በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ምዕራፍ ሁለት

መጽሐፍ ቅዱስ—አምላክ ለሰው ልጆች የሰጠው መጽሐፍ

መጽሐፍ ቅዱስ—አምላክ ለሰው ልጆች የሰጠው መጽሐፍ
  • መጽሐፍ ቅዱስ ከሌሎች መጻሕፍት ሁሉ የተለየ የሆነው በምን መንገዶች ነው?

  • መጽሐፍ ቅዱስ የሚያጋጥሙህን ችግሮች እንድትቋቋም ሊረዳህ የሚችለው እንዴት ነው?

  • በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሰፈሩትን ትንቢቶች እምነት ልትጥልባቸው የምትችለው ለምንድን ነው?

1, 2. መጽሐፍ ቅዱስ ልዩ ስጦታ የሆነው በምን መንገዶች ነው?

ከምትወደው ጓደኛህ ልዩ ስጦታ የተቀበልክበትን ጊዜ ታስታውሳለህ? እንዲህ ያለው ገጠመኝ ልዩ ስሜት የሚቀሰቅስ ብቻ ሳይሆን በጣም የሚያስደስት ነው። እንዲያውም ይህ ዓይነቱ ስጦታ ግለሰቡ ወዳጅነታችሁን ከፍ አድርጎ እንደሚመለከተው እንድትገነዘብ ያደርግሃል። ጓደኛህ አስቦ እንዲህ ያለ ስጦታ ስለሰጠህ እንደምታመሰግነው የታወቀ ነው።

2 መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ስጦታ ነው፤ ለዚህም አመስጋኞች ልንሆን ይገባል። በዓይነቱ ልዩ የሆነው ይህ መጽሐፍ በሌላ በምንም መንገድ ልናገኛቸው የማንችላቸውን መረጃዎች ይሰጠናል። ለምሳሌ ያህል በከዋክብት የተሞሉት ሰማያት፣ ምድር እንዲሁም የመጀመሪያዎቹ ወንድና ሴት ስለተፈጠሩበት ሁኔታ ይገልጽልናል። መጽሐፍ ቅዱስ በሕይወት ውስጥ የሚያጋጥሙንን ችግሮችና የሚያስጨንቁ ሁኔታዎች መቋቋም እንድንችል የሚረዱ አስተማማኝ የሆኑ መሠረታዊ መመሪያዎችን ይዟል። አምላክ ዓላማውን እንዴት ዳር እንደሚያደርስና በምድር ላይ የተሻሉ ሁኔታዎችን እንደሚያመጣ ይገልጻል። በእርግጥም መጽሐፍ ቅዱስ ልዩ ስጦታ ነው!

3. ይሖዋ መጽሐፍ ቅዱስን ለእኛ መስጠቱ ምን ያስገነዝበናል? ይህስ በጣም አስደሳች የሆነው ለምንድን ነው?

3 በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሰጪው ማለትም ስለ ይሖዋ አምላክ ስለሚናገር በጣም የሚያስደስት ስጦታ ነው። ይሖዋ ይህን መጽሐፍ  መስጠቱ በደንብ እንድናውቀው እንደሚፈልግ የሚያሳይ ማስረጃ ነው። በእርግጥም መጽሐፍ ቅዱስ ወደ ይሖዋ እንድትቀርብ ሊረዳህ ይችላል።

4. የመጽሐፍ ቅዱስን ስርጭት በተመለከተ በጣም የሚያስደንቅህ ነገር ምንድን ነው?

4 መጽሐፍ ቅዱስ ካለህ ይህ መጽሐፍ ካላቸው በርካታ ሰዎች አንዱ ነህ ማለት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ሙሉ በሙሉም ሆነ በከፊል ከ2,300 በሚበልጡ ቋንቋዎች የተዘጋጀ በመሆኑ ከዓለማችን ሕዝብ መካከል ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነው ይህን መጽሐፍ ማግኘት ይችላል። በአማካይ በየሳምንቱ ከአንድ ሚሊዮን በላይ መጽሐፍ ቅዱሶች ይሰራጫሉ! ይህ መጽሐፍ ሙሉ በሙሉም ይሁን በከፊል በቢሊዮኖች በሚቆጠሩ ቅጂዎች ታትሟል። እውነትም እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ያለ ሌላ መጽሐፍ የለም።

“የአዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም” በብዙ ቋንቋዎች ይገኛል

5. መጽሐፍ ቅዱስ ‘የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት ነው’ የምንለው በምን መንገድ ነው?

5 ከዚህም በተጨማሪ መጽሐፍ ቅዱስ ‘የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት ነው።’ (2 ጢሞቴዎስ 3:16) በምን መንገድ? መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ “ከእግዚአብሔር የተላኩ ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተመርተው ተናገሩት” ሲል መልስ ይሰጠናል። (2 ጴጥሮስ 1:21) ይህን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል:- የአንድ ድርጅት አስተዳዳሪ ጸሐፊው ደብዳቤ እንድትጽፍለት ሊያደርግ ይችላል። ደብዳቤው የአስተዳዳሪውን ሐሳብና መመሪያ የያዘ ነው። በመሆኑም ደብዳቤው የእሱ እንጂ የጸሐፊዋ አይደለም። በተመሳሳይም መጽሐፍ ቅዱስ የያዘው  የጸሐፊዎቹን ሳይሆን የአምላክን መልእክት ነው። በመሆኑም መላው መጽሐፍ ቅዱስ ‘የእግዚአብሔር ቃል’ ነው።—1 ተሰሎንቄ 2:13

እርስ በርሱ የሚስማማና ትክክለኛ

6, 7. የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ እርስ በርሱ የሚስማማ መሆኑ አስገራሚ የሆነው ለምንድን ነው?

6 መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው ከ1,600 በሚበልጡ ዓመታት ውስጥ ነው። ጸሐፊዎቹ በተለያዩ ዘመናት የኖሩ ከመሆናቸውም በላይ የተለያየ የኑሮ ደረጃ ያላቸው ናቸው። አንዳንዶቹ ገበሬዎች፣ ዓሣ አጥማጆችና እረኞች ነበሩ። ሌሎቹ ደግሞ ነቢያት፣ መሳፍንትና ነገሥታት ናቸው። የወንጌል ጸሐፊ የሆነው ሉቃስ ሐኪም ነበር። ጸሐፊዎቹ የተለያየ አስተዳደግና የኑሮ ደረጃ የነበራቸው ቢሆኑም እንኳ መጽሐፍ ቅዱስ ከዳር እስከ ዳር የያዘው ሐሳብ እርስ በርሱ ይስማማል። *

7 የመጀመሪያው የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ የሰው ልጆች ለተለያዩ ችግሮች የተዳረጉት እንዴት እንደሆነ ይገልጽልናል። የመጨረሻው መጽሐፍ ደግሞ መላዋ ምድር ገነት እንደምትሆን ይናገራል። የመጽሐፍ ቅዱስ የተለያዩ ክፍሎች በሺዎች የሚቆጠሩ ዓመታትን ታሪክ የያዙ ሲሆን እያንዳንዱ ክፍል የአምላክን ዓላማ መረዳት እንድንችል የበኩሉን አስተዋጽኦ ያበረክታል። መጽሐፍ ቅዱስ እርስ በርሱ ያለው ስምምነት የሚያስደንቅ ቢሆንም ይህ ሁኔታ አምላክ ካስጻፈው መጽሐፍ የሚጠበቅ ነገር ነው።

8. መጽሐፍ ቅዱስ ከሳይንስ አኳያ ትክክለኛ መሆኑን የሚያሳዩ ምሳሌዎች ጥቀስ።

8 መጽሐፍ ቅዱስ ከሳይንስ አንጻር ሲታይ ትክክለኛ ነው። እንዲያውም በዘመኑ የነበረው ሳይንስ ያልደረሰባቸውን መረጃዎች ይዟል። ለምሳሌ ያህል የዘሌዋውያን መጽሐፍ በበሽታ የተያዘ ሰው በሽታውን እንዳያስተላልፍ ተገልሎ እንዲቆይ ማድረግንና የጤና አጠባበቅ ዘዴን የሚመለከቱ ለጥንት እስራኤላውያን የተሰጡ ሕጎችን የያዘ ሲሆን በወቅቱ በዙሪያቸው የነበሩት ብሔራት ግን ስለ እነዚህ ነገሮች ምንም ዓይነት ግንዛቤ አልነበራቸውም። የምድርን ቅርጽ በተመለከተ የተሳሳተ አመለካከት በነበረበት ዘመን መጽሐፍ ቅዱስ ምድር ክብ ወይም ሉል እንደሆነች ጠቁሟል። (ኢሳይያስ 40:22)  በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ምድር ‘እንዲያው በባዶ ላይ እንደተንጠለጠለች’ በትክክል ገልጿል። (ኢዮብ 26:7) እርግጥ መጽሐፍ ቅዱስ የሳይንስ መማሪያ መጽሐፍ አይደለም። ሆኖም የሚጠቅሳቸው ሳይንሳዊ ጉዳዮች ትክክለኛ ናቸው። በእርግጥም ይህ፣ አምላክ ካስጻፈው መጽሐፍ የምንጠብቀው ነገር አይደለም?

9. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስ ከታሪክ አኳያ ትክክለኛና እምነት የሚጣልበት መሆኑን ያሳየው በምን መንገዶች ነው? (ለ) የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ሐቀኝነት ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ምን ያስገነዝብሃል?

9 መጽሐፍ ቅዱስ ከታሪክ አኳያም ትክክለኛና እምነት የሚጣልበት ነው። ዘገባዎቹ ምንም የማያሻሙ ናቸው። የሰዎችን ስሞች ብቻ ሳይሆን የዘር ሐረጋቸውን ጭምር የያዙ ናቸው። * የራሳቸውን ሕዝብ ሽንፈት ከማይጠቅሱት የዓለም ታሪክ ጸሐፊዎች በተለየ ሁኔታ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች የራሳቸውንም ሆነ የሕዝባቸውን ጉድለት በመጥቀስ ሐቀኞች መሆናቸውን አሳይተዋል። ለምሳሌ ያህል የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነውን የዘኍልቁን መጽሐፍ የጻፈው ሙሴ፣ ራሱ የሠራውንና ጠንከር ያለ ተግሣጽ ያስከተለበትን ከባድ ስህተት ጠቅሷል። (ዘኍልቁ 20:2-12) በሌሎች ታሪካዊ ዘገባዎች ላይ እምብዛም የማይታየው እንዲህ ያለው ሐቀኝነት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ሊንጸባረቅ የቻለው አምላክ ያስጻፈው መጽሐፍ በመሆኑ ነው።

ጠቃሚ ምክር የያዘ መጽሐፍ

10. መጽሐፍ ቅዱስ በጣም ጠቃሚ የሆነ መጽሐፍ መሆኑ የማያስደንቀው ለምንድን ነው?

10 መጽሐፍ ቅዱስ በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ መጽሐፍ በመሆኑ ‘ለማስተማር፣ ለመገሠጽ፣ ለማቅናት በጽድቅም መንገድ ለመምከር ይጠቅማል።’ (2 ጢሞቴዎስ 3:16) አዎን፣ መጽሐፍ ቅዱስ በጣም ጠቃሚ የሆነ መጽሐፍ ነው። ስለ ሰው አፈጣጠር ጥሩ አድርጎ ይገልጻል። መጽሐፍ ቅዱስን ያስጻፈው የሰው ዘር ፈጣሪ የሆነው ይሖዋ አምላክ በመሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ያለ መጽሐፍ መሆኑ ምንም አያስደንቅም! ይሖዋ አስተሳሰባችንንም ሆነ ስሜታችንን ከእኛ በተሻለ ሁኔታ ይረዳል። ከዚህም በተጨማሪ ደስተኞች መሆን እንድንችል ምን እንደሚያስፈልገን ያውቃል። እንዲሁም ልንርቀው የሚገባንን የሕይወት ጎዳና ያውቃል።

11, 12. (ሀ) ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ ወቅት ምን ጉዳዮችን አንስቷል? (ለ) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሌሎች ምን ጠቃሚ ጉዳዮች ተገልጸዋል? ምክሩ ዘመን የማይሽረው ነው የምንለውስ ለምንድን ነው?

 11 ከማቴዎስ ምዕራፍ 5 እስከ ምዕራፍ 7 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን የተራራው ስብከት በመባል የሚታወቀውን የኢየሱስ ንግግር ተመልከት። ኢየሱስ ይህን ታላቅ ትምህርት በሰጠበት ወቅት እውነተኛ ደስታ የሚገኝበትን መንገድ፣ አለመግባባቶችን እንዴት መፍታት እንደሚገባ፣ እንዴት መጸለይ እንደሚቻልና ለቁሳዊ ነገሮች ትክክለኛ አመለካከት መያዝ የሚቻልበትን መንገድ  ጨምሮ በርከት ያሉ ጉዳዮችን አንስቶ ተናግሯል። ኢየሱስ የተናገራቸው ቃላት በዚያን ጊዜ እንደነበረው ሁሉ ዛሬም በሰዎች ላይ ተጽዕኖ የማሳደር ኃይል ያላቸው ከመሆኑም በላይ ጠቃሚ ናቸው።

12 አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች የቤተሰብ ሕይወትን፣ ሥራንና ከሌሎች ጋር ያለንን ግንኙነት የሚመለከቱ ናቸው። የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ለሁሉም ሰው የሚሠሩ ከመሆናቸውም በላይ ምክሮቹ ዘመን አይሽራቸውም። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው ጠቃሚ ምክር አምላክ በነቢዩ ኢሳይያስ በኩል “እኔ እግዚአብሔር አምላክህ፣ የሚበጅህ ምን እንደ ሆነ የማስተምርህ . . . ነኝ” ሲል በተናገራቸው ቃላት ጠቅለል ተደርጎ ተገልጿል።—ኢሳይያስ 48:17

የትንቢት መጽሐፍ

የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የሆነው ኢሳይያስ ባቢሎን እንደምትወድቅ ተንብዮ ነበር

13. ይሖዋ ባቢሎንን በተመለከተ ነቢዩ ኢሳይያስ ምን ዝርዝር ጉዳዮችን እንዲጽፍ በመንፈሱ አነሳስቶታል?

13 መጽሐፍ ቅዱስ በርካታ ትንቢቶችን የያዘ ሲሆን ከእነዚህ መካከል ብዙዎቹ ፍጻሜያቸውን አግኝተዋል። አንድ ምሳሌ ተመልከት። ይሖዋ የባቢሎን ከተማ እንደምትጠፋ በስምንተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት ይኖር በነበረው በነቢዩ ኢሳይያስ በኩል አስቀድሞ ተናግሮ ነበር። (ኢሳይያስ 13:19፤ 14:22, 23) ከተማይቱ የምትያዘው እንዴት እንደሆነ የሚጠቁሙ ዝርዝር መረጃዎች ተሰጥተዋል። ወራሪው ሠራዊት የባቢሎንን ወንዝ በማድረቅ ያለምንም ውጊያ ወደ ከተማይቱ ይዘልቃል። ይህ ብቻም አይደለም። የኢሳይያስ ትንቢት ባቢሎንን ድል የሚያደርገውን ንጉሥ ማለትም ቂሮስን በስም ሳይቀር ጠቅሶ ነበር።—ኢሳይያስ 44:27 እስከ 45:2

14, 15. ኢሳይያስ ባቢሎንን አስመልክቶ በተናገረው ትንቢት ላይ የተጠቀሱ አንዳንድ ዝርዝር ጉዳዮች ፍጻሜያቸውን ያገኙት እንዴት ነው?

14 ከ200 ዓመታት ገደማ በኋላ በ539 ከክርስቶስ ልደት በፊት ጥቅምት 5/6 ሌሊት አንድ ሠራዊት በባቢሎን አቅራቢያ ሰፈረ። የሠራዊቱ አዛዥ ማን ነው? ቂሮስ የተባለ የፋርስ ንጉሥ ነው። በዚህ መንገድ አንድ አስደናቂ ትንቢት ፍጻሜውን የሚያገኝበት ሁኔታ ተመቻቸ። ይሁን እንጂ አስቀድሞ በተነገረው መሠረት የቂሮስ ሠራዊት ባቢሎንን ያላንዳች ውጊያ ይወር ይሆን?

15 የዚያን ቀን ሌሊት ባቢሎናውያን ታላቅ ግብዣ ላይ የነበሩ ሲሆን ግዙፍ በሆኑት የከተማቸው ግንቦች ተማምነው ነበር። ይህ በእንዲህ እንዳለ ቂሮስ በከተማይቱ መካከል ያልፍ የነበረውን ወንዝ በዘዴ ወደ ሌላ አቅጣጫ  እንዲፈስ አደረገ። ብዙም ሳይቆይ ውኃው በመጉደሉ ወታደሮቹ በወንዙ መካከል ተሻግረው ወደ ከተማይቱ ግንቦች ተጠጉ። ሆኖም የቂሮስ ሠራዊት የባቢሎንን ግንቦች ማለፍ የሚችለው እንዴት ነው? የዚያን ቀን ሌሊት በሆነ ምክንያት የከተማይቱ በሮች አልተዘጉም ነበር!

16. (ሀ) ኢሳይያስ የባቢሎንን የመጨረሻ ዕጣ ፈንታ አስመልክቶ ምን ትንቢት ተናግሯል? (ለ) ኢሳይያስ ባቢሎን ባድማ እንደምትሆን የተናገረው ትንቢት ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው?

16 ባቢሎንን በተመለከተ “በዘመናት ሁሉ የሚቀመጥባት አይኖርም፤ የሚቀመጥባትም የለም ዐረብ በዚያ ድንኳኑን አይተክልም፤ እረኛም መንጋውን በዚያ አያሳርፍም” የሚል ትንቢት ተነግሮ ነበር። (ኢሳይያስ 13:20) ይህ ትንቢት ከተማዋ ከወደቀች በኋላም የሚሆነውን ሁኔታ ይጠቁማል። ባቢሎን ለዘለቄታው ባድማ ሆና እንደምትቀር ያመለክታል። እነዚህ ቃላት ፍጻሜያቸውን እንዳገኙ የሚያረጋግጠውን ማስረጃ መመልከት ትችላለህ። ከኢራቅ ዋና ከተማ ከባግዳድ በስተ ደቡብ 80 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ላይ የምትገኘው ሰው አልባ የሆነችው የጥንቷ ባቢሎን ይሖዋ “በጥፋትም መጥረጊያ እጠርጋታለሁ” ሲል በኢሳይያስ በኩል የተናገረው ቃል መፈጸሙን የምታሳይ ማስረጃ ናት።—ኢሳይያስ 14:22, 23 *

የባቢሎን ፍርስራሾች

17. የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ፍጻሜ እምነት የሚያጠነክረው እንዴት ነው?

 17 መጽሐፍ ቅዱስ አስተማማኝ ትንቢት የያዘ መጽሐፍ መሆኑን ማወቁ እምነት የሚያጠነክር አይደለም? ይሖዋ አምላክ ቀደም ሲል ቃል የገባቸውን ነገሮች ከፈጸመ ምድርን ገነት ለማድረግ የገባውንም ቃል እንደሚፈጽም እርግጠኞች መሆን እንችላለን። (ዘኍልቁ 23:19) በእርግጥም ‘የማይዋሸው አምላክ ከዘመናት በፊት የገባው የዘላለም ሕይወት ተስፋ’ አለን።—ቲቶ 1:2 *

‘የእግዚአብሔር ቃል ሕያው ነው’

18. ክርስቲያኑ ሐዋርያ ጳውሎስ ስለ “እግዚአብሔር ቃል” ምን ኃይለኛ አስተያየት ሰጥቷል?

18 በዚህ ምዕራፍ ላይ እንደተመለከትነው መጽሐፍ ቅዱስ በእርግጥም በዓይነቱ ልዩ የሆነ መጽሐፍ ነው። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ ትልቅ ግምት እንዲሰጠው የሚያደርገው በውስጡ ያለው ሐሳብ እርስ በርሱ መስማማቱ፣  ከሳይንስና ከታሪክ አኳያ ትክክለኛ መሆኑ፣ ጠቃሚ ምክር ያዘለ መሆኑ እንዲሁም አስተማማኝ ትንቢት መያዙ ብቻ አይደለም። ክርስቲያኑ ሐዋርያ ጳውሎስ “የእግዚአብሔር ቃል ሕያውና የሚሠራ ነውና፤ በሁለት በኩል ስለት ካለው ሰይፍ ሁሉ ይልቅ ስለታም ነው፤ ነፍስንና መንፈስን፣ ጅማትንና ቅልጥምን እስኪለያይ ድረስ ዘልቆ ይወጋል፤ የልብንም ሐሳብና ምኞት ይመረምራል” ሲል ጽፏል።—ዕብራውያን 4:12

19, 20. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስ ራስህን እንድትመረምር ሊረዳህ የሚችለው እንዴት ነው? (ለ) የአምላክ ልዩ ስጦታ ለሆነው ለመጽሐፍ ቅዱስ አመስጋኝ መሆንህን ልታሳይ የምትችለው እንዴት ነው?

19 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን የአምላክ “ቃል” ወይም መልእክት ማንበባችን ሕይወታችንን ሊለውጠውና ቀደም ሲል አድርገነው በማናውቀው መንገድ ራሳችንን እንድንመረምር ሊረዳን ይችላል። አምላክን እንደምንወድ እንናገር ይሆናል፤ ሆኖም በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈው ቃሉ ማለትም መጽሐፍ ቅዱስ ለሚያስተምረው ትምህርት የምንሰጠው ምላሽ እውነተኛውን አስተሳሰባችንን አልፎ ተርፎም በልባችን ውስጥ ያለውን ሐሳብ ሊገልጽ ይችላል።

20 በእርግጥም መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ለሰው ልጆች የሰጠው መጽሐፍ ነው። ሊነበብ፣ ሊጠናና እንደ ውድ ነገር ሊታይ የሚገባው መጽሐፍ ነው። የመጽሐፉን ይዘት መመርመርህን በመቀጠል ለዚህ መለኮታዊ ስጦታ አመስጋኝ መሆንህን አሳይ። ይህን ስታደርግ አምላክ ለሰው ልጆች ያለውን ዓላማ በሚገባ ትረዳለህ። ይህ ዓላማ ምን እንደሆነና ዳር የሚደርሰው እንዴት እንደሆነ በሚቀጥለው ምዕራፍ ላይ ይብራራል።

^ አን.6 ምንም እንኳ አንዳንድ ሰዎች የተወሰኑት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ከሌሎቹ የመጽሐፉ ክፍሎች ጋር እንደሚጋጩ ቢናገሩም እንዲህ ያሉት አስተያየቶች መሠረተ ቢስ ናቸው። በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን መጽሐፍ ቅዱስ—የአምላክ ቃል ነው ወይስ የሰው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 7 ተመልከት።

^ አን.9 ለምሳሌ ያህል በሉቃስ 3:23-38 ላይ ተዘርዝሮ የሚገኘውን የኢየሱስ የዘር ሐረግ ተመልከት።

^ አን.16 ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ለሰው ሁሉ የሚሆን መጽሐፍ የተባለውን ብሮሹር ገጽ 27-29 ተመልከት።

^ አን.17 በባቢሎን ላይ የደረሰው ጥፋት ፍጻሜያቸውን ካገኙት የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች መካከል አንዱ ምሳሌ ብቻ ነው። ሌሎቹ ምሳሌዎች በጢሮስና በነነዌ ላይ የደረሰውን ጥፋት ያካትታሉ። (ሕዝቅኤል 26:1-5፤ ሶፎንያስ 2:13-15) በተጨማሪም የዳንኤል ትንቢት ከባቢሎን በኋላ የዓለም ኃያል መንግሥት ሆነው ተራ በተራ የሚነሱ ብሔራትን ተንብዮ ነበር። እነዚህም ሜዶ ፋርስንና ግሪክን ያጠቃልላሉ። (ዳንኤል 8:5-7, 20-22) በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ የተፈጸሙትን ስለ መሲሑ የተነገሩ በርካታ ትንቢቶች በተመለከተ ማብራሪያ ለማግኘት ከገጽ 199-201 ላይ ያለውን ተጨማሪ ክፍል ተመልከት።