ተጨማሪ ክፍል
1914—በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ውስጥ ትልቅ ትርጉም ያለው ዓመት
የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በ1914 ትልቅ ትርጉም ያላቸው ክስተቶች እንደሚፈጸሙ ብዙ አሥርተ ዓመታት ቀደም ብለው ተናግረው ነበር። እነዚህ ክስተቶች ምንድን ናቸው? በተጨማሪም 1914 ትልቅ ትርጉም ያለው ዓመት እንደሆነ የሚጠቁመው ማስረጃ ምንድን ነው?
ሉቃስ 21:24 ላይ ተመዝግቦ እንደሚገኘው ኢየሱስ “ኢየሩሳሌምም የአሕዛብ ዘመን እስኪፈጸም ድረስ፣ በአሕዛብ የተረገጠች ትሆናለች” ሲል ተናግሯል። ኢየሩሳሌም የአይሁድ ሕዝብ ዋና ከተማ ማለትም የንጉሥ ዳዊት ዘሮች የሆኑ ነገሥታት መቀመጫ ነበረች። (መዝሙር 48:1, 2) ይሁን እንጂ እነዚህ ነገሥታት ከአሕዛብ መሪዎች የተለዩ ናቸው። የአምላክ ወኪሎች ሆነው “በእግዚአብሔር ዙፋን” ላይ የሚቀመጡ ነገሥታት ነበሩ። (1 ዜና መዋዕል 29:23) ስለዚህ ኢየሩሳሌም የይሖዋን አገዛዝ ትወክል ነበር።
ይሁንና የአምላክ አገዛዝ ‘በአሕዛብ መረገጥ’ የጀመረው መቼና እንዴት ነው? ይህ የሆነው በ607 ከክርስቶስ ልደት በፊት ኢየሩሳሌም በባቢሎናውያን እጅ ስትወድቅ ነው። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ የይሖዋ ዙፋን ክፍት ሆኖ የቆየ ሲሆን የዳዊት ዘሮች ንጉሣዊ አገዛዝ ተቋርጦ ነበር። (2 ነገሥት 25:1-26) ይህ አገዛዝ ለዘላለም ‘ተረግጦ’ ይቀራል? በፍጹም፤ የሕዝቅኤል ትንቢት የኢየሩሳሌም የመጨረሻ ንጉሥ የሆነውን ሴዴቅያስን አስመልክቶ ሲናገር “ጥምጥምህን አውልቅ፤ ዘውድህን ጣል፤ . . . የሚገባው ባለ መብት እስከሚመጣ ድረስ እንደ ቀድሞው አትሆንም፤ ለእርሱም ደግሞ እሰጣታለሁ” ይላል። (ሕዝቅኤል 21:26, 27) የዳዊትን ዘውድ መድፋት “የሚገባው ባለ መብት” ክርስቶስ ኢየሱስ ነው። (ሉቃስ 1:32, 33) ስለዚህ ኢየሱስ ንጉሥ ሲሆን የአምላክ አገዛዝ ‘መረገጡ’ ያበቃል።
ይህ ታላቅ ክንውን የሚፈጸመው መቼ ነው? ኢየሱስ አሕዛብ የሚያስተዳድሩት ለተወሰነ ጊዜ እንደሆነ አመልክቷል። ዳንኤል ምዕራፍ 4 ላይ የሚገኘው ዘገባ ይህ የጊዜ ርዝመት ምን ያህል እንደሆነ ለማወቅ የሚያስችሉ ፍንጮችን ይጠቅሳል። ዘገባው የባቢሎኑ ንጉሥ ናቡከደነፆር ያየውን ትንቢታዊ ሕልም ይገልጻል። ንጉሡ የተቆረጠ ግዙፍ ዛፍ ተመልክቷል። ጉቶው በብረትና በናስ ስለታሰረ ሊያድግ አይችልም። አንድ መልአክ “ሰባት ዘመናትም ይለፉበት” ሲል ተናግሯል።—ዳንኤል 4:10-16 የ1954 ትርጉም
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ዛፎች አንዳንድ ጊዜ አገዛዝን ለማመልከት ተሠርቶባቸዋል። (ሕዝቅኤል 17:22-24፤ 31:2-5) ስለዚህ ምሳሌያዊው ዛፍ መቆረጡ በኢየሩሳሌም ነገሥታት የተወከለው የአምላክ አገዛዝ እንደሚቋረጥ ያመለክታል። ይሁን እንጂ ራእዩ ‘ኢየሩሳሌም የምትረገጠው’ ለተወሰነ ጊዜ ይኸውም ‘ለሰባት ዘመናት’ እንደሆነ ገልጿል። ይህ ጊዜ ምን ያህል ርዝማኔ አለው?
ራእይ 12:6, 14 ሦስት ተኩል ዘመን “አንድ ሺህ ሁለት መቶ ሥልሳ ቀን” እንደሆነ ይጠቁማል። ስለዚህ “ሰባት ዘመናት” የዚህ እጥፍ ወይም 2,520 ቀናት ይሆናሉ። ሆኖም አሕዛብ ኢየሩሳሌም በወደቀች በ2,520 ቀናት ውስጥ የአምላክን አገዛዝ ‘መርገጣቸውን’ አላቆሙም። ስለዚህ ይህ ትንቢት ከዚህ በጣም የሚበልጥን ጊዜ የሚያመለክት መሆን እንዳለበት በግልጽ መረዳት ይቻላል። “እያንዳንዱ ዓመት እንደ አንድ ዕለት” እንደሆነ በሚናገረው የዘኍልቍ 14:34 እና የሕዝቅኤል 4:6 ሐሳብ መሠረት ‘ሰባቱ ዘመናት’ 2,520 ዓመታት ይሆናሉ።
እነዚህ 2,520 ዓመታት የጀመሩት ጥቅምት 607 ከክርስቶስ ልደት በፊት ኢየሩሳሌም በባቢሎናውያን እጅ ስትወድቅና የዳዊት ዘር የሆነው ንጉሥ ከዙፋኑ እንዲወርድ ሲደረግ ነው። ይህ ዘመን ያበቃው ደግሞ ጥቅምት 1914 ላይ ነው። በዚህ ጊዜ የተወሰነው “የአሕዛብ ዘመን” የተፈጸመ ከመሆኑም በላይ ኢየሱስ ክርስቶስ የአምላክ ሰማያዊ ንጉሥ ሆኖ ተሹሟል። *—መዝሙር 2:1-6፤ ዳንኤል 7:13, 14
ኢየሱስ አስቀድሞ በተናገረው መሠረት ሰማያዊ ንጉሥ ሆኖ በሥልጣኑ ላይ በተገኘበት ጊዜ በዓለም ዙሪያ እንደ ጦርነት፣ ረሃብ፣ የምድር ነውጥና ቸነፈር ያሉ አስደናቂ ክስተቶች ባልተለመደ ሁኔታ ተከስተዋል። (ማቴዎስ 24:3-8፤ ሉቃስ 21:11) እንዲህ ያሉት ክስተቶች 1914 በእርግጥም የአምላክ ሰማያዊ መንግሥት የተወለደበትና አሁን ያለው ክፉ ሥርዓት ‘የመጨረሻ ዘመን’ የጀመረበት ዓመት እንደሆነ የሚያረጋግጡ አስተማማኝ ማስረጃዎች ናቸው።—2 ጢሞቴዎስ 3:1-5
^ አን.3 ከጥቅምት 607 ከክርስቶስ ልደት በፊት እስከ ጥቅምት 1 ከክርስቶስ ልደት በፊት 606 ዓመት ነው። ዜሮ የሚባል ዓመት ስለሌለ ከጥቅምት 1 ከክርስቶስ ልደት በፊት እስከ ጥቅምት 1914 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ያለው ጊዜ 1,914 ዓመት ነው። በመሆኑም 606ንና 1,914ን ስንደምር 2,520 ዓመት ይመጣል። በ607 ከክርስቶስ ልደት በፊት ኢየሩሳሌም ላይ ስለደረሰው ጥፋት ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች በተዘጋጀው ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ) በተባለው መጽሐፍ ላይ ያለውን “የዘመናት ስሌት” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።