በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ክፍል 5

አምላክ አብርሃምንና ቤተሰቡን ባረካቸው

አምላክ አብርሃምንና ቤተሰቡን ባረካቸው

የአብርሃም ዘሮች እየበለጸጉ ሄዱ። አምላክ በግብፅ ምድር ለዮሴፍ ጥበቃ አደረገለት

ይሖዋ፣ እጅግ የሚወደው ልጁ አንድ ቀን ተሠቃይቶ መሞት እንደሚኖርበት ያውቅ ነበር። በዘፍጥረት 3:15 ላይ የተመዘገበው ትንቢት ይህን ሐቅ ጠቁሟል። አምላክ፣ የልጁ ሞት ምን ያህል ከባድ መሥዋዕትነት እንደሚጠይቅበት የሰው ዘር እንዲገነዘብ ማድረግ ይችል ይሆን? መጽሐፍ ቅዱስ ሕያው የሆነ ምሳሌ ይሰጠናል። አብርሃም ውድ ልጁን ይስሐቅን መሥዋዕት አድርጎ እንዲያቀርብ አምላክ ጠየቀው።

አብርሃም ታላቅ እምነት ነበረው። አምላክ፣ አስቀድሞ የተነገረለት አዳኝ ወይም ዘር በይስሐቅ የዘር ሐረግ በኩል እንደሚመጣ ለአብርሃም ቃል እንደገባለት አስታውስ። አብርሃም አስፈላጊ ከሆነ አምላክ ይስሐቅን ከሞት እንደሚያስነሳው በመተማመን በታዛዥነት ልጁን መሥዋዕት አድርጎ ለማቅረብ ተዘጋጅቶ ነበር። ይሁን እንጂ ልክ በዚያ ሰዓት፣ ከአምላክ የተላከ አንድ መልአክ አብርሃም ልጁን መሥዋዕት እንዳያደርግ ከለከለው። አምላክ፣ አብርሃም ውድ ልጁን ለመስጠት ፈቃደኛ በመሆኑ ካመሰገነው በኋላ ቀደም ሲል ለዚህ ታማኝ ሰው ገብቶለት የነበረውን ቃል ኪዳን እንደገና አደሰለት።

ይስሐቅ ከጊዜ በኋላ ኤሳውና ያዕቆብ የሚባሉ ሁለት ወንዶች ልጆችን ወለደ። ከኤሳው በተለየ መልኩ ያዕቆብ መንፈሳዊ ነገሮችን ያደንቅ ስለነበረ ተባርኳል። አምላክ የያዕቆብን ስም እስራኤል ብሎ የለወጠው ሲሆን 12 ወንዶች ልጆቹ በእስራኤል ብሔር ውስጥ ያሉት ነገዶች አለቆች ሆኑ። ይሁን እንጂ ይህ ቤተሰብ ታላቅ ብሔር የሆነው እንዴት ነው?

ከያዕቆብ ልጆች አብዛኞቹ በታናሽ ወንድማቸው በዮሴፍ ላይ ቅንዓት ባደረባቸው ወቅት እርስ በርስ ተያያዥነት ያላቸው ሁኔታዎች መከሰት ጀመሩ። የዮሴፍ ወንድሞች ለባርነት የሸጡት ሲሆን የገዙት ሰዎች ደግሞ ወደ ግብፅ ወሰዱት። ይሁን እንጂ ታማኝና ቆራጥ የነበረውን ይህን ወጣት አምላክ ባረከው። ዮሴፍ ከባድ ችግሮች የደረሱበት ቢሆንም የኋላ ኋላ የግብፅ ንጉሥ በነበረው በፈርዖን ተመርጦ ታላቅ ሥልጣን ተሰጠው። ይህም ወቅቱን የጠበቀ ክንውን ነበር፤ በዚያን ጊዜ በተከሰተው ረሃብ ምክንያት ያዕቆብ ከግብፅ ቀለብ እንዲሸምቱ ልጆቹን ሲልካቸው በግብፅ በእህሉ ላይ በኃላፊነት የተሾመው ዮሴፍ ሆኖ አገኙት! ዮሴፍና ወንድሞቹ የተገናኙበት መንገድ አስገራሚና ስሜት የሚነካ ነበር፤ ዮሴፍ በእሱ ላይ ስላደረሱበት በደል ለተጸጸቱት ወንድሞቹ ምሕረት ያደረገላቸው ከመሆኑም ሌላ መላው ቤተሰብ ወደ ግብፅ መጥቶ እንዲኖር ዝግጅት አደረገ። በዚያም ምርጥ የሆነው ምድር የተሰጣቸው ሲሆን እነሱም በቁጥር እየበዙና እየበለጸጉ ሄዱ። አምላክ፣ የገባውን ቃል ለመፈጸም ሲል ነገሮች በዚህ መልኩ እንዲከናወኑ ማድረጉን ዮሴፍ ተገንዝቦ ነበር።

በዕድሜ የገፋው ያዕቆብ በቁጥር እየጨመረ ከነበረው ቤተሰቡ ጋር ሆኖ ቀሪ ሕይወቱን በግብፅ አሳለፈ። ያዕቆብ ከመሞቱ በፊት፣ ተስፋ የተሰጠበት ዘር ወይም አዳኝ በልጁ በይሁዳ የትውልድ ሐረግ በኩል የሚመጣ ኃያል መሪ እንደሚሆን ትንቢት ተናገረ። ከዓመታት በኋላ ደግሞ ዮሴፍ ራሱ ከመሞቱ በፊት፣ የያዕቆብን ቤተሰብ አምላክ አንድ ቀን ከግብፅ እንደሚያወጣቸው ትንቢት ተናገረ።

በዘፍጥረት ምዕራፍ 20 እስከ ምዕራፍ 50 እና በዕብራውያን 11:17-22 ላይ የተመሠረተ።