ክፍል 14
አምላክ በነቢያቱ አማካኝነት ተናገረ
ይሖዋ ፍርድን፣ ንጹሕ አምልኮንና ስለ መሲሑ የተሰጠውን ተስፋ በተመለከተ ለሕዝቡ መልእክቶችን እንዲያደርሱ ነቢያትን ሾመ
በእስራኤልና በይሁዳ ነገሥታት ዘመን የአምላክን መልእክት ለሕዝቡ የማስተላለፍ ልዩ ተልእኮ የተሰጣቸው ሰዎች ነበሩ፤ እነዚህ ሰዎች ነቢያት ይባላሉ። ነቢያት የአምላክን መልእክት የሚያውጁ አስገራሚ እምነትና ድፍረት የነበራቸው ሰዎች ናቸው። የአምላክ ነቢያት በተናገሯቸው ትንቢቶች ውስጥ የሚገኙትን አራት ዋና ዋና ጭብጦች እንመልከት።
1. የኢየሩሳሌም ጥፋት። የአምላክ ነቢያት በተለይም ኢሳይያስና ኤርምያስ፣ ኢየሩሳሌም እንደምትጠፋና ባድማ ሆና እንደምትቆይ ከረጅም ጊዜ በፊት ማስጠንቀቅ ጀምረው ነበር። እነዚህ ነቢያት አምላክ በዚህች ከተማ ላይ የተቆጣበትን ምክንያት በግልጽ ተናግረዋል። የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ይሖዋን እንደሚወክሉ ቢናገሩም ይህ እውነት አለመሆኑን በከተማዋ ውስጥ የሚፈጸሙት ከሐሰት ሃይማኖት ጋር የተያያዙ ልማዶችና የዓመፅ ድርጊቶች እንዲሁም የሕዝቡ ምግባረ ብልሹነት ያረጋግጡ ነበር።—2 ነገሥት 21:10-15፤ ኢሳይያስ 3:1-8, 16-26፤ ኤርምያስ 2:1 እስከ 3:13
2. የንጹሕ አምልኮ እንደገና መቋቋም። የአምላክ ሕዝቦች ለ70 ዓመታት በግዞት ከቆዩ በኋላ ከባቢሎን ነፃ ይወጣሉ። ሕዝቡ ባድማ ወደሆነው የትውልድ አገራቸው ተመልሰው በኢየሩሳሌም የይሖዋን ቤተ መቅደስ እንደገና ይሠራሉ። (ኤርምያስ 46:27፤ አሞጽ 9:13-15) ባቢሎንን ድል የሚያደርገውና የአምላክ ሕዝቦች ንጹሑን አምልኮ መልሰው እንዲያቋቁሙ የሚፈቅድላቸው ቂሮስ የተባለ ንጉሥ እንደሆነ ኢሳይያስ ከ200 ዓመታት በፊት ትንቢት ተናግሮ ነበር። ኢሳይያስ፣ ቂሮስ የሚጠቀምበትን ለየት ያለ የጦር ስልትም ጭምር በዝርዝር ተናግሯል።—ኢሳይያስ 44:24 እስከ 45:3
3. የመሲሑ መምጣትና የሚደርሱበት ነገሮች። መሲሑ በቤተልሔም ከተማ ይወለዳል። (ሚክያስ 5:2) እሱም ትሑት በመሆን በአህያ ላይ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም ይመጣል። (ዘካርያስ 9:9) መሲሑ ገርና ደግ ቢሆንም በሰዎች ዘንድ ይጠላል፤ እንዲሁም ብዙዎች አይቀበሉትም። (ኢሳይያስ 42:1-3፤ 53:1, 3) መሲሑ ጭካኔ በተሞላበት መንገድ ይገደላል። ታዲያ የመሲሑ ሕይወት በዚሁ አበቃ ማለት ነው? አይደለም፣ ምክንያቱም መሥዋዕት ሆኖ የሚሞተው ለብዙዎች የኃጢአት ይቅርታ ለማስገኘት ነው። (ኢሳይያስ 53:4, 5, 9-12) ይህ እንዲሆን ደግሞ ትንሣኤ ማግኘት አለበት።
4. መሲሑ ምድርን ሲገዛ የሚኖረው ሁኔታ። ፍጽምና የጎደላቸው ሰዎች ሰላም በሰፈነበት ሁኔታ ራሳቸውን ማስተዳደር ፈጽሞ አይችሉም፤ መሲሐዊው ንጉሥ ግን የሰላም ልዑል ተብሎ ይጠራል። (ኢሳይያስ 9:6, 7፤ ኤርምያስ 10:23) በእሱ አገዛዝ ሥር ሁሉም ሰዎች እርስ በርሳቸውም ሆነ ከሁሉም እንስሳት ጋር በሰላም ይኖራሉ። (ኢሳይያስ 11:3-7) በሽታ ይወገዳል። (ኢሳይያስ 33:24) ሞትም እንኳ ሳይቀር ለዘላለም ይዋጣል። (ኢሳይያስ 25:8) በመሲሑ ግዛት ወቅት፣ ሞተው የነበሩ ሰዎች እንደገና ትንሣኤ አግኝተው በምድር ላይ ይኖራሉ።—ዳንኤል 12:13
—በኢሳይያስ፣ በኤርምያስ፣ በዳንኤል፣ በአሞጽ፣ በሚክያስ እና በዘካርያስ መጻሕፍት ላይ የተመሠረተ።