ክፍል 10
ሰለሞን ጠቢብ ንጉሥ ነበር
ይሖዋ ለንጉሥ ሰለሞን ጥበበኛ ልብ ሰጠው፤ በሰለሞን የግዛት ዘመን እስራኤላውያን ተወዳዳሪ የሌለው ሰላምና ብልጽግና አግኝተው ነበር
አንድ ብሔር እና ንጉሣቸው ይሖዋን እንደ ሉዓላዊ ገዥያቸው አድርገው ቢከተሉትና ሕግጋቱን ቢታዘዙ ምን ዓይነት ሕይወት ይኖራቸዋል? በንጉሥ ሰለሞን የ40 ዓመት የግዛት ወቅት የነበረው ሁኔታ ለዚህ ጥያቄ መልስ ይሆናል።
ዳዊት ከመሞቱ በፊት ልጁን ሰለሞንን ከእሱ በኋላ እንዲነግሥ ሾመው። አምላክ ለሰለሞን በሕልም ተገልጦለት የሚፈልገውን ነገር እንዲጠይቅ ጋበዘው። ሰለሞንም ሕዝቡን በትክክልና በማስተዋል ማስተዳደር እንዲችል አምላክ ጥበብና እውቀት እንዲሰጠው ጠየቀ። ይሖዋም በጥያቄው ተደስቶ ለሰለሞን ጥበበኛና አስተዋይ ልብ ሰጠው። በተጨማሪም ሰለሞን፣ አምላክን መታዘዙን ከቀጠለ ብልጽግና፣ ክብርና ረጅም ዕድሜ እንደሚሰጠው ይሖዋ ቃል ገባለት።
ሰለሞን ጥበብ በሚንጸባረቅበት መንገድ ፍርድ በመስጠት የታወቀ ሆነ። በአንድ ወቅት አንድን ሕፃን ልጅ በተመለከተ በሁለት እናቶች መካከል ክርክር ተነስቶ ነበር፤ ሁለቱም ሴቶች ልጁ ‘የእኔ ነው’ ይሉ ነበር። ሰለሞን ሕፃኑ ለሁለት እንዲከፈልና ለእያንዳንዳቸው ግማሹ እንዲሰጣቸው አዘዘ። አንደኛዋ ሴት በዚህ ፍርድ ተስማማች፤ እውነተኛዋ እናት ግን ልጁ ሳይገደል ለሌላዋ ሴት እንዲሰጣት ለመነች። ሰለሞን የሕፃኑ እናት ርኅራኄ ያሳየችው ሴት እንደሆነች በግልጽ ስለተገነዘበ ልጁን ሰጣት። ብዙም ሳይቆይ እስራኤል ሁሉ ይህንን ፍርድ በመስማታቸው ሰለሞን የአምላክ ጥበብ እንዳለው ተገነዘቡ።
ሰለሞን ካከናወናቸው ታላላቅ ሥራዎች አንዱ የይሖዋ ቤተ መቅደስ ግንባታ ነው፤ ኢየሩሳሌም ውስጥ ዕፁብ ድንቅ በሆነ መንገድ የተሠራው ይህ ሕንፃ በእስራኤል የአምልኮ ማዕከል ሆኖ ያገለግል ነበር። በቤተ መቅደሱ ምረቃ ወቅት ሰለሞን እንዲህ በማለት ጸለየ፦ “እነሆ፤ ሰማይ፣ ከሰማያትም በላይ ያለው ሰማይ እንኳ ይይዝህ ዘንድ አይችልም፤ ታዲያ እኔ የሠራሁት ይህ ቤተ መቅደስማ ምኑ ሊበቃ!”—1 ነገሥት 8:27
የሰለሞን ዝና በሌሎች አገሮች ሌላው ቀርቶ በአረብ ምድር እስካለችው እስከ ሳባ ምድር ድረስ ተሰማ። የሳባ ንግሥት የሰለሞንን ክብርና ብልጽግና ለማየት እንዲሁም ምን ያህል ጥበበኛ እንደሆነ ለመፈተን መጣች። ንግሥቲቱ በሰለሞን ጥበብና በእስራኤል ብልጽግና በጣም ስለተደነቀች እንዲህ ያለ ጥበበኛ ንጉሥ በእስራኤል ዙፋን ላይ በማስቀመጡ ይሖዋን አመሰገነች። በእርግጥም ይሖዋ የሰለሞንን ግዛት ባርኮት ስለነበር በዘመኑ በጥንቷ እስራኤል ታሪክ ውስጥ ተወዳዳሪ የሌለው ብልጽግናና ሰላም ሰፍኖ ነበር።
የሚያሳዝነው ግን ሰለሞን ይሖዋ ከሰጠው ጥበብ ጋር በሚስማማ መንገድ መመላለሱን አልቀጠለም። የአምላክን ትእዛዝ ችላ በማለት ባዕድ አማልክትን የሚያመልኩ ሴቶችን ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሚስቶችን አገባ። ውሎ አድሮ ሚስቶቹ ይሖዋን ማምለክ እንዲተውና ልቡ ወደ ጣዖት አምልኮ እንዲያዘነብል አደረጉት። ይሖዋም ለሰለሞን ከግዛቱ ውስጥ ከፊሉ ተወስዶ ለሌላ እንደሚሰጥ ነገረው። አምላክ ከሰለሞን አባት ከዳዊት ጋር ለገባው ቃል ኪዳን ሲል ከመንግሥቱ ከፊሉን ብቻ ለቤተሰቡ እንደሚተው ገለጸ። ሰለሞን ታማኝነቱን ቢያጎድልም ይሖዋ ከዳዊት ጋር ለገባው የመንግሥት ቃል ኪዳን ታማኝ ሆኗል።
—በ1 ነገሥት ምዕራፍ 1 እስከ ምዕራፍ 11፤ በ2 ዜና ምዕራፍ 1 እስከ ምዕራፍ 9 እና በዘዳግም 17:17 ላይ የተመሠረተ።