በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የአርማጌዶን ጦርነት ምንድን ነው?

የአርማጌዶን ጦርነት ምንድን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 የአርማጌዶን ጦርነት የሚባለው በሰብዓዊ መንግሥታትና በአምላክ መንግሥት መካከል የሚካሄደው የመጨረሻው ውጊያ ነው። እነዚህ ሰብዓዊ መንግሥታትና ደጋፊዎቻቸው የአምላክን አገዛዝ ለመቀበል ፈቃደኛ ባለመሆናቸው አሁንም እንኳ አምላክን እየተቃወሙት ነው። (መዝሙር 2:2) ሰብዓዊ መንግሥታት በሙሉ በአርማጌዶን ጦርነት ወቅት ይጠፋሉ።—ዳንኤል 2:44

 “ሐር ማጌዶን” የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰው ራእይ 16:16 ላይ ብቻ ነው። ‘የዓለም ነገሥታት በዕብራይስጥ ሐር ማጌዶን የሚባል ስፍራ ላይ ሁሉን ቻይ በሆነው አምላክ ታላቅ ቀን ወደሚካሄደው ጦርነት’ እንደተሰበሰቡ በራእይ መጽሐፍ ላይ የሚገኘው ትንቢት ይናገራል።—ራእይ 16:14

 በአርማጌዶን ጦርነት ላይ የሚዋጋው ማን ነው? ኢየሱስ ክርስቶስ በሰማይ ላይ ያለ ሠራዊት እየመራ በአምላክ ጠላቶች ላይ ድል ይቀዳጃል። (ራእይ 19:11-16, 19-21) የአምላክን ሥልጣን የሚቃወሙና እሱን የማያከብሩ ሁሉ የአምላክ ጠላቶች ናቸው።—ሕዝቅኤል 39:7

 የአርማጌዶን ጦርነት የሚካሄደው በመካከለኛው ምሥራቅ በሚገኝ አንድ አካባቢ ነው? አይደለም። የአርማጌዶን ጦርነት በአንድ አካባቢ ብቻ የሚካሄድ ሳይሆን መላውን ምድር የሚነካ ነው።—ኤርምያስ 25:32-34፤ ሕዝቅኤል 39:17-20

 አርማጌዶን የሚለው ቃል (አንዳንድ ጊዜ “ሐር ማጌዶን” ተብሎም ይተረጎማል) “የመጊዶ ተራራ” የሚል ትርጉም አለው። መጊዶ በአንድ ወቅት በጥንቷ እስራኤል ውስጥ የምትገኝ ከተማ ነበረች። በዚያ ቦታ አቅራቢያ በርካታ ወሳኝ ጦርነቶች እንደተካሄዱ የታሪክ መዛግብት ይናገራሉ፤ ከእነዚህ አንዳንዶቹ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግበው ይገኛሉ። (መሳፍንት 5:19, 20፤ 2 ነገሥት 9:27፤ 23:29) ይሁንና አርማጌዶን በጥንቷ መጊዶ አካባቢ የሚደረግ ጦርነትን የሚያመለክት ሊሆን አይችልም። በአሁኑ ወቅት በዚያ ስፍራ ትልቅ ተራራ አናገኝም፤ በዚያ ላይ ደግሞ በጥንቷ መጊዶ የሚገኘው ስፍራ ይቅርና ከዚህ ቦታ ጋር ተያይዞ የሚገኘው የኢይዝራኤል ሸለቆም እንኳ በአርማጌዶን ጦርነት ወቅት በአምላክ ላይ የሚነሱትን ጠላቶች በሙሉ ሊይዝ አይችልም። በመሆኑም አርማጌዶን፣ መንግሥታት በአምላክ ላይ ለመጨረሻ ጊዜ በሚነሱበት ወቅት በመላው ዓለም ላይ የሚከሰተውን ሁኔታ የሚያመለክት ነው።

 የአርማጌዶን ጦርነት በሚካሄድበት ወቅት ምን ዓይነት ሁኔታዎች ይኖራሉ? አምላክ በአርማጌዶን ጦርነት ወቅት ኃይሉን የሚያሳየው እንዴት እንደሆነ አናውቅም፤ ሆኖም ባለፉት ጊዜያት እንዳደረገው ሁሉ እንደ በረዶ፣ የምድር መንቀጥቀጥ፣ ዶፍ ዝናብና የሚያቃጥል ድኝ እና በሽታ ያሉ አጥፊ ነገሮችን ሊጠቀም ይችላል። (ኢዮብ 38:22, 23፤ ሕዝቅኤል 38:19, 22፤ ዕንባቆም 3:10, 11፤ ዘካርያስ 14:12) በዚያን ወቅት አንዳንድ የአምላክ ጠላቶች በመካከላቸው ሽብር በመፈጠሩ የተነሳ እርስ በርስ ይገዳደላሉ፤ ያም ቢሆን እየተዋጋቸው ያለው አምላክ መሆኑን መገንዘባቸው አይቀርም።—ሕዝቅኤል 38:21, 23፤ ዘካርያስ 14:13

 የአርማጌዶን ጦርነት የዓለም መጨረሻ ነው? በዚህ ጦርነት ፕላኔቷ ምድር አትጠፋም፤ ምክንያቱም ምድር የተፈጠረችው የሰው ልጆች ለዘላለም እንዲኖሩባት ነው። (መዝሙር 37:29፤ 96:10 NW፤ መክብብ 1:4) በአርማጌዶን ጦርነት ወቅት የሰው ዘር ሙሉ በሙሉ አይጠፋም፤ ምክንያቱም “እጅግ ብዙ ሕዝብ” የሆኑ የአምላክ አገልጋዮች ከጥፋቱ ይተርፋሉ።—ራእይ 7:9, 14፤ መዝሙር 37:34

 “ዓለም” የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ምድርን ብቻ ሳይሆን አምላክን የሚቃወሙ ክፉ ሰዎችን በአጠቃላይ ለማመልከት ተሠርቶበታል። (1 ዮሐንስ 2:15-17) ከዚህ አንጻር አርማጌዶን “የዓለም መጨረሻ” ነው ሊባል ይችላል።—ማቴዎስ 24:3 አዲሱ መደበኛ ትርጉም

 አርማጌዶን የሚካሄደው መቼ ነው? ከአርማጌዶን ጦርነት በፊት ስለሚከሰተው “ታላቅ መከራ” ሲናገር ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “ስለዚያ ቀንና ሰዓት ከአብ ብቻ በቀር የሰማይ መላእክትም ሆኑ ወልድ፣ ማንም አያውቅም።” (ማቴዎስ 24:21, 36) ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው ይህ ጦርነት የሚነሳው ኢየሱስ በማይታይ ሁኔታ በሚገኝበት ጊዜ ነው፤ ይህ ጊዜ የጀመረው በ1914 ነው።—ማቴዎስ 24:37-39