መዝሙር 102:1-28

  • ጭቆና የደረሰበት ሰው ተስፋ በቆረጠ ጊዜ ያቀረበው ጸሎት

    • “በጣሪያ ላይ እንዳለች ብቸኛ ወፍ ሆንኩ” (7)

    • ‘የሕይወቴ ዘመን እንደሚጠፋ ጥላ ነው’ (11)

    • “ይሖዋ ጽዮንን ዳግመኛ ይገነባል” (16)

    • ይሖዋ ለዘላለም ይኖራል (26, 27)

ጭቆና የደረሰበት ሰው ተስፋ በቆረጠና* ጭንቀቱን በይሖዋ ፊት ባፈሰሰ ጊዜ ያቀረበው ጸሎት።+ 102  ይሖዋ ሆይ፣ ጸሎቴን ስማ፤+እርዳታ ለማግኘት የማሰማው ጩኸት ወደ አንተ ይድረስ።+   የሚያስጨንቅ ሁኔታ ባጋጠመኝ ጊዜ ፊትህን ከእኔ አትሰውር።+ ጆሮህን ወደ እኔ አዘንብል፤*ስጣራ ፈጥነህ መልስልኝ።+   የሕይወት ዘመኔ እንደ ጭስ እየበነነ ነው፤አጥንቶቼም እንደ ምድጃ ከስለዋል።+   እህል መብላት ረስቻለሁና፤ልቤ እንደ ሣር ጠውልጓል፤ ደርቋልም።+   እጅግ ከመቃተቴ የተነሳ+አጥንቶቼ ከቆዳዬ ጋር ተጣበቁ።+   የምድረ በዳ ሻላ* መሰልኩ፤በፍርስራሽ ክምር መካከል እንዳለች ጉጉት ሆንኩ።   እንቅልፍ አጥቼ አድራለሁ፤*በጣሪያ ላይ እንዳለች ብቸኛ ወፍ ሆንኩ።+   ጠላቶቼ ቀኑን ሙሉ ይሳለቁብኛል።+ የሚያፌዙብኝ ሰዎች ስሜን ለእርግማን ይጠቀሙበታል።   አመድን እንደ ምግብ እበላለሁና፤+የምጠጣውም ነገር ከእንባ ጋር ተቀላቅሏል፤+ 10  ይህም የሆነው ከቁጣህና ከንዴትህ የተነሳ ነው፤እኔን ለመጣል ወደ ላይ አንስተኸኛልና። 11  የሕይወቴ ዘመን ፀሐይ ስትጠልቅ እንደሚጠፋ* ጥላ ነው፤+እኔም እንደ ሣር ጠወለግኩ።+ 12  ይሖዋ ሆይ፣ አንተ ግን ለዘላለም ትኖራለህ፤+ዝናህም* ከትውልድ እስከ ትውልድ ይጸናል።+ 13  በእርግጥ ትነሳለህ፤ ለጽዮንም ምሕረት ታሳያለህ፤+ለእሷ ሞገስህን የምታሳይበት ጊዜ ነውና፤+የተወሰነው ጊዜ ደርሷል።+ 14  አገልጋዮችህ በድንጋዮቿ ደስ ይላቸዋልና፤+ለአፈሯም እንኳ ልዩ ፍቅር አላቸው።+ 15  ብሔራት የይሖዋን ስም፣የምድር ነገሥታትም ሁሉ ክብርህን ይፈራሉ።+ 16  ይሖዋ ጽዮንን ዳግመኛ ይገነባልና፤+በክብሩም ይገለጣል።+ 17  የድሆችን ጸሎት በትኩረት ያዳምጣል፤+ጸሎታቸውን አይንቅም።+ 18  ይህ የተጻፈው ለመጪው ትውልድ ነው፤+በመሆኑም ወደፊት የሚመጣው* ሕዝብ ያህን ያወድሳል። 19  ይሖዋ ከፍ ካለው ቅዱስ ስፍራው ወደ ታች ይመለከታልና፤+ከሰማይ ሆኖ ወደ ታች ምድርን ያያል፤ 20  ይህም የእስረኛውን ሲቃ ለመስማት፣+ሞት የተፈረደባቸውንም ነፃ ለማውጣት ነው፤+ 21  በመሆኑም የይሖዋ ስም በጽዮን፣ውዳሴውም በኢየሩሳሌም ይታወጃል፤+ 22  ይህም የሚሆነው ሕዝቦችና መንግሥታትይሖዋን ለማገልገል አንድ ላይ በሚሰበሰቡበት ጊዜ ነው።+ 23  ያለጊዜዬ ኃይል አሳጣኝ፤የሕይወት ዘመኔን አሳጠረ። 24  እኔም እንዲህ አልኩ፦“ከትውልድ እስከ ትውልድ የምትኖረው አምላኬ ሆይ፣+በሕይወት ዘመኔ እኩሌታ አታጥፋኝ። 25  አንተ ከብዙ ዘመናት በፊት የምድርን መሠረት ጣልክ፤ሰማያትም የእጆችህ ሥራ ናቸው።+ 26  እነሱ ይጠፋሉ፤ አንተ ግን ትኖራለህ፤ሁሉም እንደ ልብስ ያረጃሉ። እንደ ልብስ ትቀይራቸዋለህ፤ እነሱም ያልፋሉ። 27  አንተ ግን ያው ነህ፤ ዘመንህም ፍጻሜ የለውም።+ 28  የአገልጋዮችህ ልጆች ያለስጋት ይኖራሉ፤ዘራቸውም በፊትህ ጸንቶ ይኖራል።”+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “በደከመና።”
ወይም “ጎንበስ ብለህ ስማኝ።”
ወይም “ገርጌሶ።” ጠፍጠፍ ያለ ረጅም መንቆር ያለው ትልቅ አሞራ።
“መነመንኩ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “እንደሚረዝም።”
ወይም “ስምህም።” ቃል በቃል “መታሰቢያህም።”
ቃል በቃል “የሚፈጠረው።”