በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ክፍል 24

ጳውሎስ ለጉባኤዎች ደብዳቤ ጻፈ

ጳውሎስ ለጉባኤዎች ደብዳቤ ጻፈ

ጳውሎስ የክርስቲያን ጉባኤን የሚያበረታቱ ደብዳቤዎች ጻፈ

አዲስ የተቋቋመው የክርስቲያን ጉባኤ የይሖዋን ዓላማ በማስፈጸም ረገድ ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል። ይሁን እንጂ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረው የክርስቲያን ጉባኤ ከተቋቋመ ብዙም ሳይቆይ ጥቃት ይሰነዘርበት ጀመር። በወቅቱ የነበሩት ክርስቲያኖች ከጉባኤው ውጪ የሚደርስባቸውን ስደትም ሆነ በጉባኤ ውስጥ የሚያጋጥሟቸውን ሌሎች ስውር አደጋዎች ተቋቁመው በአምላክ ፊት ንጹሕ አቋማቸውን ጠብቀው መገኘት ይችሉ ይሆን? በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ክርስቲያኖች የሚያስፈልጋቸውን ምክርና ማበረታቻ የያዙ 21 ደብዳቤዎች ይገኛሉ።

ከሮም እስከ ዕብራውያን ያሉትን አሥራ አራት ደብዳቤዎች የጻፈው ሐዋርያው ጳውሎስ ነው። እነዚህ ደብዳቤዎች የተሰየሙት መልእክቱ በተላከለት ግለሰብ ወይም በአንድ ጉባኤ ስም ነው። በጳውሎስ ደብዳቤዎች ውስጥ የተካተቱትን አንዳንድ ርዕሰ ጉዳዮች እስቲ እንመልከት።

ሥነ ምግባርንና አኗኗርን በተመለከተ የተሰጠ ጠንከር ያለ ምክር። ዝሙት፣ ምንዝር እና ሌሎች ከባድ ኃጢአቶችን የሚፈጽሙ ሰዎች ‘የአምላክን መንግሥት አይወርሱም።’ (ገላትያ 5:19-21፤ 1 ቆሮንቶስ 6:9-11) የአምላክ አገልጋዮች ዜግነታቸው ምንም ይሁን ምን አንድነት ሊኖራቸው ይገባል። (ሮም 2:11፤ ኤፌሶን 4:1-6) ክርስቲያኖች እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን የእምነት ባልንጀሮቻቸውን ለመርዳት በደስታ ራሳቸውን ማቅረብ ይኖርባቸዋል። (2 ቆሮንቶስ 9:7) ጳውሎስ “ያለማቋረጥ ጸልዩ” ብሏል። በእርግጥም የአምላክ አገልጋዮች ወደ ይሖዋ ሲጸልዩ የልባቸውን አውጥተው እንዲነግሩት ተበረታተዋል። (1 ተሰሎንቄ 5:17፤ 2 ተሰሎንቄ 3:1፤ ፊልጵስዩስ 4:6, 7) አምላክ ጸሎታቸውን እንዲሰማላቸው ደግሞ በእምነት ሊጸልዩ ይገባል።—ዕብራውያን 11:6

የቤተሰብ ሕይወት ስኬታማ እንዲሆን የሚረዳው ምንድን ነው? ባሎች ሚስቶቻቸውን እንደ ገዛ አካላቸው አድርገው ሊወዷቸው ይገባል። ሚስቶች ባሎቻቸውን በጥልቅ ሊያከብሩ ይገባል። ልጆች ለወላጆቻቸው መታዘዛቸው ጌታን ደስ የሚያሰኝ ስለሆነ ይህን ማድረግ አለባቸው። ወላጆች መለኮታዊ መመሪያዎችን በመጠቀም ልጆቻቸውን በፍቅር መምራትና ማሠልጠን ይኖርባቸዋል።—ኤፌሶን 5:22 እስከ 6:4፤ ቆላስይስ 3:18-21

የአምላክን ዓላማ ለመረዳት የሚያስችል ብርሃን ፈነጠቀ። በሙሴ ሕግ ውስጥ የሚገኙት በርካታ መመሪያዎች ክርስቶስ እስከሚመጣ ድረስ እስራኤላውያንን ለመጠበቅና ለመምራት አገልግለዋል። (ገላትያ 3:24) ይሁንና ክርስቲያኖች ይሖዋን ለማምለክ እነዚህን ሕግጋት የግድ መታዘዝ አያስፈልጋቸውም። ጳውሎስ ከአይሁድ እምነት ለመጡት የዕብራውያን ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ የሕጉን ትርጉም በተመለከተ ብርሃን የፈነጠቀ ከመሆኑም ሌላ የአምላክ ዓላማ በክርስቶስ በኩል የተፈጸመበትን መንገድ በሚገባ አብራርቷል። ጳውሎስ በሕጉ ውስጥ የነበሩት የተለያዩ ዝግጅቶች ትንቢታዊ ጥላነት እንዳላቸው ገልጿል። ለምሳሌ በሕጉ ሥር የሚቀርበው የእንስሳት መሥዋዕት፣ እውነተኛ የኃጢአት ይቅርታ ለሚያስገኘው የኢየሱስ መሥዋዕታዊ ሞት ጥላ ነበር። (ዕብራውያን 10:1-4) ኢየሱስ ከሞተ በኋላ የሕጉ ቃል ኪዳን አስፈላጊ ባለመሆኑ አምላክ ይህንን ቃል ኪዳን ደመሰሰው።—ቆላስይስ 2:13-17፤ ዕብራውያን 8:13

ተገቢ የሆነ የጉባኤ አደረጃጀትን በተመለከተ የተሰጠ መመሪያ። በጉባኤ ውስጥ ኃላፊነት ለመሸከም ፈቃደኛ የሆኑ ወንድሞች በላቁ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች መመራትና መንፈሳዊ ብቃቶችን ማሟላት ይገባቸዋል። (1 ጢሞቴዎስ 3:1-10, 12, 13፤ ቲቶ 1:5-9) የይሖዋ አምላኪዎች እርስ በርስ ለመበረታታት እንዲችሉ ከእምነት ባልንጀሮቻቸው ጋር አዘውትረው መሰብሰብ ይኖርባቸዋል። (ዕብራውያን 10:24, 25) ለአምልኮ የሚደረጉ ስብሰባዎች የሚያንጹና ትምህርት የሚሰጡ መሆን አለባቸው።—1 ቆሮንቶስ 14:26, 31

ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ ሁለተኛውን ደብዳቤ የጻፈው ወደ ሮም ከተመለሰ በኋላ ሲሆን በዚያም እስር ቤት ሆኖ ፍርዱን እየተጠባበቀ ነበር። በወቅቱ ይጠይቁት የነበሩት ደፋር የሆኑ ጥቂት ሰዎች ብቻ ነበሩ። ጳውሎስ የቀረው ጊዜ አጭር መሆኑን ተገንዝቦ ነበር። “መልካሙን ገድል ተጋድያለሁ፤ ሩጫውን እስከ መጨረሻ ሮጫለሁ፤ እምነትን ጠብቄያለሁ” ብሏል። (2 ጢሞቴዎስ 4:7) ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ጳውሎስ ሰማዕት ሆኖ ሳይገደል አልቀረም። ሐዋርያው የጻፋቸው ደብዳቤዎች በዛሬው ጊዜ ለሚገኙ እውነተኛ የአምላክ አገልጋዮችም መመሪያ ይሰጣሉ።

በሮም፤ በ1 ቆሮንቶስ፤ በ2 ቆሮንቶስ፤ በገላትያ፤ በኤፌሶን፤ በፊልጵስዩስ፤ በቆላስይስ፤ በ1 ተሰሎንቄ፤ በ2 ተሰሎንቄ፤ በ1 ጢሞቴዎስ፤ በ2 ጢሞቴዎስ፤ በቲቶ፤ በፊልሞና እና በዕብራውያን መጻሕፍት ላይ የተመሠረተ።