ተጨማሪ ክፍል
እውነተኛ ክርስቲያኖች መስቀልን ለአምልኮ የማይጠቀሙበት ለምንድን ነው?
በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ለመስቀል ከፍተኛ ፍቅር ያላቸው ከመሆኑም በላይ ልዩ ክብር ይሰጡታል። ዚ ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ መስቀልን “የክርስቲያን ሃይማኖት ዋነኛ ምልክት” ሲል ገልጾታል። ይሁንና እውነተኛ ክርስቲያኖች መስቀልን ለአምልኮ አይጠቀሙም። ለምን?
ዋነኛው ምክንያት ኢየሱስ ክርስቶስ የሞተው በመስቀል ላይ ባለመሆኑ ነው። አብዛኛውን ጊዜ “መስቀል” ተብሎ የሚተረጎመው የግሪክኛ ቃል ስታውሮስ ነው። የዚህ ቃል መሠረታዊ ትርጉም “ቀጥ ያለ እንጨት” ነው። ዘ ከምፓንየን ባይብል እንዲህ ሲል ገልጿል:- “[ስታውሮስ] በየትኛውም አቅጣጫ የተነባበሩ ሁለት መስቀለኛ እንጨቶችን አያመለክትም . . . በግሪክኛ በተጻፈው [አዲስ ኪዳን] ውስጥ ሁለት እንጨቶችን የሚያመለክት ምንም ዓይነት ዘገባ አይገኝም።”
በርከት ባሉ ጥቅሶች ላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ኢየሱስ የሞተበትን ነገር ለማመልከት ሌላ ቃል ተጠቅመዋል። ይህም ዛይሎን የተባለው የግሪክኛ ቃል ነው። (የሐዋርያት ሥራ 5:30፤ 10:39፤ 13:29፤ ገላትያ 3:13፤ 1 ጴጥሮስ 2:24 የ1954 ትርጉም) ይህ ቃል “አጣና” አሊያም “ዱላ፣ ቆመጥ ወይም ደግሞ ዛፍ” ማለት ነው።
በሄርማን ፉልደ የተዘጋጀው ዳስ ክሮይትስ ኡንት ዲ ክሮይሲጉንግ (መስቀልና ስቅለት) የተባለው መጽሐፍ ሰዎችን በሞት ለመቅጣት ብዙውን ጊዜ አንድ ቀጥ ያለ እንጨት ይጠቀሙ የነበረው ለምን እንደሆነ ሲገልጽ እንዲህ ይላል:- “በሕዝብ ፊት የሞት ቅጣት ለማስፈጸም ይመረጡ በነበሩት ቦታዎች ዛፎች እንደልብ አይገኙም ነበር። ስለዚህ አንድ እንጨት መሬት ውስጥ ይተከላል። በዚህ እንጨት ላይ ሕገ ወጥ የሆኑ ሰዎች እጆቻቸው ወደ ላይ ተዘርግተውና ብዙውን ጊዜም እግሮቻቸው ወደ ታች ተወጥረው ይታሰራሉ ወይም በምስማር ይቸነከራሉ።”
ይሁን እንጂ ከሁሉ ይበልጥ አሳማኝ የሆነው ማስረጃ የሚገኘው በአምላክ ቃል ውስጥ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ “‘በዕንጨት ላይ የሚሰቀል ሁሉ የተረገመ ነው’ ተብሎ ስለ ተጻፈ፣ ክርስቶስ ስለ እኛ ርግማን ሆኖ ከሕግ ርግማን ዋጅቶናል” ሲል ተናግሯል። (ገላትያ 3:13) እዚህ ላይ ጳውሎስ የተናገረው ከዘዳግም 21:22, 23 ላይ ጠቅሶ ሲሆን ይህ ጥቅስ ደግሞ የሚናገረው ወጥ ስለሆነ እንጨት እንጂ ስለ መስቀል እንዳልሆነ ግልጽ ነው። እንዲህ ያለው የሞት ቅጣት ግለሰቡን “የተረገመ” ስለሚያደርገው ክርስቲያኖች ክርስቶስ በእንጨት ላይ መቸንከሩን በሚያሳዩ ምስሎች ቤቶቻቸውን ማስጌጣቸው ተገቢ አይሆንም።
ክርስቶስ ከሞተ በኋላ በነበሩት በመጀመሪያዎቹ 300 ዓመታት ክርስቲያን ነን የሚሉ ሰዎች መስቀልን ለአምልኮ ይጠቀሙበት እንደነበረ የሚያሳይ ምንም ማስረጃ የለም። ይሁን እንጂ በአራተኛው መቶ ዘመን የአረማውያን ንጉሠ ነገሥት የነበረው ቆስጠንጢኖስ እምነቱን ለውጦ የከሃዲዋ ክርስትና ተከታይ በመሆን መስቀል የክርስትና ምልክት እንዲሆን አደረገ። የቆስጠንጢኖስ ዓላማ ምንም ይሁን ምን መስቀል ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ምንም ግንኙነት የለውም። እንዲያውም መስቀል ከአረማውያን የመጣ ነው። ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፒዲያ “መስቀል ከክርስትና ዘመን በፊት በነበሩትም ሆነ ከክርስትና ውጭ ባሉት ባሕሎች ውስጥ የነበረ ነገር ነው” ሲል ሐቁን ሳይሸሽግ ተናግሯል። ሌሎች የማመሳከሪያ ጽሑፎች መስቀል ተፈጥሮን ከማምለክና ከአረማውያን የመራባት የአምልኮ ሥርዓት ጋር የተያያዘ እንደሆነ ይገልጻሉ።
ታዲያ ይህ የአረማውያን ምልክት የተስፋፋው ለምንድን ነው? አረማውያን “ክርስትናን” በቀላሉ እንዲቀበሉ ለማድረግ ይመስላል። ይሁንና ማንኛውንም የአረማውያን ምስል ማምለክ በመጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ የተወገዘ ነው። (2 ቆሮንቶስ 6:14-18) በተጨማሪም ቅዱሳን ጽሑፎች ከማንኛውም ዓይነት የጣዖት አምልኮ እንድንርቅ ያዛሉ። (ዘፀአት 20:4, 5፤ 1 ቆሮንቶስ 10:14) እንግዲያው እውነተኛ ክርስቲያኖች መስቀልን ለአምልኮ አለመጠቀማቸው ተገቢ ነው። *
^ አን.4 መስቀልን በተመለከተ ይበልጥ ዝርዝር የሆነ ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ከቅዱሳን ጽሑፎች እየጠቀሱ ማመራመር የተባለውን መጽሐፍ ከገጽ 87-91 ተመልከት።