በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ምዕራፍ አሥራ አራት

የቤተሰብህን ሕይወት አስደሳች ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?

የቤተሰብህን ሕይወት አስደሳች ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?
  • ጥሩ ባል ለመሆን የሚያስፈልገው ነገር ምንድን ነው?

  • አንዲት ሴት የሚስትነት ድርሻዋን በተሳካ ሁኔታ መወጣት የምትችለው እንዴት ነው?

  • ጥሩ ወላጅ መሆን ምን ይጠይቃል?

  • ልጆች የቤተሰብን ሕይወት አስደሳች ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው?

1. አስደሳች ለሆነ የቤተሰብ ሕይወት ቁልፉ ምንድን ነው?

ይሖዋ አምላክ የቤተሰብህ ሕይወት አስደሳች እንዲሆን ይፈልጋል። ቃሉ መጽሐፍ ቅዱስ እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል ሊጫወተው የሚገባውን ሚና በተመለከተ አምላክ የሰጠውን መመሪያ ይዟል። የቤተሰብ አባላት አምላክ ከሰጠው ምክር ጋር በሚስማማ መንገድ የየራሳቸውን ድርሻ ሲወጡ የሚገኘው ውጤት በጣም አስደሳች ይሆናል። ኢየሱስ “ብፁዓንስ [“ደስተኛስ፣” NW] የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተው የሚታዘዙት ናቸው” ብሏል።—ሉቃስ 11:28

2. የቤተሰብ ደስታ የተመካው ምን ነገር በመገንዘባችን ላይ ነው?

2 የቤተሰብ ደስታ በዋነኝነት የተመካው ቤተሰብ የተገኘው ኢየሱስ “አባታችን” ሲል ከጠራው ከይሖዋ መሆኑን በመገንዘባችን ላይ ነው። (ማቴዎስ 6:9) በምድር ላይ ያለውን እያንዳንዱን ቤተሰብ ወደ ሕልውና ያመጣው ሰማያዊ አባታችን በመሆኑ ቤተሰቦችን ደስተኛ ሊያደርጋቸው የሚችለው ነገር ምን እንደሆነ ያውቃል። (ኤፌሶን 3:14, 15) ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስ እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል ስላለው ድርሻ ምን ያስተምራል?

ቤተሰብን የመሠረተው አምላክ ነው

3. መጽሐፍ ቅዱስ የሰብዓዊውን ቤተሰብ አመሠራረት የሚገልጸው እንዴት ነው? ይህን አስመልክቶ የሚሰጠው ሐሳብ ትክክል ነው የምንለውስ ለምንድን ነው?

3 ይሖዋ የመጀመሪያዎቹን ሰዎች ማለትም አዳምንና ሔዋንን ከፈጠረ  በኋላ ባልና ሚስት አደረጋቸው። ውብ በሆነች ምድራዊ ገነት ይኸውም በኤደን የአትክልት ሥፍራ ውስጥ በማስቀመጥ ልጆች እንዲወልዱ አዘዛቸው። “ብዙ ተባዙ፤ ምድርን ሙሏት” አላቸው። (ዘፍጥረት 1:26-28፤ 2:18, 21-24) ኢየሱስ የዘፍጥረት መጽሐፍ ስለ ቤተሰብ ሕይወት አመሠራረት የሚናገረው ነገር ትክክል እንደሆነ ያመለከተ በመሆኑ ይህ ልብ ወለድ ወይም አፈ ታሪክ አይደለም። (ማቴዎስ 19:4, 5) በአሁኑ ጊዜ ያለው ሕይወት በችግር የተሞላና አምላክ መጀመሪያ ከነበረው ዓላማ ፈጽሞ የተለየ ቢሆንም በቤተሰብ ውስጥ ደስታ ማግኘት ይቻላል የምንለው ለምን እንደሆነ እስቲ እንመርምር።

4. (ሀ) እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል ለቤተሰቡ ደስታ አስተዋጽኦ ማበርከት የሚችለው እንዴት ነው? (ለ) በቤተሰብ ሕይወት ደስተኛ ለመሆን የኢየሱስን ሕይወት ማጥናት በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

4 እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል ፍቅር በማሳየት ረገድ የአምላክን ምሳሌ በመኮረጅ የቤተሰቡን ሕይወት አስደሳች ለማድረግ የበኩሉን አስተዋጽኦ ማበርከት ይችላል። (ኤፌሶን 5:1, 2) ይሁንና አምላክን ልናየው ስለማንችል የእሱን ምሳሌ እንዴት ልንኮርጅ እንችላለን? ይሖዋ የበኩር ልጁን ከሰማይ ወደ ምድር ልኮት የነበረ በመሆኑ የተለያዩ ነገሮችን የሚያከናውንበትን መንገድ ከእሱ ልንማር እንችላለን። (ዮሐንስ 1:14, 18) የአምላክ ልጅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ በነበረበት ወቅት የሰማያዊ አባቱን ምሳሌ በሚገባ በመኮረጁ ኢየሱስን ማየትና መስማት ከይሖዋ ጋር የመሆንና እሱን የመስማት ያህል ነበር። (ዮሐንስ 14:9) ስለዚህ ኢየሱስ ያሳየውን ፍቅር በመማርና የእሱን ምሳሌ በመከተል እያንዳንዳችን የቤተሰባችንን ሕይወት ይበልጥ አስደሳች ለማድረግ የበኩላችንን አስተዋጽኦ ማበርከት እንችላለን።

ለባሎች የሚሆን አርዓያ

5, 6. (ሀ) ኢየሱስ ጉባኤውን የያዘበት መንገድ ለባሎች ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው እንዴት ነው? (ለ) የኃጢአት ይቅርታ ለማግኘት ምን ማድረግ ያስፈልጋል?

5 መጽሐፍ ቅዱስ ባሎች ሚስቶቻቸውን ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን በያዘበት መንገድ መያዝ እንዳለባቸው ይናገራል። የሚከተለውን የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ ተመልከት:- “ባሎች ሆይ፤ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን እንደ ወደዳትና ራሱንም ስለ እርሷ አሳልፎ እንደ ሰጠ፣ እናንተም ሚስቶቻችሁን ውደዱ፤ . . . ባሎችም እንደዚሁ ሚስቶቻቸውን እንደ ገዛ ሥጋቸው መውደድ ይገባቸዋል። ሚስቱን የሚወድ ራሱን ይወዳል። የገዛ  ሥጋውን የሚጠላ ማንም የለም፤ ይመግበዋል፤ ይንከባከበዋል፤ ክርስቶስም ለቤተ ክርስቲያን ያደረገው ልክ እንደዚሁ ነው።”ኤፌሶን 5:23, 25-29

6 ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ላቀፈው ጉባኤው ያሳየው ፍቅር ለባሎች ፍጹም ምሳሌ ነው። ደቀ መዛሙርቱ ፍጹማን ባይሆኑም እንኳ ኢየሱስ ሕይወቱን ለእነሱ በመሠዋት ‘እስከ መጨረሻው ወዷቸዋል።’ (ዮሐንስ 13:1 የ1954 ትርጉም፤ 15:13) በተመሳሳይም ባሎች “ሚስቶቻችሁን ውደዱ፤ መራራም አትሁኑባቸው” የሚል ማሳሰቢያ ተሰጥቷቸዋል። (ቈላስይስ 3:19) አንድ ባል በተለይ ሚስቱ አንዳንድ ጊዜ ማስተዋል የጎደለው ድርጊት የምትፈጽም ከሆነ እንዲህ ያለውን ምክር ተግባራዊ እንዲያደርግ ምን ሊረዳው ይችላል? ራሱም ስህተት እንደሚሠራና የአምላክን ይቅርታ ለማግኘት ሊያደርገው የሚገባውን ነገር ማስታወስ ይኖርበታል። ሊያደርገው የሚገባው ነገር ምንድን ነው? ሚስቱን ጨምሮ ሌሎች የሚፈጽሙበትን በደል ይቅር ማለት አለበት። እሷም እንዲሁ ማድረግ እንዳለባት የታወቀ ነው። (ማቴዎስ 6:12, 14, 15) አንዳንዶች ስኬታማ ትዳር የሁለት ይቅር ባዮች ጥምረት ውጤት ነው የሚሉት ለምን እንደሆነ አስተዋልክ?

7. ኢየሱስ ግምት ውስጥ ያስገባው ነገር ምንድን ነው? ለባሎችስ ምን ምሳሌ ትቷል?

7 በተጨማሪም ባሎች ኢየሱስ ምንጊዜም ለደቀ መዛሙርቱ አሳቢነት ያሳይ እንደነበር ማስተዋል ያስፈልጋቸዋል። ያለባቸውን የአቅም ገደብና አካላዊ ፍላጎቶቻቸውን ግምት ውስጥ ያስገባ ነበር። ለምሳሌ ያህል ደክሟቸው በነበረበት ወቅት “እስቲ ብቻችሁን ከእኔ ጋር ወደ አንድ ገለልተኛ ስፍራ እንሂድና ጥቂት ዕረፉ” ብሏቸዋል። (ማርቆስ 6:30-32) ባሎችም ለሚስቶቻቸው ከፍተኛ አሳቢነት ሊያሳዩ ይገባል። መጽሐፍ ቅዱስ ሚስቶችን እንደ “ተሰባሪ ዕቃ [NW]” አድርጎ የሚገልጻቸው ሲሆን ባሎችም ‘እንዲያከብሯቸው’ ታዘዋል። ለምን? ምክንያቱም ‘የሕይወትን በረከት’ ባሎች ብቻ ሳይሆኑ ሚስቶችም በእኩል ደረጃ ያገኛሉ። (1 ጴጥሮስ 3:7) ባሎች አንድን ሰው በአምላክ ፊት ውድ የሚያደርገው ወንድ ወይም ሴት መሆኑ ሳይሆን ታማኝነቱ እንደሆነ ማስታወስ ይኖርባቸዋል።—መዝሙር 101:6

8. (ሀ) “ሚስቱን የሚወድ [ባል] ራሱን ይወዳል” ሊባል የሚችለው እንዴት ነው? (ለ) ባልና ሚስት “አንድ ሥጋ” መሆናቸው ምን ትርጉም አለው?

8 መጽሐፍ ቅዱስ “ሚስቱን የሚወድ [ባል] ራሱን ይወዳል” ይላል። ይህ የሆነበት ምክንያት ኢየሱስ እንዳመለከተው ባልና ሚስት ‘አንድ ሥጋ  እንጂ ሁለት ስላልሆኑ’ ነው። (ማቴዎስ 19:6) ስለዚህ ከትዳር ጓደኛቸው ውጭ ከሌላ ከማንም ሰው ጋር የጾታ ግንኙነት ማድረግ አይገባቸውም። (ምሳሌ 5:15-21፤ ዕብራውያን 13:4) ከራስ ወዳድነት መንፈስ ነፃ በሆነ መንገድ አንዳቸው ለሌላው ፍላጎት የሚያስቡ ከሆነ ይህን ማድረግ ይችላሉ። (1 ቆሮንቶስ 7:3-5) “የገዛ ሥጋውን የሚጠላ ማንም የለም፤ ይመግበዋል፤ ይንከባከበዋል” የሚለው ማሳሰቢያ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ነው። ባሎች የእነሱ ራስ በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ ፊት ተጠያቂዎች መሆናቸውን በማስታወስ ራሳቸውን እንደሚወዱ ሚስቶቻቸውንም ሊወዱ ይገባል።—ኤፌሶን 5:29፤ 1 ቆሮንቶስ 11:3

9. በፊልጵስዩስ 1:8 ላይ የተጠቀሰው የኢየሱስ ባሕርይ ምንድን ነው? ባሎች ይህን ባሕርይ ለሚስቶቻቸው ማሳየት ያለባቸውስ ለምንድን ነው?

9 ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ “ክርስቶስ ኢየሱስ ፍቅር” ተናግሮ ነበር። (ፊልጵስዩስ 1:8) የኢየሱስ ጥልቅ ፍቅር መንፈስ የሚያድስ ሲሆን ደቀ መዛሙርቱ የሆኑት ሴቶች በዚህ ባሕርይው ይወዱት ነበር። (ዮሐንስ 20:1, 11-13, 16) ሚስቶችም ባሎቻቸው እንዲህ ያለ ጥልቅ ፍቅር እንዲያሳዩአቸው ይፈልጋሉ።

ለሚስቶች የሚሆን ምሳሌ

10. ኢየሱስ ለሚስቶች ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው እንዴት ነው?

10 ቤተሰብ ራሱን የቻለ ድርጅታዊ መዋቅር ያለው ሲሆን በተቃና ሁኔታ እንዲሠራ አመራር የሚሰጥ ራስ ያስፈልገዋል። ኢየሱስ እንኳ የሚገዛለት ራስ አለው። ‘የሴት ራስ ወንድ’ እንደሆነ ሁሉ “የክርስቶስም ራስ እግዚአብሔር ነው።” (1 ቆሮንቶስ 11:3) ሁላችንም ልንገዛለት የሚገባ ራስ ስላለን ኢየሱስ ለአምላክ የራስነት ሥልጣን መገዛቱ ጥሩ ምሳሌ ይሆነናል።

11. አንዲት ሚስት ለባሏ ምን አመለካከት ሊኖራት ይገባል? አኗኗሯስ ምን ውጤት ሊያስገኝ ይችላል?

11 ፍጽምና የጎደላቸው ወንዶች የሚሳሳቱ ከመሆኑም በላይ ብዙውን ጊዜ መሥፈርቱን ሙሉ በሙሉ የሚያሟሉ የቤተሰብ ራሶች ሆነው አይገኙም። ስለዚህ አንዲት ሚስት ምን ማድረግ ይኖርባታል? ባልዋ የሚያደርገውን ነገር ማንቋሸሽም ሆነ የራስነት ሥልጣኑን ለመውሰድ መሞከር የለባትም። አንዲት ሚስት የጭምትነትና የገርነት መንፈስ በአምላክ ፊት ትልቅ ዋጋ እንዳለው ማስታወስ ይኖርባታል። (1 ጴጥሮስ 3:4) እንዲህ ያለ መንፈስ የምታንጸባርቅ ከሆነ ፈታኝ የሆኑ ሁኔታዎች በሚኖሩበት  ጊዜም እንኳ አምላክ ላወጣው የራስነት ሥልጣን ለመገዛት አትቸገርም። ከዚህም በተጨማሪ መጽሐፍ ቅዱስ “ሚስትም ባሏን ታክብር” ይላል። (ኤፌሶን 5:33) ሆኖም ባልየው ለክርስቶስ የራስነት ሥልጣን የማይገዛ ቢሆንስ? መጽሐፍ ቅዱስ ሚስቶችን እንዲህ ሲል አጥብቆ ይመክራል:- “ለባሎቻችሁ ተገዙ፤ አንዳንድ ለቃሉ የማይታዘዙ ቢኖሩ፣ ያለ ቃል በሚስቶቻቸው አኗኗር ተማርከው ይመለሳሉ፤ ይህም የሚሆነው ንጹሕና ፍጹም አክብሮት የተሞላውን ኑሮአችሁን ሲመለከቱ ነው።”—1 ጴጥሮስ 3:1, 2

12. አንዲት ሚስት ሐሳቧን አክብሮት በተሞላበት መንገድ መግለጿ ስህተት ያልሆነው ለምንድን ነው?

12 አንዲት ሚስት ባሏ አማኝ ሆነም አልሆነ ጥበብ በተሞላበት መንገድ ከባሏ ለየት ያለ ሐሳብ ብታቀርብ አክብሮት ጎድሏታል ሊያሰኛት አይችልም። ያቀረበችው ሐሳብ ትክክል ሊሆንና ባሏ ሐሳቧን ከተቀበለ መላው ቤተሰብ ሊጠቀም ይችል ይሆናል። አብርሃም ሚስቱ ማለትም ሣራ በቤተሰባቸው ውስጥ ለተፈጠረ አንድ ችግር ጥሩ መፍትሔ የሚሆን ሐሳብ ባቀረበች ጊዜ በሐሳቧ ባይስማማም እንኳ አምላክ “የምትልህን ሁሉ ስማ” ብሎታል። (ዘፍጥረት 21:9-12) እርግጥ አንድ ባል ከአምላክ ሕግ ጋር የማይጋጭ ውሳኔ በሚያደርግበት ጊዜ ሚስቱ ውሳኔውን በመደገፍ ለራስነት ሥልጣኑ እንደምትገዛ ታሳያለች።—የሐዋርያት ሥራ 5:29፤ ኤፌሶን 5:24

ሣራ ለሚስቶች ምን ግሩም ምሳሌ ትታለች?

13. (ሀ) ቲቶ 2:4, 5 ያገቡ ሴቶች ምን እንዲያደርጉ አጥብቆ ይመክራል? (ለ) መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መለያየትና ስለ ፍቺ ምን ይላል?

13 አንዲት ሚስት ቤተሰቧን በመንከባከብ ረገድ ያላትን ድርሻ በብዙ መንገዶች መወጣት ትችላለች። ለምሳሌ ያህል መጽሐፍ ቅዱስ ያገቡ ሴቶች ‘ባሎቻቸውንና ልጆቻቸውን የሚወዱ፣ ራሳቸውን የሚገዙና ንጹሓን፣ በቤት ውስጥ በሥራ የተጠመዱ፣ ቸሮችና ለባሎቻቸው የሚገዙ’ መሆን እንዳለባቸው ይገልጻል። (ቲቶ 2:4, 5) በዚህ መንገድ የሚስትነትም ሆነ የእናትነት ኃላፊነቷን የምትወጣ ሴት ለዘለቄታው የቤተሰቧን ፍቅርና አክብሮት ታተርፋለች። (ምሳሌ 31:10, 28) ይሁን እንጂ ትዳር ፍጽምና የጎደላቸው ሁለት ሰዎች ጥምረት በመሆኑ አንዳንድ የከፉ ሁኔታዎች እስከ መለያየት ወይም መፋታት ሊያደርሱ ይችላሉ። መጽሐፍ ቅዱስ መለያየትን የሚፈቅድባቸው አንዳንድ ሁኔታዎች ቢኖሩም “ሚስት ከባሏ አትለያይ፤ . . . ባልም ሚስቱን አይፍታት” በማለት የሚመክር በመሆኑ መለያየትን  አቅልለን ልንመለከተው አይገባም። (1 ቆሮንቶስ 7:10, 11) በተጨማሪም በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት ባልና ሚስት ለፍቺ ሊበቁ የሚችሉት አንዳቸው ዝሙት በሚፈጽሙበት ጊዜ ብቻ ነው።—ማቴዎስ 19:9

ለወላጆች የሚሆን ፍጹም ምሳሌ

14. ኢየሱስ ልጆችን ይይዝ የነበረው እንዴት ነው? ልጆች ከወላጆቻቸው የሚፈልጉት ነገርስ ምንድን ነው?

14 ኢየሱስ ልጆችን ይይዝ የነበረበት መንገድ ለወላጆች ፍጹም ምሳሌ ይሆናል። ሌሎች ሰዎች ሕፃናት ወደ እሱ እንዳይመጡ ለመከልከል በሞከሩበት ጊዜ ኢየሱስ “ሕፃናት ወደ እኔ ይምጡ፤ አትከልክሏቸው” ሲል ተናግሯል። ከዚያም “ሕፃናቱንም ዐቀፋቸው፤ እጁንም ጭኖ ባረካቸው” በማለት መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ማርቆስ 10:13-16) ኢየሱስ ከሕፃናት ጋር ጊዜ ካሳለፈ አንተስ ከራስህ ወንዶችና ሴቶች ልጆች ጋር ጊዜ ማሳለፍ አይኖርብህም? ልጆችህ ጥቂት ሳይሆን ሰፋ ያለ ጊዜ እንድትመድብላቸው ይፈልጋሉ። ይሖዋ ወላጆች ልጆቻቸውን እንዲያስተምሩ መመሪያ የሰጠ በመሆኑ ልጆችህን ለማስተማር ጊዜ መመደብ ያስፈልግሃል።—ዘዳግም 6:4-9

15. ወላጆች ልጆቻቸውን ለመጠበቅ ምን ሊያደርጉ ይችላሉ?

15 ይህ ዓለም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋ በመሄዱ ልጆች የወላጆቻቸው ጥበቃ በእጅጉ ያስፈልጋቸዋል። በተለይ ደግሞ ሕፃናትን ከሚያስነውሩና ሌሎች መጥፎ ድርጊቶችን ከሚፈጽሙ አደገኛ ሰዎች ጥበቃ ማግኘት  አለባቸው። ኢየሱስ “ልጆቼ” በማለት ፍቅራዊ በሆነ መንገድ የጠራቸውን ደቀ መዛሙርቱን እንዴት ጥበቃ እንዳደረገላቸው ተመልከት። በተያዘበትና የሚገደልበት ጊዜ በተቃረበበት ወቅት ደቀ መዛሙርቱ ማምለጥ የሚችሉበትን ሁኔታ አመቻችቶላቸዋል። (ዮሐንስ 13:33፤ 18:7-9) ወላጅ እንደመሆንህ መጠን ዲያብሎስ ልጆችህን ለመጉዳት የሚያደርጋቸውን ሙከራዎች በንቃት መከታተል አለብህ። አስቀድመህ ማስጠንቀቂያ ልትሰጣቸው ይገባል። * (1 ጴጥሮስ 5:8) አካላዊ፣ መንፈሳዊና ሥነ ምግባራዊ ደኅንነታቸው የአሁኑን ያህል አደጋ ላይ የወደቀበት ጊዜ የለም።

ወላጆች ኢየሱስ ልጆችን ከያዘበት መንገድ ምን ትምህርት ሊያገኙ ይችላሉ?

16. ወላጆች ኢየሱስ የደቀ መዛሙርቱን ጉድለቶች ካስተካከለበት መንገድ ምን ትምህርት ሊያገኙ ይችላሉ?

16 ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት ባሳለፈው የመጨረሻ ምሽት ደቀ መዛሙርቱ  ከመካከላቸው ማን እንደሚበልጥ ክርክር አንስተው ነበር። ኢየሱስ በዚህ ከመበሳጨት ይልቅ ፍቅራዊ በሆነ መንገድ በቃልና በተግባር ማስተማሩን ቀጥሏል። (ሉቃስ 22:24-27፤ ዮሐንስ 13:3-8) ወላጅ ከሆንክ ለልጆችህ እርማት በመስጠት ረገድ የኢየሱስን ምሳሌ እንዴት ልትከተል እንደምትችል አስተዋልክ? ልጆች ተግሣጽ እንደሚያስፈልጋቸው የታወቀ ነው፤ ሆኖም ተግሣጽ ሊሰጣቸው የሚገባው “በመጠኑ” ከመሆኑም በላይ በቁጣ መሆን የለበትም። ‘እንደሚዋጋ ሰይፍ’ በሚጎዳና አሳቢነት በጎደለው መንገድ ልትናገራቸው አይገባም። (ኤርምያስ 30:11፤ ምሳሌ 12:18) ተግሣጽ የምትሰጥበት መንገድ ከጊዜ በኋላ ልጅህ ተግሣጹ ተገቢ መሆኑን እንዲገነዘብ የሚያደርግ መሆን ይኖርበታል።—ኤፌሶን 6:4፤ ዕብራውያን 12:9-11

ለልጆች የሚሆን አርዓያ

17. ኢየሱስ ለልጆች ፍጹም ምሳሌ የተወው በምን መንገዶች ነው?

17 ልጆች ከኢየሱስ ሊማሩ ይችላሉ? አዎን፣ ይችላሉ! ኢየሱስ ልጆች ለወላጆቻቸው እንዴት ሊታዘዙ እንደሚገባ የሚያሳይ ምሳሌ ትቷል። ‘አብ ያስተማረኝን እናገራለሁ’ ብሏል። አክሎም ‘ምንጊዜም የሚያስደስተውን አደርጋለሁ’ ሲል ገልጿል። (ዮሐንስ 8:28, 29) ኢየሱስ ለሰማያዊ አባቱ ታዛዥ የነበረ ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስ ልጆች ለወላጆቻቸው እንዲታዘዙ ይመክራል። (ኤፌሶን 6:1-3) ምንም እንኳ ኢየሱስ ፍጹም ልጅ የነበረ ቢሆንም ፍጽምና ይጎድላቸው የነበሩትን ወላጆቹን ማለትም ዮሴፍንና ማርያምን ይታዘዝ ነበር። ይህ ለመላው የኢየሱስ ቤተሰብ አባላት ደስታ እንዳስገኘ ጥርጥር የለውም።—ሉቃስ 2:4, 5, 51, 52

18. ኢየሱስ በሰማይ ያለውን አባቱን ምንጊዜም ይታዘዝ የነበረው ለምንድን ነው? በዛሬው ጊዜ ልጆች ወላጆቻቸውን ሲታዘዙ ማን ይደሰታል?

18 ልጆች ኢየሱስን ይበልጥ በመምሰል ወላጆቻቸውን ማስደሰት የሚችሉባቸው መንገዶች ይኖራሉ? እርግጥ ነው፣ አንዳንድ ጊዜ ልጆች ወላጆቻቸውን መታዘዝ በጣም ከባድ እንደሆነ ሊሰማቸው ይችላል፤ ሆኖም አምላክ ልጆች ወላጆቻቸውን እንዲታዘዙ ይፈልጋል። (ምሳሌ 1:8፤ 6:20) ኢየሱስ አስቸጋሪ በሆኑ ሁኔታዎች ሳይቀር በሰማይ ያለውን አባቱን ይታዘዝ ነበር። የአምላክን ፈቃድ ለመፈጸም ሲል አንድ በጣም ከባድ የሆነ ነገር ማከናወን አስፈልጎት በነበረበት ወቅት “ይህችን ጽዋ [እንዲያከናውን ይፈለግበት የነበረውን ነገር] ከእኔ ውሰድ” ብሎ ነበር። ያም ሆኖ ኢየሱስ አባቱ የተሻለውን ነገር እንደሚያውቅ ስለተገነዘበ አምላክ  የጠየቀውን ነገር ከመፈጸም ወደኋላ አላለም። (ሉቃስ 22:42) ልጆች ታዛዥነትን በመማር ወላጆቻቸውንና የሰማዩን አባታቸውን ማስደሰት ይችላሉ። *ምሳሌ 23:22-25

ልጆች ትክክል ያልሆነ ነገር ለማድረግ በሚፈተኑበት ጊዜ ምን ማስታወስ ይኖርባቸዋል?

19. (ሀ) ሰይጣን ልጆችን የሚፈትነው እንዴት ነው? (ለ) የልጆች መጥፎ ምግባር በወላጆቻቸው ላይ ምን ውጤት ሊያስከትል ይችላል?

19 ዲያብሎስ ኢየሱስን እንደፈተነው ሁሉ ልጆችንም ትክክል ያልሆነ ነገር እንዲሠሩ በመገፋፋት እንደሚፈትናቸው እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። (ማቴዎስ 4:1-10) ሰይጣን ዲያብሎስ ለመቋቋም ከባድ የሆነውን የእኩዮች ተጽዕኖ መሣሪያ አድርጎ ይጠቀማል። እንግዲያው ልጆች መጥፎ ምግባር ካላቸው ጋር ጓደኝነት አለመመሥረታቸው በጣም አስፈላጊ ነው! (1 ቆሮንቶስ 15:33) የያዕቆብ ልጅ ዲና ይሖዋን ከማያመልኩ ሰዎች ጋር ባልንጀርነት መመሥረቷ ትልቅ ችግር አስከትሏል። (ዘፍጥረት 34:1, 2) ከአንድ ቤተሰብ አባላት አንዱ የጾታ ብልግና ቢፈጽም ቤተሰቡ ምን ያህል ሊጎዳ እንደሚችል አስበው!—ምሳሌ 17:21, 25

ለቤተሰብ ደስታ ቁልፍ የሆነው ነገር

20. እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል የቤተሰብ ሕይወቱ አስደሳች ይሆን ዘንድ ምን ማድረግ ይኖርበታል?

20 የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር ተግባራዊ ማድረግ ከተቻለ የቤተሰብ ችግሮችን በቀላሉ መወጣት ይቻላል። እንዲያውም ለቤተሰብ ደስታ  ቁልፉ የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር ተግባራዊ ማድረግ ነው። ስለዚህ ባሎች የሆናችሁ ሚስቶቻችሁን ውደዱ እንዲሁም ኢየሱስ ጉባኤውን በያዘበት መንገድ ያዟቸው። ሚስቶች የሆናችሁ ለባሎቻችሁ የራስነት ሥልጣን ተገዙ እንዲሁም በምሳሌ 31:10-31 ላይ የተገለጸችውን ባለሙያ ሚስት ምሳሌ ተከተሉ። ወላጆች የሆናችሁ ልጆቻችሁን አሠልጥኑ። (ምሳሌ 22:6) አባቶች የሆናችሁ ‘የገዛ ቤተሰባችሁን በአግባቡ አስተዳድሩ።’ (1 ጢሞቴዎስ 3:4, 5፤ 5:8) ልጆች የሆናችሁ ደግሞ ወላጆቻችሁን ታዘዙ። (ቈላስይስ 3:20) ሁሉም ስህተት ስለሚሠሩ በቤተሰብ ውስጥ ፍጹም የሆነ ሰው የለም። ስለዚህ በትሕትና አንዳችሁ ሌላውን ይቅርታ ጠይቁ።

21. ከፊታችን ምን አስደሳች ተስፋዎች ይጠብቁናል? በአሁኑ ጊዜ የቤተሰብ ሕይወታችንን አስደሳች ማድረግ የምንችለውስ እንዴት ነው?

21 በእርግጥም መጽሐፍ ቅዱስ የቤተሰብን ሕይወት በተመለከተ ጠቃሚ የሆኑ በርካታ ምክሮችንና መመሪያዎችን ይዟል። ከዚህም በተጨማሪ አምላክ አዲስ ዓለም እንደሚያመጣና ምድር ገነት ሆና ይሖዋን በሚያመልኩ ደስተኛ ሰዎች እንደምትሞላ ያስተምረናል። (ራእይ 21:3, 4) እንዴት ያሉ አስደሳች ተስፋዎች ይጠብቁናል! በዚህ ሥርዓትም እንኳ በቃሉ ማለትም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሠፈሩትን የአምላክ መመሪያዎች ተግባራዊ በማድረግ የቤተሰብ ሕይወታችንን አስደሳች ማድረግ እንችላለን።

^ አን.15 ልጆችን ለመጠበቅ የሚረዳ ሐሳብ በይሖዋ ምሥክሮች በተዘጋጀው ከታላቁ አስተማሪ ተማሩ በተባለው መጽሐፍ ምዕራፍ 32 ላይ ይገኛል።

^ አን.18 አንድ ልጅ ወላጁን መታዘዝ የማይኖርበት የአምላክን ሕግ የሚያስጥስ ነገር እንዲያደርግ በሚጠየቅበት ጊዜ ብቻ ነው።—የሐዋርያት ሥራ 5:29