ክፍል 22
ሐዋርያት በድፍረት ሰበኩ
የክርስቲያን ጉባኤ ስደት ቢያጋጥመውም በፍጥነት እያደገ ሄደ
ኢየሱስ ወደ ሰማይ ካረገ ከአሥር ቀናት በኋላ በ33 ዓ.ም. በተከበረው ጴንጤቆስጤ የተባለ የአይሁድ በዓል ዕለት 120 የሚያህሉ ደቀ መዛሙርት ኢየሩሳሌም በሚገኝ አንድ ቤት ውስጥ ተሰብስበው ነበር። ድንገትም እንደ ኃይለኛ ነፋስ ያለ ድምፅ ቤቱን ሞላው። ደቀ መዛሙርቱ በማያውቋቸው ቋንቋዎች ተአምራዊ በሆነ መንገድ መናገር ጀመሩ። እንዲህ ያለው አስገራሚ ክስተት ሊፈጸም የቻለው እንዴት ነው? አምላክ በደቀ መዛሙርቱ ላይ መንፈስ ቅዱስን ስላወረደ ነው።
የጴንጤቆስጤ በዓልን ለማክበር ከተለያየ አገር የመጡ በጣም ብዙ ሰዎች ተሰብስበው ነበር። እነዚህ ሰዎች በገዛ ቋንቋቸው የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ሲናገሩ በመስማታቸው በጣም ተገረሙ። ጴጥሮስ የተከናወነውን ነገር ሲያብራራ አምላክ ‘መንፈሱን እንደሚያፈስ’ በነቢዩ ኢዩኤል በኩል የተናገረውን ትንቢት ጠቅሷል፤ ይህ መንፈስ የወረደባቸው ሰዎች ተአምራዊ ስጦታዎችን ይቀበላሉ። (ኢዩኤል 2:28, 29) መንፈስ ቅዱስ በደቀ መዛሙርቱ ላይ መውረዱን የሚጠቁመው ይህ ጠንካራ ማስረጃ ታላቅ ለውጥ እንደተከናወነ በግልጽ ያሳያል፤ ይህም አምላክ የእስራኤልን ብሔር ትቶ አዲስ የተቋቋመውን የክርስቲያን ጉባኤ መቀበሉ ነው። ከዚህ በኋላ አምላክን እሱ በሚቀበለው መንገድ ለማገልገል የሚፈልጉ ሁሉ የክርስቶስ ተከታዮች መሆን አለባቸው።
በዚህ ጊዜ በደቀ መዛሙርቱ ላይ የተነሳው ተቃውሞ እየተባባሰ የመጣ ሲሆን ጠላቶቻቸው እስር ቤት አስገቧቸው። ይሁን እንጂ አንድ የይሖዋ መልአክ በሌሊት መጥቶ ለደቀ መዛሙርቱ የእስር ቤቱን በር ከከፈተላቸው በኋላ ስብከታቸውን እንዲቀጥሉ ነገራቸው። በማግስቱ ደቀ መዛሙርቱ መስበካቸውን ቀጠሉ። ወደ ቤተ መቅደሱ በመግባት ስለ ኢየሱስ የሚናገረውን ምሥራች ማስተማር ጀመሩ። የሚቃወሟቸው ሃይማኖታዊ መሪዎች በዚህ እጅግ ተቆጥተው መስበካቸውን እንዲያቆሙ አዘዟቸው። ሐዋርያቱ ግን “ከሰው ይልቅ አምላክን እንደ ገዥያችን አድርገን ልንታዘዝ ይገባል” በማለት በድፍረት መለሱላቸው።—የሐዋርያት ሥራ 5:28, 29
ስደቱ ይበልጥ እየተባባሰ ሄደ። አንዳንድ አይሁዳውያን ‘አምላክን ተሳድበሃል’ ብለው ደቀ መዝሙሩን እስጢፋኖስን በመወንጀል በድንጋይ ወግረው ገደሉት። ሳኦል የተባለ አንድ የጠርሴስ ሰው በእስጢፋኖስ መገደል በመስማማት ቆሞ ይመለከታቸው ነበር። ከዚያም ይህ ወጣት፣ የክርስቶስ ተከታይ የሆኑ ሰዎችን ሁሉ ለማሰር ወደ ደማስቆ ሄደ። ሳኦል ወደ ደማስቆ እየተጓዘ ሳለ ከሰማይ የመጣ ብርሃን በዙሪያው አንጸባረቀ፤ ከዚያም “ሳኦል፣ ሳኦል ለምን ታሳድደኛለህ?” የሚል ድምፅ ሰማ። በብርሃኑ ምክንያት የታወረው ሳኦል “አንተ ማን ነህ?” በማለት ጠየቀ። እሱም “ኢየሱስ ነኝ” አለው።—የሐዋርያት ሥራ 9:3-5
ከሦስት ቀናት በኋላ ኢየሱስ፣ የሳኦልን ዓይን እንዲያበራለት ሐናንያ የተባለውን ደቀ መዝሙር ላከው። ሳኦል ከተጠመቀ በኋላ ስለ ኢየሱስ በድፍረት መስበክ ጀመረ። ከጊዜ በኋላ ሳኦል፣ ሐዋርያው ጳውሎስ ተብሎ የተጠራ ሲሆን በቅንዓት የሚያገለግል የክርስቲያን ጉባኤ አባል ሆነ።
የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት መጀመሪያ ላይ የአምላክን መንግሥት ምሥራች የሚሰብኩት ለአይሁዳውያንና ለሳምራውያን ብቻ ነበር። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ አንድ መልአክ፣ ፈሪሃ አምላክ ላለው ቆርኔሌዎስ የተባለ የሮም ሠራዊት መቶ አለቃ ከተገለጠለት በኋላ ሐዋርያው ጴጥሮስን እንዲያስጠራው ነገረው። ጴጥሮስ ከሌሎች የእምነት ባልንጀሮቹ ጋር በመሆን ለቆርኔሌዎስና ለቤተሰቦቹ ሰበከላቸው። ጴጥሮስ እየተናገረ እያለ ከአሕዛብ ወገን በሆኑት በእነዚህ አማኞች ላይ መንፈስ ቅዱስ ወረደባቸው፤ በዚህ ጊዜ ሐዋርያው በኢየሱስ ስም እንዲጠመቁ አዘዛቸው። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራው መንገድ ከሁሉም ብሔራት ለተውጣጡ ሰዎች ክፍት ሆነ። የክርስቲያን ጉባኤ ምሥራቹን በስፋት ለመስበክ ተዘጋጅቶ ነበር።
—በሐዋርያት ሥራ 1:1 እስከ 11:21 ላይ የተመሠረተ።