መዝሙር 31:1-24

  • ይሖዋን መጠጊያ ማድረግ

    • “መንፈሴን በእጅህ አደራ እሰጣለሁ” (5)

    • ‘የእውነት አምላክ የሆነው ይሖዋ’ (5)

    • የአምላክ ጥሩነት ብዙ ነው (19)

ለሙዚቀኞች ቡድን መሪ። የዳዊት ማህሌት። 31  ይሖዋ ሆይ፣ አንተን መጠጊያ አድርጌአለሁ።+ ፈጽሞ አልፈር።+ ከጽድቅህ የተነሳ ታደገኝ።+   ጆሮህን ወደ እኔ አዘንብል።* ፈጥነህ ታደገኝ።+ እኔን ለማዳን በተራራ ላይ ያለ ምሽግ፣የተመሸገ ስፍራም ሁንልኝ።+   አንተ ቋጥኜና ምሽጌ ነህና፤+ለስምህ ስትል+ ትመራኛለህ፤ የምሄድበትንም መንገድ ታሳየኛለህ።+   አንተ መሸሸጊያዬ ስለሆንክ፣+እነሱ በስውር ከዘረጉብኝ ወጥመድ ታስጥለኛለህ።+   መንፈሴን በእጅህ አደራ እሰጣለሁ።+ የእውነት* አምላክ የሆንከው ይሖዋ ሆይ፣+ ዋጅተኸኛል።   የማይረቡና ከንቱ የሆኑ ጣዖቶችን የሚያመልኩ ሰዎችን እጠላለሁ፤እኔ ግን በይሖዋ እታመናለሁ።   በታማኝ ፍቅርህ እጅግ ሐሴት አደርጋለሁ፤ጉስቁልናዬን አይተሃልና፤+በጭንቀት መዋጤን* ታውቃለህ።   ለጠላት አሳልፈህ አልሰጠኸኝም፤ይልቁንም ደህንነት በማገኝበት ስፍራ አቆምከኝ።*   ይሖዋ ሆይ፣ በጭንቀት ስለተዋጥኩ ሞገስ አሳየኝ። መከራ ዓይኔንም ሆነ መላ ሰውነቴን አድክሞታል።*+ 10  ሕይወቴ በሐዘን፣ዕድሜዬም በመቃተት አልቋል።+ ከፈጸምኩት ኃጢአት የተነሳ ጉልበቴ ተሟጠጠ፤አጥንቶቼ ደከሙ።+ 11  ባላጋራዎቼ ሁሉ፣በተለይ ደግሞ ጎረቤቶቼ ተሳለቁብኝ።+ የሚያውቁኝ ሰዎችም እጅግ ፈሩኝ፤በአደባባይ ሲያዩኝ ከእኔ ይሸሻሉ።+ 12  የሞትኩ ያህል ከልባቸው ወጣሁ፤* ደግሞም ተረሳሁ፤እንደተሰበረ ማሰሮ ነኝ። 13  ብዙ መጥፎ ወሬ ሰምቻለሁ፤ሽብር ከቦኛል።+ ግንባር ፈጥረው በእኔ ላይ በተነሱ ጊዜሕይወቴን* ለማጥፋት ያሴራሉ።+ 14  ይሖዋ ሆይ፣ እኔ ግን በአንተ እታመናለሁ።+ “አንተ አምላኬ ነህ” እላለሁ።+ 15  የሕይወት ዘመኔ በእጅህ ነው። ከጠላቶቼና ከሚያሳድዱኝ እጅ ታደገኝ።+ 16  ፊትህ በአገልጋይህ ላይ እንዲበራ አድርግ።+ በታማኝ ፍቅርህ አድነኝ። 17  ይሖዋ ሆይ፣ አንተን በጠራሁ ጊዜ አልፈር።+ ክፉዎች ግን ይፈሩ፤+በመቃብር* ውስጥ ዝም ይበሉ።+ 18  በትዕቢትና በንቀት በጻድቁ ላይ በእብሪት የሚናገሩሐሰተኛ ከንፈሮች ዱዳ ይሁኑ።+ 19  ጥሩነትህ ምንኛ ብዙ ነው!+ አንተን ለሚፈሩ ጠብቀህ አቆይተኸዋል፤+እንዲሁም አንተን መጠጊያ ለሚያደርጉ ስትል በሰዎች ሁሉ ፊት አሳይተኸዋል።+ 20  አንተ ባለህበት ሚስጥራዊ ቦታ፣ከሰዎች ሴራ ትሸሽጋቸዋለህ፤+በመጠለያህ ውስጥከክፉ ጥቃት* ትሰውራቸዋለህ።+ 21  በተከበበ ከተማ ውስጥ+ ታማኝ ፍቅሩን በአስደናቂ ሁኔታ ስላሳየኝ+ይሖዋ የተመሰገነ ይሁን። 22  እኔ በድንጋጤ ተውጬ “ከፊትህ መጥፋቴ ነው” አልኩ።+ አንተ ግን እርዳታ ለማግኘት በጮኽኩ ጊዜ ልመናዬን ሰማህ።+ 23  እናንተ ለእሱ ታማኝ የሆናችሁ ሁሉ፣ ይሖዋን ውደዱ!+ ይሖዋ ታማኞችን ይጠብቃል፤+ትዕቢተኛ የሆነን ሰው ግን ክፉኛ ይቀጣል።+ 24  እናንተ ይሖዋን የምትጠባበቁ ሁሉ፣+ደፋር ሁኑ፤ ልባችሁም ይጽና።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ጎንበስ ብለህ ስማኝ።”
ወይም “ታማኝ።”
ወይም “የነፍሴን ጭንቀት።”
ወይም “ሰፊ በሆነ ስፍራ አቆምከኝ።”
ወይም “ነፍሴንና ሆዴን አድክሞታል።”
ወይም “ከአእምሯቸው ወጣሁ።”
ወይም “ነፍሴን።”
ወይም “በሲኦል።” የሰው ልጆችን ሁሉ መቃብር ያመለክታል። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ቃል በቃል “ከምላስ ጠብ።”