ይሖዋን ፍራ ትእዛዙንም ጠብቅ

ይሖዋን ፍራ ትእዛዙንም ጠብቅ

ይሖዋን ፍራ ትእዛዙንም ጠብቅ

ይህ የሰው ሁለንተናው [“ሁለንተናዊ ግዴታው፣” Nw ] ነውና፤ እግዚአብሔርን ፍራ፣ ትእዛዙንም ጠብቅ።”​—⁠መክብብ 12:13

1, 2. (ሀ) ፍርሃት አካላዊ ጉዳት እንዳይደርስብን ሊጠብቀን የሚችለው እንዴት ነው? (ለ) አስተዋይ የሆኑ ወላጆች በልጆቻቸው አእምሮ ጤናማ ፍርሃት ለመቅረጽ የሚጥሩት ለምንድን ነው?

 ሊዮናርዶ ዳ ቪንቺ “ድፍረት ሕይወትን ለአደጋ ሊያጋልጥ እንደሚችል ሁሉ ፍርሃት ከአደጋ ሊጠብቅ ይችላል” ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል። አጉል ድፍረት ወይም ጀብደኝነት አንድ ሰው ዓይኑን ጨፍኖ አደጋ ውስጥ እንዲገባ የሚያደርገው ሲሆን ፍርሃት ግን ቆም ብሎ እንዲያስብ ያደርገዋል። ለምሳሌ ያህል ጭው ያለ ገደል አፋፍ ላይ ቆመን ወደታች ብንመለከት አብዛኞቻችን በደመ ነፍስ ወደኋላ እንደምናፈገፍግ የታወቀ ነው። በተመሳሳይም ጤናማ ፍርሃት ማዳበር ከአምላክ ጋር ጥሩ ዝምድና እንዲኖረን ማድረግ ብቻ ሳይሆን ቀደም ባለው ርዕሰ ትምህርት ላይ እንደተመለከተው ከጉዳት እንድንርቅም ይረዳናል።

2 ሆኖም በዛሬው ዘመናዊ ዓለም ውስጥ ካሉት ብዙ አደገኛ ሁኔታዎች ጋር በተያያዘ የሚያድርብን ፍርሃት በትምህርት የምናገኘው ነው። ትንንሽ ልጆች ስለ ኤሌክትሪክ ወይም ስለ መኪና አደጋ ስለማያውቁ በቀላሉ ከባድ ጉዳት ሊደርስባቸው ይችላል። a አስተዋይ የሆኑ ወላጆች በአካባቢያቸው ስለሚገኙ አደጋ ሊያስከትሉ ስለሚችሉ ነገሮች ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ በመስጠት በልጆቻቸው አእምሮ ውስጥ ጤናማ ፍርሃት ለመቅረጽ ይጥራሉ። ወላጆች ይህ ዓይነቱ ፍርሃት የልጆቻቸውን ሕይወት ከአደጋ ሊታደግ እንደሚችል ያውቃሉ።

3. ይሖዋ መንፈሳዊ አደጋ እንዳይደርስብን የሚያስጠነቅቀን ለምንና እንዴት ነው?

3 በተመሳሳይም ይሖዋ ስለ እኛ ደህንነት በጣም ያስባል። አፍቃሪ አባት እንደመሆኑ መጠን በቃሉና በድርጅቱ አማካኝነት የሚረባንን ነገር ያስተምረናል። (ኢሳይያስ 48:17) የዚህ መለኮታዊ ትምህርት ፕሮግራም አንዱ ገጽታ መንፈሳዊ ወጥመዶች ለሚያስከትሉት አደጋዎች ጤናማ ፍርሃት ማዳበር እንችል ዘንድ “በተደጋጋሚ” ማስጠንቀቂያ መስጠትን የሚጨምር ነው። (2 ዜና መዋዕል 36:15 NW ፤ 2 ጴጥሮስ 3:1) ‘ሰዎች አምላክን የሚፈራና ትእዛዛቱን የሚጠብቅ ልብ ቢኖራቸው’ ኖሮ በታሪክ ዘመናት ሁሉ የታዩትን ብዙዎቹን መንፈሳዊ ውድቀቶችና የተለያዩ ሥቃዮች ማስቀረት በተቻለ ነበር። (ዘዳግም 5:29) ‘በዚህ አስጨናቂ ዘመን’ ልባችን አምላክን እንዲፈራና መንፈሳዊ አደጋ እንዳይደርስብን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?​—⁠2 ጢሞቴዎስ 3:​1

ከክፉ ሽሽ

4. (ሀ) ክርስቲያኖች ሊኮተኩቱት የሚገባ ጥላቻ የትኛው ነው? (ለ) መጥፎ ድርጊትን በተመለከተ ይሖዋ የሚሰማው እንዴት ነው? (የግርጌ ማስታወሻውን ተመልከት።)

4 መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔርን መፍራት ክፋትን መጥላት ነው” በማለት ይገልጻል። (ምሳሌ 8:13 አ.መ.ት) አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ይህን ጥላቻ “ለምንቃወመው፣ ለምንጠላው፣ ለምንጸየፈው እንዲሁም ምንም ዓይነት ንክኪ ወይም ግንኙነት እንዲኖረን ለማንፈልገው ሰው ወይም ነገር የሚኖረን ስሜታዊ ዝንባሌ” ሲል ገልጾታል። ስለዚህ አምላካዊ ፍርሃት ይሖዋ ለሚጠላቸው ነገሮች በሙሉ ከፍተኛ ጥላቻ ወይም የመጸየፍ ስሜት ማሳደርን ይጨምራል። b (መዝሙር 97:10) በተፈጥሮ ያለን የፍርሃት ስሜት ማስጠንቀቂያ ሲሰጠን ከገደሉ አፋፍ ወደኋላ እንደምናፈገፍግ ሁሉ አምላካዊ ፍርሃትም ከክፉ እንድንሸሽ ያደርገናል። መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔርንም በመፍራት ሰው ከክፋት ይመለሳል” ይላል።​—⁠ምሳሌ 16:6

5. (ሀ) ለአምላክ ያለንን ፍርሃትና ለመጥፎ ነገር ያለንን ጥላቻ ይበልጥ ማጠናከር የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) በዚህ ረገድ የእስራኤል ብሔር ታሪክ ምን ያስተምረናል?

5 ኃጢአት የሚያስከትለውን መዘዝ በማሰብ ለመጥፎ ነገር ያለንን ጤናማ የሆነ ፍርሃትና ጥላቻ ይበልጥ ማጠናከር እንችላለን። በሥጋም እንዝራ በመንፈስ፣ መጽሐፍ ቅዱስ የዘራነውን እንደምናጭድ ያረጋግጥልናል። (ገላትያ 6:7, 8) ስለሆነም ይሖዋ ትእዛዛቱን ችላ ማለትና እውነተኛውን አምልኮ መተው የሚያስከትለውን ውጤት በማያሻማ መንገድ ገልጾልናል። መለኮታዊ ጥበቃ ባይኖረው ኖሮ አቅመ ቢስ የነበረው የእስራኤል ብሔር ጨካኝና ኃያል በነበሩት ጎረቤቶቹ እጅ ይወድቅ ነበር። (ዘዳግም 28:15, 45-48) የእስራኤላውያን ዓመፀኝነት ያስከተለው አሳዛኝ ውጤት ‘ማስጠንቀቂያ’ እንዲሆን ማለትም ለእኛ ትምህርት እንዲሆነንና አምላካዊ ፍርሃት እንድንኮተኩት እንዲረዳን ሲባል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በዝርዝር ሰፍሮልናል።​—⁠1 ቆሮንቶስ 10:11

6. አምላካዊ ፍርሃትን ለመማር ልንመረምራቸው የምንችላቸው አንዳንድ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምሳሌዎች የትኞቹ ናቸው? (የግርጌ ማስታወሻውን ተመልከት።)

6 መጽሐፍ ቅዱስ በጠቅላላው የእስራኤል ብሔር ላይ ከደረሰው ሁኔታ ሌላ በቅናት፣ በሥነ ምግባር ብልግና፣ በስግብግብነት ወይም በኩራት የወደቁ ግለሰቦችን እውነተኛ የሕይወት ታሪክ ይዟል። c ከእነዚህ ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ ይሖዋን ለብዙ ዓመታት ያገለገሉ ነበሩ፤ ሆኖም በሕይወታቸው ውስጥ በአንድ ወሳኝ ወቅት ላይ ለአምላክ ያላቸው ፍርሃት የተፈለገውን ያህል ጠንካራ ሳይሆን በመቅረቱ አሳዛኝ ውድቀት ደርሶባቸዋል። በእነዚህ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምሳሌዎች ላይ ማሰላሰላችን ተመሳሳይ ስህተት ላለመድገም ያደረግነውን ቁርጥ ውሳኔ ሊያጠነክርልን ይችላል። አምላክ የሚሰጠውን ምክር ከመቀበል ይልቅ በራሳችን ላይ መከራ እስኪደርስ ድረስ ብንጠብቅ ምንኛ የሚያሳዝን ይሆናል! መከራ ይምከረው የሚለው የተለመደ አባባል በእኛ ላይ እንዲሠራ አንፈልግም።​—⁠መዝሙር 19:7

7. ይሖዋ በምሳሌያዊ ድንኳኑ ውስጥ እንዲያድር የሚጋብዘው ማንን ነው?

7 አምላካዊ ፍርሃትን እንድንኮተኩት የሚገፋፋን ሌላው ዋነኛ ምክንያት ከአምላክ ጋር ያለንን ዝምድና ጠብቀን ለማቆየት ያለን ፍላጎት ነው። ከይሖዋ ጋር ያለንን ወዳጅነት ከምንም ነገር በላይ ከፍ አድርገን ስለምንመለከት እሱን እንዳናሳዝነው እንፈራለን። አምላክ እንደ ወዳጁ አድርጎ በመመልከት በምሳሌያዊ ድንኳኑ ውስጥ እንዲያድር የሚጋብዘው ማንን ነው? ‘በቅንነት የሚሄደውንና ጽድቅን የሚያደርገውን’ ብቻ ነው። (መዝሙር 15:1, 2) ከፈጣሪያችን ጋር ያለንን ይህን ዝምድና ከፍ አድርገን የምንመለከተው ከሆነ በፊቱ ያለ ነቀፋ ለመመላለስ እንጠነቀቃለን።

8. በሚልክያስ ዘመን የነበሩ አንዳንድ እስራኤላውያን ከአምላክ ጋር የነበራቸውን ወዳጅነት ያቃለሉት እንዴት ነው?

8 የሚያሳዝነው በሚልክያስ ዘመን የነበሩ አንዳንድ እስራኤላውያን ከአምላክ ጋር የነበራቸውን ወዳጅነት አቃልለው ተመልክተውት ነበር። ይሖዋን በመፍራትና በማክበር ፋንታ በሽተኛና አንካሳ እንስሳ በመሠዊያው ላይ ያቀርቡ ነበር። ለጋብቻ የነበራቸው ዝንባሌም አምላካዊ ፍርሃት እንደሌላቸው የሚያንጸባርቅ ነበር። ወጣት ሚስቶችን ለማግባት ሲሉ በረባ ባልረባው የልጅነት ሚስቶቻቸውን ይፈቱ ነበር። ሚልክያስ፣ ይሖዋ “መፋታትን” እንደሚጠላና የአታላይነት መንፈሳቸው ከአምላክ እንዲርቁ እንዳደረጋቸው ነግሯቸዋል። በምሳሌያዊ አነጋገር መሠዊያው ባሎቻቸው የተዉአቸው ሚስቶች በሚያፈሱት የምሬት እንባ ርሶ ሳለ አምላክ የሚያቀርቡትን መሥዋዕት እንዴት ሊቀበል ይችላል? ላወጣቸው የአቋም ደረጃዎች ባሳዩት ዓይን ያወጣ ንቀት የተነሳ ይሖዋ “መፈራቴ ወዴት አለ?” ብሎ ለመጠየቅ ተገድዷል።​—⁠ሚልክያስ 1:6-8፤ 2:13-16

9, 10. ከይሖዋ ጋር ያለንን ወዳጅነት ከፍ አድርገን እንደምንመለከተው ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

9 ዛሬም በተመሳሳይ ራስ ወዳድና ምግባረ ብልሹ በሆኑ ባሎችና አባቶች አልፎ ተርፎም እናቶችና ሚስቶች በደረሰባቸው ከፍተኛ በደል ሳቢያ ልባቸው በሐዘን የተሰበረውን ብዙ ባለትዳሮች እንዲሁም ልጆች ይሖዋ ይመለከታል። በዚህ በጣም እንደሚያዝን ምንም ጥርጥር የለውም። የአምላክ ወዳጅ የሆነ ሰው ነገሮችን አምላክ በሚያይበት መንገድ የሚያይ ሲሆን የጋብቻ ቁርኝትን አቃልሎ የሚመለከተውን የዓለም አስተሳሰብ በማስወገድ ትዳሩን ለማጠንከር የተቻለውን ሁሉ ይጥራል፤ እንዲሁም ‘ከዝሙት ይሸሻል።’​—⁠1 ቆሮንቶስ 6:​18

10 በትዳርም ይሁን በሌላ የሕይወታችን ዘርፍ በይሖዋ ዓይን መጥፎ ለሆኑት ነገሮች ጥላቻ ካዳበርን እንዲሁም ከእርሱ ጋር ላለን ወዳጅነት የላቀ ግምት ከሰጠን የእሱን ሞገስና ተቀባይነት እናገኛለን። ሐዋርያው ጴጥሮስ “እግዚአብሔር ለሰው ፊት እንዳያደላ ነገር ግን በአሕዛብ ሁሉ እርሱን የሚፈራና ጽድቅን የሚያደርግ በእርሱ የተወደደ እንደ ሆነ በእውነት አስተዋልሁ” ሲል በእርግጠኝነት ተናግሯል። (ሥራ 10:34, 35) የተለያዩ ፈታኝ ሁኔታዎች የገጠሟቸው ሰዎች ትክክል የሆነውን ነገር እንዲያደርጉ አምላካዊ ፍርሃት የገፋፋቸው እንዴት እንደሆነ የሚያሳዩ በርካታ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምሳሌዎች አሉልን።

አምላክን ይፈሩ የነበሩ ሦስት ሰዎች

11. አብርሃም ‘እግዚአብሔርን የሚፈራ’ መሆኑን ያሳየው በምን ሁኔታ ሥር ነው?

11 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይሖዋ ራሱ ወዳጄ ብሎ የጠራው አንድ ሰው አለ። ይህ ሰው ፓትርያርኩ አብርሃም ነው። (ኢሳይያስ 41:8) አምላክ የአብርሃምን ዘር ታላቅ ሕዝብ ለማድረግ የገባውን ቃል የሚፈጽመው በይስሐቅ በኩል ሲሆን አብርሃም ይህን አንድያ ልጁን መሥዋዕት አድርጎ እንዲያቀርብ በተጠየቀ ጊዜ ለአምላክ የነበረው ፍርሃት ተፈተነ። (ዘፍጥረት 12:2, 3፤ 17:19) ‘የይሖዋ ወዳጅ’ ይህን ከባድ ፈተና ያልፍ ይሆን? (ያዕቆብ 2:23) አብርሃም ይስሐቅን ለማረድ ቢላዋውን ሲያነሳ የይሖዋ መልአክ እንደሚከተለው ሲል ተናገረ:- “በብላቴናው ላይ እጅህን አትዘርጋ፣ አንዳችም አታድርግበት፤ አንድ ልጅህን ለእኔ አልከለከልህምና እግዚአብሔርን የምትፈራ እንደ ሆንህ አሁን አውቄአለሁ።”​—⁠ዘፍጥረት 22:10-12

12. አብርሃም አምላካዊ ፍርሃት እንዲያሳይ ያነሳሳው ምንድን ነው? እኛም ተመሳሳይ መንፈስ ልናሳይ የምንችለው እንዴት ነው?

12 ምንም እንኳ አብርሃም ቀደም ሲልም ይሖዋን የሚፈራ መሆኑን ያስመሰከረ ቢሆንም በዚህ ጊዜ በላቀ ሁኔታ ይህን ባሕርይ አሳይቷል። ይስሐቅን መሥዋዕት ለማድረግ ፈቃደኛ የሆነው እንዲያው አክብሮታዊ ታዛዥነት ለማሳየት በመፈለግ ብቻ አልነበረም። አብርሃም ለተግባር የተነሳሳው ካስፈለገ አምላክ ይስሐቅን ከሞት በማስነሳት የገባውን ቃል መፈጸም እንደሚችል በሰማያዊ አባቱ ላይ ሙሉ ትምክህት ስለ ነበረው ነው። ጳውሎስ እንደጻፈው አብርሃም ‘እግዚአብሔር የሰጠውን ተስፋ ሊፈጽም እንደሚችል ሙሉ እምነት’ ነበረው። (ሮሜ 4:16-21) ትልቅ መሥዋዕትነት ሊጠይቅብን የሚችል ቢሆንም እንኳ የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ ዝግጁዎች ነን? ይሖዋ ‘ለሚፈልጉት ዋጋ እንደሚሰጥ’ በማወቅ እንዲህ ዓይነቱን ታዛዥነት ማሳየት ዘላቂ ጥቅም እንደሚያመጣ ሙሉ ትምክህት አለን? (ዕብራውያን 11:6) እውነተኛ አምላካዊ ፍርሃት ማለት ይህ ነው።​—⁠መዝሙር 115:11

13. ዮሴፍ ራሱን ‘እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው’ እንደሆነ አድርጎ መግለጹ ተገቢ የሆነው ለምንድን ነው?

13 አምላካዊ ፍርሃት እንዳለው በተግባር ያሳየውን ሌላውን ምሳሌያችንን ማለትም ዮሴፍን እንመልከት። ዮሴፍ በጶጢፋር ቤት አገልጋይ በነበረበት ጊዜ ዝሙት እንዲፈጽም በየዕለቱ ግፊት ይደረግበት ነበር። ከእርሷ ጋር ብልግና እንዲፈጽም ሳታሰልስ ትወተውተው ከነበረችው ከጌታው ሚስት መራቅ የሚችልበት አጋጣሚ የነበረው አይመስልም። በመጨረሻም አንድ ቀን ‘ልብሱን ተጠማጥማ ስትይዘው ሸሽቶ ወደ ውጭ ወጣ።’ ከክፉ በመሸሽ ረገድ አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስድ የገፋፋው ምንድን ነው? እንዲህ ዓይነት እርምጃ እንዲወስድ ያደረገው ነገር “ይህን ትልቅ ክፉ ነገር” ከመፈጸም ለመራቅ የነበረው ውስጣዊ ግፊት ማለትም አምላካዊ ፍርሃት እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም። (ዘፍጥረት 39:7-12) ዮሴፍ ራሱን ‘እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው’ እንደሆነ አድርጎ መግለጹ ተገቢ ነው።​—⁠ዘፍጥረት 42:18

14. ዮሴፍ ያሳየው ምሕረት እውነተኛ አምላካዊ ፍርሃት እንደነበረው የሚያንጸባርቀው እንዴት ነው?

14 ዮሴፍ ዓመታት ካለፉ በኋላ ያለ ርኅራኄ ለባርነት አሳልፈው ከሸጡት ወንድሞቹ ጋር በግንባር ተገናኘ። ወንድሞቹ የግድ ምግብ ማግኘት ስለነበረባቸው ዮሴፍ የፈጸሙበትን በደል ለመበቀል በቀላሉ ይህን አጋጣሚ ሊጠቀምበት ይችል ነበር። ሆኖም በሰዎች ላይ መጨከን አምላክን የሚፈራ ሰው ባሕርይ አይደለም። (ዘሌዋውያን 25:43) ስለዚህ ዮሴፍም ወንድሞቹ በእርግጥ እንደተለወጡ ሲመለከት በምሕረት ይቅር አላቸው። እንደ ዮሴፍ ሁሉ እኛም ለአምላክ ያለን ፍርሃት ክፉን በመልካም እንድናሸንፍ ሊያደርገን እንዲሁም በፈተና እንዳንወድቅ ሊጠብቀን ይችላል።​—⁠ዘፍጥረት 45:1-11፤ መዝሙር 130:3, 4፤ ሮሜ 12:17-21

15. የኢዮብ አኗኗር የይሖዋን ልብ ደስ ሊያሰኝ የቻለው ለምንድን ነው?

15 አምላክን በመፍራት ረገድ ኢዮብ ሌላው ጎልቶ የሚጠቀስ ምሳሌ ነው። ይሖዋ ለዲያብሎስ “በውኑ ባሪያዬን ኢዮብን ተመለከትኸውን? በምድር ላይ እንደ እርሱ ፍጹምና ቅን፣ እግዚአብሔርንም የሚፈራ፣ ከክፋትም የራቀ ሰው የለም” ብሎት ነበር። (ኢዮብ 1:8) ኢዮብ ከነቀፋ ነፃ በሆነ አኗኗሩ ለብዙ ዓመታት የሰማያዊ አባቱን ልብ ደስ ሲያሰኝ ኖሯል። ኢዮብ አምላክን ይፈራ የነበረው እንዲህ ማድረግ ትክክለኛና የተሻለ የሕይወት መንገድ እንደሆነ ስላወቀ ነው። “እነሆ፣ እግዚአብሔርን መፍራት ጥበብ ነው፤ ከኃጢአትም መራቅ ማስተዋል ነው” ሲል ተናግሯል። (ኢዮብ 28:28) ኢዮብ ባለትዳር እንደመሆኑ መጠን ለወጣት ሴቶች ተገቢ ያልሆነ ዝንባሌም ሆነ የዝሙት ሐሳብ በልቡ ውስጥ አልነበረም። ሀብታም የነበረ ቢሆንም እንኳ በሀብቱ የማይመካና ከማንኛውም ዓይነት የጣዖት አምልኮ የሚርቅ ሰው ነበር።​—⁠ኢዮብ 31:1, 9-11, 24-28

16. (ሀ) ኢዮብ ፍቅራዊ ደግነት ያሳየው በምን መንገድ ነው? (ለ) ኢዮብ ምሕረት ከማሳየት ወደኋላ ያላለው እንዴት ነው?

16 ሆኖም አምላክን መፍራት ማለት ከክፉ መሸሽ ብቻ ሳይሆን መልካም ማድረግንም ይጨምራል። ስለሆነም ኢዮብ ለዓይነ ስውር፣ ለአንካሳና ለድሀ በደግነት ያስብ ነበር። (ዘሌዋውያን 19:14፤ ኢዮብ 29:15, 16) ኢዮብ “ለወዳጁ በጎነት የማያሳይ ሰው፣ ሁሉን የሚችለውን አምላክ መፍራት” እንደሚተው ተረድቷል። (ኢዮብ 6:14 አ.መ.ት ) ፍቅራዊ ደግነት አለማሳየት ማለት ይቅር ለማለት ፈቃደኛ አለመሆንን ወይም ቂም መያዝን ሊጨምር ይችላል። ኢዮብ አምላክ በሰጠው መመሪያ መሠረት ለእነዚያ በመከራው ላይ መከራ ለጨመሩበት ሦስት ጓደኞቹ ጸልዮአል። (ኢዮብ 42:7-10) እኛም በሆነ መንገድ ለጎዳን የእምነት ባልንጀራችን ተመሳሳይ የይቅር ባይነት መንፈስ ማሳየት እንችላለን? ስላስቀየመን ሰው ልባዊ ጸሎት ማቅረብ ያደረብንን ቅሬታ ለማሸነፍ ሊረዳን ይችላል። ኢዮብ ላሳየው አምላካዊ ፍርሃት ያገኘው በረከት ‘ይሖዋ እርሱን ለሚፈሩት የሰወረው ብዙ ቸርነት’ ምን እንደሆነ ፍንጭ ሊሰጠን ይችላል።​—⁠መዝሙር 31:19፤ ያዕቆብ 5:11

አምላካዊ ፍርሃት እና የሰው ፍርሃት

17. ሰዎችን መፍራት እንዴት ሊነካን ይችላል? ይህ ዓይነቱ ፍርሃት ጊዜያዊ ነው የምንለው ለምንድን ነው?

17 አምላክን መፍራት ትክክለኛ የሆነውን ነገር እንድናደርግ የሚገፋፋን ሲሆን ሰውን መፍራት ግን እምነታችንን ሊያዳክም ይችላል። ኢየሱስ ሐዋርያቱ ቀናተኛ የምሥራቹ ሰባኪዎች እንዲሆኑ ሲያበረታታቸው “ሥጋን የሚገድሉትን ነፍስን ግን መግደል የማይቻላቸውን አትፍሩ፤ ይልቅስ ነፍስንም ሥጋንም በገሃነም ሊያጠፋ የሚቻለውን ፍሩ” ያላቸው ለዚህ ነው። (ማቴዎስ 10:28) ሰዎች የወደፊት ሕይወት ተስፋችንን ሊያጠፉ ስለማይችሉ ኢየሱስ ሰውን መፍራት ጊዜያዊ እንደሆነ አብራርቷል። ከዚህም በተጨማሪ አስፈሪ ኃይል እንዳለው ስለምንገነዘብ አምላክን እንፈራለን፤ የብሔራት ኃይል ከእሱ ጋር ሲወዳደር ከምንም የሚቆጠር አይደለም። (ኢሳይያስ 40:15) እንደ አብርሃም ሁሉ እኛም ይሖዋ ታማኝ አገልጋዮቹን ከሞት ለማስነሳት የሚያስችል ኃይል እንዳለው ሙሉ ትምክህት አለን። (ራእይ 2:10) ስለዚህ በትምክህት “እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ማን ይቃወመናል?” እንላለን።​—⁠ሮሜ 8:31

18. ይሖዋ ለሚፈሩት ወሮታ የሚከፍለው እንዴት ነው?

18 ተቃውሞ የሚያደርስብን በቤተሰብ አባልም ይሁን ትምህርት ቤት ባለ ጉልበተኛ “እግዚአብሔርን ለሚፈራ ጠንካራ መታመን” እንዳለው እናስተውላለን። (ምሳሌ 14:26) ጸሎታችንን እንደሚሰማ በመተማመን ብርታት እንዲሰጠን ወደ አምላክ መጸለይ እንችላለን። (መዝሙር 145:19) ይሖዋ እሱን የሚፈሩትን በፍጹም አይዘነጋም። በነቢዩ ሚልክያስ አማካኝነት እንዲህ የሚል ማረጋገጫ ሰጥቶናል:- “የዚያን ጊዜ እግዚአብሔርን የሚፈሩ እርስ በእርሳቸው ተነጋገሩ፤ እግዚአብሔርም አደመጠ፣ ሰማም፣ እግዚአብሔርንም ለሚፈሩ ስሙንም ለሚያስቡ የመታሰቢያ መጽሐፍ በፊቱ ተጻፈ።”​—⁠ሚልክያስ 3:16

19. የትኛው ዓይነት ፍርሃት ይወገዳል? የትኛው ዓይነት ፍርሃትስ ለዘላለም ይኖራል?

19 እያንዳንዱ የምድር ነዋሪ ይሖዋን የሚያመልክበትና ሰውን መፍራት የሚያከትምበት ጊዜ ሩቅ አይደለም። (ኢሳይያስ 11:9) በዚህ ጊዜ ረሃብን፣ ሞትን፣ ወንጀልንና ጦርነትን መፍራት አይኖርም። ይሁን እንጂ በሰማይም ሆነ በምድር ያሉ ታማኝ አገልጋዮቹ የሚገባውን አክብሮትና ታዛዥነት ስለሚያሳዩት አምላክን መፍራት ለዘላለም ይኖራል። (ራእይ 15:​3, 4) እስከዚያው ጊዜ ድረስ እኛ ሁላችን “ልብህ በኃጢአተኞች አይቅና፤ ነገር ግን ቀኑን ሙሉ እግዚአብሔርን በመፍራት ኑር፤ በእውነት ፍጻሜ አለህና፣ ተስፋህም አይጠፋምና” የሚለውን በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈውን የሰሎሞንን ምክር ልብ የምንል እንሁን።​—⁠ምሳሌ 23:17, 18

[የግርጌ ማስታወሻ]

a አንዳንድ ሰዎች የሥራ ጠባያቸው ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ ይላመዱትና ከጊዜ በኋላ የነበራቸው ፍርሃት ሁሉ ይጠፋል። አንድ የብዙ ጊዜ ልምድ ያለው የእጅ ባለሙያ ብዙ አናጢዎች ጣተ ቆራጣ የሆኑት ለምን እንደሆነ ተጠይቆ ሲመልስ “ከፍተኛ ፍጥነት ላላቸው የኤሌክትሪክ መጋዞች የነበራቸው ፍርሃት ስለሚጠፋ ነው” ሲል ተናግሯል።

b ይሖዋ ራሱ ተመሳሳይ የሆነ የመጸየፍ ስሜት አለው። ለምሳሌ ያህል ኤፌሶን 4:​29 ጸያፍ አነጋገርን “ብልሹ ቃል” በማለት ይገልጸዋል። “ብልሹ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል የበሰበሰን ፍሬ፣ ዓሣ ወይም ሥጋ ያመለክታል። ይህ መግለጫ ክፉ ቃልን ወይም ጸያፍ አነጋገርን በተመለከተ ሊኖረን የሚገባንን የመጸየፍ ስሜት ሕያው አድርጎ ይገልጻል። በተመሳሳይም በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ጣዖታት ብዙውን ጊዜ እንደ “አዛባ” ተደርገው ተገልጸዋል። (ዘዳግም 29:17 NW፤ ሕዝቅኤል 6:9 NW) ለአዛባ ወይም ለዕዳሪ በተፈጥሮ ያለን የመጸየፍ ስሜት አምላክ ማንኛውንም የጣዖት ዓይነት ምን ያህል እንደሚጸየፍ እንድናስተውል ይረዳናል።

c ለምሳሌ ያህል ስለ ቃየን (ዘፍጥረት 4:3-12)፣ ስለ ዳዊት (2 ሳሙኤል 11:​2–12:​14)፣ ስለ ግያዝ (2 ነገሥት 5:​20-27) እና ስለ ዖዝያን (2 ዜና መዋዕል 26:16-21) የሚገልጹትን ቅዱስ ጽሑፋዊ ታሪኮች መርምር።

ታስታውሳለህን?

• መጥፎ የሆነውን መጥላት የምንማረው እንዴት ነው?

• በሚልክያስ ዘመን የነበሩ አንዳንድ እስራኤላውያን ከይሖዋ ጋር የነበራቸውን ወዳጅነት ያቃለሉት እንዴት ነበር?

• አምላክን ስለ መፍራት ከአብርሃም፣ ከዮሴፍና ከኢዮብ ምን እንማራለን?

• ጸንቶ የሚኖረው ፍርሃት የትኛው ነው? ለምንስ?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አስተዋይ የሆኑ ወላጆች በልጆቻቸው ልብ ውስጥ ጤናማ ፍርሃት ይቀርጻሉ

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በተፈጥሮ ያለ ፍርሃት ከአደጋ እንድንርቅ እንደሚጠብቀን ሁሉ አምላካዊ ፍርሃትም ከክፉ እንድንሸሽ ያደርገናል

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢዮብ በሦስቱ የሐሰት ወዳጆቹ ፊት እንኳ የነበረውን አምላካዊ ፍርሃት አላጠፋም

[ምንጭ]

From the Bible translation Vulgata Latina, 1795