በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የመዝሙር ሦስተኛና አራተኛ መጻሕፍት ጎላ ያሉ ነጥቦች

የመዝሙር ሦስተኛና አራተኛ መጻሕፍት ጎላ ያሉ ነጥቦች

የይሖዋ ቃል ሕያው ነው

የመዝሙር ሦስተኛና አራተኛ መጻሕፍት ጎላ ያሉ ነጥቦች

መዝሙራዊው ለአምላክ ባቀረበው ጸሎት ላይ “ምሕረትህ በመቃብር ውስጥ፣ ታማኝነትህስ እንጦርጦስ ይነገራልን?” ሲል ጠይቋል። (መዝሙር 88:11) እርግጥ፣ መልሱ ‘አይነገርም’ ነው። ከሞትን ይሖዋን ልናወድሰው አንችልም። አምላክን ለማወደስ ያለን ፍላጎት በሕይወት ለመኖር እንድንጓጓ የሚያደርገን ሲሆን ሕይወት ማግኘታችን ደግሞ ይሖዋን ለማመስገን ሊያነሳሳን ይገባል።

የመዝሙር ሦስተኛና አራተኛ መጻሕፍት፣ ከመዝሙር 73 እስከ 106 ያሉትን ምዕራፎች የሚሸፍኑ ሲሆን ፈጣሪያችንን እንድናወድስና ስሙን እንድንቀድስ የሚያነሳሱ እጅግ በርካታ ምክንያቶችን ይዘረዝራሉ። በእነዚህ መዝሙሮች ላይ ማሰላሰላችን ‘ለአምላክ ቃል’ ያለን አድናቆት እንዲጨምርና ለአምላክ በምናቀርበው ውዳሴ ረገድም ማሻሻያ እንድናደርግ ይረዳናል። (ዕብራውያን 4:12) እስቲ መጀመሪያ ትኩረታችንን በሦስተኛው የመዝሙር መጽሐፍ ላይ እናድርግ።

“ወደ እግዚአብሔር መቅረብ ይሻለኛል”

(መዝሙር 73:1 እስከ 89:52)

በሦስተኛው የመዝሙር መጽሐፍ ውስጥ የተካተቱት የመጀመሪያዎቹ 11 መዝሙሮች በአሳፍ ወይም የእርሱ ቤተሰብ አባላት በሆኑ ሰዎች የተቀናበሩ ናቸው። የመክፈቻው መዝሙር፣ አሳፍ በተሳሳተ አስተሳሰብ እንዳይወሰድ ያደረገው ምን እንደሆነ ይገልጻል። አሳፍ ትክክለኛው መደምደሚያ ላይ ደርሷል። በመሆኑም “ለእኔ ግን ወደ እግዚአብሔር መቅረብ ይሻለኛል” ሲል ዘምሯል። (መዝሙር 73:28) መዝሙር 74 ስለ ኢየሩሳሌም ጥፋት የተነገረ የሐዘን እንጉርጉሮ ይዟል። መዝሙር 75፣ 76 እና 77 ይሖዋ በጽድቅ የሚፈርድ፣ ጎስቋሎችን የሚያድንና ጸሎትን የሚሰማ አምላክ መሆኑን ይገልጻሉ። መዝሙር 78 ደግሞ እስራኤላውያን ከሙሴ አንስቶ እስከ ዳዊት ዘመን ድረስ ያሳለፉትን ታሪክ ያወሳል። ሰባ ዘጠነኛው መዝሙር ስለ ቤተ መቅደሱ መጥፋት የሚናገር የሐዘን እንጉርጉሮ ነው። ቀጥሎ ባለው ምዕራፍ ላይ የአምላክ ሕዝብ ተመልሶ እንዲቋቋም የሚጠይቅ ጸሎት እናገኛለን። መዝሙር 81 ይሖዋን የመታዘዝን አስፈላጊነት በተመለከተ ምክር ይሰጣል። መዝሙር 82 ክፉ በሆኑት ፈራጆች ላይ፣ መዝሙር 83 ደግሞ በአምላክ ጠላቶች ላይ መለኮታዊ ፍርድ እንዲፈጸም የሚጠይቁ ጸሎቶችን ይዘዋል።

የቆሬ ልጆች “ነፍሴ የእግዚአብሔርን አደባባዮች ትናፍቃለች፤ እጅግም ትጓጓለታለች” በማለት ዘምረዋል። (መዝሙር 84:2) መዝሙር 85 አምላክ ከስደት በተመለሱት ሰዎች ላይ በረከቱን እንዲያፈስ የቀረበ ልመናን ይዟል። መዝሙሩ ከቁሳዊ ሀብት ይልቅ መንፈሳዊ ብልጽግና እጅግ የላቀ ዋጋ እንዳለው ጎላ አድርጎ ይገልጻል። ዳዊት በመዝሙር 86 ላይ ይሖዋ እንዲጠብቀውና እንዲመራው ተማጽኗል። በመዝሙር 87 ላይ ስለ ጽዮንና በውስጧ ስለተወለዱት ልጆች የሚናገር መዝሙር የሰፈረ ሲሆን ቀጣዩ ምዕራፍ ማለትም መዝሙር 88 ደግሞ ለይሖዋ የቀረበ ጸሎት ይዟል። በሰሎሞን ዘመን ከነበሩት አራት ጠቢባን መካከል አንዱ እንደሆነ የሚገመተው ኤታን ያቀናበረው 89ኛው መዝሙር፣ በዳዊት ቃል ኪዳን ውስጥ የሚንጸባረቀውን የይሖዋን ፍቅራዊ ደግነት ጎላ አድርጎ ይገልጻል።—1 ነገሥት 4:31

ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው፦

73:9—ክፉዎች ‘አፋቸውን በሰማይ ላይ የሚያላቅቁትና አንደበታቸው ምድርን የሚያካልለው’ እንዴት ነው? ክፉዎች በሰማይም ሆነ በምድር ለሚገኝ ለማንኛውም አካል አክብሮት ስለሌላቸው በአፋቸው የአምላክን ስም ከማጉደፍ አይመለሱም። በምላሳቸው የሰዎችን ስምም ያጠፋሉ።

74:13, 14—ይሖዋ ‘የባሕሩን አውሬ ራሶች በውሃ ውስጥ የቀጠቀጠውና የሌዋታንን ራሶች ያደቀቀው መቼ’ ነው? “የግብፅ ንጉሥ ፈርዖን” ‘በወንዞች መካከል የሚተኛ ታላቅ አውሬ’ ተብሎ ተጠርቷል። (ሕዝቅኤል 29:3) ሌዋታን የሚለው አገላለጽ ‘የፈርዖንን ብሩቱዎች’ የሚያመለክት ሊሆን ይችላል። (መዝሙር 74:14 የአዲስ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ) የሌዋታን ራሶች መድቀቅ ይሖዋ፣ እስራኤላውያንን ከግብጽ ባርነት ሲያወጣቸው ፈርዖንና ሠራዊቱ የደረሰባቸውን ከባድ ሽንፈት እንደሚያመለክት ከሁኔታው መረዳት ይቻላል።

75:4, 5, 10—“ቀንድ” የሚለው አባባል ምን ያመለክታል? እንስሳት ቀንዳቸውን እንደ ኃይለኛ መሣሪያ ይጠቀሙበታል። በመሆኑም “ቀንድ” የሚለው ቃል ምሳሌያዊ በሆነ መንገድ ኃይልን ወይም ጥንካሬን ለማመልከት ተሠርቶበታል። ይሖዋ የሕዝቡን ቀንድ ከፍ ከፍ በማድረግ እንዲደሰቱ ሲያደርግ ‘የክፉዎችን ቀንድ ግን ይሰብራል።’ የኩራትና የትዕቢት መንፈስ እንዳይጠናወተን “ቀንድህን ከፍ አታድርግ” የሚል ምክር ተሰጥቶናል። ከፍ ከፍ ያደረገን ይሖዋ በመሆኑ በጉባኤ ውስጥ የሚሰጡንን ኃላፊነቶች ከእርሱ እንደተቀበልናቸው አድርገን መመልከት ይኖርብናል።—መዝሙር 75:7

76:10 —“የሰዎች ቊጣ” (የ1980 ትርጉም) ለይሖዋ ምስጋና የሚያመጣው እንዴት ነው? ይሖዋ፣ አገልጋዮቹ በመሆናችን ምክንያት ሰዎች በእኛ ላይ እንዲቆጡ መፍቀዱ መልካም ውጤት ሊያስገኝ ይችላል። አገልጋዮቹ በመሆናችን ምክንያት የሚደርስብን ማንኛውም መከራ አንድ ዓይነት ሥልጠና ይሰጠናል። ይሖዋ መከራ እንዲደርስብን የሚፈቅደው እንዲህ ያለውን ሥልጠና እስክናገኝ ብቻ ነው። (1 ጴጥሮስ 5:10) ከዚህ ‘የተረፈውን ቊጣ ራሱ ይገታዋል።’ ለሞት የሚዳርግ ሥቃይ ቢደርስብንስ? የእኛን በታማኝነት መቆም የሚመለከቱ ሰዎች ይሖዋን ለማወደስ እንዲገፋፉ ሊያደርግ ስለሚችል ይህም ቢሆን እርሱን ያስከብራል።

78:24, 25—መና ‘የሰማይ መብል’ እና ‘የመላእክት እንጀራ’ ተብሎ የተጠራው ለምንድን ነው? ሁለቱም አገላለጾች መና የመላእክት ምግብ መሆኑን አያመለክቱም። መና የተገኘው ከሰማይ በመሆኑ ‘የሰማይ እንጀራ’ ተብሏል። (መዝሙር 105:40) መላእክት ደግሞ የሚኖሩት በሰማይ ነው፤ በመሆኑም ‘የመላእክት እንጀራ’ የሚለው አገላለጽ በሰማይ ከሚኖረው አምላክ የተሰጠ መሆኑን የሚያመለክት ሊሆን ይችላል። (መዝሙር 11:4) በሌላ በኩል፣ ይሖዋ ለእስራኤላውያን መና ለመስጠት በመላእክት ተጠቅሞም ይሆናል።

82:1, 6—“አማልክት” እና “የልዑል ልጆች” የተባሉት እነማን ናቸው? ሁለቱም አባባሎች የሚያመለክቱት በእስራኤል ውስጥ ይኖሩ የነበሩትን ሰብዓዊ ዳኞች ነው። እነዚህ ዳኞች የይሖዋ ቃል አቀባይና ወኪል ስለነበሩ እንዲህ መባላቸው ተገቢ ነው።—ዮሐንስ 10:33-36

83:2—‘ራስን ቀና’ ማድረግ ምን ያመለክታል? ራስን ቀና ማድረግ ሥልጣንን ለመጠቀም ወይም አንድ ዓይነት እርምጃ ለመውሰድ፣ አብዛኛውን ጊዜ ደግሞ ለመቃወም፣ ለመዋጋት አሊያም ሌሎችን ለመጨቆን መዘጋጀትን ያመለክታል።

ምን ትምህርት እናገኛለን?

73:2-5, 18-20, 25, 28 የክፉዎች ብልጽግና ሊያስቀናንና አምላክ የሚጠላውን አኗኗራቸውን እንድንከተል ሊገፋፋን አይገባም። ክፉዎች በሚያዳልጥ ስፍራ እንደቆሙ ያህል ነው። በመሆኑም ‘ወደ ጥፋት መውረዳቸው’ አይቀርም። ከዚህም በተጨማሪ ፍጹም ባልሆነው ሰብዓዊ አገዛዝ ሥር እስካለን ድረስ ክፋት ሊወገድ ስለማይችል፣ ክፋትን በራሳችን ኃይል ለማጥፋት መጣራችን ከንቱ ነው። አሳፍ እንዳደረገው ሁሉ ክፋትን ተቋቁመን ለመኖር “ወደ እግዚአብሔር መቅረብ” እና ከእርሱ ጋር ጥብቅ ዝምድና መመሥረት ጥበብ ነው።

73:3, 6, 8, 27 ከኩራት፣ ከእብሪት፣ ከፌዝና ከማጭበርበር መራቅ ይኖርብናል። ይህን የምናደርገው ደግሞ እንዲህ ዓይነቶቹ ባሕርያት አንድ ዓይነት ጥቅም የሚያስገኙ በሚመስሉበት ጊዜም መሆን ይኖርበታል።

73:15-17 ግራ የሚያጋባ ሁኔታ ሲያጋጥመን እንደዚህ እንዲሰማን ያደረገውን ጉዳይ ላገኘነው ሰው ሁሉ ከመናገር መቆጠብ ይኖርብናል። እንዲህ ዓይነቱን ጉዳይ ለሌሎች መናገር ተስፋ እንዲቆርጡ ከማድረግ ያለፈ ፋይዳ አይኖረውም። በጉዳዩ ላይ በዝምታ ማሰላሰልና ከሌሎች ጋር መሰብሰባችንን ሳንተው ለገጠመን ጉዳይ መፍትሔ መሻት ተገቢ ይሆናል።—ምሳሌ 18:1

73:21-24 ክፉዎች የተሳካላቸው መስለው በመታየታቸው ከልክ በላይ ‘መመረር’ እንደማያመዛዝኑት እንስሳት ሊያስቆጥር ይችላል። ይህ ዓይነቱ ዝንባሌ በደንብ ያልታሰበበትና ከስሜታዊነት የሚመነጭ ነው። ከዚህ ይልቅ በይሖዋ ምክር መመራት ይገባናል፤ እንዲሁም ይሖዋ ‘ቀኝ እጃችንን እንደሚይዘንና’ እንደሚደግፈን ሙሉ በሙሉ መተማመን ይኖርብናል። እንዲህ ስናደርግ ይሖዋ ‘ወደ ክብሩ ያስገባናል’ ማለትም ከእርሱ ጋር የቅርብ ዝምድና እንድንመሠርት ያስችለናል።

77:6 ለመንፈሳዊ እውነቶች ከልብ የመነጨ ፍላጎት ማሳደርና እነዚህን እውነቶች ፈልጎ ማግኘት ለጥናትና ለማሰላሰል ጊዜ መመደብ ይጠይቃል። እንዲህ ለማድረግ የሚያስችለን ለብቻችን የምንሆንበት ጊዜ መመደባችን ምንኛ አስፈላጊ ነው!

79:9 ይሖዋ፣ በተለይም ከስሙ መቀደስ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ጠቅሰን ስንጸልይ ጸሎታችንን ይሰማል።

81:13, 16 የይሖዋን ድምጽ መስማትና በመንገዱ መሄድ የተትረፈረፈ በረከት ያስገኛል።—ምሳሌ 10:22

82:2, 5 የፍትህ መጓደል ‘የምድርን መሠረቶች’ ያናውጣል። ኢፍትሐዊ ድርጊቶች የሰው ልጅ ማኅበረሰብ ተረጋግቶ እንዳይኖር ያደርጋሉ።

84:1-4, 10-12 መዘምራኑ ለይሖዋ የአምልኮ ቤት አድናቆት ማሳየታቸውና ባገኟቸው ልዩ መብቶች መደሰታቸው ለእኛ ግሩም ምሳሌ ይሆነናል።

86:5 ይሖዋ “ይቅር ባይ” በመሆኑ ምንኛ አመስጋኞች መሆን ይገባናል! ለአንድ ንስሐ የገባ ኃጢአተኛ ምሕረት ለማሳየት የሚያበቃ ምክንያት በሚኖርበት ጊዜ ሁሉ ይሖዋ ይቅር ለማለት ዝግጁ ነው።

87:5, 6 ገነት በምትሆነው ምድር ላይ የሚኖሩ ሰዎች ትንሣኤ አግኝተው ወደ ሰማይ ያረጉትን ሰዎች ስም ማወቅ ይችሉ ይሆን? ጥቅሱ እንዲህ ሊሆን እንደሚችል ያሳያል።

88:13, 14 አንድን ችግር አስመልክቶ ያቀረብነው ጸሎት ቶሎ ምላሽ ያላገኘው ይሖዋ ለእርሱ ያለን ፍቅር ምን ያህል እውነተኛ መሆኑን ለማየት ስለፈለገ ሊሆን ይችላል።

“አመስግኑት፤ ስሙንም ባርኩ”

(መዝሙር 90:1 እስከ 106:48)

በአራተኛው የመዝሙር ስብስብ ውስጥ የሚገኙትን ይሖዋን እንድናወድስ የሚገፋፉ የተለያዩ ምክንያቶች ተመልከት። በመዝሙር 90 ላይ ሙሴ ‘የዘላለማዊውን ንጉሥ’ ሕልውና ብልጭ ብሎ ከሚጠፋው የሰው ልጅ ሕይወት ጋር እያወዳደረ ይናገራል። (1 ጢሞቴዎስ 1:17) ሙሴ በመዝሙር 91:2 ላይ ይሖዋ ‘መጠጊያውና ምሽጉ’ ማለትም የደኅንነቱ ምንጭ እንደሆነ ጠቅሷል። ቀጣዮቹ ጥቂት መዝሙሮች ስለ ይሖዋ ግሩም ባሕርያት፣ ስለማይመረመረው ሐሳቡና ስለ ድንቅ ሥራው ይዘረዝራሉ። ሦስት መዝሙሮች ደግሞ የሚጀምሩት “እግዚአብሔር ነገሠ” በሚለው ሐረግ ነው። (መዝሙር 93:1፤ 97:1፤ 99:1) መዝሙራዊው፣ ይሖዋ ፈጣሪያችን መሆኑን በመግለጽ “አመስግኑት፤ ስሙንም ባርኩ” የሚል ግብዣ አቅርቦልናል።—መዝሙር 100:4

ይሖዋን የሚፈራ ንጉሥ ሕዝቡን ማስተዳደር ያለበት እንዴት ነው? በንጉሥ ዳዊት የተቀናበረው መዝሙር 101 መልሱን ይሰጠናል። ቀጣዩ መዝሙር ደግሞ ይሖዋ “ወደ ችግረኞች ጸሎት ይመለከታል፤ ልመናቸውንም አይንቅም” ይላል። (መዝሙር 102:17) መዝሙር 103 በይሖዋ ፍቅራዊ ደግነትና መሐሪነት ላይ ያተኩራል። መዝሙራዊው ይሖዋ በምድር ላይ የፈጠራቸውን በርካታ ነገሮች ከዘረዘረ በኋላ “እግዚአብሔር ሆይ፤ ሥራህ እንዴት ብዙ ነው! ሁሉን በጥበብ ሠራህ” ሲል በአድናቆት ተናግሯል። (መዝሙር 104:24) በአራተኛው የመዝሙር መጽሐፍ መጨረሻ ላይ ያሉት ሁለት መዝሙሮች ይሖዋን ስለ ድንቅ ሥራው ያወድሳሉ።—መዝሙር 105:2, 5፤ 106:7, 22

ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው፦

91:1, 2የልዑል መጠጊያ [“ምሥጢራዊ ቦታ፣” NW]’ የተባለው ምንድን ነው? በዚያ ‘መኖር’ የምንችለውስ እንዴት ነው? ይህ ስፍራ፣ ከመንፈሳዊ ጥቃት የምንጠለልበትን ሁኔታ ማለትም መንፈሳዊ ደኅንነትና ጥበቃ የምናገኝበትን ምሳሌያዊ ቦታ ያመለክታል። በአምላክ የማይታመኑ ሰዎች ይህ ስፍራ የት እንዳለ ማወቅ ስለማይችሉ ቦታው ምስጢራዊ ነው። ይሖዋን እንደ መጠጊያችንና ምሽጋችን አድርገን በመመልከት፣ የጽንፈ ዓለም ሉዓላዊ ገዥ እንደመሆኑ መጠን እርሱን በማወደስና የመንግሥቱን ምሥራች በመስበክ በልዑል መጠጊያ መኖር እንችላለን። ይሖዋ እኛን ለመርዳት ምንጊዜም ዝግጁ መሆኑን ማወቃችን መንፈሳዊ ደኅንነት እንዲሰማን ያደርጋል።—መዝሙር 90:1

92:12—ጻድቃን ‘እንደ ዘንባባ የሚንሰራፉት’ እንዴት ነው? የዘንባባ ዛፍ ፍሬያማ በመሆኑ ይታወቃል። ጻድቅ ሰውም ልክ እንደ ዘንባባ ዛፍ በይሖዋ ፊት ቅን ነገሮችን ማድረጉንና መልካም ሥራዎችን ጨምሮ በሌሎች ጉዳዮችም “ጥሩ ፍሬ” ማፍራቱን ይቀጥላል።—ማቴዎስ 7:17-20

ምን ትምህርት እናገኛለን?

90:7, 8, 13, 14 ኃጢአት መሥራት ምንጊዜም ቢሆን ከእውነተኛው አምላክ ጋር ያለንን ዝምድና ያበላሽብናል። በስውር የተሠራ ኃጢአት ከአምላክ ዓይን ሊሸሸግ አይችልም። ሆኖም እውነተኛ ንስሐ የምንገባና ከስህተት መንገዳችን የምንመለስ ከሆነ ይሖዋ ዳግመኛ ሞገሱን ያሳየናል፤ ‘ምሕረቱንም [“ፍቅራዊ ደግነቱንም፣” NW] ያጠግበናል።’

90:10, 12 ሕይወት አጭር በመሆኑ “ዕድሜያችንን መቍጠር” ይኖርብናል። ግን እንዴት? “ጥበብን የተሞላ ልብ” እንዲኖረን በማድረግ ወይም ቀሪው ዕድሜያችንን ከማባከን ይልቅ ይሖዋን በሚያስደስት መንገድ ለመኖር የሚያስችል ጥበብ በማዳበር እንዲህ ማድረግ እንችላለን። ይህም ለመንፈሳዊ ጉዳዮች ቅድሚያ መስጠትንና ጊዜያችንን በጥበብ መጠቀምን ይጠይቃል።—ኤፌሶን 5:15, 16፤ ፊልጵስዩስ 1:10

90:17፦ ‘የእጆቻችንን ሥራ ፍሬያማ እንዲያደርግልንና’ አገልግሎታችንን እንዲባርክልን ወደ ይሖዋ መጸለያችን የተገባ ነው።

92:14, 15 አረጋውያን፣ ከይሖዋ ሕዝቦች ጋር አዘውትረው በመሰብሰብና የአምላክን ቃል በትጋት በማጥናት መንፈሳዊ ቅንዓታቸው ሳይዳከም “እንደ ለመለሙና እንደ ጠነከሩ” መኖር ይችላሉ። በዚህ መንገድም ለጉባኤው በረከት መሆናቸውን ያስመሰክራሉ።

94:19 ‘ያስጨነቀን’ ጉዳይ ምንም ይሁን ምን በአምላክ ቃል ውስጥ ያሉትን ‘ማጽናኛዎች’ ማንበባችንና በእነርሱ ላይ ማሰላሰላችን ያጽናናናል።

95:7, 8 ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክሮችን ማዳመጥ፣ ለማሳሰቢያዎቹ ትኩረት መስጠትና ያለማንገራገር መታዘዝ ልባችን እንዳይደነድን ያደርጋል።—ዕብራውያን 3:7, 8

106:36, 37 ይህ ጥቅስ የጣዖት አምልኮን ለአጋንንት ከመሠዋት ጋር አያይዞታል። ይህም ጣዖትን የሚያመልክ ሰው በዲያብሎስ ቁጥጥር ሥር ሊሆን እንደሚችል ያሳያል። መጽሐፍ ቅዱስ “ራሳችሁን ከጣዖቶች ጠብቁ” በማለት ያሳስበናል።—1 ዮሐንስ 5:21

“እናንት ሕዝቦች፣ ያህን አወድሱ!”

በአራተኛው የመዝሙር መጽሐፍ መጨረሻ ላይ ያሉት ሦስት መዝሙሮች የሚደመድሙት “ሃሌ ሉያ [“እናንት ሕዝቦች፣ ያህን አወድሱ!፣” NW]” በሚለው ማሳሰቢያ ነው። በዚሁ መጽሐፍ ውስጥ የመጨረሻው መዝሙር የሚጀምረውም በእነዚሁ ቃላት ነው። (መዝሙር 104:35፤ 105:45፤ 106:1, 48) “ሃሌ ሉያ” የሚለው አባባል በአራተኛው የመዝሙር መጽሐፍ ውስጥ በተደጋጋሚ ተጠቅሶ ይገኛል።

ይሖዋን የምናወድስባቸው በርካታ ምክንያቶች እንዳሉን እሙን ነው። ከመዝሙር 73 እስከ 106 ያሉት ምዕራፎች ልናሰላስልባቸው የምንችላቸው በርካታ ሐሳቦችን የያዙ ሲሆን ይህም ልባችን በሰማይ ለሚኖረው አባታችን ባለን የአመስጋኝነት ስሜት እንዲሞላ ያደርጋል። በአሁኑ ጊዜ እያደረገልን ስላለውና ወደፊትም ስለሚያደርግልን ነገሮች ስናስብ ባለን ኃይል ሁሉ ‘ያህን ለማወደስ’ አንገፋፋም?

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አሳፍ እንዳደረገው ሁሉ እኛም ‘ወደ አምላክ በመቅረብ’ ክፋትን መቋቋም እንችላለን

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ፈርዖን በቀይ ባሕር ታላቅ ሽንፈት ገጥሞታል

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መና ‘የመላእክት እንጀራ’ ተብሎ የተጠራው ለምን እንደሆነ ታውቃለህ?

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

‘ጭንቀታችንን’ ለማስወገድ ምን ይረዳናል?