በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ክፍል 2

በገነት ውስጥ የመኖር መብት አጡ

በገነት ውስጥ የመኖር መብት አጡ

አዳምና ሔዋን የተባሉት የመጀመሪያዎቹ ወንድና ሴት የአምላክን አገዛዝ እንዳይቀበሉ አንድ ዓመፀኛ መልአክ ገፋፋቸው። በዚህም ምክንያት የሰው ዘር ኃጢአትና ሞትን ወረሰ

አምላክ ሰዎችን ከመፍጠሩ ከረጅም ጊዜ በፊት በዓይን የማይታዩ በርካታ መንፈሳዊ ፍጥረታትን ማለትም መላእክትን ፈጥሮ ነበር። በኤደን ውስጥ አንድ ዓመፀኛ መልአክ፣ አምላክ ከከለከለው ፍሬ እንድትበላ ሔዋንን ለማሳሳት ጥረት አደረገ፤ ይህ መልአክ ከጊዜ በኋላ ሰይጣን ዲያብሎስ ተብሎ ተጠርቷል።

ሰይጣን በእባብ በመጠቀም፣ አምላክ እነዚህን ባልና ሚስት አንድ ጠቃሚ ነገር እንደነፈጋቸው የሚጠቁም ሐሳብ ተናገረ። ይህ መልአክ ለሔዋን እሷና ባሏ ከተከለከለው ፍሬ ቢበሉ እንደማይሞቱ ነገራት። በዚህ መንገድ ሰይጣን፣ ፈጣሪ ሰብዓዊ ልጆቹን እንደዋሻቸው በመግለጽ አምላክን ወነጀለው። ይህ አታላይ፣ አምላክን አለመታዘዝ ልዩ የሆነ የእውቀት ብርሃንና ነፃነት እንደሚያስገኝ አስመስሎ አቀረበላቸው። ይሁን እንጂ የተናገረው ነገር ሁሉ ውሸት ነበር፤ እንዲያውም በምድር ላይ የተነገረው የመጀመሪያው ውሸት ይህ ነው። ሰይጣን ያነሳው ጉዳይ በዋነኝነት ከአምላክ ሉዓላዊነት ወይም የበላይ ገዥነት ጋር የተያያዘ ነበር፤ ሰይጣን የአምላክን የመግዛት መብት በተመለከተ ጥያቄ ያነሳ ከመሆኑም ሌላ ይሖዋ የሚገዛው ጽድቅ በሰፈነበትና ተገዢዎቹን በሚጠቅም መንገድ መሆኑ አጠያያቂ እንዲሆን አደረገ።

ዘሩ “ራስህን ይቀጠቅጣል፤ አንተም ተረከዙን ትቀጠቅጣለህ።” ዘፍጥረት 3:15

ሔዋን የሰይጣንን ውሸት ስላመነች ፍሬውን መመኘት ጀመረች፤ ከዚያም ፍሬውን ቀጥፋ በላች። በኋላም ለባሏ ሰጠችውና እሱም አብሯት በላ። በዚህ መንገድ ሁለቱም ኃጢአተኞች ሆኑ። ቀላል የሚመስለው ይህ ድርጊታቸው በአምላክ ላይ እንዳመፁ የሚያሳይ ነበር። አዳምና ሔዋን ሆን ብለው አምላክን ላለመታዘዝ በመምረጣቸው ፍጹም ሕይወትን ጨምሮ ሁሉንም ነገር የሰጣቸውን የፈጣሪያቸውን አገዛዝ ለመቀበል አሻፈረን አሉ።

በመሆኑም አምላክ በእነዚህ ዓመፀኞች ላይ የፍርድ ውሳኔ አስተላለፈ። ይሖዋ፣ በእባብ ተመስሎ የቀረበውን ሰይጣንን የሚያጠፋ ዘር ወይም አዳኝ እንደሚመጣ ተስፋ ሰጠ። አምላክ በአዳምና በሔዋን ላይ የሞት ፍርድ የሚፈጸምበትን ጊዜ በማዘግየት ገና ላልተወለዱት ዘሮቻቸው ምሕረት አሳይቷል። ተስፋ የተሰጠበት ዘር፣ በኤደን የተነሳው ዓመፅ ያስከተላቸውን አሳዛኝ መዘዞች ሁሉ ስለሚያስወግድ አዳምና ሔዋን የሚወልዷቸው ልጆች ተስፋ ይኖራቸዋል። አምላክ ወደፊት ከሚመጣው ከዚህ አዳኝ ጋር በተያያዘ ያለው ዓላማ እንዴት እንደሚፈጸምና ይህ አዳኝ ማን እንደሚሆን የተገለጸው በጊዜ ሂደት ነበር፤ የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ሲጻፉ ይህ ሐሳብ ቀስ በቀስ ግልጽ እየሆነ ሄደ።

አምላክ አዳምንና ሔዋንን ከገነት አስወጣቸው። አዳምና ሔዋን ከኤደን ገነት ውጪ ሲኖሩ የሚያስፈልጋቸውን ነገር አርሰው ለማግኘት ብዙ መጣርና መልፋት ነበረባቸው። ከጊዜ በኋላ ሔዋን አረገዘችና የመጀመሪያ ልጃቸው የሆነውን ቃየንን ወለደች። ባልና ሚስቱ አቤልንና የኖኅ ቅድመ አያት የሆነውን ሴትን ጨምሮ ሌሎች ወንዶችና ሴቶች ልጆችም ወልደዋል።

በዘፍጥረት ምዕራፍ 3 እስከ ምዕራፍ 5 እና በራእይ 12:9 ላይ የተመሠረተ።