በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ተጨማሪ ክፍል

ኢየሱስ የተወለደው በታኅሣሥ ወር ነው?

ኢየሱስ የተወለደው በታኅሣሥ ወር ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ መቼ እንደተወለደ አይነግረንም። ይሁን እንጂ ኢየሱስ የተወለደው በታኅሣሥ ወር አይደለም እንድንል የሚያደርገን አጥጋቢ ምክንያት ይሰጠናል።

በታኅሣሥ ወር አካባቢ ኢየሱስ በተወለደባት በቤተልሔም ከተማ የሚኖረውን የአየር ጠባይ እንመልከት። በአይሁዶች አቆጣጠር ካሴሉ (ኅዳር/ታኅሣሥ) የተባለው የአይሁዶች ወር ቅዝቃዜና ዝናብ ያለበት ወቅት ነው። ከዚያ ቀጥሎ ያለው ወር ቴቤት (ታኅሣሥ/ጥር) ነው። በዚህ ወር የሚኖረው የሙቀት መጠን በዓመቱ ውስጥ ከሚመዘገበው ሁሉ በጣም አነስተኛው ሲሆን አልፎ አልፎም በከፍታ ቦታዎች ላይ በረዶ ይጋገራል። መጽሐፍ ቅዱስ በዚያ ክልል ስላለው የአየር ጠባይ ምን እንደሚል እስቲ እንመልከት።

የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የሆነው ዕዝራ ካሴሉ በእርግጥም ቅዝቃዜና ዝናብ የሚያይልበት ወር እንደሆነ አመልክቷል። በኢየሩሳሌም ብዙ ሰዎች እንደተሰበሰቡ ከገለጸ በኋላ ‘በዘጠነኛው ወር [ካሴሉ] በሃያኛውም ቀን ሕዝቡ በከባዱ ዝናብ የተነሳ ይጨነቁ [‘ይንቀጠቀጡ፣’ የ1954 ትርጉም]’ እንደነበር ዘግቧል። የተሰበሰቡት ሰዎች ራሳቸው በዚህ ወቅት ያለውን የአየር ሁኔታ  አስመልክተው ሲናገሩ “ወቅቱም ክረምት ነው፤ ስለዚህ ውጭ መቆም አንችልም” ብለዋል። (ዕዝራ 10:9, 13፤ ኤርምያስ 36:22) በታኅሣሥ ወር በቤተልሔም አካባቢ የሚኖሩ እረኞችም ሆኑ መንጎቻቸው በሌሊት ውጭ አለማደራቸው ምንም አያስገርምም!

ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚገልጸው ኢየሱስ በተወለደበት ሌሊት እረኞች መንጎቻቸውን በሜዳ እየጠበቁ ነበር። እንዲያውም የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የሆነው ሉቃስ በዚያ ወቅት እረኞች በቤተልሔም አቅራቢያ ‘መንጋቸውን ሲጠብቁ በሜዳ እንዳደሩ’ ገልጿል። (ሉቃስ 2:8-12) እረኞቹ ቀን ውጭ መዋል ብቻ ሳይሆን ሌሊት በሜዳ መንጎቻቸውን እየጠበቁ እንዳደሩ ልብ በል። ውጭ እንዳደሩ የሚገልጸው ይህ ዘገባ በታኅሣሥ ወር በቤተልሔም ከሚኖረው በጣም የሚበርድና ዝናባማ የሆነ የአየር ጠባይ ጋር ሊጣጣም ይችላል? ፈጽሞ ሊጣጣም አይችልም። ስለዚህ ኢየሱስ በተወለደበት ጊዜ የነበሩት ሁኔታዎች የተወለደው በታኅሣሥ ወር እንዳልሆነ ይጠቁማሉ። *

የአምላክ ቃል ኢየሱስ የሞተበትን ትክክለኛ ጊዜ የሚነግረን ቢሆንም የተወለደበትን ጊዜ ግን በቀጥታ ለይቶ አይጠቅስልንም። ይህም “መልካም ስም ከመልካም ሽቱ ይበልጣል፤ ከልደትም ቀን የሞት ቀን ይሻላል” የሚሉትን የንጉሥ ሰሎሞን ቃላት ያስታውሰናል። (መክብብ 7:1) እንግዲያው መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ኢየሱስ አገልግሎትና አሟሟት ብዙ ዝርዝር መግለጫዎች የሚሰጥ ቢሆንም እንኳ ስለተወለደበት ጊዜ ብዙም የሚጠቅሰው ነገር አለመኖሩ አያስደንቅም።

ኢየሱስ በተወለደበት ጊዜ እረኞችና መንጎቻቸው በሌሊት ሜዳ ላይ ነበሩ

^ አን.1 ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ከቅዱሳን ጽሑፎች እየጠቀሱ ማመራመር የተባለውን መጽሐፍ ከገጽ 176-179 ተመልከት።