በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ክፍል 20

ኢየሱስ ክርስቶስ ተገደለ

ኢየሱስ ክርስቶስ ተገደለ

ኢየሱስ አንድ አዲስ በዓል አቋቋመ፤ ከዚያም አልፎ ተሰጠ እንዲሁም ተሰቀለ

ኢየሱስ ለሦስት ዓመት ተኩል ሲሰብክና ሲያስተምር ከቆየ በኋላ በምድር ላይ የሚያሳልፈው ጊዜ ሊያበቃ መቃረቡን አውቆ ነበር። የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች ሊገድሉት እያሴሩ የነበረ ቢሆንም ነቢይ እንደሆነ የሚያምኑት ሰዎች ሁከት እንዳያስነሱ ፈርተዋል። ይህ በዚህ እንዳለ ከኢየሱስ 12 ሐዋርያት አንዱ የሆነው ይሁዳ ኢየሱስን አሳልፎ እንዲሰጠው ሰይጣን አነሳሳው። የሃይማኖት መሪዎቹ ይሁዳ ኢየሱስን አሳልፎ ከሰጣቸው 30 የብር ሳንቲሞች ሊሰጡት ተስማሙ።

ኢየሱስ ሰው ሆኖ በምድር ላይ ባሳለፈው የመጨረሻ ምሽት ላይ ከሐዋርያቱ ጋር የፋሲካን በዓል ለማክበር ተሰብስበው ነበር። ኢየሱስ ይሁዳን ካሰናበተው በኋላ የጌታ ራት የሚባለውን አዲስ በዓል አቋቋመ። ቂጣ አንስቶ ጸሎት ካቀረበ በኋላ ለቀሩት 11 ሐዋርያት እንዲበሉ ሰጣቸው። ከዚያም “ይህ ስለ እናንተ የሚሰጥ ሥጋዬ ማለት ነው። ይህን ሁልጊዜ ለመታሰቢያዬ አድርጉት” አላቸው። ወይን የያዘውን ጽዋም አንስቶ “ይህ . . . በሚፈሰው ደሜ አማካኝነት የሚመሠረተው አዲሱ ቃል ኪዳን ማለት ነው” አላቸው።—ሉቃስ 22:19, 20

ኢየሱስ በዚያ ምሽት ለሐዋርያቱ የሚነግራቸው ብዙ ነገር ነበረው። አንዳቸው ለሌላው ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር እንዲኖራቸው በመምከር አዲስ ትእዛዝ ሰጣቸው። “በመካከላችሁ ፍቅር ካለ ሰዎች ሁሉ ደቀ መዛሙርቴ እንደሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ” አላቸው። (ዮሐንስ 13:34, 35) እንዲሁም በዚያን ዕለት በሚፈጸሙት አሳዛኝ ነገሮች ልባቸው እንዳይረበሽ መከራቸው። ኢየሱስ እነሱን በተመለከተ ልባዊ ጸሎት አቀረበ። ከዚያም አንድ ላይ የምስጋና መዝሙር ከዘመሩ በኋላ በጨለማ ወደ ጌቴሴማኒ የአትክልት ስፍራ ሄዱ።

በጌቴሴማኒ የአትክልት ስፍራ ኢየሱስ ተንበርክኮ ወደ አምላክ ከልብ የመነጨ ጸሎት አቀረበ። ብዙም ሳይቆይ መሣሪያ የታጠቁ ወታደሮች፣ ካህናትና ሌሎች ብዙ ሰዎች ኢየሱስን ሊይዙት መጡ። ይሁዳ ወደ ኢየሱስ ቀርቦ እሱን በመሳም የሚፈልጉትን ሰው ጠቆማቸው። ወታደሮቹ ኢየሱስን ሲያስሩት ሐዋርያቱ ሸሹ።

ኢየሱስ በአይሁድ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፊት በቀረበበት ወቅት የአምላክ ልጅ መሆኑን በግልጽ ተናገረ። ፍርድ ቤቱም ይህ አምላክን እንደ መሳደብ እንደሚቆጠርና በሞት የሚያስቀጣ ወንጀል እንደሆነ ገለጸ። ከዚያም ኢየሱስ ጳንጥዮስ ጲላጦስ ወደተባለው ሮማዊ ገዥ ተወሰደ። ጲላጦስ ኢየሱስን ምንም ወንጀል ባያገኝበትም እንዲገደል በመጠየቅ ይጮኽ ለነበረው ሕዝብ አሳልፎ ሰጠው።

ሮማውያን ወታደሮች ኢየሱስን ጎልጎታ ወደተባለው ስፍራ ወስደው በእንጨት ላይ ሰቀሉት። ይህ ሲሆን ጊዜው ቀን የነበረ ቢሆንም በተአምራዊ ሁኔታ አካባቢው በጨለማ ተዋጠ። በዚያኑ ዕለት ከሰዓት በኋላ ኢየሱስ የሞተ ሲሆን ታላቅ የምድር መናወጥ ሆነ። የኢየሱስ አስከሬን ከዐለት ተፈልፍሎ በተሠራ መቃብር ውስጥ ተቀበረ። በቀጣዩ ቀን ካህናት መቃብሩን ካሸጉት በኋላ ደጃፉ ላይ ሆነው የሚጠብቁ ዘበኞች መደቡ። ኢየሱስ በመቃብሩ ውስጥ ይቀር ይሆን? በፍጹም። ከተአምራት ሁሉ የሚበልጠው ተአምር ሊፈጸም ነው።

በማቴዎስ ምዕራፍ 26 እና ምዕራፍ 27፤ በማርቆስ ምዕራፍ 14 እና ምዕራፍ 15፤ በሉቃስ ምዕራፍ 22 እና ምዕራፍ 23፤ በዮሐንስ ምዕራፍ 12 እስከ ምዕራፍ 19 ላይ የተመሠረተ።

^ አን.15 የኢየሱስ መሥዋዕታዊ ሞት የሚያስገኘውን ጥቅም በተመለከተ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 5 ተመልከት።