ክፍል 13
ጥሩ እና መጥፎ ነገሥታት
የእስራኤል ብሔር ለሁለት ተከፈለ። ዘመን አልፎ ዘመን ሲተካ ብዙ ነገሥታት በእስራኤል የገዙ ሲሆን አብዛኞቹ ታማኞች አልሆኑም። ባቢሎናውያን ኢየሩሳሌምን አጠፏት
ሰለሞን ንጹሑን አምልኮ ከተወ በኋላ ይሖዋ አስቀድሞ እንደተናገረው የእስራኤል ብሔር ተከፈለ። የሰለሞን ልጅ የሆነውና ከእሱ በኋላ የነገሠው ሮብዓም ጨቋኝ ንጉሥ ነበር። በዚህም የተነሳ አሥሩ የእስራኤል ነገዶች በሮብዓም ላይ ዓምፀው ሰሜናዊውን የእስራኤል መንግሥት አቋቋሙ። የተቀሩት ሁለት ነገዶች ደግሞ በዳዊት የዘር ሐረግ ለመጣውና በኢየሩሳሌም ሆኖ ለሚገዛው ንጉሥ ታማኞች በመሆን ደቡባዊውን የይሁዳ መንግሥት መሠረቱ።
የሁለቱም መንግሥታት አገዛዝ ሁከት የነገሠበት ሲሆን ለዚህም ዋነኛው ምክንያት ነገሥታቶቻቸው እምነተ ቢስ መሆናቸውና አምላክን አለመታዘዛቸው ነበር። የሰሜናዊው የእስራኤል መንግሥት ነገሥታት ከመጀመሪያው አንስቶ የሐሰት አምልኮን በማራመዳቸው በዚያ የነበረው ሁኔታ ከይሁዳ መንግሥትም የከፋ ነበር። እንደ ኤልያስና ኤልሳዕ ያሉት ነቢያት፣ ሙታንን ማስነሳትን ጨምሮ ታላላቅ ተአምራትን ቢፈጽሙም ሕዝቡ በተደጋጋሚ ጊዜ ወደ መጥፎ አካሄዱ ይመለስ ነበር። በመጨረሻም አምላክ፣ አሦራውያን ሰሜናዊውን መንግሥት እንዲያጠፉት ፈቀደ።
ሰሜናዊው የእስራኤል መንግሥት ከጠፋ በኋላ የይሁዳ መንግሥት ከመቶ ዓመት ለሚበልጥ ጊዜ መቆየት ቢችልም ከአምላክ ቅጣት አላመለጠም። የአምላክ ነቢያት የሰጡትን ማስጠንቀቂያ ሰምተው ብሔሩ ወደ ይሖዋ እንዲመለስ ለማድረግ የሞከሩት ጥቂት የይሁዳ ነገሥታት ብቻ ነበሩ። ለምሳሌ ያህል፣ ንጉሥ ኢዮስያስ ይሁዳን ከሐሰት አምልኮ ማጽዳት የጀመረ ከመሆኑም በላይ የይሖዋን ቤተ መቅደስ አድሶ ነበር። በሙሴ በኩል የተሰጠው የአምላክ ሕግ የመጀመሪያው ቅጂ በተገኘ ጊዜ ኢዮስያስ በሕጉ ላይ በሰፈረው መልእክት ልቡ በጥልቅ ስለተነካ የሐሰት አምልኮን ለማስወገድ የጀመረውን ዘመቻ ይበልጥ አጠናከረው።
የሚያሳዝነው ግን ከኢዮስያስ በኋላ የገዙት ነገሥታት የዚህን ንጉሥ መልካም አርዓያ አልተከተሉም። በመሆኑም ይሖዋ፣ የባቢሎን መንግሥት ይሁዳን ድል በማድረግ ኢየሩሳሌምንና ቤተ መቅደሷን እንዲያጠፋ ፈቀደ። ከጥፋቱ የተረፉት ሰዎች በምርኮ ወደ ባቢሎን ተጋዙ። አምላክ፣ ሕዝቡ ለ70 ዓመታት በግዞት እንደሚቆይ ትንቢት ተናግሮ ነበር። ይሖዋ አስቀድሞ ቃል በገባው መሠረት ብሔሩ እንደገና ወደገዛ ምድሩ እንዲመለስ እስኪፈቀድለት ድረስ በእነዚያ ሁሉ ዓመታት ይሁዳ ባድማ ሆና ቆየች።
ከዚያ በኋላም ቢሆን ተስፋ የተሰጠበት አዳኝ ማለትም በትንቢት አስቀድሞ የተነገረለት መሲሕ መግዛት እስኪጀምር ድረስ ከዳዊት የዘር ሐረግ የሚነሱ ነገሥታት አይኖሩም። በኢየሩሳሌም ውስጥ በዳዊት ዙፋን ላይ ከተቀመጡት ነገሥታት በአብዛኞቹ አገዛዝ እንደታየው ፍጽምና የጎደላቸው ሰዎች ለመግዛት ብቃት የላቸውም። ለመግዛት ትክክለኛ ብቃት ያለው መሲሑ ብቻ ነው። በመሆኑም ይሖዋ መሲሑን በተመለከተ እንዲህ ብሏል፦ “በያዕቆብ ቤትም ላይ ለዘላለም ንጉሥ ሆኖ ይገዛል፤ መንግሥቱም መጨረሻ የለውም።”—ሉቃስ 1:33
—በ1 ነገሥት፤ በ2 ነገሥት፤ በ2 ዜና መዋዕል ምዕራፍ 10 እስከ ምዕራፍ 36 እንዲሁም በኤርምያስ 25:8-11 ላይ የተመሠረተ።