በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ክፍል 26

ምድር ገነት ትሆናለች!

ምድር ገነት ትሆናለች!

ይሖዋ በክርስቶስ በሚተዳደረው መንግሥት አማካኝነት ስሙን ያስቀድሳል፤ ሉዓላዊነቱን ያስከብራል እንዲሁም ክፋትን በሙሉ ያስወግዳል

ራእይ ወይም አፖካሊፕስ የተባለው የመጨረሻው የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ለሁሉም የሰው ዘሮች የሚሆን ተስፋ ይዟል። በሐዋርያው ዮሐንስ የተጻፈው ይህ መጽሐፍ በተለያዩ ራእዮች አማካኝነት የይሖዋን ዓላማ ፍጻሜ ያሳየናል።

ከሞት የተነሳው ኢየሱስ በርከት ላሉ ጉባኤዎች የላከው ምስጋናና እርማት በመጀመሪያው ራእይ ላይ ተገልጿል። በሁለተኛው ራእይ ላይ ደግሞ ዮሐንስ በሰማይ ያለውን የአምላክ ዙፋን የተመለከተ ሲሆን በዚያም መንፈሳዊ ፍጥረታት ለይሖዋ ውዳሴ ያቀርባሉ።

የአምላክ ዓላማ ፍጻሜውን እያገኘ ሲሄድ በጉ ማለትም ኢየሱስ ክርስቶስ በሰባት ማኅተሞች የታሸገ ጥቅልል ተቀበለ። የመጀመሪያዎቹ አራት ማኅተሞች ሲከፈቱ ምሳሌያዊ ፈረሰኞች በዓለም መድረክ ላይ ብቅ አሉ። በነጭ ፈረስ ላይ የሚጋልበው የመጀመሪያው ፈረሰኛ ኢየሱስ ሲሆን ንጉሥ ሆኖ አክሊል ደፍቷል። ቀጥሎም የተለያየ ቀለም ባላቸው ፈረሶች ላይ የተቀመጡ ጋላቢዎች ብቅ አሉ፤ እነዚህ ጋላቢዎች በትንቢታዊ ሁኔታ ጦርነትን፣ ረሃብንና ቸነፈርን የሚያመለክቱ ሲሆን እነዚህ ነገሮች በሙሉ የሚፈጸሙት በዚህ ሥርዓት የመጨረሻ ቀኖች ውስጥ ነው። ሰባተኛው ማኅተም ሲከፈት የአምላክን የፍርድ መልእክት መታወጅ የሚያመለክቱ ሰባት ምሳሌያዊ መለከቶች ተነፉ። ይህ ደግሞ ምሳሌያዊ የሆኑ ሰባት መቅሠፍቶች ወይም የአምላክ የቁጣ መግለጫዎች እንዲወርዱ ምክንያት ሆነ።

አዲስ በተወለደ ወንድ ልጅ የተመሰለው የአምላክ መንግሥት በሰማይ ተቋቋመ። በሰማይ ጦርነት ተነሳ፤ ሰይጣንና እሱን የተከተሉት ክፉ መላእክት ወደ ምድር ተወረወሩ። አንድ ታላቅ ድምፅ “ምድርና ባሕር . . . ወዮላችሁ!” ሲል ተሰማ። ዲያብሎስ ጥቂት ጊዜ እንደቀረው ስላወቀ በታላቅ ቁጣ ተሞልቷል።—ራእይ 12:12

ዮሐንስ በበግ የተመሰለውን ኢየሱስን በሰማይ ተመለከተ፤ ከእሱም ጋር ከሰው ልጆች መካከል የተመረጡ 144,000ዎች ነበሩ። እነዚህም ከኢየሱስ ጋር “ነገሥታት ሆነው . . . ይገዛሉ።” የራእይ መጽሐፍ፣ ተስፋ የተሰጠበት ዘር ሁለተኛ ክፍል አባላት 144,000 እንደሚሆኑ በግልጽ ያሳያል።—ራእይ 14:1፤ 20:6

የምድር ነገሥታት ወደ አርማጌዶን ይኸውም “ሁሉን ቻይ ወደሆነው አምላክ ታላቅ የጦርነት ቀን” ተሰበሰቡ። እነዚህ ነገሥታት የሰማይ ሠራዊትን ከሚመራውና ነጩን ፈረስ ከሚጋልበው ከኢየሱስ ጋር ይዋጋሉ። የዚህ ዓለም ገዥዎች በሙሉ ይጠፋሉ። ሰይጣን የሚታሰር ሲሆን ኢየሱስና 144,000ዎቹ በምድር ላይ “ለአንድ ሺህ ዓመት” ይገዛሉ። በሺው ዓመት መጨረሻ ላይ ሰይጣን ይደመሰሳል።—ራእይ 16:14፤ 20:4

ለአንድ ሺህ ዓመት የሚቆየው የክርስቶስና የተባባሪዎቹ የግዛት ዘመን ታዛዥ ለሆኑ ሰዎች ምን ያስገኛል? ዮሐንስ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “[ይሖዋ] እንባን ሁሉ ከዓይኖቻቸው ላይ ይጠርጋል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም፤ ሐዘንም ሆነ ጩኸት እንዲሁም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም። ቀድሞ የነበሩት ነገሮች አልፈዋል።” (ራእይ 21:4) ምድር ገነት ትሆናለች!

የራእይ መጽሐፍ፣ የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት በዚህ መንገድ ያጠቃልለዋል። መሲሐዊው መንግሥት የይሖዋን ስም ያስቀድሳል እንዲሁም ሉዓላዊነቱ ለዘላለም ሙሉ በሙሉ እንዲረጋገጥ ያደርጋል!

በራእይ መጽሐፍ ላይ የተመሠረተ።