በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ምዕራፍ አሥራ ዘጠኝ

ከአምላክ ፍቅር አትውጣ

ከአምላክ ፍቅር አትውጣ
  • አምላክን መውደድ ሲባል ምን ማለት ነው?

  • ከአምላክ ፍቅር እንዳንወጣ ምን ሊረዳን ይችላል?

  • ይሖዋ ከእሱ ፍቅር የማይወጡትን ሰዎች የሚክሳቸው እንዴት ነው?

ዝናብ እንደቀላቀለ አውሎ ነፋስ በሚነዋወጠው ዓለም ውስጥ ይሖዋን መጠጊያህ ታደርገዋለህ?

1, 2. ዛሬ አስተማማኝ መጠጊያ ልናገኝ የምንችለው የት ነው?

ከባድ ዝናብ ያዘለ ኃይለኛ ነፋስ በሚነፍስበት ቀን በእግርህ እየተጓዝክ ነው እንበል። ሰማዩ እየጠቆረ ነው። መብረቅ ብልጭ ይላል፤ ነጎድጓዱ ያስገመግማል። ከዚያም ዶፍ ዝናብ ይዘንባል። መጠለያ ፍለጋ ወዲያና ወዲህ እያማተርክ በጥድፊያ ትራመዳለህ። በዚህ መካከል መንገድ ዳር ያለ አንድ መጠለያ ትመለከታለህ። መጠለያው ጠንካራ ከመሆኑም በላይ ዝናብ የማያፈስና አመቺ ነው። ይህን መጠለያ በማግኘትህ እጅግ እንደምትደሰት ጥርጥር የለውም!

2 ዛሬ የምንኖረው ከባድ ዝናብ እንደቀላቀለ አውሎ ነፋስ በሚነዋወጥ ዓለም ውስጥ ነው። የዓለም ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ሄዷል። ሆኖም ዘላቂ ከሆነ ጉዳት ሊጠብቀን የሚችል አስተማማኝ መጠለያ ወይም መጠጊያ አለ። ይህ መሸሸጊያ ምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚል ተመልከት:- “እግዚአብሔርን፣ ‘መጠጊያዬ፣ ምሽጌ፣ የምታመንብህ አምላኬ’ እለዋለሁ።”—መዝሙር 91:2

3. ይሖዋን መጠጊያችን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

3 ይህ ምን ማለት እንደሆነ አስበው! የጽንፈ ዓለሙ ፈጣሪና ሉዓላዊ ገዥ የሆነው ይሖዋ መጠጊያ ሊሆንልን ይችላል። ይሖዋ ጉዳት ሊያደርስብን ከሚችል  ከማንኛውም ፍጡርም ሆነ ከማንኛውም ነገር የበለጠ ኃይል ያለው በመሆኑ ሊጠብቀን ይችላል። ጉዳት ቢደርስብን እንኳ የደረሰብንን ጉዳት ሁሉ ለማስተካከል የሚያስችል ኃይል አለው። ይሖዋን መጠጊያችን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? በእርሱ በመታመን ነው። ከዚህም በተጨማሪ የአምላክ ቃል “በእግዚአብሔር ፍቅር ራሳችሁን ጠብቁ” ሲል አጥብቆ ያሳስበናል። (ይሁዳ 21) አዎን፣ ከሰማያዊ አባታችን ጋር የመሠረትነውን ፍቅራዊ ግንኙነት በማጠናከር ከአምላክ ፍቅር ሳንወጣ መኖር አለብን። እንዲህ ካደረግን መጠጊያችን እንደሚሆን እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ይሁን እንጂ እንዲህ ያለ የጠበቀ ግንኙነት መፍጠር የምንችለው እንዴት ነው?

የአምላክን ፍቅር ማስተዋልና ምላሽ መስጠት

4, 5. ይሖዋ ለእኛ ያለውን ፍቅር ከገለጸባቸው መንገዶች መካከል አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው?

4 ከአምላክ ፍቅር ሳንወጣ ለመኖር ይሖዋ ለእኛ ያለውን ፍቅር የገለጸባቸውን መንገዶች መረዳት ያስፈልገናል። በዚህ መጽሐፍ አማካኝነት የተማርካቸውን አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች መለስ ብለህ ለማሰብ ሞክር። ፈጣሪ የሆነው ይሖዋ ምድርን አስደሳች መኖሪያ አድርጎ ሰጥቶናል። በተትረፈረፈ እህልና ውኃ፣ በተፈጥሮ ሀብቶች፣ ማራኪ በሆኑ እንስሳትና ውብ በሆኑ መልክዓ ምድሮች እንድትሞላ አድርጓል። አምላክ፣ ቃሉ በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ስሙንና ባሕርያቱን ገልጾልናል። ከዚህም በተጨማሪ ቃሉ ተወዳጅ ልጁ የሆነውን ኢየሱስን ወደ ምድር በመላክ ለእኛ ሲል እንዲሠቃይና እንዲሞት እንደፈቀደ ይገልጽልናል። (ዮሐንስ 3:16) ይህ ስጦታ ለእኛ ያስገኘው ጥቅም ምንድን ነው? ወደፊት የሚመጣውን አስደሳች ጊዜ በተስፋ እንድንጠባበቅ አስችሎናል።

5 የወደፊት ተስፋችን አምላክ ባከናወነው ሌላ ነገርም ላይ የተመካ ነው። ይሖዋ ሰማያዊ መስተዳድር ማለትም መሲሐዊ መንግሥት አቋቁሟል። ይህ መንግሥት በቅርቡ መከራን ሁሉ በማስወገድ ምድርን ገነት ያደርጋል። ይህ ምን ማለት እንደሆነ እስቲ አስበው! በዚያች ገነት ውስጥ በሰላምና በደስታ ለዘላለም መኖር እንችላለን። (መዝሙር 37:29) እስከዚያው ጊዜ ድረስ ግን አምላክ ባለንበት ዘመን ውስጥ ከሁሉ በተሻለ መንገድ መኖር የምንችልበትን መመሪያ ሰጥቶናል። በተጨማሪም ከእሱ ጋር ያለ ገደብ መነጋገር የምንችልበትን የጸሎት መብት ሰጥቶናል። እነዚህ ይሖዋ ለሰው ዘር በጥቅሉም ሆነ ለአንተ በግለሰብ ደረጃ ያለውን  ፍቅር ከገለጸባቸው መንገዶች ጥቂቶቹ ናቸው።

6. ይሖዋ ላሳየህ ፍቅር ምላሽ መስጠት የምትችለው እንዴት ነው?

6 አሁን አንተ ልታስብበት የሚገባው ትልቁ ጥያቄ ‘ይሖዋ ላሳየኝ ፍቅር ምላሽ የምሰጠው እንዴት ነው?’ የሚለው ነው። ብዙዎች “እኔም በምላሹ ይሖዋን ልወደው ይገባል” ይላሉ። አንተስ የሚሰማህ እንደዚህ ነው? ኢየሱስ የሚከተለው ትእዛዝ ከትእዛዛት ሁሉ የላቀ እንደሆነ ገልጿል:- “ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ሐሳብህ ውደድ።” (ማቴዎስ 22:37) በእርግጥም ይሖዋ አምላክን እንድትወድ የሚገፋፉህ ብዙ ምክንያቶች አሉ። ሆኖም ይሖዋን በፍጹም ልብህ፣ ነፍስህና ሐሳብህ መውደድ ሲባል ለእሱ እንዲህ ያለ ፍቅራዊ ስሜት ሊሰማህ ይገባል ማለት ብቻ ነው?

7. አምላክን መውደድ ከስሜት የበለጠ ነገርን ይጨምራል? አብራራ።

7 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደተገለጸው አምላክን መውደድ ከስሜት የበለጠ ነገርን ይጨምራል። ለይሖዋ ፍቅራዊ ስሜት ሊያድርብን የሚገባ ቢሆንም እንኳ ይህ ለእሱ ያለንን እውነተኛ ፍቅር የምናሳይበት የመጀመሪያ እርምጃ ብቻ ነው። ፍሬ የሚያፈራ የፖም ዛፍ ለማሳደግ የፖም ዘር እንደሚያስፈልግ የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ ፖም ብትፈልግና አንድ ሰው የፖም ዘር ብቻ ቢሰጥህ በቂ ይሆናል? እንደማይሆን የታወቀ ነው! በተመሳሳይም ለይሖዋ አምላክ ፍቅራዊ ስሜት ማሳየታችን ጥሩ ጅምር ቢሆንም ብቻውን በቂ አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔርን መውደድ ትእዛዛቱን መፈጸም ነውና። ትእዛዛቱም ከባድ አይደሉም” ሲል ያስተምራል። (1 ዮሐንስ 5:3) ለአምላክ ያለን ፍቅር ከልብ የመነጨ መሆኑ የሚታየው መልካም ፍሬ ሲያፈራ ነው። ይህ ፍቅር በተግባር መገለጽ አለበት።—ማቴዎስ 7:16-20

8, 9. አምላክን እንደምንወደውና ላደረገልን ነገር አመስጋኞች እንደሆንን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

8 ለአምላክ ፍቅር እንዳለን የምናሳየው ትእዛዛቱን ስንጠብቅና መሠረታዊ ሥርዓቶቹን ሥራ ላይ ስናውል ነው። ይህ ደግሞ ከባድ አይደለም። የይሖዋ ሕግጋት ሸክም አይደሉም፤ ከዚህ ይልቅ ደስታና እርካታ ያለው ሕይወት መኖር እንድንችል እኛን ለመርዳት ተብለው የተዘጋጁ ናቸው። (ኢሳይያስ 48:17, 18) ከይሖዋ መመሪያ ጋር ተስማምተን በመኖር በሰማይ  ያለው አባታችን ላደረገልን ነገር ሁሉ ከልብ አመስጋኞች መሆናችንን በተግባር እናሳያለን። የሚያሳዝነው ዛሬ ባለው ዓለም ውስጥ እንዲህ ያለ የአመስጋኝነት መንፈስ ያላቸው ሰዎች በጣም ጥቂት ናቸው። ኢየሱስ በምድር ላይ በኖረበት ዘመን እንደነበሩት አንዳንድ ሰዎች ምስጋና ቢሶች መሆን የለብንም። ኢየሱስ በሥጋ ደዌ በሽታ ተይዘው የነበሩ አሥር ሰዎችን የፈወሰ ቢሆንም ተመልሶ ያመሰገነው አንዱ ብቻ ነው። (ሉቃስ 17:12-17) ምስጋና ቢሶች እንደሆኑት ዘጠኙ ሰዎች ሳይሆን አመስጋኝ እንደሆነው ሰው መሆን እንደምንፈልግ የተረጋገጠ ነው!

9 ታዲያ ልንጠብቃቸው የሚገቡት የይሖዋ ትእዛዛት ምንድን ናቸው? ከትእዛዛቱ መካከል የተወሰኑትን በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የተመለከትናቸው ቢሆንም እስቲ ጥቂቶቹን እንከልሳቸው። የአምላክን ትእዛዛት መጠበቃችን ከአምላክ ፍቅር ሳንወጣ እንድንኖር ይረዳናል።

ከምንጊዜውም ይበልጥ ወደ ይሖዋ ቅረብ

10. ስለ ይሖዋ አምላክ እውቀት መቅሰም በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምን እንደሆነ ግለጽ።

10 ወደ ይሖዋ ይበልጥ መቅረብ እንድንችል ስለ እሱ መማራችን በጣም ወሳኝ ነው። ስለ እሱ መማራችንን መቼም ቢሆን ማቆም የለብንም። ኃይለኛ የሆነ ብርድ ባለበት ምሽት ውጭ ተቀምጠህ እሳት  እየሞቅክ ቢሆን እሳቱ እየከሰመ ሲሄድና ሲጠፋ ዝም ብለህ ታየዋለህ? እንዲህ እንደማታደርግ የታወቀ ነው። እሳቱ መንደዱንና ሙቀት መስጠቱን እንዲቀጥል እንጨት ትጨምርበታለህ። በሕይወት የመቆየትህ ሁኔታ ራሱ በዚህ ላይ የተመካ ሊሆን ይችላል! እንጨት እሳትን እንደሚያቀጣጥል ሁሉ “አምላክንም ማወቅ” ለይሖዋ ያለን ፍቅር ጠንካራ ሆኖ እንዲቀጥል ያደርጋል።—ምሳሌ 2:1-5

ለይሖዋ ያለህ ፍቅር ምንጊዜም እንዳይጠፋ ልክ እንደ እሳት የሚያቀጣጥል ነገር ያስፈልገዋል

11. ኢየሱስ የሰጣቸው ትምህርት በተከታዮቹ ላይ ምን ውጤት አስከትሏል?

11 ኢየሱስ ተከታዮቹ ለይሖዋና ውድ ለሆነው የእውነት ቃሉ ያላቸው የጋለ ፍቅር እንዳይቀዘቅዝ ይፈልግ ነበር። ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የሚገኙትን በእሱ ላይ የተፈጸሙ አንዳንድ ትንቢቶች አስመልክቶ ለሁለት ደቀ መዛሙርቱ ትምህርት ሰጥቷቸዋል። ይህ ምን ውጤት አስገኘ? ከተለያቸው በኋላ “በመንገድ ሳለን፣ እያነጋገረን ቅዱሳት መጻሕፍትንም ገልጦ ሲያስረዳን፣ ልባችን እንደ እሳት ይቃጠልብን አልነበረምን?” ሲሉ ተናግረዋል።—ሉቃስ 24:32

12, 13. (ሀ) በዘመናችን ያሉት አብዛኞቹ ሰዎች ለአምላክና ለመጽሐፍ ቅዱስ ያላቸው ፍቅር ምን ሆኗል? (ለ) ፍቅራችን እንዳይቀዘቅዝ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

12 መጀመሪያ ላይ ትክክለኛውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ስትማር የደስታ፣ የቅንዓትና አምላክን የመውደድ ስሜት በልብህ ውስጥ አልተቀጣጠለም? እንዲህ ያለ ስሜት እንደተሰማህ ጥርጥር የለውም። ብዙዎች ይህ ስሜት ተሰምቷቸዋል። አሁን ትልቁ ፈተና ይህን የጋለ ፍቅር ጠብቆ ማቆየትና እየጠነከረ እንዲሄድ ማድረጉ ነው። በዘመናችን ባለው ዓለም ውስጥ የሚታየውን አዝማሚያ መከተል አንፈልግም። ኢየሱስ “የብዙ ሰዎች ፍቅር ይቀዘቅዛል” ሲል ተንብዮአል። (ማቴዎስ 24:12) ለይሖዋና ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ያለህ ፍቅር እንዳይቀዘቅዝ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?

13 ስለ ይሖዋ አምላክና ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እውቀት መቅሰምህን ቀጥል። (ዮሐንስ 17:3) ‘ይህ ትምህርት ስለ ይሖዋ አምላክ ምን ያስተምረኛል? ይሖዋን በፍጹም ልቤ፣ ሐሳቤና ነፍሴ እንድወደው የሚያደርግ ምን ተጨማሪ ሐቅ ያስገነዝበኛል?’ እያልክ ራስህን በመጠየቅ ከአምላክ ቃል በምታገኘው ትምህርት ላይ አሰላስል ወይም በጥሞና አስብ። (1 ጢሞቴዎስ 4:15 የ1954 ትርጉም) በዚህ መንገድ ማሰላሰልህ ለይሖዋ ያለህ ፍቅር እንደጋለ እንዲቀጥል ለማድረግ ያስችልሃል።

14. ጸሎት ለይሖዋ ያለንን ፍቅር ጠብቀን እንድንኖር ሊረዳን የሚችለው እንዴት ነው?

 14 ለይሖዋ ያለህ ፍቅር እንዳይቀዘቅዝ ሊረዳህ የሚችለው ሌላው ነገር አዘውትሮ መጸለይ ነው። (1 ተሰሎንቄ 5:17) በዚህ መጽሐፍ 17ኛ ምዕራፍ ላይ ጸሎት ከአምላክ የተገኘ ውድ ስጦታ እንደሆነ ተምረናል። ከሰዎች ጋር አዘውትረን በነፃነት ስንነጋገር ወዳጅነታችን እየጎለበተ እንደሚሄድ ሁሉ አዘውትረን ወደ ይሖዋ ስንጸልይም ከእሱ ጋር ያለን ዝምድና እንደጠነከረና ሕያው እንደሆነ ይቀጥላል። ጸሎቶቻችን በዘልማድ የሚቀርቡ ማለትም ተደጋጋሚና እውነተኛ ስሜት የማይንጸባረቅባቸው ወይም ትርጉም የለሽ እንዳይሆኑ መጠንቀቅ ይኖርብናል። ይሖዋን ልናነጋግረው የሚገባን አንድ ትንሽ ልጅ የሚወደውን አባቱን በሚያነጋግርበት መንገድ መሆን ይኖርበታል። እርግጥ ነው፣ በአክብሮት ልናናግረው የሚገባን ቢሆንም በምንጸልይበት ጊዜ ስሜታችንን አውጥተን ለመግለጽ ነፃነት ሊሰማን ያስፈልጋል፤ እንዲሁም ጸሎታችን ሐቀኝነት የሚንጸባረቅበትና ከልብ የመነጨ መሆን ይኖርበታል። (መዝሙር 62:8) አዎን፣ የግል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትና ከልብ የመነጨ ጸሎት ወሳኝ የሆኑ የአምልኳችን ገጽታዎች ከመሆናቸውም በላይ ከአምላክ ፍቅር ሳንወጣ እንድንኖር ይረዱናል።

በአምልኮህ ደስታ ለማግኘት ጥረት አድርግ

15, 16. የመንግሥቱን ስብከት ሥራ እንደ መብትና እንደ ከበረ ነገር አድርገን መመልከታችን ተገቢ የሆነው ለምንድን ነው?

15 የግል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትና ጸሎት በግላችን ልናከናውናቸው የምንችላቸው የአምልኮ ገጽታዎች ናቸው። ይሁን እንጂ በሰዎች ፊት የምናከናውነውን አንድ የአምልኮ ዘርፍ እስቲ እንመልከት። ይህ የአምልኮ ዘርፍ የምናምንባቸውን ነገሮች ለሌሎች መንገር ነው። አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን ለሌሎች መንገር ጀምረሃል? ጀምረህ ከሆነ ልዩ በሆነ መብት እየተካፈልክ ነው ማለት ነው። (ሉቃስ 1:74 የ1954 ትርጉም) ስለ ይሖዋ አምላክ የተማርናቸውን እውነቶች ለሌሎች የምናካፍል ከሆነ ለሁሉም ክርስቲያኖች የተሰጠውን በጣም አስፈላጊ የሆነ ተልእኮ ማለትም ስለ አምላክ መንግሥት የሚገልጸውን ምሥራች የመስበኩን ሥራ እየፈጸምን ነው።—ማቴዎስ 24:14፤ 28:19, 20

16 ሐዋርያው ጳውሎስ አገልግሎቱን እንደ ውድ ነገር በመመልከት የከበረ ነገር ሲል ጠርቶታል። (2 ቆሮንቶስ 4:7) ስለ ይሖዋ አምላክና ስለ ዓላማዎቹ ለሰዎች ከመናገር የተሻለ ልታከናውነው የምትችለው ምንም  ሥራ የለም። ይህን አገልግሎት የምናከናውነው ተወዳዳሪ ለማይገኝለት ጌታችን ከመሆኑም በላይ ሥራው የሚያስገኘው ጥቅምም ቢሆን ወደር አይገኝለትም። በዚህ ሥራ መካፈልህ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች በሰማይ ወዳለው አባታችን እንዲቀርቡና ወደ ዘላለም ሕይወት በሚወስደው ጎዳና ላይ እንዲጓዙ ለመርዳት ያስችልሃል! ከዚህ የላቀ እርካታ ሊያስገኝ የሚችል  ሥራ ይኖራል? ከዚህም በተጨማሪ ስለ ይሖዋና ስለ ቃሉ መመሥከርህ እምነት ይጨምርልሃል እንዲሁም ለይሖዋ ያለህን ፍቅር ያጠነክርልሃል። ይሖዋ ደግሞ የምታደርገውን ጥረት ከፍ አድርጎ ይመለከተዋል። (ዕብራውያን 6:10) በዚህ ሥራ መጠመድህ ከአምላክ ፍቅር ሳትወጣ እንድትኖር ይረዳሃል።—1 ቆሮንቶስ 15:58

17. በአሁኑ ጊዜ ክርስቲያናዊው አገልግሎት አጣዳፊ የሆነው ለምንድን ነው?

17 የመንግሥቱ ስብከት ሥራ አጣዳፊ መሆኑን ማስታወሳችን አስፈላጊ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “ቃሉን በጥድፊያ ስሜት ስበክ” ይላል። (2 ጢሞቴዎስ 4:2 NW) በአሁኑ ጊዜ ይህን ማድረጋችን በጣም አጣዳፊ የሆነው ለምንድን ነው? የአምላክ ቃል “ታላቁ የእግዚአብሔር ቀን ቅርብ ነው፤ ቅርብ ነው ፈጥኖም ይመጣል” ሲል ይነግረናል። (ሶፎንያስ 1:14) አዎን፣ ይሖዋ ይህን ሥርዓት የሚያጠፋበት ጊዜ በጣም እየቀረበ ነው። ሰዎች ማስጠንቀቂያ ሊሰጣቸው ይገባል! ይሖዋን ሉዓላዊ ገዥያቸው አድርገው የሚመርጡበት ጊዜ አሁን እንደሆነ ማወቅ ያስፈልጋቸዋል። መጨረሻው “አይዘገይም።”—ዕንባቆም 2:3

18. ከእውነተኛ ክርስቲያኖች ጋር ሆነን ይሖዋን በይፋ ማምለክ ያለብን ለምንድን ነው?

18 ይሖዋ ከእውነተኛ ክርስቲያኖች ጋር በአንድነት ሆነን በይፋ እንድናመልከው ይፈልጋል። ቃሉ “እርስ በርሳችንም ለፍቅርና ለመልካም ሥራ እንዴት እንደምንነቃቃ እናስብ። አንዳንዶች ማድረጉን እንደተዉት መሰብሰባችንን አንተው፤ ይልቁንም ቀኑ እየተቃረበ መምጣቱን ስታዩ እርስ በርሳችን እንበረታታ” የሚለው ለዚህ ነው። (ዕብራውያን 10:24, 25) በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር ስንሰበሰብ ተወዳጁን አምላካችንን ማወደስና ማምለክ የምንችልበት ግሩም አጋጣሚ እናገኛለን። በተጨማሪም እርስ በርሳችን እንተናነጻለን እንዲሁም እንበረታታለን።

19. በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ያለውን ፍቅር ማጠንከር የምንችለው እንዴት ነው?

19 ከሌሎች የይሖዋ አምላኪዎች ጋር ስንሰበሰብ በጉባኤው ውስጥ ያለውን የፍቅርና የወዳጅነት መንፈስ እናጠነክረዋለን። ይሖዋ የእኛን መልካም ጎን እንደሚመለከት ሁሉ አንዳችን የሌላውን መልካም ጎን መመልከታችን አስፈላጊ ነው። ከእምነት ባልንጀሮችህ ፍጽምናን መጠበቅ የለብህም። ሁሉም በተለያየ የመንፈሳዊ እድገት ደረጃ ላይ እንዳሉና ሁላችንም እንደምንሳሳት አስታውስ። (ቈላስይስ 3:13) ለይሖዋ የጠለቀ ፍቅር ካላቸው ጋር የጠበቀ ወዳጅነት የምትመሠርት ከሆነ በመንፈሳዊ ታድጋለህ። አዎን፣ ከመንፈሳዊ ወንድሞችህና እህቶችህ ጋር ሆነህ ይሖዋን  ማምለክህ ከአምላክ ፍቅር ሳትወጣ እንድትኖር ይረዳሃል። ይሖዋ እርሱን በታማኝነት የሚያመልኩትንና ከእሱ ፍቅር የማይወጡትን ሰዎች የሚክሳቸው እንዴት ነው?

“እውነተኛውን ሕይወት” ለማግኘት ተጣጣር

20, 21. ‘እውነተኛው ሕይወት’ የትኛው ነው? አስደሳች ተስፋ ነው የምንለውስ ለምንድን ነው?

20 ይሖዋ ታማኝ አገልጋዮቹን ሕይወት በመስጠት ይክሳቸዋል፤ ይሁንና የሚሰጣቸው ምን ዓይነት ሕይወት ነው? አሁን በእርግጥ እየኖርክ እንዳለህ ሆኖ ይሰማሃል? አብዛኞቻችን ይሄማ ምን ጥያቄ አለው? ብለን እንደምንመልስ የታወቀ ነው። እርግጥ ነው፣ እንተነፍሳለን፣ እንበላለን እንዲሁም እንጠጣለን። ስለዚህ በሕይወት እየኖርን እንዳለን ጥርጥር የለውም። በጣም ስንደሰት ደግሞ “የሕይወትን ጣዕም ያወቅኩት አሁን ነው!” እስከማለት እንደርሳለን። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ በጣም አስፈላጊ ከሆነ አንድ ሁኔታ አንጻር ሲታይ በአሁኑ ጊዜ ማንም ሰው በእርግጥ እየኖረ ነው ሊባል እንደማይችል ያመለክታል።

ይሖዋ “እውነተኛውን ሕይወት” እንድታገኝ ይፈልጋል። አንተ ለዚያ ትበቃ ይሆን?

21 የአምላክ ቃል ‘እውነተኛውን ሕይወት አጥብቀን እንድንይዝ’ አበክሮ ያሳስበናል። (1 ጢሞቴዎስ 6:18, 19 የ1954 ትርጉም) እነዚህ ቃላት ‘እውነተኛው ሕይወት’ ወደፊት እንደምናገኘው በተስፋ የምንጠብቀው ነገር እንደሆነ ይጠቁሙናል። አዎን፣ ፍጹማን ስንሆን አምላክ መጀመሪያ ባለመው መንገድ የምንኖር በመሆኑ ከቃሉ ሙሉ ትርጉም ጋር በሚስማማ መንገድ እንኖራለን። ገነት በምትሆነው ምድር ውስጥ የተሟላ ጤንነት፣ ሰላምና ደስታ አግኝተን ስንኖር ያን ጊዜ “እውነተኛውን ሕይወት” ይኸውም የዘላለምን ሕይወት እናጣጥማለን። (1 ጢሞቴዎስ 6:12) ይህ አስደሳች ተስፋ አይደለም?

22. ‘እውነተኛውን ሕይወት አጥብቀህ መያዝ’ የምትችለው እንዴት ነው?

22 ‘እውነተኛውን ሕይወት አጥብቀን መያዝ’ የምንችለው እንዴት ነው? ጳውሎስ እዚያው ጥቅስ ላይ ክርስቲያኖች ‘መልካም እንዲያደርጉ’ እና ‘በበጎ ሥራ ባለ ጠጎች እንዲሆኑ’ አጥብቆ መክሯል። (1 ጢሞቴዎስ 6:18, 19 የ1954 ትርጉም) እንግዲያው ይህ በአብዛኛው የተመካው ከመጽሐፍ ቅዱስ የተማርናቸውን እውነቶች ተግባራዊ በምናደርግበት መንገድ ላይ እንደሆነ በግልጽ መረዳት ይቻላል። ይሁን እንጂ ጳውሎስ ‘እውነተኛው ሕይወት’ መልካም ሥራዎች በመሥራት የምናገኘው ዋጋ እንደሆነ አድርጎ መናገሩ ነው? በፍጹም፤ እንደነዚህ ያሉትን አስደናቂ ተስፋዎች  ልንወርስ የምንችለው በአምላክ ‘ፀጋ’ ነው። (ሮሜ 5:15) ሆኖም ይሖዋ እርሱን በታማኝነት የሚያገለግሉትን መካስ ያስደስተዋል። “እውነተኛውን ሕይወት” ስትኖር ማየት ይፈልጋል። ከአምላክ ፍቅር የማይወጡ ሰዎች እንዲህ ያለ አስደሳችና ሰላማዊ የሆነ የዘላለም ሕይወት ይጠብቃቸዋል።

23. ከአምላክ ፍቅር ሳንወጣ መኖራችን በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

23 እያንዳንዳችን ‘አምላክን እያመለክሁ ያለሁት እሱ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በገለጸው መንገድ ነው?’ ብለን ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል። ዘወትር ራሳችንን ስንመረምር ለዚህ ጥያቄ የምንሰጠው መልስ አዎንታዊ ከሆነ በትክክለኛው ጎዳና ላይ እየተጓዝን ነው ማለት ነው። ይህን እያደረግን ከሆንን ይሖዋ መጠጊያችን እንደሚሆንልን እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ይሖዋ ታማኝ ሕዝቦቹ ደኅንነታቸው እንደተጠበቀ አስቸጋሪ የሆኑትን የዚህን አሮጌ ሥርዓት የመጨረሻ ቀኖች እንዲሻገሩ ያደርጋል። በተጨማሪም በቅርቡ የሚመጣውን እጅግ አስደናቂ የሆነ አዲስ ሥርዓት ያወርሰናል። ለዚያ ዘመን ስንበቃ ምንኛ ሐሴት እናደርግ ይሆን! በተጨማሪም በእነዚህ የመጨረሻ ቀኖች ትክክለኛ ምርጫዎች በማድረጋችን ምንኛ እንደሰት ይሆን! በአሁኑ ዘመን እንዲህ ያሉ ምርጫዎች የምታደርግ ከሆነ ይሖዋ አምላክ መጀመሪያ ላይ ያለመውን ‘እውነተኛ ሕይወት’ ለዘላለም ዓለም እያጣጣምክ ትኖራለህ!