አሞጽ 1:1-15
1 በይሁዳ ንጉሥ በዖዝያና+ በእስራኤል ንጉሥ በዮአስ+ ልጅ በኢዮርብዓም+ ዘመን፣ የመሬት መንቀጥቀጡ+ ከመከሰቱ ከሁለት ዓመት በፊት በተቆአ+ ከነበሩት በግ አርቢዎች መካከል አንዱ ለሆነው ለአሞጽ* ስለ እስራኤል በራእይ የተገለጠለት ቃል።
2 እሱ እንዲህ ብሏል፦
“ይሖዋ ከጽዮን እንደ አንበሳ ያገሳል፤ከኢየሩሳሌምም ድምፁን በኃይል ያሰማል።
የእረኞቹ ማሰማሪያዎች ያለቅሳሉ፤የቀርሜሎስም አናት ይደርቃል።”+
3 “ይሖዋ እንዲህ ይላል፦‘“ስለ ሦስቱ የደማስቆ ዓመፅ* ብሎም ስለ አራቱ እጄን አልመልስም፤ምክንያቱም በብረት ማሄጃ ጊልያድን ወቅተዋል።+
4 በመሆኑም በሃዛኤል+ ቤት ላይ እሳት እሰዳለሁ፤የቤንሃዳድንም የማይደፈሩ ማማዎች ይበላል።+
5 የደማስቆን በሮች መቀርቀሪያ እሰብራለሁ፤+የቢቃትአዌን ነዋሪዎችን አጠፋለሁ፤በቤትኤደን ተቀምጦ የሚገዛውን* አስወግዳለሁ፤የሶርያ ሰዎችም ወደ ቂር በግዞት ይሄዳሉ”+ ይላል ይሖዋ።’
6 ይሖዋ እንዲህ ይላል፦‘“ስለ ሦስቱ የጋዛ ዓመፅ+ ብሎም ስለ አራቱ እጄን አልመልስም፤ምክንያቱም ሕዝቡን ሁሉ ማርከው+ ለኤዶም አሳልፈው ሰጥተዋል።
7 በመሆኑም በጋዛ ቅጥር ላይ እሳት እሰዳለሁ፤+የማይደፈሩ ማማዎቿንም ይበላል።
8 የአሽዶድን ነዋሪዎች አጠፋለሁ፤+በአስቀሎን ተቀምጦ የሚገዛውንም* አስወግዳለሁ፤+እጄን በኤቅሮን ላይ እዘረጋለሁ፤+የተረፉት ፍልስጤማውያንም ይጠፋሉ”+ ይላል ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ።’
9 ይሖዋ እንዲህ ይላል፦‘ስለ ሦስቱ የጢሮስ ዓመፅ+ ብሎም ስለ አራቱ እጄን አልመልስም፤ምክንያቱም ሕዝቡን ሁሉ ማርከው ለኤዶም አሳልፈው ሰጥተዋል፤ደግሞም የወንድማማቾችን ቃል ኪዳን አላስታወሱም።+
10 በመሆኑም በጢሮስ ቅጥር ላይ እሳት እሰዳለሁ፤የማይደፈሩ ማማዎቿንም ይበላል።’+
11 ይሖዋ እንዲህ ይላል፦‘ስለ ሦስቱ የኤዶም ዓመፅ+ ብሎም ስለ አራቱ እጄን አልመልስም፤ምክንያቱም የገዛ ወንድሙን በሰይፍ አሳዷል፤+ምሕረት ለማሳየትም እንቢተኛ ሆኗል፤በቁጣው ያላንዳች ፋታ ይዘነጣጥላቸዋል፤አሁንም ቢሆን በእነሱ ላይ ቁጣው አልበረደም።+
12 በመሆኑም በቴማን+ ላይ እሳት እሰዳለሁ፤የቦስራንም የማይደፈሩ ማማዎች ይበላል።’+
13 “ይሖዋ እንዲህ ይላል፦‘“ስለ ሦስቱ የአሞናውያን ዓመፅ+ ብሎም ስለ አራቱ እጄን አልመልስም፤ምክንያቱም ግዛታቸውን ለማስፋት ሲሉ የጊልያድን ነፍሰ ጡር ሴቶች ሆድ ቀደዋል።+
14 በመሆኑም በራባ ቅጥር ላይ እሳት እሰዳለሁ፤+የማይደፈሩ ማማዎቿንም ይበላል፤በውጊያው ቀን ቀረርቶ ይሰማል፤አውሎ ነፋስ በሚነሳበትም ቀን ነውጥ ይኖራል።
15 ንጉሣቸውም ከመኳንንቱ ጋር በግዞት ይወሰዳል”+ ይላል ይሖዋ።’

