ክፍል 15
በግዞት ያለው ነቢይ ስለ መጪው ጊዜ ራእይ ተመለከተ
ዳንኤል ስለ አምላክ መንግሥትና ስለ መሲሑ መምጣት ትንቢት ተናገረ። ባቢሎን ወደቀች
ዳንኤል የተባለ ንጹሕ አቋሙን በመጠበቅ ረገድ ግሩም ምሳሌ የሆነ ወጣት ኢየሩሳሌም ከመጥፋቷ በፊት በምርኮ ወደ ባቢሎን ተወስዶ ነበር። ባቢሎናውያን፣ ድል ካደረጉት የይሁዳ መንግሥት ማርከው ለወሰዷቸው ጥቂት አይሁዳውያንና ለዳንኤል መጠነኛ የሆነ ነፃነት ሰጥተዋቸው ነበር። ዳንኤል በባቢሎን ባሳለፈው ረጅም ዘመን አምላክ በጣም ባርኮታል፤ ይህ የአምላክ አገልጋይ ወደ አንበሶች ጉድጓድ ተጥሎ በነበረበት ወቅት እንኳ ከሞት ተርፏል፤ እንዲሁም ወደፊት ስለሚሆነው ነገር ራእይ ተመልክቷል። ዳንኤል ከተናገራቸው ትንቢቶች መካከል ዋና ዋናዎቹ በመሲሑና በአገዛዙ ላይ ያተኮሩ ናቸው።
ዳንኤል መሲሑ የሚገለጥበትን ጊዜ አወቀ። የአምላክ ሕዝቦች “ገዥው መሲሕ” ይገለጣል ብለው መጠበቅ የሚችሉበትን ጊዜ ለዳንኤል ተነግሮት ነበር፤ ዳንኤል የኢየሩሳሌምን ቅጥር ለማደስና ለመጠገን ትእዛዝ ከወጣ ከ69 የዓመታት ሳምንታት በኋላ መሲሑ እንደሚገለጥ አውቆ ነበር። አንድ ሳምንት ወይም ሱባዔ፣ ሰባት ቀኖችን የያዘ በመሆኑ አንድ የዓመታት ሳምንት ሰባት ዓመትን የያዘ ይሆናል። የኢየሩሳሌም ቅጥር እንዲታደስና እንዲጠገን ትእዛዝ የወጣው ዳንኤል ከሞተ ከረጅም ጊዜ በኋላ ይኸውም በ455 ዓ.ዓ. ነበር። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ 69 “ሱባዔ” ማለትም 483 ዓመታት ስንቆጥር 29 ዓ.ም. ላይ ያደርሰናል። በዚያ ዓመት ምን እንደተከናወነ በቀጣዩ ክፍል ላይ እንመለከታለን። ዳንኤል መሲሑ ኃጢአትን ለማስተሰረይ ‘እንደሚገደልም’ አስቀድሞ ተመልክቶ ነበር።—ዳንኤል 9:24-26
መሲሑ በሰማይ ንጉሥ ይሆናል። ዳንኤል በሰማይ ያለውን ነገር በራእይ የመመልከት ልዩ መብት ያገኘ ሲሆን “የሰውን ልጅ የሚመስል” ተብሎ የተጠራው መሲሑ ወደ ይሖዋ ዙፋን ሲቀርብ ተመልክቷል። ይሖዋ ለመሲሑ “ግዛትና ክብር፣ መንግሥት” [የ1954 ትርጉም] ሰጠው። ይህ መንግሥት ለዘላለም ይገዛል። ዳንኤል ስለ መሲሐዊው መንግሥት ሌላም የሚያስደንቅ ነገር ማወቅ ችሏል፦ ንጉሡ በመንግሥቱ ላይ የሚገዛው ‘የልዑሉ ቅዱሳን’ ተብለው ከተጠሩ ሰዎች ጋር በመሆን ነው።—ዳንኤል 7:13, 14, 27
ይህ መንግሥት የዚህን ዓለም መንግሥታት ያጠፋል። የባቢሎን ንጉሥ የነበረው ናቡከደነፆር ግራ እንዲጋባ ያደረገውን አንድ ሕልም የመተርጎም ችሎታ አምላክ ለዳንኤል ሰጥቶት ነበር። ንጉሡ በሕልሙ አንድ ግዙፍ ምስል ያየ ሲሆን የምስሉ ራስ ከወርቅ፣ ደረቱና ክንዶቹ ከብር፣ ሆዱና ጭኖቹ ከነሐስ፣ ቅልጥሞቹ ከብረት፣ እግሮቹ ደግሞ ከሸክላ ጋር ከተቀላቀለ ብረት የተሠሩ ነበሩ። ከተራራ ላይ የተፈነቀለ አንድ ድንጋይ ጠንካራ ያልሆነውን የምስሉን እግር ሲመታው ምስሉ ተሰባብሮ አመድ ሆነ። ዳንኤል፣ የምስሉ ክፍሎች በወርቅ ራስ ከተመሰለው ከባቢሎን ጀምሮ በየተራ የተፈራረቁትን ኃያላን የዓለም መንግሥታት እንደሚያመለክቱ ገለጸ። የመጨረሻዎቹ የዚህ ክፉ ዓለም መንግሥታት በሚገዙበት ዘመን የአምላክ መንግሥት እርምጃ እንደሚወስድ ዳንኤል ተመልክቷል። የአምላክ መንግሥት የዚህን ዓለም መንግሥታት በሙሉ ያደቃል። ከዚያም ለዘላለም ይገዛል።—ዳንኤል ምዕራፍ 2
ዳንኤል ዕድሜው ከገፋ በኋላ ባቢሎን ስትወድቅ ተመልክቷል። ነቢያት አስቀድመው በትንቢት እንደተናገሩት ንጉሥ ቂሮስ ባቢሎንን ድል አደረጋት። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ አይሁድ ከምርኮ ነፃ ወጡ፤ ይህ የሆነው በትንቢት በተነገረው መሠረት የትውልድ አገራቸው ባድማ ሆና የምትቆይባቸው 70 ዓመታት እንዳበቁ ነበር። ከጊዜ በኋላ የአይሁድ ሕዝብ ታማኝ በሆኑ ገዥዎች፣ ካህናትና ነቢያት እየተመሩ ኢየሩሳሌምንና የይሖዋን ቤተ መቅደስ እንደገና ገነቡ። ይሁንና በትንቢት የተነገሩት 483 ዓመታት ሲያበቁ ምን ይፈጸማል?
—በዳንኤል መጽሐፍ ላይ የተመሠረተ።