በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ክፍል 17

ኢየሱስ ስለ አምላክ መንግሥት አስተማረ

ኢየሱስ ስለ አምላክ መንግሥት አስተማረ

ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ብዙ ነገሮችን ያስተማረ ቢሆንም ይበልጥ ትኩረት ያደረገው በአንድ ጭብጥ ይኸውም በአምላክ መንግሥት ላይ ነው

ኢየሱስ በምድር ላይ እንዲያከናውን የተሰጠው ተልእኮ ምን ነበር? እሱ ራሱ እንዲህ ብሏል፦ “የአምላክን መንግሥት ምሥራች ማወጅ አለብኝ፤ ምክንያቱም የተላክሁት ለዚህ ዓላማ ነው።” (ሉቃስ 4:43) ኢየሱስ የስብከቱ ዋና ጭብጥ ስለሆነው ስለ አምላክ መንግሥት ያስተማራቸውን አራት ነገሮች እንመልከት።

1. የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ኢየሱስ ነው። ኢየሱስ በትንቢት የተነገረለት መሲሕ እሱ መሆኑን በቀጥታ ተናግሯል። (ዮሐንስ 4:25, 26) በተጨማሪም ኢየሱስ፣ ነቢዩ ዳንኤል በራእይ ያየው ንጉሥ እሱ መሆኑን ገልጿል። ኢየሱስ ወደፊት “ክብር በተላበሰው ዙፋኑ” ላይ እንደሚቀመጥ ለሐዋርያቱ የነገራቸው ከመሆኑም ሌላ እነሱም በዙፋኖች ላይ እንደሚቀመጡ ገልጾላቸዋል። (ማቴዎስ 19:28) ከእሱ ጋር በዙፋኖች ላይ ተቀምጠው የሚገዙትን ሰዎች ያቀፈውን ቡድን “ትንሽ መንጋ” በማለት የጠራው ሲሆን የዚህ ቡድን አባላት ያልሆኑ “ሌሎች በጎች” እንዳሉትም ተናግሯል።—ሉቃስ 12:32፤ ዮሐንስ 10:16

2. የአምላክ መንግሥት እውነተኛ ፍትሕን ያሰፍናል። ይህ መንግሥት፣ የይሖዋ አምላክን ስም በመቀደስና ሰይጣን በኤደን ዓመፅ ካስነሳበት ጊዜ ጀምሮ በስሙ ላይ የተሰነዘረውን ነቀፋ በሙሉ በማስወገድ ከሁሉ የከፋውን የፍትሕ መጓደል እንደሚያስተካክል ኢየሱስ ጠቁሟል። (ማቴዎስ 6:9, 10) ከዚህም በተጨማሪ ኢየሱስ ወንድ ሴት፣ ሀብታም ድሃ ሳይል ሁሉንም በማስተማር የማያዳላ ሰው መሆኑን በዕለት ተዕለት ሕይወቱ አሳይቷል። የኢየሱስ ዋነኛ ተልእኮ እስራኤላውያንን ማስተማር ቢሆንም ሳምራውያንንና አሕዛብን ወይም አይሁድ ያልሆኑ ሰዎችን ለመርዳትም ጥረት አድርጓል። በዘመኑ ከነበሩት የሃይማኖት መሪዎች በተለየ መልኩ ኢየሱስ ምንም ዓይነት አድልዎ አላደረገም።

3. የአምላክ መንግሥት የዚህ ዓለም ክፍል አይደለም። ኢየሱስ በምድር ላይ በኖረበት ወቅት ፖለቲካዊ ብጥብጥ ነበር። የትውልድ አገሩ በሌላ መንግሥት ቅኝ ግዛት ሥር ነበረች። ሆኖም አንዳንድ ሰዎች በወቅቱ በነበረው ፖለቲካዊ ጉዳይ ውስጥ ኢየሱስ ጣልቃ እንዲገባ ለማድረግ በሞከሩ ጊዜ ከእነሱ ገለል ብሏል። (ዮሐንስ 6:14, 15) ኢየሱስ ለአንድ የፖለቲካ ሰው “መንግሥቴ የዚህ ዓለም ክፍል አይደለም” ብሎታል። (ዮሐንስ 18:36) ተከታዮቹን ደግሞ ‘የዓለም ክፍል አይደላችሁም’ ብሏቸዋል። (ዮሐንስ 15:19) ተከታዮቹ እሱን ከጥቃት ለመከላከል እንኳ የጦር መሣሪያ እንዲጠቀሙ አልፈቀደላቸውም።—ማቴዎስ 26:51, 52

“የአምላክን መንግሥት ምሥራች እየሰበከና እያወጀ . . . ከመንደር ወደ መንደር ይጓዝ ነበር።”ሉቃስ 8:1

4. የክርስቶስ አገዛዝ በፍቅር ላይ የተመሠረተ ይሆናል። ኢየሱስ ለሰዎች እረፍት እንደሚሰጣቸውና ሸክማቸውን እንደሚያቀልላቸው ቃል ገብቷል። (ማቴዎስ 11:28-30) ደግሞም ቃሉን ጠብቋል። ጭንቀትን ለመቋቋምና ፍቅረ ንዋይን ለመዋጋት እንዲሁም ደስታ ለማግኘትና ከሰዎች ጋር ጥሩ ግንኙነት ለመመሥረት የሚረዱ ተግባራዊ መሆን የሚችሉ ምክሮችን ኢየሱስ በፍቅር ተነሳስቶ ሰጥቷል። (ማቴዎስ ምዕራፍ 5 እስከ ምዕራፍ 7) ኢየሱስ ለሰዎች ፍቅር ያሳይ ስለነበር የተለያየ የኑሮ ሁኔታ ያላቸው ሰዎች ወደ እሱ መቅረብ አልከበዳቸውም። በግፍ የተጨቆኑ ሰዎችም እንኳ እሱ በደግነትና በክብር እንደሚይዛቸው እርግጠኞች ስለነበሩ ወደ እሱ ይመጡ ነበር። ኢየሱስ ግሩም መሪ እንደሚሆን በግልጽ መመልከት ይቻል ነበር!

ኢየሱስ ስለ አምላክ መንግሥት ያስተማረበት ሌላም ግሩም መንገድ አለ። ብዙ ተአምራትን ፈጽሟል። እንዲህ ያደረገው ለምን ነበር? ይህን በሚቀጥለው ክፍል ላይ እንመለከታለን።

በማቴዎስ፣ በማርቆስ፣ በሉቃስና በዮሐንስ መጻሕፍት ላይ የተመሠረተ።