በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ክፍል 7

አምላክ እስራኤላውያንን ነፃ አወጣቸው

አምላክ እስራኤላውያንን ነፃ አወጣቸው

ይሖዋ ግብፅን በተለያዩ መቅሰፍቶች ሲመታ ሙሴ የእስራኤልን ልጆች እየመራ ከዚያ አወጣቸው። አምላክ በሙሴ በኩል ለእስራኤላውያን ሕግ ሰጣቸው

የእስራኤል ልጆች በግብፅ ውስጥ ለብዙ ዓመታት የኖሩ ሲሆን ቁጥራቸው እየጨመረና እየበለጸጉ ሄዱ። ይሁን እንጂ ከጊዜ በኋላ ሌላ ፈርዖን ሥልጣን ያዘ። ይህ ንጉሥ ዮሴፍን አያውቀውም ነበር። እስራኤላውያን መብዛታቸው ያስፈራው ይህ አረመኔና አምባገነን ገዥ፣ እነዚህን ሕዝቦች ባሪያዎች ያደረጋቸው ከመሆኑም በላይ የሚወልዷቸው ወንዶች ልጆች በሙሉ አባይ ወንዝ ውስጥ ተጥለው እንዲሞቱ አዘዘ። ይሁንና ደፋር የሆነች አንዲት እናት፣ ሕፃን ልጇን በቅርጫት ውስጥ አስቀምጣ በወንዙ ዳር ባለው ቄጠማ መካከል በመደበቅ እንዳይገደል አደረገች። የፈርዖን ሴት ልጅ ይህን ሕፃን አገኘችው፤ እሷም ሕፃኑን ሙሴ ብላ የሰየመችው ሲሆን በግብፅ የንጉሣውያን ቤተሰብ መካከል አሳደገችው።

ሙሴ 40 ዓመት ሲሞላው፣ አንድን እስራኤላዊ ጨቋኝ ከሆነው ግብፃዊ አሠሪው ለማዳን ባደረገው ጥረት ችግር ውስጥ ገባ። በዚህም የተነሳ ከግብፅ ሸሽቶ ሩቅ አገር በመሄድ በግዞት መኖር ጀመረ። ሙሴ 80 ዓመት ሲሆነው ፈርዖን ፊት ቀርቦ የአምላክን ሕዝቦች እንዲለቃቸው እንዲጠይቅ ይሖዋ ወደ ግብፅ ላከው።

ፈርዖን ግን እስራኤላውያንን ለመልቀቅ አሻፈረኝ አለ። በዚህም ምክንያት አምላክ ግብፅን በአሥር መቅሠፍቶች መታ። እያንዳንዱ መቅሠፍት ከመምጣቱ በፊት ፈርዖን ሐሳቡን እንዲቀይርና ሌላ መቅሠፍት እንዳይመጣባቸው የማድረግ አጋጣሚ እንዲያገኝ ሲል ሙሴ በፊቱ ቀርቦ ቢያነጋግረውም ፈርዖን እሱንም ሆነ የላከውን አምላክ ባለመስማት በእምቢተኝነቱ ገፋበት። በመጨረሻም በአሥረኛው መቅሠፍት በአገሪቱ የነበሩት የበኩር ልጆች በሙሉ ሞቱ፤ በዚህ መቅሠፍት ያልተነኩት መሥዋዕት የሆነውን ጠቦት ደም በበሮቻቸው መቃንና ጉበኖች ላይ በመቀባት ይሖዋን የታዘዙት ቤተሰቦች ብቻ ነበሩ። የበኩር ልጆችን እንዲያጠፋ አምላክ የላከው መልአክ እነዚህን ቤተሰቦች ሳይነካቸው አለፈ። ከዚያ በኋላ እስራኤላውያን አስደናቂ በሆነ መንገድ የዳኑበትን ይህን ቀን ለማሰብ ፋሲካ ተብሎ የሚጠራውን በዓል በየዓመቱ ማክበር ጀመሩ።

ፈርዖን የበኩር ልጁ ከሞተ በኋላ ሙሴም ሆነ እስራኤላውያን በሙሉ ግብፅን ለቀው እንዲወጡ አዘዘ። ወዲያውኑ ሥፍር ቁጥር የሌለው ሕዝብ ከግብፅ ወጣ። ይሁን እንጂ ብዙም ሳይቆይ ፈርዖን ሐሳቡን ለወጠ። ብዙ ጦረኞችንና ሠረገሎችን አስከትሎ እስራኤላውያንን ያሳድዳቸው ጀመር። እስራኤላውያን የቀይ ባሕር ዳርቻ ጋ ሲደርሱ አጣብቂኝ ውስጥ የገቡ ይመስል ነበር። ሆኖም ይሖዋ ቀይ ባሕርን በመክፈል ውኃው በቀኝና በግራ እንደ ግድግዳ እንዲቆምና ሕዝቡ በባሕሩ መካከል በደረቅ መሬት ላይ እንዲሻገሩ አደረገ! ግብፃውያን ከኋላቸው ተከትለው ወደ ባሕሩ ሲገቡ አምላክ ውኃውን ወደ ቦታው እንዲመለስ ስላደረገው ፈርዖንና ሠራዊቱ ሰጠሙ።

ከተወሰነ ጊዜ በኋላ እስራኤላውያን በሲና ተራራ አጠገብ ሲሰፍሩ ይሖዋ ከእነሱ ጋር ቃል ኪዳን ገባ። አምላክ ሙሴን እንደ መካከለኛ በመጠቀም ለእስራኤላውያን በሁሉም የሕይወታቸው ዘርፎች መመሪያና ጥበቃ የሚሆኗቸውን ሕጎች ሰጣቸው። ሕዝቡ የአምላክን አመራር በታማኝነት እስከተቀበሉ ድረስ ይሖዋ ከእነሱ ጋር ይሆናል፤ እንዲሁም ብሔሩን ለሌሎች ሕዝቦች በረከት እንዲሆን ያደርገዋል።

ይሁን እንጂ አብዛኞቹ እስራኤላውያን እምነት የለሾች በመሆን አምላክን አሳዘኑት። በዚህም ምክንያት ይሖዋ ያንን ትውልድ ለ40 ዓመታት በምድረ በዳ እንዲንከራተት አደረገው። ከዚያም ሙሴ፣ ጻድቅ ሰው የነበረውን ኢያሱን በእሱ ምትክ ሕዝቡን እንዲመራ ሾመው። በመጨረሻም እስራኤላውያን፣ አምላክ ለአብርሃም ቃል ገብቶለት ወደነበረው ምድር ለመግባት ዝግጁ ሆኑ።

በዘፀአትበዘሌዋውያንበዘኍልቍና በዘዳግም መጻሕፍት እንዲሁም በመዝሙር 136:10-15 እና በሐዋርያት ሥራ 7:17-36 ላይ የተመሠረተ።