በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ክፍል 19

ኢየሱስ መላውን ዓለም የሚነካ ትንቢት ተናገረ

ኢየሱስ መላውን ዓለም የሚነካ ትንቢት ተናገረ

ኢየሱስ፣ በንጉሣዊ ሥልጣኑ መገኘቱንና የዚህ ሥርዓት መደምደሚያ መቅረቡን የሚጠቁሙ ምልክቶችን ተናገረ

ኢየሱስ፣ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ኢየሩሳሌምንና ቤተ መቅደሷን ቁልቁል ማየት በሚቻልበት ቦታ ተቀምጦ ሳለ ከሐዋርያቱ መካከል አራቱ ለብቻቸው ወደ እሱ ቀርበው ቀደም ሲል ስለተናገረው ነገር ጠየቁት። ኢየሱስ በኢየሩሳሌም የሚገኘው ቤተ መቅደስ እንደሚጠፋ ተናግሮ ነበር። ከዚያ ቀደም ብሎ በሌላ ጊዜ ደግሞ ‘ስለዚህ ሥርዓት መደምደሚያ’ ገልጾ ነበር። (ማቴዎስ 13:40, 49) በዚህ ወቅት ሐዋርያቱ “የመገኘትህና የዚህ ሥርዓት መደምደሚያ ምልክትስ ምንድን ነው?” ብለው ጠየቁት።—ማቴዎስ 24:3

ኢየሱስ ለሐዋርያቱ በሰጠው መልስ ላይ ኢየሩሳሌም ከመጥፋቷ በፊት ስለሚፈጸሙ ነገሮች ገልጾ ነበር። ይሁን እንጂ የተናገረው ነገር ኢየሩሳሌም ከጠፋች በኋላ ወደፊት የሚፈጸሙትን ክንውኖችም ያመለክታል። ኢየሱስ የተናገረው ትንቢት ከጊዜ በኋላ በመላው ዓለም ላይ ታላቅ ፍጻሜ ይኖረዋል። ኢየሱስ ወደፊት በዓለም ላይ ስለሚፈጸሙ ሁኔታዎችና ክስተቶች ትንቢት ተናግሯል፤ እነዚህ ሁሉ ክንውኖች በአንድ ላይ ተጣምረው መፈጸማቸው ኢየሱስ በሰማይ ንጉሥ ሆኖ የሚገኝበት ጊዜ መጀመሩን በምድር ላይ ለሚኖሩ ሰዎች ምልክት ይሆናቸዋል። በሌላ አነጋገር ይህ ምልክት፣ ይሖዋ አምላክ ኢየሱስን ከረጅም ጊዜ በፊት ተስፋ የተሰጠበት መሲሐዊ መንግሥት ንጉሥ እንዳደረገው ይጠቁማል። ይህ ምልክት የአምላክ መንግሥት ክፋትን የሚያስወግድበትና ለሰው ልጆች እውነተኛ ሰላም የሚያመጣበት ጊዜ መቅረቡንም ያሳያል። በመሆኑም ኢየሱስ የተነበያቸው ነገሮች፣ አሁን ያለውን ሃይማኖታዊና ፖለቲካዊ እንዲሁም ማኅበራዊ ሥርዓት ያቀፈው አሮጌው ሥርዓት በመጨረሻው ቀን ላይ እንደሚገኝና አዲስ ሥርዓት የሚጀምርበት ጊዜ እንደቀረበ ያመለክታሉ።

ኢየሱስ በሰማይ ንጉሥ ሆኖ በሚገኝበት ጊዜ በምድር ላይ የሚፈጸሙትን ነገሮች ሲገልጽ ዓለም አቀፍ ጦርነቶች፣ የምግብ እጥረትና ታላላቅ የምድር መናወጦች እንደሚኖሩ እንዲሁም በብዙ ቦታዎች በሽታ እንደሚስፋፋ ተናግሯል። ሕገ ወጥነት ይስፋፋል። የኢየሱስ እውነተኛ ደቀ መዛሙርት የአምላክን መንግሥት ምሥራች በመላው ምድር ላይ ይሰብካሉ። እነዚህ ሁሉ ነገሮች እስከዛሬ ድረስ ሆኖ በማያውቅ “ታላቅ መከራ” ይደመደማሉ።—ማቴዎስ 24:21

ታዲያ የኢየሱስ ተከታዮች ይህ መከራ መቅረቡን የሚያውቁት እንዴት ነው? ኢየሱስ “የበለስን ዛፍ እንደ ምሳሌ በመውሰድ . . . ተማሩ” ብሏል። (ማቴዎስ 24:32) የበለስ ቅጠሎች በዛፉ ቅርንጫፎች ላይ ማቆጥቆጣቸው በጋ መቅረቡን የሚያሳይ ምልክት ነው። በተመሳሳይም ኢየሱስ በትንቢት የተናገራቸው ነገሮች በሙሉ በአንድ ወቅት ላይ መፈጸማቸው መጨረሻው መቅረቡን የሚያሳይ ግልጽ ምልክት ይሆናል። እርግጥ ነው፣ ታላቁ መከራ የሚጀምርበትን ትክክለኛ ቀንና ሰዓት ከአብ በቀር የሚያውቅ የለም። በመሆኑም ኢየሱስ “የተወሰነው ጊዜ መቼ እንደሆነ ስለማታውቁ . . . ዘወትር ነቅታችሁ ጠብቁ” በማለት ደቀ መዛሙርቱን መክሯቸዋል።—ማርቆስ 13:33

በማቴዎስ ምዕራፍ 24 እና 25፤ በማርቆስ ምዕራፍ 13 እንዲሁም በሉቃስ ምዕራፍ 21 ላይ የተመሠረተ።

^ አን.14 ኢየሱስ የተናገረውን ትንቢት በተመለከተ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ መጽሐፍ ምዕራፍ 9 ተመልከት።