በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ምዕራፍ አሥራ አንድ

አምላክ በሰው ልጆች ላይ መከራ እንዲደርስ የፈቀደው ለምንድን ነው?

አምላክ በሰው ልጆች ላይ መከራ እንዲደርስ የፈቀደው ለምንድን ነው?
  • በዓለም ላይ ያለውን መከራ ያመጣው አምላክ ነው?

  • በኤደን ገነት ምን ክርክር ተነስቷል?

  • አምላክ በሰዎች ላይ እየደረሰ ያለውን ሥቃይና መከራ የሚያስወግደው እንዴት ነው?

1, 2. ዛሬ ሰዎች ምን ዓይነት መከራ ይደርስባቸዋል? ይህስ ብዙዎች ምን ጥያቄዎች እንዲያነሱ ይገፋፋቸዋል?

በጦርነት ስትታመስ በቆየች አንዲት አገር ውስጥ በጣም አሰቃቂ የሆነ ውጊያ ከተካሄደ በኋላ በውጊያው ሕይወታቸውን ያጡ በሺዎች የሚቆጠሩ ሲቪል ሴቶችና ሕፃናት ዙሪያውን በመስቀል ምልክቶች በታጠረ አንድ መቃብር በጅምላ ተቀበሩ። በእያንዳንዱ ምልክት ላይ “ለምን?” የሚል ጥያቄ ተጽፎበት ነበር። አንዳንድ ጊዜ ሰዎች በደረሰባቸው ጥልቅ ሐዘን ሲመረሩ ይህን ጥያቄ ያነሳሉ። ሰዎች ጦርነት፣ ድንገተኛ አደጋ፣ በሽታ ወይም ወንጀል ምንም ጥፋት ያልሠሩትን በጣም የሚወዷቸውን ሰዎች ሕይወት ሲቀጥፍ፣ ቤታቸውን ሲያወድም ወይም ይህ ነው የማይባል መከራና ሥቃይ ሲያስከትልባቸው በሐዘን ተውጠው ይህን ጥያቄ ለማንሳት ይገደዳሉ። እንዲህ ያሉ አሳዛኝ ሁኔታዎች የሚደርሱባቸው ለምን እንደሆነ ማወቅ ይፈልጋሉ።

2 አምላክ በሰው ልጆች ላይ መከራ እንዲደርስ የፈቀደው ለምንድን ነው? ይሖዋ አምላክ ሁሉን ለማድረግ የሚያስችል ኃይል ካለው እንዲሁም አፍቃሪ፣ ጥበበኛና ፍትሐዊ ከሆነ ዓለም በጥላቻና በግፍ የተሞላው ለምንድን ነው? ከዚህ በፊት ስለዚህ ጉዳይ አስበህ ታውቃለህ?

3, 4. (ሀ) አምላክ በሰው ልጆች ላይ መከራ እንዲደርስ የፈቀደው ለምንድን ነው ብሎ መጠየቁ ስህተት እንዳልሆነ የሚያሳየው ምንድን ነው? (ለ) ይሖዋ ክፋትንና መከራን በተመለከተ ምን ይሰማዋል?

3 አምላክ በሰው ልጆች ላይ መከራ እንዲደርስ የፈቀደው ለምን እንደሆነ  መጠየቅ ስህተት ነው? አንዳንዶች እንዲህ ያለ ጥያቄ መጠየቃቸው እምነት እንደሚጎድላቸው ወይም ለአምላክ አክብሮት እንደሌላቸው የሚያሳይ እንደሆነ አድርገው በማሰብ ስጋት ያድርባቸዋል። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስን ስታነብ ፈሪሃ አምላክ የነበራቸው ታማኝ ሰዎችም ተመሳሳይ ጥያቄ አቅርበው እንደነበረ ትገነዘባለህ። ለምሳሌ ያህል ነቢዩ ዕንባቆም “ስለ ምን በደልን እንዳይ አደረግኸኝ? እንዴትስ ግፍ ሲፈጸም ትታገሣለህ? ጥፋትና ግፍ በፊቴ አለ፤ ጠብና ግጭት በዝቶአል” ሲል ይሖዋን ጠይቋል።—ዕንባቆም 1:3

ይሖዋ ሁሉንም ዓይነት መከራ ያስወግዳል

4 ይሖዋ ታማኙ ነቢይ ዕንባቆም እንዲህ ያለ ጥያቄ በማንሳቱ ገሥጾታል? በፍጹም። ከዚህ ይልቅ ዕንባቆም በቅንነት የተናገራቸው ቃላት በመንፈሱ አነሳሽነት በተጻፈው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዲሰፍሩ አድርጓል። ከዚህም በተጨማሪ ስላሉት ሁኔታዎች የተሻለ ግንዛቤ እንዲያገኝና እምነቱ እየጠነከረ እንዲሄድ ረድቶታል። ይሖዋ ለአንተም እንዲሁ ማድረግ ይፈልጋል። መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ‘ስለ አንተ እንደሚያስብ’ የሚናገር መሆኑን አስታውስ። (1 ጴጥሮስ 5:7) አምላክ ክፋትንና በክፋት ሳቢያ እየደረሰ ያለውን መከራ ከማንኛውም ሰው በላይ ይጠላል። (ኢሳይያስ 55:8, 9) ታዲያ በዓለም ላይ ይህን ያህል መከራ የበዛው ለምንድን ነው?

መከራ የበዛው ለምንድን ነው?

5. በሰዎች ላይ መከራ የሚደርሰው ለምን እንደሆነ ለማስረዳት አንዳንድ ጊዜ ምን ምክንያቶች ይቀርባሉ? ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ ምን ያስተምራል?

5 የተለያዩ ሃይማኖቶች ተከታይ የሆኑ ሰዎች ይህን ያህል መከራ የበዛው  ለምን እንደሆነ የሃይማኖት መሪዎቻቸውንና አስተማሪዎቻቸውን ይጠይቃሉ። ብዙውን ጊዜ የሚሰጣቸው መልስ መከራ የአምላክ ፈቃድ እንደሆነና አሳዛኝ የሆኑ ክስተቶችን ጨምሮ በምድር ላይ የሚፈጸመው ሁኔታ ሁሉ አምላክ አስቀድሞ የወሰነው እንደሆነ የሚገልጽ ነው። ብዙዎች፣ የአምላክ መንገዶች ምሥጢራዊ እንደሆኑ ወይም ደግሞ ሕፃናትን ጨምሮ ሰዎች ከእሱ ጋር በሰማይ እንዲኖሩ ሲል በሞት እንደሚነጥቃቸው ይነገራቸዋል። ይሁን እንጂ ቀደም ሲል እንደተማርከው ይሖዋ አምላክ ክፉ ነገር አያደርግም። መጽሐፍ ቅዱስ “ክፋትን ማድረግ ከእግዚአብሔር ዘንድ፣ በደልንም መፈጸም ሁሉን ከሚችል አምላክ ይራቅ” ይላል።—ኢዮብ 34:10

6. ብዙ ሰዎች በዓለም ላይ እየደረሰ ላለው መከራ አምላክን ተጠያቂ የሚያደርጉት ለምንድን ነው?

6 ሰዎች በዓለም ላይ እየደረሰ ላለው መከራ ተጠያቂው አምላክ ነው የሚል የተሳሳተ አመለካከት የሚያድርባቸው ለምን እንደሆነ ታውቃለህ? ብዙውን ጊዜ ሁሉን ቻይ የሆነውን አምላክ ተጠያቂ የሚያደርጉት በቀጥታ ይህን ዓለም እየገዛ ያለው እሱ እንደሆነ አድርገው ስለሚያስቡ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረውን ቀላል ግን በጣም አስፈላጊ የሆነ አንድ እውነት አያውቁም። ይህን እውነት በዚህ መጽሐፍ ሦስተኛ ምዕራፍ ላይ ተምረሃል። የዚህ ዓለም ገዥ ሰይጣን ዲያብሎስ ነው።

7, 8. (ሀ) ዓለም የገዥውን ባሕርይ እያንጸባረቀ ያለው እንዴት ነው? (ለ) ሰብዓዊ አለፍጽምና እንዲሁም “ጊዜና አጋጣሚ” በሰው ልጆች ላይ መከራ እንዲደርስ ምክንያት የሆኑት እንዴት ነው?

7 መጽሐፍ ቅዱስ ‘መላው ዓለም በክፉው ሥር እንደ ሆነ’ በግልጽ ይናገራል። (1 ዮሐንስ 5:19) ካለው ሁኔታ አንጻር ስታየው ይህ አባባል ትክክል አይመስልህም? ያለንበት ኅብረተሰብ ‘ዓለምን ሁሉ የሚያስተውን’ የማይታይ መንፈሳዊ ፍጡር ባሕርይ የሚያንጸባርቅ ነው። (ራእይ 12:9) ሰይጣን በጥላቻ የተሞላ፣ አታላይና ጨካኝ ነው። ስለዚህ በእሱ ተጽዕኖ ሥር ያለው ዓለምም በጥላቻ፣ በማታለልና በጭካኔ ድርጊት የተሞላ ነው። መከራ ሊበዛ የቻለበት አንዱ ምክንያት ይህ ነው።

8 መከራ በጣም ሊበዛ የቻለበት ሁለተኛው ምክንያት በምዕራፍ 3 ላይ እንደተገለጸው በኤደን ገነት ዓመጽ ከተነሳበት ጊዜ አንስቶ የሰው ዘር ፍጽምና የጎደለውና ኃጢአተኛ መሆኑ ነው። ኃጢአተኛ የሆኑ ሰዎች የሌላው  የበላይ ለመሆን የሚታገሉ ሲሆን ይህም ጦርነት፣ ጭቆናና መከራ ያስከትላል። (መክብብ 4:1፤ 8:9) መከራ ሊበዛ የቻለበት ሦስተኛው ምክንያት ደግሞ “ጊዜና አጋጣሚ” ነው። (መክብብ 9:11 NW) ይሖዋ በማይገዛውና ጥበቃ በማያደርግበት ዓለም ውስጥ ሰዎች ባልሆነ ሰዓት ያልሆነ ቦታ ላይ በመገኘታቸው ለመከራ ሊዳረጉ ይችላሉ።

9. ይሖዋ በሰው ልጆች ላይ መከራ እንዲደርስ የፈቀደው በቂ ምክንያት ቢኖረው ነው ብለን በእርግጠኝነት መናገር የምንችለው ለምንድን ነው?

9 በሰው ልጆች ላይ እየደረሰ ላለው መከራ መንስኤው አምላክ እንዳልሆነ ማወቃችን ያጽናናናል። የሰው ልጆችን ለሥቃይ እየዳረገ ላለው ጦርነት፣ ወንጀል፣ ጭቆና ብሎም የተፈጥሮ አደጋ ተጠያቂው እሱ አይደለም። ይሁንና ይሖዋ ይህ ሁሉ መከራ እንዲደርስ የፈቀደበትን ምክንያት ማወቅ ያስፈልገናል። ሁሉን ቻይ ከሆነ ይህን መከራ ማስቆም የሚችልበት ኃይል አለው ማለት ነው። ታዲያ እርምጃ ያልወሰደው ለምንድን ነው? አፍቃሪ የሆነው አምላካችን እርምጃ ያልወሰደው በቂ ምክንያት ቢኖረው ነው።—1 ዮሐንስ 4:8

አንድ ወሳኝ ጥያቄ ተነሳ

10. ሰይጣን ጥያቄ ያነሳው በምን ላይ ነው? እንዴትስ?

10 አምላክ በሰው ልጆች ላይ መከራ እንዲደርስ የፈቀደበትን ምክንያት ለማወቅ መከራ የጀመረበትን ጊዜ ወደ ኋላ መለስ ብለን ማሰብ ያስፈልገናል። ሰይጣን አዳምና ሔዋን በይሖዋ ላይ እንዲያምጹ ሲያደርግ አንድ ትልቅ ጥያቄ ተነስቷል። ሰይጣን በይሖዋ ኃይል ላይ ጥያቄ አላነሳም። ሌላው ቀርቶ የይሖዋ ኃይል ገደብ እንደሌለው ያውቃል። ከዚህ ይልቅ ሰይጣን ጥያቄ ያነሳው ይሖዋ ባለው የመግዛት መብት ላይ ነው። ይሖዋ ተገዥዎቹን መልካም ነገር የሚነፍግ ውሸታም አምላክ ነው በማለት ሰይጣን ይሖዋን መጥፎ ገዥ እንደሆነ አድርጎ ወንጅሎታል። (ዘፍጥረት 3:2-5) ሰይጣን ይህን ሲናገር የሰው ዘር ከአምላክ አገዛዝ ነፃ ቢሆን የተሻለ እንደሚሆን ማመልከቱ ነው። ይህ በይሖዋ ሉዓላዊነትና በመግዛት መብቱ ላይ የተሰነዘረ ጥቃት ነው።

11. ይሖዋ በኤደን ያመጹትን ወዲያውኑ ያላጠፋቸው ለምንድን ነው?

11 አዳምና ሔዋን በይሖዋ ላይ ዓመጹ። ‘ይሖዋ እንዲገዛን አንፈልግም። ጥሩና መጥፎ የሆነውን ነገር ራሳችን ለራሳችን መወሰን እንችላለን’  ያሉ ያህል ነበር። ይሖዋ ለዚህ ጉዳይ እልባት መስጠት የሚችለው እንዴት ነው? የማሰብ ችሎታ ያላቸው ፍጥረታቱ በሙሉ፣ ዓመጸኞቹ እንደተሳሳቱና የእሱ መንገድ ከሁሉ የተሻለ እንደሆነ እንዲገነዘቡ ማድረግ የሚችለው እንዴት ነው? አንዳንዶች አምላክ ዓመጸኞቹን በማጥፋት ሌሎች ሰዎችን መፍጠር ነበረበት ይሉ ይሆናል። ሆኖም ይሖዋ ምድርን በአዳምና ሔዋን ዘሮች ለመሙላት ዓላማ እንዳለው የገለጸ ሲሆን ዘሮቻቸው በምድራዊ ገነት ውስጥ እንዲኖሩ ይፈልግ ነበር። (ዘፍጥረት 1:28) ይሖዋ ምንጊዜም ዓላማውን የሚፈጽም አምላክ ነው። (ኢሳይያስ 55:10, 11) ከዚህም በተጨማሪ ዓመጸኞቹን ማጥፋት በይሖዋ የመግዛት መብት ላይ ለተነሳው ጥያቄ መልስ አያስገኝም።

12, 13. ይሖዋ፣ ሰይጣን የዚህ ዓለም ገዥ እንዲሆንና የሰው ልጆች ራሳቸውን እንዲገዙ የፈቀደው ለምን እንደሆነ በምሳሌ አስረዳ።

12 እስቲ አንድ ምሳሌ እንመልከት። አንድ አስተማሪ ተማሪዎቹ አንድን ውስብስብ የሆነ የሒሳብ ስሌት እንዴት መሥራት እንደሚቻል እየነገራቸው ነው እንበል። አንድ ጎበዝ ግን ዓመጸኛ የሆነ ተማሪ አስተማሪው ስሌቱን የሚሠራበት መንገድ የተሳሳተ እንደሆነ ይናገራል። ተማሪው፣ አስተማሪው ብቁ እንዳልሆነ ለማሳየት ስሌቱን በተሻለ መንገድ ሊሠራው እንደሚችል በመግለጽ ይከራከራል። አንዳንዶቹ ተማሪዎች ተማሪው ትክክል እንደሆነ በማሰብ እነሱም ያምጻሉ። በዚህ ጊዜ አስተማሪው ማድረግ ያለበት ነገር  ምንድን ነው? ዓመጸኞቹን ተማሪዎች ከክፍል ቢያባርር ሌሎቹ ተማሪዎች ምን ይሰማቸዋል? በአስተማሪው ላይ ያመጸው ተማሪም ሆነ ከእሱ ጋር ያበሩት ተማሪዎች ትክክል ናቸው ማለት ነው የሚል ስሜት አያድርባቸውም? በክፍሉ ውስጥ የቀሩት ተማሪዎች በሙሉ አስተማሪው እንዲህ ያለ እርምጃ የወሰደው መሳሳቱ እንዳይታወቅበት ብሎ ነው ብለው በማሰብ ለአስተማሪው ያላቸው አክብሮት ሊጠፋ ይችላል። ይሁን እንጂ አስተማሪው ዓመጸኛው ተማሪ ስሌቱን እንዴት ለመሥራት እንዳሰበ ለክፍሉ ተማሪዎች እንዲያሳይ ፈቀደለት እንበል።

ተማሪው ከመምህሩ የተሻለ ብቃት አለው?

13 ይሖዋ የወሰደው እርምጃ አስተማሪው ካደረገው ነገር ጋር ተመሳሳይ ነው። በኤደን ካመጹት በተጨማሪ ሁኔታውን የሚከታተሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ መላእክት እንደነበሩ አስታውስ። (ኢዮብ 38:7፤ ዳንኤል 7:10) ይሖዋ ከዓመጹ ጋር በተያያዘ የሚወስደው እርምጃ እነዚህን ሁሉ መላእክት ብሎም የማሰብ ችሎታ ያላቸውን ፍጥረታት በሙሉ በእጅጉ የሚነካ ነው። ታዲያ ይሖዋ ምን አደረገ? ሰይጣን የሰው ዘሮችን እንዴት እንደሚገዛ እንዲያሳይ ፈቀደለት። በተጨማሪም አምላክ የሰው ልጆች በሰይጣን አመራር ሥር ሆነው ራሳቸውን እንዲገዙ ፈቀደላቸው።

14. ይሖዋ የሰው ልጆች ራሳቸውን እንዲገዙ መፍቀዱ ምን ጥቅም አለው?

14 በምሳሌው ላይ የተጠቀሰው አስተማሪ፣ ዓመጸኛው ተማሪም ሆነ ከእሱ ጎን የወገኑት ተማሪዎች እንደተሳሳቱ ያውቃል። ይሁንና ያሰቡትን በተግባር እንዲያሳዩ አጋጣሚ መስጠቱ የክፍሉን ተማሪዎች በሙሉ እንደሚጠቅም ያውቃል። ዓመጸኞቹ ሳይሳካላቸው ሲቀር ሐቀኛ የሆኑት ተማሪዎች በሙሉ ክፍሉን የመምራት ብቃት ያለው መምህሩ ብቻ እንደሆነ ይገነዘባሉ። ከዚያ በኋላ አስተማሪው ማንኛውንም ዓመጸኛ ተማሪ ከክፍል የሚያባርርበት ምክንያት ግልጽ ይሆንላቸዋል። በተመሳሳይም ይሖዋ ቅን አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎችና መላእክት፣ ሰይጣንና በዓመጽ ድርጊቱ የተባበሩት ሁሉ እንዳልተሳካላቸውና ሰዎች ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር እንደማይችሉ መመልከታቸው በእጅጉ እንደሚጠቅማቸው ያውቃል። በጥንት ዘመን እንደነበረው እንደ ኤርምያስ የሚከተለውን መሠረታዊ የሆነ እውነት መገንዘብ እንዲችሉ ይረዳቸዋል:- “እግዚአብሔር ሆይ፤ የሰው ሕይወት በራሱ እጅ እንዳልሆነች፣ አካሄዱንም በራሱ አቃንቶ ሊመራ እንደማይችል ዐውቃለሁ።”—ኤርምያስ 10:23

 ይህን ያህል ረጅም ጊዜ የፈቀደው ለምንድን ነው?

15, 16. (ሀ) ይሖዋ መከራ ለረጅም ጊዜ እንዲቀጥል የፈቀደው ለምንድን ነው? (ለ) ይሖዋ አሰቃቂ ወንጀሎችም ሆኑ ሌሎች ችግሮች እንዳይደርሱ ያልተከላከለው ለምንድን ነው?

15 ይሁንና ይሖዋ መከራ ለረጅም ጊዜ እንዲቀጥል የፈቀደው ለምንድን ነው? መጥፎ ነገሮች እንዳይደርሱ የማይከላከለውስ ለምንድን ነው? በምሳሌው ላይ የተጠቀሰው አስተማሪ የማያደርጋቸውን ሁለት ነገሮች ተመልከት። በመጀመሪያ ደረጃ ዓመጸኛው ተማሪ ስሌቱን ለመሥራት የተሻለ ነው ብሎ ያሰበውን መንገድ ማብራራት ሲጀምር አያስቆመውም። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ተማሪው ራሱ ባሰበው መንገድ ስሌቱን ለመሥራት ሲሞክር አስተማሪው አይረዳውም። በተመሳሳይም ይሖዋ ላለማድረግ የወሰናቸውን ሁለት ነገሮች ተመልከት። በመጀመሪያ ደረጃ ሰይጣንና ከእሱ ጎን የወገኑት ሁሉ ትክክል መሆናቸውን ለማሳየት ሲሞክሩ አላስቆማቸውም። ይህ እንዲሆን ደግሞ ጊዜ ያስፈልጋል። ሰዎች ብዙ ሺህ ዓመታት ባስቆጠረው የሰው ዘር ታሪክ ሁሉንም ዓይነት ሰብዓዊ መስተዳድሮች መሞከር ችለዋል። የሰው ልጆች በሳይንስና በሌሎችም መስኮች አንዳንድ እመርታዎችን ያሳዩ ቢሆንም የፍትሕ መጓደል፣ ድህነት፣ ወንጀልና ጦርነት ከምንጊዜውም ይበልጥ እየተባባሱ ሄደዋል። ሰብዓዊው አገዛዝ እንዳልተሳካለት በግልጽ ታይቷል።

16 በሁለተኛ ደረጃ ሰይጣን ይህን ዓለም ለመግዛት ጥረት ሲያደርግ ይሖዋ ምንም ዓይነት እገዛ አላደረገለትም። ለምሳሌ ይሖዋ አሰቃቂ የሆኑ ወንጀሎች እንዳይደርሱ ቢከላከል ኖሮ በተዘዋዋሪ መንገድ ዓመጸኞቹን መደገፍ አይሆንበትም ነበር? አምላክ እንዲህ ቢያደርግ ኖሮ ሰዎች፣ የሰው ልጅ ምንም ዓይነት ጉዳት ሳይደርስበት ራሱን በራሱ ማስተዳደር ይችላል ማለት ነው የሚል አስተሳሰብ እንዲያድርባቸው አያደርግም? ይሖዋ እንዲህ ያለ እርምጃ ቢወስድ ኖሮ የውሸት ተባባሪ ይሆን ነበር። ሆኖም “እግዚአብሔር ከቶ ሊዋሽ አይችልም።”—ዕብራውያን 6:18

17, 18. ይሖዋ በሰው ልጆች አገዛዝና ሰይጣን ባሳደረው ተጽዕኖ ምክንያት ከደረሰው ጉዳት ጋር በተያያዘ ምን እርምጃ ይወስዳል?

17 ይሁንና የሰው ልጅ በአምላክ ላይ ካመጸ በኋላ ባለፉት ረጅም ዘመናት ውስጥ ስለደረሰው ጉዳትስ ምን ለማለት ይቻላል? ይሖዋ ሁሉን ቻይ መሆኑን ማስታወስ ይኖርብናል። ስለሆነም በሰው ዘር ላይ እየደረሰ ያለው መከራ ያስከተለውን ውጤት በሙሉ ማስወገድ ይችላል ደግሞም ያስወግዳል። ቀደም ሲል እንደተማርነው በፕላኔታችን ላይ የደረሰው ጥፋት  ተወግዶ ምድር ወደ ገነትነት ትለወጣለች። የኃጢአት ውጤቶች ጻድቃን ሰዎች በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ላይ በሚኖራቸው እምነት አማካኝነት የሚደመሰሱ ሲሆን ሞት ያስከተላቸው ውጤቶች ደግሞ በትንሣኤ አማካኝነት ይወገዳሉ። በዚህ መንገድ አምላክ ‘የዲያብሎስን ሥራ ለማፍረስ’ ኢየሱስን ይጠቀምበታል። (1 ዮሐንስ 3:8) ይሖዋ ይህን ሁሉ የሚያከናውነው በትክክለኛው ጊዜ ላይ ነው። ይሖዋ ቶሎ እርምጃ ባለመውሰዱ ደስተኞች ነን፤ እውነትን የመማርና እሱን የማገልገል አጋጣሚ ያገኘነው በመታገሱ ነው። (2 ጴጥሮስ 3:9, 10) በዚህ መካከል አምላክ ቅን ልብ ያላቸውን አምላኪዎች ሲፈልግና በችግር በተሞላው በዚህ ዓለም ውስጥ የሚደርስባቸውን መከራ ሁሉ እንዲቋቋሙ ሲረዳ ቆይቷል።—ዮሐንስ 4:23፤ 1 ቆሮንቶስ 10:13

18 አንዳንዶች፣ አምላክ አዳምንና ሔዋንን ማመጽ እንዳይችሉ አድርጎ ቢፈጥራቸው ኖሮ ይህ ሁሉ መከራ ሊወገድ አይችልም ነበር? ብለው ይጠይቁ ይሆናል። ይህን ጥያቄ ለመመለስ ይሖዋ የሰጠህን አንድ ውድ ስጦታ ማስታወስ ያስፈልግሃል።

ከአምላክ ያገኘኸውን ስጦታ የምትጠቀምበት እንዴት ነው?

አምላክ መከራን መቋቋም እንድትችል ይረዳሃል

19. ይሖዋ ምን ውድ ስጦታ ሰጥቶናል? ከፍ አድርገን ልንመለከተው የሚገባንስ ለምንድን ነው?

19 ምዕራፍ 5 ላይ እንደተገለጸው ሰዎች ሲፈጠሩ የመምረጥ ነፃነት ተሰጥቷቸዋል። ይህ ምን ያህል ውድ ስጦታ እንደሆነ ትገነዘባለህ? አምላክ ሥፍር ቁጥር የሌላቸውን እንስሳት የፈጠረ ሲሆን እነዚህ እንስሳት የሚንቀሳቀሱት በደመ ነፍስ ነው። የሰው ልጅ፣ የተሰጣቸውን መመሪያ ተከትለው የሚሠሩ ማሽኖች ወይም ሮቦቶች ሠርቷል። አምላክ በዚህ መንገድ ቢፈጥረን ኖሮ ደስ ይለን ነበር? በፍጹም፤ ምን ዓይነት ሰው መሆን እንደምንፈልግ፣ ምን ዓይነት የሕይወት ጎዳና እንደምንከተል፣ ምን ዓይነት ወዳጅነት መመሥረት እንደምንፈልግም ሆነ እነዚህን በመሰሉ ሌሎች ጉዳዮች የራሳችንን ምርጫ  የማድረግ ነፃነት የተሰጠን መሆኑ ያስደስተናል። የሰው ልጆች ስንባል በተፈጥሯችን በተወሰነ ደረጃ ነፃነት ማግኘት እንፈልጋለን፤ አምላክም እንዲህ ያለ ነፃነት እንዲኖረን ይፈልጋል።

20, 21. ይሖዋ የሰጠንን የመምረጥ ነፃነት ከሁሉ በተሻለ መንገድ ልንጠቀምበት የምንችለው እንዴት ነው? ይህን ማድረጋችን አስፈላጊ የሆነውስ ለምንድን ነው?

20 ይሖዋ በግዴታ የሚቀርብ አገልግሎት አያስደስተውም። (2 ቆሮንቶስ 9:7) ይህን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል:- አንድ ወላጅ ይበልጥ የሚደሰተው ልጁ ከልቡ ተገፋፍቶ “እወድሃለሁ” ቢለው ነው ወይስ ተገድዶ? ስለዚህ ይሖዋ የሰጠህን የመምረጥ ነፃነት እንዴት ትጠቀምበታለህ? የሚለውን ጥያቄ ማንሳቱ በጣም አስፈላጊ ነው። ሰይጣን፣ አዳምና ሔዋን የመምረጥ ነፃነታቸውን የተጠቀሙበት ከሁሉ በከፋ መንገድ ነው። ለይሖዋ አምላክ ለመገዛት አሻፈረን ብለዋል። አንተስ ምን ታደርግ ይሆን?

21 ያገኘኸውን ድንቅ የሆነ ስጦታ ማለትም የመምረጥ ነፃነትህን ከሁሉ በተሻለ መንገድ መጠቀም የምትችልበት አጋጣሚ አለህ። ይሖዋን ለመደገፍ ከመረጡት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ጎን መሰለፍ ትችላለህ። እነዚህ ሰዎች ሰይጣን ውሸታም እንደሆነና የሰው ልጆችን ለመግዛት ያደረገው ጥረት እንደከሸፈ በማረጋገጥ ረገድ ትልቅ ሚና የሚጫወቱ በመሆኑ የአምላክን ልብ ደስ ያሰኛሉ። (ምሳሌ 27:11) አንተም ትክክለኛውን የሕይወት ጎዳና በመምረጥ ይህን ማድረግ ትችላለህ። የሚቀጥለው ምዕራፍ ይህን ያብራራል።