በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ክፍል 6

ኢዮብ ንጹሕ አቋሙን ጠበቀ

ኢዮብ ንጹሕ አቋሙን ጠበቀ

ሰይጣን የኢዮብን ንጹሕ አቋም በተመለከተ በአምላክ ፊት ጥያቄ አነሳ፤ ይሁን እንጂ ኢዮብ እስከ መጨረሻው ለይሖዋ ታማኝ ሆነ

መታዘዝ ምንም ዓይነት ቁሳዊ ጥቅም የማያስገኝ በሚመስልበት ሁኔታ ውስጥ በጣም ከባድ ፈተና ቢደርስበት ለአምላክ ታማኝ የሚሆን ሰው ይኖራል? ኢዮብ ከተባለ ሰው ጋር በተያያዘ ይህ ጥያቄ ተነስቶ የነበረ ሲሆን መልስም አግኝቷል።

እስራኤላውያን ገና በግብፅ ሳሉ፣ የአብርሃም ዘመድ የነበረው ኢዮብ ዛሬ የዓረብ አገሮች በሚገኙበት አካባቢ ይኖር ነበር። በዚህ ጊዜ በሰማይ ያሉት መላእክት በአምላክ ፊት ተሰብስበው ሳሉ ዓመፀኛው ሰይጣንም በመካከላቸው ተገኘ። በሰማይ በተደረገው በዚህ ስብሰባ ላይ ይሖዋ በታማኝ አገልጋዩ በኢዮብ እንደሚተማመንበት ገለጸ። እንዲያውም ይሖዋ በምድር ላይ እንደ ኢዮብ ያለ ታማኝ ሰው እንደሌለ ተናገረ። ይሁን እንጂ ሰይጣን፣ ኢዮብ አምላክን የሚያገለግለው ስለባረከውና ጥበቃ ስላደረገለት እንደሆነ ገለጸ። ሰይጣን፣ ኢዮብ ያለውን ነገር ሁሉ ቢያጣ አምላክን እንደሚሰድብ ተናገረ።

በመሆኑም አምላክ፣ ሰይጣን በመጀመሪያ የኢዮብን ሀብትና ልጆቹን ቀጥሎም ጤንነቱን እንዲያሳጣው ፈቀደለት። ኢዮብ ከደረሰበት ነገር ሁሉ በስተጀርባ ያለው ሰይጣን መሆኑን ስላላወቀ አምላክ ይህ ሁሉ መከራ እንዲደርስበት የፈቀደው ለምን እንደሆነ ሊገባው አልቻለም። ያም ቢሆን ኢዮብ በፍጹም አምላክን አልተሳደበም።

በዚህ ወቅት፣ የኢዮብ ወዳጆች ነን የሚሉ ሦስት ሰዎች ወደ እሱ መጡ። በኢዮብ መጽሐፍ ውስጥ ሰፍሮ እንደሚገኘው እነዚህ ሰዎች፣ ኢዮብ በስውር በፈጸማቸው ኃጢአቶች የተነሳ አምላክ እየቀጣው መሆኑን ለማሳመን ተራ በተራ ጥረት አደረጉ፤ በእርግጥ ያቀረቡት ሐሳብ የተሳሳተ ነበር። ሦስቱ ሰዎች ይባስ ብለው አምላክ በአገልጋዮቹ ደስ እንደማይሰኝና በእነሱ እንደማይተማመን ተናገሩ። ኢዮብ እነዚህ ሰዎች ያቀረቡትን የተሳሳተ ሐሳብ አልተቀበለውም። ኢዮብ እስከ ሞት ድረስ ንጹሕ አቋሙን ጠብቆ እንደሚኖር በእርግጠኝነት ገለጸ!

ይሁን እንጂ ኢዮብ፣ ንጹሕ መሆኑን በማረጋገጥ ላይ ከመጠን ያለፈ ትኩረት በማድረጉ ስህተት ፈጽሟል። በኢዮብና በጓደኞቹ መካከል የተደረገው ክርክር ተጀምሮ እስኪያበቃ ሲያዳምጥ የቆየ ኤሊሁ የሚባል ወጣት በመጨረሻ ሐሳቡን ተናገረ። የይሖዋ ሉዓላዊነት መረጋገጡ የማንም ሰው ትክክለኛነት ከመረጋገጡ ይበልጥ ትልቅ ቦታ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ እንደሆነ ኢዮብ ሳይገነዘብ በመቅረቱ ኤሊሁ ገሠጸው። ኤሊሁ ለኢዮብ የሐሰት ወዳጆችም ጠንከር ያለ ተግሣጽ ሰጣቸው።

ከዚያም ይሖዋ አምላክ፣ ለኢዮብ እርማት በመስጠት አስተሳሰቡን እንዲያስተካክል ረዳው። ይሖዋ፣ አስደናቂ የሆኑ በርካታ የፍጥረት ሥራዎችን በመጥቀስ ከአምላክ ታላቅነት ጋር ሲወዳደር ሰው ኢምንት መሆኑን ኢዮብ እንዲገነዘብ አደረገ። ኢዮብም አምላክ የሰጠውን እርማት በትሕትና ተቀበለ። ይሖዋ “ከአንጀት የሚራራና መሐሪ” በመሆኑ ለኢዮብ ጤንነቱን የመለሰለት ሲሆን ሀብቱንም ከበፊቱ እጥፍ አድርጎ ሰጠው፤ እንዲሁም አሥር ልጆች በመስጠት ባረከው። (ያዕቆብ 5:11) ኢዮብ ከባድ ፈተና ቢደርስበትም ንጹሕ አቋሙን ጠብቆ ከይሖዋ ጎን በመቆሙ፣ ሰዎች ፈተና ሲደርስባቸው ለአምላክ ታማኝ እንደማይሆኑ ሰይጣን ለሰነዘረው ክስ አጥጋቢ መልስ ሰጥቷል።

በኢዮብ መጽሐፍ ላይ የተመሠረተ።