በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በመጽሐፍ ቅዱስ የዘመን ስሌት መሠረት 1914 ምን የሆነበት ዓመት ነው?

በመጽሐፍ ቅዱስ የዘመን ስሌት መሠረት 1914 ምን የሆነበት ዓመት ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 በመጽሐፍ ቅዱስ የዘመን ስሌት መሠረት 1914 የአምላክ መንግሥት በሰማይ ላይ የተቋቋመበት ዓመት ነው። በዳንኤል መጽሐፍ ምዕራፍ 4 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው ትንቢት ይህን ይጠቁማል።

 ስለ ትንቢቱ አጭር መግለጫ። አምላክ፣ የባቢሎን ንጉሥ የሆነው ናቡከደነፆር ትንቢታዊ ይዘት ያለው ሕልም እንዲያልም አደረገ፤ ናቡከደነፆር በሕልሙ አንድ ትልቅ ዛፍ ሲቆረጥ ተመለከተ። የዛፉ ጉቶ “ሰባት ዓመት” ለሚያህል ጊዜ ሳያድግ እንዲቆይ ታሰረ፤ ይህ ጊዜ ካለፈ በኋላ እንደገና ማደግ ይጀምራል።—ዳንኤል 4:1, 10-16

 የትንቢቱ የመጀመሪያ ፍጻሜ። ትልቁ ዛፍ የሚያመለክተው ራሱን ንጉሥ ናቡከደነፆርን ነው። (ዳንኤል 4:20-22) ንጉሡ አእምሮውን በመሳቱ ለሰባት ዓመት ከንግሥናው ወርዶ ነበር፤ በመሆኑም በምሳሌያዊ ሁኔታ ‘ተቆርጧል’ ሊባል ይችላል። (ዳንኤል 4:25) በኋላ ላይ አምላክ፣ ናቡከደነፆር አእምሮው እንዲመለስለት ስላደረገ እንደገና ዙፋኑን ያዘ፤ እንዲሁም የአምላክን ገዢነት አምኖ ተቀበለ።—ዳንኤል 4:34-36

 ትንቢቱ ሌላ ዋና ፍጻሜ እንዳለው የሚያሳይ ማስረጃ። የዚህ ትንቢት ዋና ዓላማ “ልዑል በሰዎች መንግሥታት ሁሉ ላይ እንደሚገዛና እነዚህንም መንግሥታት ለወደደው እንደሚሰጥ፣ ከሰዎችም የተናቁትን በላያቸው እንደሚሾም፣ ሕያዋን ሁሉ ያውቁ ዘንድ ነው።” (ዳንኤል 4:17) ታዲያ አምላክ ከጊዜ በኋላ መንግሥትን ለመስጠት የወደደው ኩሩ ለነበረው ለናቡከደነፆር ነው? አይደለም፤ ምክንያቱም አምላክ ከዚያ በፊት ለናቡከደነፆር ባሳየው ሕልም ላይ፣ እሱም ሆነ ሌላ የትኛውም ገዥ ለዚህ ሹመት እንደማይበቁ ጠቁሟል። ከዚህ ይልቅ አምላክ ራሱ “ፈጽሞ የማይፈርስ መንግሥት ይመሠርታል።”

 ከዚያ ቀደም ብሎ አምላክ የእሱን አገዛዝ እንዲወክል በምድር ላይ ያቋቋመው መንግሥት የጥንቱ የእስራኤል ብሔር ነበር። የዚህ ብሔር ገዥዎች ታማኝ ሆነው ባለመገኘታቸው አምላክ ምድሩ “ባድማ” እንዲሆን ፈቀደ፤ ይሁን እንጂ አምላክ አስቀድሞ እንደተናገረው “የሚገባው ባለ መብት” ሲመጣ ንጉሣዊ ሥልጣን ይሰጠዋል። (ሕዝቅኤል 21:25-27) መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያሳየው ይህን ዘላለማዊ መንግሥት የመቀበል ሕጋዊ መብት ያለው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። (ሉቃስ 1:30-33) አስቀድሞ በትንቢት እንደተነገረው ኢየሱስ ከናቡከደነፆር በተለየ መልኩ ‘በልቡ ትሑት’ ነው።—ማቴዎስ 11:29

 በዳንኤል ምዕራፍ 4 ላይ ያለው ዛፍ ምን ይወክላል? በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ዛፎች አገዛዝን ለማመልከት የተሠራባቸው ጊዜያት አሉ። (ሕዝቅኤል 17:22-24፤ 31:2-5) ዳንኤል ምዕራፍ 4 ላይ ያለው ትንቢት ዋና ፍጻሜ ላይ ትልቁ ዛፍ የሚወክለው የአምላክን አገዛዝ ነው።

 ዛፉ መቆረጡ ምን ትርጉም አለው? ዛፉ መቆረጡ የናቡከደነፆር ንግሥና ለተወሰነ ጊዜ መቋረጡን እንደሚያመለክት አይተናል፤ በተመሳሳይም በትንቢቱ ዋና ፍጻሜ መሠረት የአምላክ አገዛዝ በምድር ላይ ለተወሰነ ጊዜ ይቋረጣል። ይህም የሆነው ናቡከደነፆር ኢየሩሳሌምን ባጠፋበት ወቅት ነው፤ የአምላክ ወኪሎች ተደርገው የሚቆጠሩት የእስራኤል ነገሥታት “በእግዚአብሔር ዙፋን” ላይ የሚቀመጡት በዚህች ከተማ ነበር።—1 ዜና መዋዕል 29:23

 “ሰባት ዓመት” የተባለው ጊዜ ምን ያመለክታል? “ሰባት ዓመት” የተባለው ጊዜ፣ አምላክ በምድር ላይ ያቋቋመው እሱን የሚወክል መንግሥት ሳይኖር ብሔራት ምድርን እንዲገዙ የሚፈቅድበትን ወቅት ያመለክታል። ይህ ወቅት የጀመረው ጥቅምት 607 ዓ.ዓ. ነው፤ በመጽሐፍ ቅዱስ የዘመን ስሌት መሠረት ኢየሩሳሌም በባቢሎናውያን የጠፋችው በዚህ ጊዜ ነው። a2 ነገሥት 25:1, 8-10

 “ሰባት ዓመት” የተባለው ጊዜ ምን ያህል ርዝመት አለው? ትንቢቱ ከናቡከደነፆር ጋር በተያያዘ ፍጻሜውን ሲያገኝ ይህ ጊዜ ቃል በቃል ሰባት ዓመታትን እንደሚያመለክት አይተናል፤ ዋነኛ ፍጻሜውን በሚያገኝበት ወቅት ግን ሁኔታው ከዚህ የተለየ ነው። ኢየሱስ እንደሚከተለው በማለት የተናገረው ሐሳብ መልሱን ይሰጠናል፦ “የተወሰኑት የአሕዛብ ዘመናት እስኪፈጸሙ ድረስም ኢየሩሳሌም [የአምላክን አገዛዝ ትወክል ነበር] በአሕዛብ ትረገጣለች።” (ሉቃስ 21:24) እዚህ ላይ “የተወሰኑት የአሕዛብ ዘመናት” የተባሉትና አምላክ አገዛዙ ‘በአሕዛብ እንዲረገጥ’ የፈቀደባቸው ዘመናት በዳንኤል ምዕራፍ 4 ላይ “ሰባት ዓመት” ከተባለው ጊዜ ጋር አንድ ናቸው። በመሆኑም ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ወቅትም እንኳ ‘ሰባቱ ዓመት’ እንዳላበቃ ማየት ይቻላል።

 ትንቢታዊ ትርጉም ያለው “ሰባት ዓመት” ምን ያህል ጊዜን እንደሚያመለክት መረዳት የምንችልበትን መንገድ መጽሐፍ ቅዱስ ይጠቁመናል። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ሦስት አንድ ሁለተኛ “ዘመናት” ወይም ዓመታት 1,260 ቀናትን እንደሚያመለክቱ ተገልጿል፤ “ሰባት ዓመት” ደግሞ የዚህ እጥፍ በመሆኑ 2,520 ቀናትን ያመለክታል። (ራእይ 12:6, 14) “ለእያንዳንዱ ዓመት አንድ ቀን” በሚለው ለትንቢቶች የሚሠራ ደንብ መሠረት ደግሞ 2,520 ቀናት 2,520 ዓመታትን ይወክላሉ። በመሆኑም ‘ሰባቱ ዓመት’ የሚቆይባቸው 2,520 ዓመታት በጥቅምት 1914 ያበቃሉ።—ዘኍልቍ 14:34፤ ሕዝቅኤል 4:6

a ኢየሩሳሌም የጠፋችው በ607 ዓ.ዓ. እንደሆነ የተገለጸበትን ምክንያት በተመለከተ ዝርዝር ማብራሪያ ለማግኘት በጥቅምት 1, 2011 መጠበቂያ ግንብ ላይ ያለውን “የጥንቷ ኢየሩሳሌም የጠፋችው መቼ ነው?—ክፍል አንድ” የሚለውን ርዕስ እንዲሁም በኅዳር 1, 2011 መጠበቂያ ግንብ ላይ ያለውን “የጥንቷ ኢየሩሳሌም የጠፋችው መቼ ነው?—ክፍል ሁለት” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።