ሕዝቅኤል 6:1-14

  • በእስራኤል ተራሮች ላይ የተነገረ ትንቢት (1-14)

    • አስጸያፊ የሆኑት ጣዖታት ውርደት ይከናነባሉ (4-6)

    • ‘እኔ ይሖዋ እንደሆንኩ ታውቃላችሁ’ (7)

6  የይሖዋ ቃል ዳግመኛ እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፦  “የሰው ልጅ ሆይ፣ ፊትህን ወደ እስራኤል ተራሮች አዙረህ በእነሱ ላይ ትንቢት ተናገር።  እንዲህም በል፦ ‘የእስራኤል ተራሮች ሆይ፣ የሉዓላዊውን ጌታ የይሖዋን ቃል ስሙ፦ ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ ለተራሮቹ፣ ለኮረብቶቹ፣ ለጅረቶቹና ለሸለቆዎቹ እንዲህ ይላል፦ “እነሆ፣ እኔ በእናንተ ላይ ሰይፍ አመጣለሁ፤ ከፍ ያሉትን የማምለኪያ ቦታዎቻችሁንም አጠፋለሁ።  መሠዊያዎቻችሁ ይፈርሳሉ፤ የዕጣን ማጨሻዎቻችሁ ይሰባበራሉ፤+ የታረዱ ወገኖቻችሁንም አስጸያፊ በሆኑት ጣዖቶቻችሁ* ፊት እጥላለሁ።+  የእስራኤልን ሕዝብ ሬሳ አስጸያፊ በሆኑት ጣዖቶቻቸው ፊት እጥላለሁ፤ አጥንቶቻችሁንም በመሠዊያዎቻችሁ ዙሪያ እበትናለሁ።+  በምትኖሩባቸው ቦታዎች ሁሉ ያሉት ከተሞች ይወድማሉ፤+ ከፍ ያሉት የማምለኪያ ቦታዎቹም ፈራርሰው ባድማ ይሆናሉ።+ መሠዊያዎቻችሁ ፈራርሰው እንዳልነበሩ ይሆናሉ፤ አስጸያፊ የሆኑት ጣዖቶቻችሁ ይወገዳሉ፤ የዕጣን ማጨሻዎቻችሁ ተገንድሰው ይወድቃሉ፤ የሠራችኋቸው ሥራዎችም ተጠራርገው ይጠፋሉ።  የታረዱትም ሰዎች በመካከላችሁ ይወድቃሉ፤+ እኔም ይሖዋ እንደሆንኩ ታውቃላችሁ።+  “‘“ይሁንና የተወሰኑ ቀሪዎች እንዲኖሩ አደርጋለሁ፤ በየአገሩ በምትበተኑበት ጊዜ፣ ከእናንተ ውስጥ አንዳንዶቻችሁ በብሔራት መካከል ስትኖሩ ከሰይፍ ታመልጣላችሁና።+  የተረፉትም ሰዎች በምርኮ በተወሰዱባቸው ብሔራት መካከል ሆነው እኔን ያስታውሳሉ።+ ከእኔ በራቀው ከሃዲ* ልባቸውና+ አስጸያፊ የሆኑ ጣዖቶቻቸውን በፍትወት ስሜት በተመለከቱት* ዓይኖቻቸው የተነሳ+ ምን ያህል ልቤ እንዳዘነ ይገነዘባሉ። በሠሯቸው መጥፎና አስነዋሪ ነገሮች ሁሉ ያፍራሉ፤ እነዚህንም ነገሮች ይጸየፋሉ።+ 10  እኔ ይሖዋ እንደሆንኩና ይህን ጥፋት እንደማመጣባቸው የዛትኩት በከንቱ እንዳልሆነ ያውቃሉ።”’+ 11  “ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘የእስራኤል ቤት ሰዎች በሠሯቸው ክፉና አስጸያፊ ነገሮች ሁሉ የተነሳ በሰይፍ፣ በረሃብና በቸነፈር ስለሚወድቁ በእጅህ እያጨበጨብክ፣ በእግርህም መሬቱን እየደበደብክ አልቅስ።+ 12  በሩቅ ያለው በቸነፈር ይሞታል፤ በቅርብ ያለው በሰይፍ ይወድቃል፤ ከእነዚህ ነገሮች ያመለጠና በሕይወት የተረፈ ሁሉ በረሃብ ያልቃል፤ ቁጣዬንም ሁሉ በእነሱ ላይ አወርዳለሁ።+ 13  የታረዱት ወገኖቻቸው አስጸያፊ በሆኑት ጣዖቶቻቸው መካከል፣ በመሠዊያዎቻቸው ዙሪያ፣ ከፍ ባለ ኮረብታ ሁሉና በተራሮች አናት ሁሉ ላይ፣ ከለመለመ ዛፍ ሁሉ በታች እንዲሁም በትላልቅ ዛፎች ቅርንጫፎች ሥር ይኸውም አስጸያፊ የሆኑ ጣዖቶቻቸውን ሁሉ ቁጣ ለማብረድ፣ ደስ የሚያሰኝ ሽታ ያላቸው መባዎች*+ ባቀረቡባቸው ቦታዎች በሚወድቁበት ጊዜ+ እኔ ይሖዋ እንደሆንኩ ያውቃሉ።+ 14  በእነሱ ላይ እጄን እዘረጋለሁ፤ ምድሪቱንም ባድማ አደርጋለሁ፤ መኖሪያ ቦታዎቻቸውም ሁሉ በዲብላ አቅራቢያ ካለው ምድረ በዳ የባሰ ባድማ ይሆናሉ። እነሱም እኔ ይሖዋ እንደሆንኩ ያውቃሉ።’”

የግርጌ ማስታወሻዎች

እዚህ ላይ የገባው የዕብራይስጥ ቃል “ፋንድያ” ከሚለው ቃል ጋር ዝምድና ሊኖረው የሚችል ሲሆን ንቀትን ለማመልከት ተሠርቶበታል።
ወይም “ሥነ ምግባር በጎደለው መንገድ በተከተሉት።”
ወይም “ሥነ ምግባር የጎደለው፤ ሴሰኛ።”
ወይም “ደስ የሚያሰኙ መዓዛዎች።”