መዝሙር 86:1-17
የዳዊት ጸሎት።
86 ይሖዋ ሆይ፣ ጆሮህን ወደ እኔ አዘንብል፤* ደግሞም መልስልኝ፤ጎስቋላና ድሃ ነኝና።+
2 እኔ ታማኝ ስለሆንኩ ሕይወቴን* ጠብቃት።+
በአንተ የሚታመነውን አገልጋይህን አድነው፤አንተ አምላኬ ነህና።+
3 ይሖዋ ሆይ፣ ሞገስ አሳየኝ፤+ቀኑን ሙሉ አንተን እጣራለሁና።+
4 አገልጋይህን ደስ አሰኘው፤*ይሖዋ ሆይ፣ የአንተን እርዳታ እሻለሁና።*
5 ይሖዋ ሆይ፣ አንተ ጥሩ ነህና፤+ ይቅር ለማለትም ዝግጁ ነህ፤+አንተን ለሚጠሩ ሁሉ የምታሳየው ታማኝ ፍቅር ወሰን የለውም።+
6 ይሖዋ ሆይ፣ ጸሎቴን አዳምጥ፤እርዳታ ለማግኘት የማቀርበውንም ልመና በትኩረት ስማ።+
7 አንተ መልስ ስለምትሰጠኝ፣+በተጨነቅኩ ቀን አንተን እጣራለሁ።+
8 ይሖዋ ሆይ፣ ከአማልክት መካከል እንደ አንተ ያለ የለም፤+ከአንተ ሥራ ጋር የሚወዳደር አንድም ሥራ የለም።+
9 ይሖዋ ሆይ፣ አንተ የሠራሃቸው ብሔራት ሁሉ ይመጣሉ፤በፊትህም ይሰግዳሉ፤+ለስምህም ክብር ይሰጣሉ።+
10 አንተ ታላቅ ነህና፤ ድንቅ ነገሮችም ትሠራለህ፤+አንተ አምላክ ነህ፤ ከአንተ ሌላ የለም።+
11 ይሖዋ ሆይ፣ መንገድህን አስተምረኝ።+
በእውነትህ እሄዳለሁ።+
ስምህን እፈራ ዘንድ ልቤን አንድ አድርግልኝ።*+
12 ይሖዋ አምላኬ ሆይ፣ በሙሉ ልቤ አወድስሃለሁ፤+ስምህንም ለዘላለም ከፍ ከፍ አደርጋለሁ፤
13 ለእኔ የምታሳየው ታማኝ ፍቅር ታላቅ ነውና፤ሕይወቴንም* ጥልቅ ከሆነው መቃብር* አድነሃል።+
14 አምላክ ሆይ፣ እብሪተኛ ሰዎች በእኔ ላይ ተነስተዋል፤+የጨካኞች ቡድን ሕይወቴን* ይሻታል፤አንተንም ከምንም አልቆጠሩም።*+
15 ይሖዋ ሆይ፣ አንተ ግን መሐሪና ሩኅሩኅ፣*ለቁጣ የዘገየህ እንዲሁም ታማኝ ፍቅርህና ታማኝነትህ* የበዛ አምላክ ነህ።+
16 ወደ እኔ ተመልከት፤ ሞገስም አሳየኝ።+
ለአገልጋይህ ብርታትህን ስጠው፤+የሴት ባሪያህንም ልጅ አድን።
17 እኔን የሚጠሉ አይተው እንዲያፍሩ፣የጥሩነትህን ምልክት* አሳየኝ።
ይሖዋ ሆይ፣ አንተ ረዳቴና አጽናኜ ነህና።
የግርጌ ማስታወሻዎች
^ ወይም “ጎንበስ ብለህ ስማኝ።”
^ ወይም “ነፍሴን።”
^ ወይም “የአገልጋይህን ነፍስ ደስ አሰኛት።”
^ ወይም “ነፍሴን ወደ አንተ አነሳለሁና።”
^ ወይም “ያልተከፋፈለ ልብ ስጠኝ።”
^ ወይም “ሲኦል።” የሰው ልጆችን ሁሉ መቃብር ያመለክታል። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
^ ወይም “ነፍሴንም።”
^ ወይም “ነፍሴን።”
^ ወይም “አንተንም በፊታቸው አላደረጉም።”
^ ወይም “ቸር።”
^ ወይም “እውነትህ።”
^ ወይም “ማስረጃ።”