መያዝ እንዳለብን ይናገራል። (1 ጢሞቴዎስ 5:1, 2) በዚህ መሥፈርት የምትመሪ ከሆነ ጓደኞችሽ ከሆኑ ወንዶች ጋር ያለሽ ግንኙነት አይበላሽም።

   “ያገባሁ ብሆን የሌላን ሰው የትዳር ጓደኛ አላሽኮረምምም። ስለዚህ አሁን ሳላገባ ከወንዶች ጋር ባለኝ ግንኙነት ረገድ ጠንቃቃ መሆኔ ለወደፊቱ ይጠቅመኛል።”—ሊያ

 •   መጽሐፍ ቅዱስ “ከቃላት ብዛት ስህተት አይታጣም” ይላል። (ምሳሌ 10:19) ይህ መመሪያ ከንግግር ብቻ ሳይሆን መልእክት ከመጻጻፍ ጋር በተያያዘም ይሠራል፤ ከአንድ ሰው ጋር ምን ያህል እንደምትጻጻፊ እንዲሁም የመልእክቱን ይዘት ልታስቢበት ይገባል።

   “ከአንዲት ልጅ ጋር የፍቅር ግንኙነት የመመሥረት ሐሳብ ከሌለህ በስተቀር በየቀኑ ከእሷ ጋር የምትጻጻፍበት ምክንያት የለም።”—ብራየን

 •   መጽሐፍ ቅዱስ “ከሰማይ የሆነው ጥበብ ግን በመጀመሪያ ንጹሕ ነው” ይላል። (ያዕቆብ 3:17) አንድን ወንድ ያቀፍሽው ሌላ ነገር ሳታስቢ ሊሆን ይችላል፤ በሌላ በኩል ግን ለልጁ የፍቅር ስሜት እንዳለሽ ተደርጎ ሊወሰድም ይችላል።

   “ከወንዶች ጋር በነፃነት ብጨዋወትም ከመጠን በላይ ላለመቀራረብ እጠነቀቃለሁ።”—ማሪያ

 ዋናው ነጥብ፦ ከወንዶች ጋር ያለሽ ቅርርብ ምን ዓይነት እንደሆነ በጥንቃቄ አስቢ። ጄኒፈር የተባለች በአሥራዎቹ ዕድሜ የምትገኝ ልጅ እንዲህ ብላለች፦ “ጥሩ ጓደኞች ማግኘት አስቸጋሪ ነው፤ በመሆኑም ግራ የሚያጋባ መልእክት በማስተላለፍ ጓደኞቻችሁን ማጣት አትፈልጉም።”

 ጠቃሚ ምክር

 •    ሌሎች ሰዎች የሚሰጡትን አስተያየት ልብ ብለሽ ስሚ። አንድ ሰው “ከእገሌ ጋር እየተጠናናችሁ ነው እንዴ?” ብሎ ከጠየቀሽ ይህ ከግለሰቡ ጋር ከልክ በላይ እንደተቀራረብሽ የሚጠቁም ሊሆን ይችላል።

 •    ወንዶች የሆኑ ጓደኞችሽን የምትቀርቢያቸው በተመሳሳይ መንገድ ይሁን። አንዱን ከሌሎቹ በማስበለጥ የተለየ ትኩረት አትስጪው።

 •   የጽሑፍ መልእክት ከመላክ ጋር በተያያዘ ጥንቃቄ አድርጊ፤ ምን ያህል አዘውትረሽ እንደምትላላኪ፣ ምን ዓይነት መልእክት እንደምትልኪ እንዲሁም ምን ሰዓት ላይ እንደምትልኪ አስቢበት። አሊሳ “ተቃራኒ ፆታ ካለው ሰው ጋር እኩለ ሌሊት ላይ መልእክት መላላክ ተገቢ አይደለም” በማለት ተናግራለች።

a ለአጻጻፍ እንዲያመች ሲባል በሴት ፆታ የተጠቀምን ቢሆንም የቀረቡት ነጥቦች ለሁለቱም ፆታዎች ይሠራሉ።