ተጨማሪ ክፍል
የፍርድ ቀን ምንድን ነው?
የፍርድ ቀን ሲባል ወደ አእምሮህ የሚመጣው ምንድን ነው? ብዙ ሰዎች በፍርድ ቀን በቢሊዮን የሚቆጠሩ ነፍሳት አንድ በአንድ በአምላክ ዙፋን ፊት ይቀርባሉ ብለው ያስባሉ። ከዚያም በእያንዳንዱ ግለሰብ ላይ ፍርድ ይበየናል። አንዳንዶች ሰማይ ቤት ሄደው ገነት ውስጥ ሲገቡ ሌሎች ደግሞ ዘላለማዊ ሥቃይ ይፈረድባቸዋል ይላሉ። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ወቅት አስመልክቶ የሚሰጠው መግለጫ ከዚህ ፈጽሞ የተለየ ነው። የአምላክ ቃል በሚገልጸው መሠረት የፍርድ ቀን አስፈሪ ወቅት ሳይሆን የተስፋና የተሃድሶ ጊዜ ነው።
ሐዋርያው ዮሐንስ የፍርድ ቀንን አስመልክቶ ራእይ 20:11, 12 ላይ የሰጠው መግለጫ እንዲህ ይላል:- “ታላቅ ነጭ ዙፋንና በእርሱም ላይ የተቀመጠውን አየሁ። ምድርና ሰማይ ከፊቱ ሸሹ፤ ስፍራም አልተገኘላቸውም። ሙታንን፣ ታላላቆችንና ታናናሾችን በዙፋኑ ፊት ቆመው አየሁ፤ መጻሕፍትም ተከፈቱ። ሌላም መጽሐፍ፣ እርሱም የሕይወት መጽሐፍ ተከፈተ፤ ሙታንም በመጻሕፍቱ ተጽፎ በተገኘው መሠረት እንደ ሥራቸው መጠን ተፈረደባቸው።” እዚህ ላይ የተገለጸው ፈራጅ ማን ነው?
ከማንም በላይ በሰው ዘር ላይ የመፍረድ ሥልጣን ያለው ይሖዋ አምላክ ነው። ይሁን እንጂ የፍርዱን ሥራ ለሌላ ወኪል ሰጥቷል። የሐዋርያት ሥራ 17:31 እንደሚገልጸው ሐዋርያው ጳውሎስ፣ አምላክ “በመረጠው ሰው አማካይነት በዓለም ላይ በጽድቅ የሚፈርድበትን ቀን ወስኖአል” ሲል ተናግሯል። ይህ የተሾመው ፈራጅ ከሞት የተነሳው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። (ዮሐንስ 5:22) ይሁንና የፍርድ ቀን የሚጀምረው መቼ ነው? የሚቆየውስ ለምን ያህል ጊዜ ነው?
የራእይ መጽሐፍ የፍርድ ቀን የሚጀምረው በምድር ላይ ያለው የሰይጣን ሥርዓት በአርማጌዶን ጦርነት ከጠፋ በኋላ እንደሆነ ይገልጻል። * (ራእይ 16:14, 16፤ 19:19 እስከ 20:3) ከአርማጌዶን በኋላ ሰይጣንና አጋንንቱ በጥልቁ ውስጥ ለሺህ ዓመት ይታሰራሉ። በዚያን ጊዜ 144,000ዎቹ ተባባሪ የሰማይ ወራሾች ፈራጆች ይሆናሉ እንዲሁም ነገሥታት ሆነው “ከክርስቶስ ጋር ሺህ ዓመት” ይገዛሉ። (ራእይ 14:1-3፤ 20:1-4፤ ሮሜ 8:17) የፍርድ ቀን ለ24 ሰዓት ብቻ የሚቆይ በጥድፊያ የሚከናወን ነገር አይደለም። ለሺህ ዓመት የሚዘልቅ ነው።
በሺው ዓመት ጊዜ ውስጥ ኢየሱስ ክርስቶስ ‘በሕያዋንና በሙታን ላይ ይፈርዳል።’ (2 ጢሞቴዎስ 4:1) “ሕያዋን” የተባሉት ከአርማጌዶን የሚተርፉ “እጅግ ብዙ ሕዝብ” ናቸው። (ራእይ 7:9-17) ከዚህም በተጨማሪ ሐዋርያው ዮሐንስ ‘ሙታን በፍርድ ዙፋን ፊት ቆመው’ ተመልክቷል። ኢየሱስ ቃል በገባው መሠረት “መቃብር ውስጥ ያሉ ሁሉ” የክርስቶስን ድምፅ ሰምተው በትንሣኤ አማካኝነት ይነሣሉ። (ዮሐንስ 5:28, 29፤ የሐዋርያት ሥራ 24:15) ሆኖም ሁሉም የሚፈረድባቸው በምን መሠረት ነው?
ሐዋርያው ዮሐንስ ባየው ራእይ ላይ ‘መጻሕፍት የተከፈቱ’ ሲሆን ‘ሙታን በመጻሕፍቱ ተጽፎ በተገኘው መሠረት እንደ ሥራቸው መጠን ተፈርዶባቸዋል።’ እነዚህ መጻሕፍት ሰዎች ቀደም ሲል የፈጸሟቸው ድርጊቶች የተመዘገቡባቸው ናቸው? አይደሉም፤ ፍርዱ የሚሰጠው ሰዎች ቀደም ሲል በፈጸሟቸው ድርጊቶች ላይ ተመርኩዞ አይደለም። ይህን እንዴት እናውቃለን? መጽሐፍ ቅዱስ “የሞተ ከኀጢአት ነጻ ወጥቶአል” ይላል። (ሮሜ 6:7) ስለዚህ እነዚህ ሰዎች ከሞት የሚነሱት የቀድሞ ኃጢአታቸው ተሽሮላቸው ነው። በመሆኑም መጻሕፍቱ አምላክ ወደፊት የሚያወጣቸውን መሥፈርቶች የሚያመለክቱ መሆን አለባቸው። ከአርማጌዶን የሚተርፉትም ሆኑ ከሞት የሚነሱት ሰዎች ለዘላለም መኖር እንዲችሉ ይሖዋ በሺው ዓመት ወቅት ሊያወጣቸው የሚችላቸውን መሥፈርቶች ጨምሮ ሁሉንም የአምላክ ትእዛዛት ማክበር ያስፈልጋቸዋል። ስለዚህ ሰዎች ፍርድ የሚሰጣቸው በፍርድ ቀን የሚፈጽሙትን ድርጊት መሠረት በማድረግ ነው።
በፍርድ ቀን በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ስለ አምላክ ፈቃድ መማርና ከፈቃዱ ጋር ተስማምተው መኖር የሚችሉበት አጋጣሚ ያገኛሉ። በመሆኑም መጠነ ሰፊ የሆነ የማስተማር ሥራ ይካሄዳል ማለት ነው። በእርግጥም “የዓለም ሕዝቦች ጽድቅን ይማራሉ።” (ኢሳይያስ 26:9) ይሁን እንጂ ከአምላክ ፈቃድ ጋር ተስማምተው ለመኖር ፈቃደኛ የሚሆኑት ሁሉም አይደሉም። ኢሳይያስ 26:10 “ክፉዎች ርኅራኄ ቢደረግላቸው እንኳ፣ ጽድቅን አይማሩም፤ በቅንነት ምድር እንኳ ክፋትን ያደርጋሉ፤ የእግዚአብሔርንም ግርማ አያስተውሉም” ይላል። እነዚህ ክፉዎች በፍርድ ቀን ውስጥ ለዘለቄታው እንዲጠፉ ይደረጋል።—ኢሳይያስ 65:20
በፍርድ ቀን መጨረሻ ላይ የቀሩት ሰዎች ፍጹማን በመሆን ሙሉ በሙሉ ሕያዋን ይሆናሉ። በመሆኑም በፍርድ ቀን የሰው ዘር ቀድሞ የነበረውን ፍጹም ሕይወት መልሶ ያገኛል። (1 ቆሮንቶስ 15:24-28) ከዚያ በኋላ የመጨረሻ ፈተና ይኖራል። ሰይጣን ከታሰረበት ይፈታና ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የሰውን ዘር ለማሳት ሙከራ ማድረግ የሚችልበት ዕድል ይሰጠዋል። (ራእይ 20:3, 7-10) ሰይጣንን የሚቃወሙ ሰዎች “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፤ በእርሷም ለዘላለም ይኖራሉ” የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ ሙሉ በሙሉ ይፈጸምላቸዋል። (መዝሙር 37:29) አዎን፣ የፍርድ ቀን ታማኝ ለሆኑ የሰው ዘሮች በሙሉ በረከት ያስገኛል!
^ አን.1 አርማጌዶንን በተመለከተ ማብራሪያ ለማግኘት ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ) ጥራዝ 1፣ ገጽ 594-595, 1037-1038፣ ከቅዱሳን ጽሑፎች እየጠቀሱ ማመራመር ገጽ 43-47 እንዲሁም እውነተኛውን አንድ አምላክ አምልክ የተባለውን መጽሐፍ 20ኛ ምዕራፍ ተመልከት። ሁሉም የተዘጋጁት በይሖዋ ምሥክሮች ነው።