ክፍል 3
የሰው ዘር ከጥፋት ውኃ ዳነ
አምላክ ክፉውን ዓለም ሲያጠፋ ኖኅንና ቤተሰቡን አዳናቸው
የሰው ዘር እየበዛ ሲሄድ ኃጢአትና ክፋትም በምድር ላይ በፍጥነት ተስፋፋ። ሄኖክ የሚባል አንድ ነቢይ፣ አምላክ ክፉ ሰዎችን የሚያጠፋበት ቀን እንደሚመጣ ብቻውን ሆኖ ያስጠነቅቅ ነበር። ያም ሆኖ ክፋት እየተስፋፋ እንዲያውም እየተባባሰ ሄደ። አንዳንድ መላእክት በሰማይ የተሰጣቸውን ቦታ ትተው ሰብዓዊ አካል ለብሰው ወደ ምድር በመምጣትና የሰው ሴቶች ልጆችን በማግባት በይሖዋ ላይ ዓመፁ። ከተፈጥሮ ውጪ ከሆነው ከዚህ ዓይነቱ ጋብቻ የተገኙት ኔፊሊም ተብለው የሚጠሩ ልጆች በጣም ግዙፍና ጉልበተኛ ነበሩ፤ እነሱም ዓመፅ እንዲባባስና ምድር በደም መፋሰስ እንድትሞላ አደረጉ። አምላክ በምድር ላይ ያለው ፍጥረቱ ምን ያህል እንደተበላሸ ሲመለከት እጅግ አዘነ።
ሄኖክ ከሞተ በኋላም ክፉ በሆነው በዚያ ዓለም ውስጥ ከሌሎች የተለየ አቋም ያለው አንድ ሰው ነበረ። ስሙ ኖኅ ይባላል። እሱና ቤተሰቡ በአምላክ ፊት ትክክል የሆነውን ለማድረግ ይጥሩ ነበር። አምላክ በዚያ ወቅት የነበሩትን ክፉ ሰዎች ለማጥፋት ሲወስን ኖኅንና በምድር ላይ ያሉትን እንስሳት ለማዳን ፈለገ። ስለዚህ አራት ማዕዘን ቅርጽ ያለው አንድ ትልቅ መርከብ እንዲሠራ ለኖኅ ነገረው። ኖኅና ቤተሰቡ እንዲሁም በርካታ የእንስሳት ዝርያዎች በመርከቡ ውስጥ በመሆን አምላክ ከሚያመጣው ዓለም አቀፍ የጥፋት ውኃ ይድናሉ። ኖኅ አምላክን በመታዘዝ ቀጣዮቹን አሥርተ ዓመታት መርከቡን በመሥራት አሳለፈ፤ ከዚህም በተጨማሪ ኖኅ “የጽድቅ ሰባኪ” ነበረ። (2 ጴጥሮስ 2:5) ኖኅ የጥፋት ውኃ እንደሚመጣ ሕዝቡን ቢያስጠነቅቅም እነሱ ግን አልሰሙትም። በመጨረሻም ኖኅና ቤተሰቡ ከእንስሳቱ ጋር ወደ መርከቡ የሚገቡበት ጊዜ ደረሰ። አምላክ የመርከቡን በር ዘጋው። ከዚያም ዝናቡ መጣል ጀመረ።
መላዋ ምድር በውኃ እስክትሸፈን ድረስ ለ40 ቀንና ለ40 ሌሊት ኃይለኛ ዝናብ ጣለ። በዚህ መንገድ ክፉዎቹ ሰዎች ጠፉ። የተወሰኑ ወራት ካለፉ በኋላ ውኃው እየጎደለ ሲሄድ መርከቡ በአንድ ተራራ ላይ አረፈ። ኖኅና ቤተሰቡ እንዲሁም አብረዋቸው የነበሩት እንስሳት በመርከቡ ውስጥ አንድ ዓመት ሙሉ ከቆዩ በኋላ ከመርከቡ ወጡ። ከዚያም ኖኅ ይሖዋን ለማመስገን መሥዋዕት አቀረበ። አምላክም ሕይወት ያለውን ሁሉ ከምድር ገጽ ለማጥፋት ዳግመኛ የጥፋት ውኃ እንደማያመጣ ለኖኅና ለቤተሰቡ ቃል ገባላቸው። ይሖዋ ይህንን የሚያጽናና ቃል ኪዳን ለማስታወስ ምልክት እንዲሆን ቀስተ ደመናን ሰጠ።
ከጥፋት ውኃው በኋላ አምላክ ለሰው ልጆች አዳዲስ ትእዛዛትንም ሰጣቸው። የእንስሳትን ሥጋ እንዲበሉ ፈቀደላቸው። ይሁን እንጂ ደም እንዳይበሉ ከልክሏቸው ነበር። በተጨማሪም የኖኅ ዝርያዎች በምድር ሁሉ ተበትነው ምድርን እንዲሞሏት አዘዛቸው፤ አንዳንዶቹ ግን ለመታዘዝ ፈቃደኞች አልነበሩም። ሰዎች ናምሩድ የሚባለውን መሪ በመከተል፣ ከጊዜ በኋላ ባቢሎን ተብላ በተጠራችው በባቤል ከተማ አንድ ትልቅ ግንብ መሥራት ጀመሩ። ዓላማቸው አምላክ በመላው ምድር ተበትነው እንዲኖሩ የሰጣቸውን ትእዛዝ መቃወም ነበር። ይሁን እንጂ አምላክ፣ እነዚህ ዓመፀኞች አንድ ቋንቋ ከመናገር ይልቅ በተለያዩ ልሳኖች እንዲናገሩ በማድረግ እቅዳቸውን አከሸፈው። ሰዎቹ እርስ በርስ መግባባት ስላቃታቸው የጀመሩትን ግንባታ ትተው ተበታተኑ።
—በዘፍጥረት ምዕራፍ 6 እስከ ምዕራፍ 11 እና በይሁዳ 14, 15 ላይ የተመሠረተ።