መዝሙር 106:1-48

  • እስራኤል አድናቆት ሳያሳይ ቀረ

    • አምላክ ያደረገውን ነገር ወዲያውኑ ረሱ (13)

    • የአምላክን ክብር በኮርማ ምስል ለወጡ (19, 20)

    • ‘አምላክ በገባው ቃል ላይ እምነት አልነበራቸውም’ (24)

    • ‘ባአልን አመለኩ’ (28)

    • ልጆቻቸውን ለአጋንንት ሠዉ (37)

106  ያህን አወድሱ!* ይሖዋ ጥሩ+ ስለሆነ ምስጋና አቅርቡለት፤ታማኝ ፍቅሩ ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።+  2  የይሖዋን ታላላቅ ሥራዎች ሙሉ በሙሉ ሊያስታውቅ የሚችለው ማን ነው?ወይስ የሚያስመሰግኑ ተግባሮቹን ሁሉ ሊያውጅ የሚችለው ማን ነው?+  3  ፍትሐዊ ድርጊት የሚፈጽሙ፣ምንጊዜም ትክክል የሆነውን የሚያደርጉ+ ደስተኞች ናቸው።  4  ይሖዋ ሆይ፣ ለሕዝብህ ሞገስ* በምታሳይበት ጊዜ እኔንም አስታውሰኝ።+ ተንከባከበኝ፤ ደግሞም አድነኝ፤  5  ይህም ለተመረጡ አገልጋዮችህ+ የምታሳየውን ጥሩነት እንድቀምስ፣ከሕዝብህ ጋር ሐሴት እንዳደርግ፣ከርስትህም ጋር አንተን በኩራት እንዳወድስ* ነው።  6  እኛም እንደ አባቶቻችን ኃጢአት ሠርተናል፤+በድለናል፤ ክፉ ነገርም አድርገናል።+  7  አባቶቻችን በግብፅ በነበሩበት ጊዜ፣ ድንቅ ሥራዎችህን በአድናቆት አልተመለከቱም።* የታማኝ ፍቅርህን ብዛት አላስታወሱም፤ከዚህ ይልቅ በባሕሩ አጠገብ ይኸውም ቀይ ባሕር አጠገብ ዓመፁ።+  8  ይሁንና ኃያልነቱ እንዲታወቅ ሲል፣+ለስሙ ብሎ አዳናቸው።+  9  ቀይ ባሕርን ገሠጸ፤ ባሕሩም ደረቀ፤በበረሃ* የሚሄዱ ያህል በጥልቅ ውኃው መካከል መራቸው፤+ 10  ከባላጋራዎቻቸው እጅ አዳናቸው፤+ከጠላቶቻቸውም እጅ ታደጋቸው።+ 11  ውኃው ጠላቶቻቸውን ዋጠ፤ከእነሱ አንድ ሰው እንኳ አልዳነም።+ 12  በዚያን ጊዜ በገባው ቃል አመኑ፤+የውዳሴ መዝሙር ይዘምሩለት ጀመር።+ 13  ይሁን እንጂ ያደረገውን ነገር ወዲያውኑ ረሱ፤+እሱ የሚሰጣቸውን ምክር በትዕግሥት አልጠበቁም። 14  በምድረ በዳ በራስ ወዳድነት ምኞት ተሸነፉ፤+በበረሃ አምላክን ተፈታተኑት።+ 15  እሱም የለመኑትን ሰጣቸው፤ነገር ግን በሚያመነምን* በሽታ መታቸው።+ 16  በሰፈር ውስጥ በሙሴ፣ደግሞም የይሖዋ ቅዱስ አገልጋይ+ በሆነው በአሮን ቀኑ።+ 17  በዚህ ጊዜ ምድር ተከፍታ ዳታንን ዋጠች፤ከአቤሮንም ጋር ያበሩትን ሰለቀጠች።+ 18  እሳትም በማኅበራቸው መካከል ነደደች፤ነበልባልም ክፉዎችን በላች።+ 19  በኮሬብ ጥጃ ሠሩ፤ከብረት ለተሠራም ሐውልት* ሰገዱ፤+ 20  ሣር በሚበላ ኮርማ ምስልክብሬን ለወጡ።+ 21  በግብፅ ታላላቅ ነገሮች ያደረገውን፣+አዳኛቸው የሆነውን አምላክ ረሱ፤+ 22  በካም ምድር አስደናቂ ሥራዎች፣+በቀይ ባሕር የሚያስፈሩ* ነገሮች ያከናወነውን+ አምላክ ዘነጉ። 23  እንዲጠፉ ሊያዝዝ ምንም አልቀረውም ነበር፤ሆኖም እሱ የመረጠው አገልጋዩ ሙሴ፣አጥፊ ቁጣውን እንዲመልስ አምላክን ተማጸነ።*+ 24  ከዚያም የተወደደችውን ምድር ናቁ፤+በገባው ቃል ላይ እምነት አልነበራቸውም።+ 25  በድንኳኖቻቸው ውስጥ ሆነው ማጉረምረማቸውን ቀጠሉ፤+የይሖዋን ድምፅ አልሰሙም።+ 26  በመሆኑም በምድረ በዳ ሊጥላቸው፣ስለ እነሱ እጁን አንስቶ ማለ፤+ 27  ዘራቸውን በብሔራት መካከል እንደሚጥል፣በየአገሩ እንደሚበትናቸውም ማለ።+ 28  ከዚያም በፌጎር የነበረውን ባአል አመለኩ፤*+ለሙታን የቀረቡትን መሥዋዕቶችም* በሉ። 29  በሥራቸው አምላክን አስቆጡት፤+በመካከላቸውም መቅሰፍት ተነሳ።+ 30  ሆኖም ፊንሃስ ተነስቶ እርምጃ በወሰደ ጊዜ፣መቅሰፍቱ ተገታ።+ 31  ይህም በትውልዶች ሁሉ፣ ለዘላለምጽድቅ ሆኖ ተቆጠረለት።+ 32  በመሪባ* ውኃ አጠገብ አምላክን አስቆጡት፤በእነሱም የተነሳ ሙሴ ችግር ላይ ወደቀ።+ 33  መንፈሱን አስመረሩት፤እሱም በከንፈሮቹ በችኮላ ተናገረ።+ 34  ይሖዋ ባዘዛቸው መሠረት፣+ሕዝቦቹን ከማጥፋት ወደኋላ አሉ።+ 35  ይልቁንም በዚያ ከነበሩት ብሔራት ጋር ተቀላቀሉ፤+የእነሱንም መንገድ ተከተሉ።*+ 36  ጣዖቶቻቸውን አመለኩ፤+እነሱም ወጥመድ ሆኑባቸው።+ 37  ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውንለአጋንንት መሥዋዕት አድርገው ያቀርቡ ነበር።+ 38  ንጹሕ ደም፣ይኸውም ለከነአን ጣዖቶች የሠዉአቸውን+የገዛ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን ደም አፈሰሱ፤+ምድሪቱም በደም ተበከለች። 39  በሥራቸው ረከሱ፤በድርጊታቸውም መንፈሳዊ ምንዝር ፈጸሙ።+ 40  በመሆኑም የይሖዋ ቁጣ በሕዝቡ ላይ ነደደ፤ርስቱንም ተጸየፈ። 41  በተደጋጋሚ ጊዜያት በብሔራት እጅ አሳልፎ ሰጣቸው፤+ይህም የሚጠሏቸው ሰዎች እንዲገዟቸው ነው።+ 42  ጠላቶቻቸው ጨቆኗቸው፤ለእነሱም ሥልጣን* ተገዢ ሆኑ። 43  ብዙ ጊዜ ታደጋቸው፤+እነሱ ግን ያምፁና ለመታዘዝ አሻፈረኝ ይሉ ነበር፤+ከሠሩት ጥፋት የተነሳም ተዋረዱ።+ 44  እሱ ግን ጭንቀታቸውን ይመለከት፣+እርዳታ ለማግኘት የሚያሰሙትንም ጩኸት ይሰማ ነበር።+ 45  ለእነሱ ሲል ቃል ኪዳኑን ያስታውስ ነበር፤ታላቅ በሆነው* ታማኝ ፍቅሩ ተገፋፍቶ ያዝንላቸው* ነበር።+ 46  የማረኳቸው ሰዎች ሁሉበሐዘኔታ እንዲይዟቸው ያደርግ ነበር።+ 47  ይሖዋ አምላካችን ሆይ፣ አድነን፤+ደግሞም ለቅዱስ ስምህ ምስጋና እንድናቀርብ፣አንተንም በማወደስ ሐሴት እንድናደርግ፣*+ከብሔራት ሰብስበን።+ 48  የእስራኤል አምላክ ይሖዋከዘላለም እስከ ዘላለም ይወደስ፤+ ሕዝቦችም ሁሉ “አሜን!”* ይበሉ። ያህን አወድሱ!*

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ሃሌሉያህ!” “ያህ” የይሖዋ ስም አጭር መጠሪያ ነው።
ወይም “በጎ ፈቃድ።”
ወይም “በአንተ እንድኩራራ።”
ወይም “የድንቅ ሥራዎችህን ትርጉም መረዳት አልቻሉም።”
ወይም “በምድረ በዳ።”
ወይም “ነፍሳቸውን በሚያመነምን።”
ወይም “ቀልጦ ለተሠራ ሐውልት።”
ወይም “አክብሮታዊ ፍርሃት የሚያሳድሩ።”
ቃል በቃል “ክፍተቱ ላይ በእሱ ፊት ቆመ።”
ወይም “በፌጎር ከነበረው ባአል ጋር ራሳቸውን አቆራኙ።”
ለሞቱ ሰዎች ወይም ሕይወት ለሌላቸው አማልክት የቀረቡ መሥዋዕቶችን ያመለክታል።
ይህ ቃል “ጠብ” የሚል ትርጉም አለው።
ወይም “ተማሩ።”
ቃል በቃል “እጅ።”
ወይም “ይጸጸት።”
ወይም “ወሰን በሌለው።”
ወይም “በውዳሴህ ሐሴት እንድናደርግ።”
ወይም “ይሁን!”
ወይም “ሃሌሉያህ!” “ያህ” የይሖዋ ስም አጭር መጠሪያ ነው።