ዘዳግም 28:1-68

  • መታዘዝ የሚያስገኘው በረከት (1-14)

  • አለመታዘዝ የሚያስከትለው እርግማን (15-68)

28  “እኔ ዛሬ የማዝህን የአምላክህን የይሖዋን ትእዛዛት ሁሉ በጥንቃቄ በመፈጸም ቃሉን በእርግጥ ብትሰማ አምላክህ ይሖዋ በምድር ላይ ካሉ ብሔራት ሁሉ በላይ ከፍ ከፍ ያደርግሃል።+  የአምላክህን የይሖዋን ቃል ከሰማህ እነዚህ ሁሉ በረከቶች ይወርዱልሃል፤ ተከታትለውም ይደርሱብሃል፦+  “በከተማ የተባረክ ትሆናለህ፤ በእርሻም የተባረክ ትሆናለህ።+  “የሆድህ ፍሬ፣+ የመሬትህ ፍሬ፣ የቤት እንስሳህ ግልገል፣ ጥጃህና የበግህ ግልገል የተባረከ ይሆናል።+  “ቅርጫትህና+ ቡሃቃህ+ የተባረከ ይሆናል።  “ስትገባ የተባረክ ትሆናለህ፤ ስትወጣም የተባረክ ትሆናለህ።  “ይሖዋ በአንተ ላይ የሚነሱ ጠላቶችህ በፊትህ ድል እንዲሆኑ ያደርጋል።+ ከአንድ አቅጣጫ ጥቃት ይሰነዝሩብሃል፤ ሆኖም በሰባት አቅጣጫ ከፊትህ ይሸሻሉ።+  ይሖዋ በጎተራህና በምታከናውነው ሥራ ሁሉ ላይ በረከት እንዲፈስልህ ያዛል፤+ አምላክህ ይሖዋ በሚሰጥህም ምድር ይባርክሃል።  የአምላክህን የይሖዋን ትእዛዛት ከጠበቅክና በመንገዶቹ ከሄድክ ይሖዋ በማለልህ መሠረት+ ለእሱ ቅዱስ ሕዝብ አድርጎ ያቆምሃል።+ 10  የምድር ሕዝቦች ሁሉ የይሖዋ ስም በአንተ አማካኝነት እንደሚጠራ ያያሉ፤+ እነሱም ይፈሩሃል።+ 11  “ይሖዋ ለአንተ ለመስጠት ለአባቶችህ በማለላቸው ምድር+ ላይ ይሖዋ የሆድህ ፍሬ እንዲበዛ፣ የቤት እንስሶችህ እንዲረቡና መሬትህ ፍሬያማ እንዲሆን+ በማድረግ ያበለጽግሃል። 12  ይሖዋ በምድርህ ላይ በወቅቱ ዝናብን ለማዝነብና የእጅህን ሥራ ሁሉ ለመባረክ ሲል መልካም የሆነውን ጎተራውን ይኸውም ሰማይን ይከፍትልሃል።+ አንተም ለብዙ ብሔራት ታበድራለህ፤ አንተ ግን አትበደርም።+ 13  ይሖዋ ራስ እንጂ ጅራት አያደርግህም፤ ትጠብቃቸውና ትፈጽማቸው ዘንድ እኔ ዛሬ የማዝህን የአምላክህን የይሖዋን ትእዛዛት ከፈጸምክ መቼም ቢሆን ከላይ+ እንጂ ከታች አትሆንም። 14  ሌሎች አማልክትን ለማገልገል+ ብላችሁ እነሱን በመከተል እኔ ዛሬ ከምሰጣችሁ ትእዛዛት ሁሉ ወደ ቀኝም ሆነ ወደ ግራ ዞር አትበሉ።+ 15  “እኔ ዛሬ የማዝህን የእሱን ትእዛዛትና ደንቦች በሙሉ በጥንቃቄ የማትፈጽምና የአምላክህን የይሖዋን ቃል የማትሰማ ከሆነ ግን እነዚህ ሁሉ እርግማኖች ይወርዱብሃል፤ ተከታትለውም ይደርሱብሃል፦+ 16  “በከተማ የተረገምክ ትሆናለህ፤ በእርሻም የተረገምክ ትሆናለህ።+ 17  “ቅርጫትህና+ ቡሃቃህ+ የተረገመ ይሆናል። 18  “የሆድህ ፍሬ፣+ የመሬትህ ፍሬ፣ ጥጃህና የበግህ ግልገል የተረገመ ይሆናል።+ 19  “ስትገባ የተረገምክ ትሆናለህ፤ ስትወጣም የተረገምክ ትሆናለህ። 20  “ይሖዋ በፈጸምካቸው መጥፎ ድርጊቶችና እኔን በመተውህ የተነሳ ፈጥነህ እስክትደመሰስ እንዲሁም እስክትጠፋ ድረስ፣ በምታከናውነው በማንኛውም ሥራ ላይ እርግማንን፣ ግራ መጋባትንና ቅጣትን ያመጣብሃል።+ 21  ይሖዋ ከምትወርሳት ምድር ላይ ጨርሶ እስኪያጠፋህ ድረስ በሽታ እንዲጣበቅብህ ያደርጋል።+ 22  ይሖዋ በሳንባ በሽታ፣ በኃይለኛ ትኩሳት፣+ ሰውነትን በሚያስቆጣ በሽታ፣ በሚያነድ ትኩሳት፣ በሰይፍ፣+ ሰብል በሚለበልብ ነፋስና በዋግ+ ይመታሃል፤ እነሱም እስክትጠፋ ድረስ ያሳድዱሃል። 23  ከራስህ በላይ ያለው ሰማይ መዳብ፣ ከበታችህ ያለውም ምድር ብረት ይሆንብሃል።+ 24  ይሖዋ በምድርህ ላይ የሚዘንበውን ዝናብ ትቢያና አቧራ ያደርገዋል፤ ይህም እስክትጠፋ ድረስ ከሰማይ ይወርድብሃል። 25  ይሖዋ በጠላቶችህ ፊት እንድትሸነፍ ያደርግሃል።+ በአንድ አቅጣጫ ጥቃት ትሰነዝርባቸዋለህ፤ ሆኖም በሰባት አቅጣጫ ከፊታቸው ትሸሻለህ፤ የምድርም መንግሥታት ሁሉ በአንተ ላይ የደረሰውን ሲያዩ በፍርሃት ይርዳሉ።+ 26  ሬሳህ ለሰማይ ወፎችና ለምድር አራዊት ሁሉ ምግብ ይሆናል፤ አስፈራርቶ የሚያባርራቸውም አይኖርም።+ 27  “ይሖዋ ፈውስ ልታገኝ በማትችልበት የግብፅ እባጭ፣ ኪንታሮት፣ ችፌና ሽፍታ ይመታሃል። 28  ይሖዋ በእብደት፣ በዕውርነትና+ በግራ መጋባት ይመታሃል። 29  ጨለማ የዋጠው ዓይነ ስውር በዳበሳ እንደሚሄድ ሁሉ አንተም በእኩለ ቀን በዳበሳ ትሄዳለህ፤+ የምታደርገው ነገር ሁሉ አይሳካልህም፤ ሁልጊዜ ትጭበረበራለህ፤ እንዲሁም ትዘረፋለህ፤ የሚያስጥልህም የለም።+ 30  አንዲትን ሴት ታጫለህ፤ ሆኖም ሌላ ሰው ይደፍራታል። ቤት ትሠራለህ፤ ሆኖም አትኖርበትም።+ ወይን ትተክላለህ፤ ግን አትበላውም።+ 31  በሬህ ዓይንህ እያየ ይታረዳል፤ ሆኖም ከእሱ ላይ ምንም አትቀምስም። አህያህም ከፊትህ ተዘርፎ ይወሰዳል፤ ሆኖም አይመለስልህም። በጎችህ ለጠላቶችህ ይሰጣሉ፤ የሚደርስልህ ግን የለም። 32  ወንዶችና ሴቶች ልጆችህ ዓይንህ እያየ ለሌላ ሕዝብ ይሰጣሉ፤+ አንተም ሁልጊዜ የእነሱን መመለስ ትናፍቃለህ፤ ሆኖም እጆችህ ምንም ኃይል አይኖራቸውም። 33  የምድርህን ፍሬና ያመረትከውን ሁሉ የማታውቀው ሕዝብ ይበላዋል፤+ አንተም ሁልጊዜ ትጭበረበራለህ፤ ደግሞም ትረገጣለህ። 34  ዓይንህ የሚያየውም ነገር ያሳብድሃል። 35  “ይሖዋ በሚያሠቃይና ሊድን በማይችል እባጭ ጉልበቶችህንና እግሮችህን ይመታል፤ እባጩም ከእግር ጥፍርህ እስከ ራስ ቅልህ ድረስ ይወርስሃል። 36  ይሖዋ አንተንና በላይህ ያነገሥከውን ንጉሥ፣ አንተም ሆንክ አባቶችህ ወደማታውቁት ብሔር ይወስዳችኋል፤+ እዚያም ሌሎች አማልክትን ይኸውም ከእንጨትና ከድንጋይ የተሠሩ አማልክትን ታገለግላለህ።+ 37  ይሖዋ በሚያስገባህ ሕዝብ ሁሉ መካከል ማስፈራሪያ፣ መቀለጃና* መሳለቂያ ትሆናለህ።+ 38  “ወደ እርሻህ ብዙ ዘር ይዘህ ትወጣለህ፤ የምትሰበስበው ግን ጥቂት ይሆናል፤+ ምክንያቱም አንበጦች ያወድሙታል። 39  ወይን ትተክላለህ፤ ታለማለህም፤ ይሁንና ምንም የወይን ጠጅ አትጠጣም፤ እንዲሁም አንዳች አትሰበስብም፤+ ምክንያቱም ትል ይበላዋል። 40  በግዛትህ ሁሉ የወይራ ዛፍ ይኖርሃል፤ ሰውነትህን የምትቀባው ዘይት ግን አይኖርህም፤ ምክንያቱም የወይራ ፍሬዎችህ ይረግፋሉ። 41  ወንዶችና ሴቶች ልጆችን ትወልዳለህ፤ ሆኖም በምርኮ ስለሚወሰዱ የአንተ አይሆኑም።+ 42  ዛፎችህንና የምድርህን ፍሬ ሁሉ የሚርመሰመሱ ነፍሳት ይወሩታል። 43  አንተ ዝቅ ዝቅ እያልክ ስትሄድ በመካከልህ የሚኖረው የባዕድ አገር ሰው ግን በአንተ ላይ ከፍ ከፍ እያለ ይሄዳል። 44  እሱ ያበድርሃል እንጂ አንተ አታበድረውም።+ እሱ ራስ ይሆናል፤ አንተ ግን ጅራት ትሆናለህ።+ 45  “አምላክህ ይሖዋ ያዘዘህን የእሱን ትእዛዛትና ደንቦች ባለመጠበቅ ቃሉን ስላልሰማህ እነዚህ እርግማኖች ሁሉ+ እስክትጠፋ ድረስ ይወርዱብሃል፤+ ያሳድዱሃል፤ ተከታትለውም ይደርሱብሃል።+ 46  እነሱም በአንተና በልጆችህ ላይ ለዘላለም ምልክትና ማስጠንቀቂያ ይሆናሉ፤+ 47  ምክንያቱም ሁሉም ነገር ተትረፍርፎልህ ሳለ አምላክህን ይሖዋን በደስታና በሐሴት አላገለገልከውም።+ 48  ይሖዋ ጠላቶችህን በአንተ ላይ ያስነሳቸዋል፤ አንተም ተርበህ፣+ ተጠምተህ፣ ተራቁተህና ሁሉን ነገር አጥተህ እያለ ታገለግላቸዋለህ።+ እሱም እስኪያጠፋህ ድረስ በአንገትህ ላይ የብረት ቀንበር ይጭንብሃል። 49  “ይሖዋ ቋንቋውን የማትረዳውን+ በሩቅ ያለን አንድ ብሔር ከምድር ጫፍ አስነስቶ ያመጣብሃል፤+ እሱም እንደ ንስር ተምዘግዝጎ ይወርድብሃል፤+ 50  ይህ ብሔር ለሽማግሌ የማያዝን ወይም ለወጣት የማይራራ ፊቱ የሚያስፈራ ብሔር ነው።+ 51  እስክትጠፋም ድረስ የእንስሶችህን ግልገልና የምድርህን ፍሬ ይበላሉ። አንተንም እስኪያጠፉህ ድረስ ምንም እህል፣ አዲስ የወይን ጠጅም ሆነ ዘይት፣ ጥጃም ሆነ የበግ ግልገል አያስተርፉልህም።+ 52  የምትተማመንባቸው ረጃጅምና የተመሸጉ ቅጥሮችህ እስኪወድቁም ድረስ በከተሞችህ* ውስጥ እንዳለህ ዘግተውብህ ይከቡሃል። አምላክህ ይሖዋ በሚሰጥህም ምድር ሁሉ ላይ በከተሞችህ ውስጥ እንዳለህ ይከቡሃል።+ 53   ከሚያስጨንቀው ከበባና ጠላትህ በአንተ ላይ ከሚያደርሰው ሥቃይ የተነሳ አምላክህ ይሖዋ የሰጠህን የሆድህን ፍሬ ይኸውም የወንዶችና የሴቶች ልጆችህን ሥጋ ትበላለህ።+ 54  “ሌላው ቀርቶ በመካከልህ ያለ በምቾትና በቅምጥልነት ይኖር የነበረ ሰው እንኳ በወንድሙ፣ በሚወዳት ሚስቱ ወይም በተረፉት ልጆቹ ላይ ይጨክናል፤ 55  ከሚበላው የልጆቹ ሥጋ ላይ ምንም ነገር አያካፍላቸውም፤ ምክንያቱም ከሚያስጨንቀው ከበባና ጠላትህ በከተሞችህ ላይ ከሚያመጣው ሥቃይ የተነሳ የሚተርፈው ምንም ነገር አይኖረውም።+ 56  ከቅምጥልነቷ የተነሳ መሬት ለመርገጥ እንኳ ትጸየፍ የነበረች+ በመካከልህ ያለች ቅምጥልና በምቾት የምትኖር ሴትም በምትወደው ባሏ፣ በወንድ ልጇ ወይም በሴት ልጇ ላይ ትጨክናለች፤ 57   ሌላው ቀርቶ ከወሊድ በኋላ ከእግሮቿ መካከል በሚወጣው ነገር ሁሉና በምትወልዳቸው ልጆች ላይ ትጨክናለች፤ ምክንያቱም ከሚያስጨንቀው ከበባና ጠላትህ በከተሞችህ ላይ ከሚያመጣው ሥቃይ የተነሳ በድብቅ ትበላቸዋለች። 58  “በዚህ መጽሐፍ ላይ የተጻፈውን የዚህን ሕግ+ ቃላት ሁሉ በጥንቃቄ የማትጠብቅ እንዲሁም ክብራማና አስፈሪ የሆነውን የአምላክህን የይሖዋን ስም+ የማትፈራ ከሆነ 59  ይሖዋ በአንተና በልጆችህ ላይ ከባድ የሆኑ መቅሰፍቶችን ይኸውም ታላቅና ለረጅም ጊዜ የሚዘልቁ መቅሰፍቶችን እንዲሁም አስከፊና ለረጅም ጊዜ የሚቆዩ በሽታዎችን+ ያመጣል። 60  ትፈራቸው የነበሩትን የግብፅ በሽታዎች ሁሉ መልሶ ያመጣብሃል፤ እነሱም በአንተ ላይ ይጣበቃሉ። 61  በተጨማሪም ይሖዋ በዚህ የሕግ መጽሐፍ ውስጥ ያልተጻፉ በሽታዎችን ወይም መቅሰፍቶችን ሁሉ እስክትጠፋ ድረስ በአንተ ላይ ያመጣብሃል። 62  ብዛታችሁ በሰማያት ላይ እንዳሉ ከዋክብት+ የነበረ ቢሆንም የአምላካችሁን የይሖዋን ቃል ስላልሰማችሁ የምትቀሩት በጣም ጥቂት ትሆናላችሁ።+ 63  “ይሖዋ እናንተን በማበልጸግና በማብዛት እጅግ ይደሰት እንደነበረው ሁሉ ይሖዋ እናንተን በማጥፋትና በመደምሰስም እጅግ ይደሰታል፤ ገብታችሁ ከምትወርሷት ምድር ላይ ተጠራርጋችሁ ትጠፋላችሁ። 64  “ይሖዋ ከአንዱ የምድር ጫፍ እስከ ሌላኛው የምድር ጫፍ በብሔራት ሁሉ መካከል ይበትንሃል፤+ እዚያም አንተም ሆንክ አባቶችህ የማታውቋቸውን ከእንጨትና ከድንጋይ የተሠሩ አማልክት ታገለግላለህ።+ 65  በእነዚያም ብሔራት መካከል ሰላም አይኖርህም፤+ ወይም ለእግርህ ማሳረፊያ የሚሆን ቦታ አታገኝም። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ በዚያ ልብህ እንዲሸበር፣+ ዓይንህ እንዲፈዝና በተስፋ መቁረጥ እንድትዋጥ ያደርጋል።*+ 66  ሕይወትህ ለከፍተኛ አደጋ ይጋለጣል፤ ሌሊትና ቀንም በፍርሃት ትዋጣለህ፤ ለሕይወትህም ዋስትና ታጣለህ። 67  በልብህ ውስጥ ካለው ፍርሃትና በዓይንህ ከምታየው ነገር የተነሳ ጠዋት ላይ ‘ምነው በመሸ!’ ትላለህ፤ ምሽት ላይ ደግሞ ‘ምነው በነጋ!’ ትላለህ። 68  ‘ዳግመኛ አታያትም’ ባልኩህ መንገድ ይሖዋ ወደ ግብፅ በመርከቦች ይመልስሃል፤ በዚያም ራሳችሁን ለጠላቶቻችሁ ወንድ ባሪያዎችና ሴት ባሪያዎች አድርጋችሁ ለመሸጥ ትገደዳላችሁ፤ የሚገዛችሁ ግን አይኖርም።”

የግርጌ ማስታወሻዎች

ቃል በቃል “መተረቻና።”
ቃል በቃል “በደጆችህ።”
ወይም “ተስፋ የቆረጠ ነፍስ ይሰጥሃል።”