ምዕራፍ አሥራ አምስት
አምላክ የሚቀበለው አምልኮ
ሁሉም ሃይማኖቶች አምላክን ያስደስታሉ?
እውነተኛውን ሃይማኖት ለይተን ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው?
በአሁኑ ጊዜ በምድር ላይ ያሉ እውነተኛዎቹ የአምላክ አገልጋዮች እነማን ናቸው?
1. አምላክን በትክክለኛው መንገድ ማምለካችን ምን ጥቅም ያስገኝልናል?
ይሖዋ አምላክ ከልብ የሚያስብልን በመሆኑ ከፍቅራዊ አመራሩ እንድንጠቀም ይፈልጋል። በትክክለኛው መንገድ የምናመልከው ከሆነ ደስተኞች እንሆናለን እንዲሁም በሕይወት ውስጥ ከሚያጋጥሙ ብዙ ችግሮች እንጠበቃለን። በተጨማሪም የእሱን በረከትና እርዳታ እናገኛለን። (ኢሳይያስ 48:17) ይሁን እንጂ ስለ አምላክ ትክክለኛውን ነገር እንደሚያስተምሩ የሚናገሩ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ሃይማኖቶች አሉ። ሆኖም ስለ አምላክ ማንነትም ሆነ እሱ ከእኛ ስለሚፈልገው ነገር የሚሰጡት ትምህርት በእጅጉ ይለያያል።
2. ይሖዋን ማምለክ የምንችልበትን ትክክለኛ መንገድ መማር የምንችለው እንዴት ነው? ይህን ለማስተዋል የሚረዳን ምሳሌስ የትኛው ነው?
2 ይሖዋን ማምለክ የሚቻልበትን ትክክለኛ መንገድ ማወቅ የምትችለው እንዴት ነው? ሁሉም ሃይማኖቶች የሚያስተምሯቸውን ትምህርቶች ማጥናትና ማወዳደር አያስፈልግህም። የሚያስፈልግህ መጽሐፍ ቅዱስ እውነተኛውን አምልኮ በተመለከተ የሚያስተምረውን ትክክለኛ ትምህርት ማወቅ ብቻ ነው። ይህን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል:- በብዙ አገሮች ውስጥ የሐሰት ገንዘብ አስመስሎ የመሥራት ችግር አለ። እንዲህ ያለውን የሐሰት ገንዘብ የመለየት ሥራ ቢሰጥህ ምን ታደርጋለህ? እያንዳንዱ የሐሰት ገንዘብ ምን እንደሚመስል በቃልህ ለማጥናት ትሞክራለህ? እንደዚያ አታደርግም። ከዚህ ይልቅ እውነተኛውን ገንዘብ ማጥናቱ ተመራጭ ነው። እውነተኛው ገንዘብ ምን እንደሚመስል በሚገባ ካጠናህ የሐሰት ገንዘብን መለየት ትችላለህ። በተመሳሳይም እውነተኛውን ሃይማኖት እንዴት ለይተን ማወቅ እንደምንችል ስንማር የሐሰት ሃይማኖቶችን መለየት እንችላለን።
3. ኢየሱስ በገለጸው መሠረት በአምላክ ፊት ተቀባይነት ማግኘት ከፈለግን ምን ማድረግ ይኖርብናል?
3 ይሖዋን እሱ በሚፈልገው መንገድ ማምለካችን በጣም አስፈላጊ ነው። ብዙ ሰዎች ሁሉም ሃይማኖቶች አምላክን የሚያስደስቱ ይመስላቸዋል፤ መጽሐፍ ቅዱስ ግን እንደዚያ ብሎ አያስተምርም። ሌላው ቀርቶ አንድ ሰው ክርስቲያን ነኝ ማለቱ ብቻ በቂ አይሆንም። ኢየሱስ “በሰማይ ያለውን ያባቴን ፈቃድ ሳይፈጽም ‘ጌታ ሆይ፤ ጌታ ሆይ፤’ የሚለኝ ሁሉ ወደ መንግሥተ ሰማይ አይገባም” ሲል ተናግሯል። ስለዚህ በአምላክ ፊት ተቀባይነት ለማግኘት አምላክ ከእኛ የሚፈልገውን ነገር ማወቅና ማድረግ ይኖርብናል። ኢየሱስ የአምላክን ፈቃድ የማያደርጉ ሰዎችን “ክፉዎች” ሲል ጠርቷቸዋል። (ማቴዎስ 7:21-23) ልክ እንደ ሐሰት ገንዘብ የሐሰት ሃይማኖትም እውነተኛ ዋጋ የለውም። እንዲያውም እንዲህ ያለው ሃይማኖት ጉዳት ያስከትላል።
4. ኢየሱስ ሁለቱን መንገዶች አስመልክቶ የተናገረው ቃል ምን ትርጉም አለው? መንገዶቹስ ወዴት ይመራሉ?
4 ይሖዋ በምድር ላይ ያለ እያንዳንዱ ሰው የዘላለም ሕይወት ማግኘት የሚችልበትን አጋጣሚ ከፍቷል። ይሁን እንጂ በገነት ለዘላለም ለመኖር አምላክን በትክክለኛው መንገድ ማምለክ ያለብን ከመሆኑም በላይ አኗኗራችን በእሱ ዘንድ ተቀባይነት ያለው መሆን ይኖርበታል። የሚያሳዝነው ብዙዎች እንዲህ ለማድረግ ፈቃደኞች አይደሉም። ኢየሱስ እንዲህ ሲል የተናገረው በዚህ ምክንያት ነው:- “በጠባቡ በር ግቡ፤ ወደ ጥፋት የሚወስደው መንገድ ትልቅ፣ በሩም ሰፊ ነውና፤ ብዙዎችም በዚያ ይገባሉ። ወደ ሕይወት የሚያደርሰው ግን መንገዱ ቀጭን፣ በሩም ጠባብ ነው፤ የሚገቡበትም ጥቂቶች ብቻ ናቸው።” (ማቴዎስ 7:13, 14) እውነተኛ ሃይማኖት ወደ ዘላለም ሕይወት ይመራል። ሐሰተኛ ሃይማኖት ግን ወደ ጥፋት ይወስዳል። ይሖዋ ማንም ሰው እንዲጠፋ አይፈልግም፤ በየትኛውም ቦታ የሚኖሩ ሰዎች ስለ እሱ መማር የሚችሉበትን አጋጣሚ የከፈተው ለዚህ ነው። (2 ጴጥሮስ 3:9) ስለዚህ አምላክን የምናመልክበት መንገድ ሕይወት ያስገኝልናል አሊያም ሞት ያስከትልብናል።
እውነተኛውን ሃይማኖት ለይቶ ማወቅ የሚቻልበት መንገድ
5. እውነተኛውን ሃይማኖት የሚከተሉ ሰዎችን እንዴት ለይተን ማወቅ እንችላለን?
5 ‘ወደ ሕይወት የሚያደርሰውን መንገድ’ ማግኘት የሚቻለው እንዴት ነው? ኢየሱስ እውነተኛው ሃይማኖት በተከታዮቹ ሕይወት ላይ በግልጽ እንደሚንጸባረቅ ተናግሯል። “ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ” ብሏል። “ጥሩ ዛፍ ሁሉ ጥሩ ፍሬ . . . ያፈራል።” (ማቴዎስ 7:16, 17) በሌላ አነጋገር እውነተኛውን ሃይማኖት የሚከተሉ ሰዎች በእምነታቸውና በምግባራቸው ተለይተው ይታወቃሉ ማለት ነው። እውነተኛ አምላኪዎች ፍጽምና የሌላቸውና የሚሳሳቱ ቢሆኑም እንኳ በቡድን ደረጃ የአምላክን ፈቃድ ለመፈጸም ጥረት ያደርጋሉ። እስቲ እውነተኛውን ሃይማኖት የሚከተሉ ሰዎች ተለይተው የሚታወቁባቸውን ስድስት ገጽታዎች እንመልከት።
6, 7. የአምላክ አገልጋዮች መጽሐፍ ቅዱስን በተመለከተ ምን አመለካከት አላቸው? ኢየሱስ በዚህ ረገድ ጥሩ ምሳሌ የተወውስ እንዴት ነው?
6 የአምላክ አገልጋዮች ትምህርቶቻቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ እንዲህ ይላል:- “ቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለባቸው ናቸው፤ ለማስተማር፣ ለመገሠጽ፣ ለማቅናት በጽድቅም መንገድ ለመምከር ይጠቅማሉ፤ ይኸውም የእግዚአብሔር ሰው ለመልካም ሥራ ሁሉ ብቁ ሆኖ እንዲገኝ ነው።” (2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17) ሐዋርያው ጳውሎስ ለክርስቲያን ባልንጀሮቹ ‘ከእኛ የሰማችሁትን የእግዚአብሔር ቃል በተቀበላችሁ ጊዜ፣ እንደ እግዚአብሔር ቃል እንጂ እንደ ሰው ቃል አድርጋችሁ አልተቀበላችሁትም’ ሲል ጽፏል። (1 ተሰሎንቄ 2:13) ስለዚህ የእውነተኛው ሃይማኖት እምነቶችና ልማዶች በሰብዓዊ አመለካከት ወይም ወግ ላይ የተመሠረቱ አይደሉም። ከዚህ ይልቅ በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት በተጻፈው ቃሉ ማለትም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ናቸው።
7 ኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርቶቹ በአምላክ ቃል ላይ የተመሠረቱ እንዲሆኑ በማድረግ ጥሩ ምሳሌ ትቷል። ለሰማያዊ አባቱ ባቀረበው ጸሎት ላይ “ቃልህ እውነት ነው” ሲል ተናግሯል። (ዮሐንስ 17:17) ኢየሱስ በአምላክ ቃል ያምን የነበረ ከመሆኑም በላይ ያስተማረው ትምህርት በሙሉ ከቅዱሳን ጽሑፎች ጋር የሚስማማ ነበር። ብዙውን ጊዜ ጥቅስ በመጥቀስ እንዲህ “ተብሎ ተጽፎአል” እያለ ይናገር ነበር። (ማቴዎስ 4:4, 7, 10) በተመሳሳይም ዛሬ ያሉ የአምላክ አገልጋዮች የራሳቸውን ሐሳብ አያስተምሩም። መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል እንደሆነ የሚያምኑ ሲሆን ትምህርቶቻቸውም ሙሉ በሙሉ በቃሉ ላይ የተመሠረቱ ናቸው።
8. ይሖዋን ማምለክ ምን ነገርን ይጨምራል?
8 እውነተኛውን ሃይማኖት የሚከተሉ ሰዎች ይሖዋን ብቻ የሚያመልኩ ከመሆኑም በላይ ስሙን ያስታውቃሉ። ኢየሱስ “ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ስገድ፤ እርሱንም ብቻ አምልክ” ሲል ተናግሯል። (ማቴዎስ 4:10) በመሆኑም የአምላክ አገልጋዮች ይሖዋን ብቻ ያመልካሉ። ይህ አምልኮ የእውነተኛው አምላክ ስም ማን እንደሆነና ምን ባሕርያት እንዳሉት ለሰዎች ማሳወቅን ይጨምራል። መዝሙር 83:18 “ስምህ እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] የሆነው አንተ ብቻ በምድር ሁሉ ላይ ልዑል [ነህ]” ይላል። ኢየሱስ “ለእነዚህ ከዓለም ለሰጠኸኝ ሰዎች ስምህን ገልጬላቸዋለሁ” በማለት በጸሎቱ ላይ እንደገለጸው ሌሎች አምላክን እንዲያውቁ በመርዳት ረገድ ግሩም ምሳሌ ትቷል። (ዮሐንስ 17:6) በተመሳሳይም ዛሬ ያሉ እውነተኛ አምላኪዎች ሌሎችን ስለ አምላክ ስም፣ ስለ ዓላማዎቹና ስለ ባሕርያቱ ያስተምራሉ።
9, 10. እውነተኛ ክርስቲያኖች አንዳቸው ለሌላው ፍቅር የሚያሳዩት በምን መንገዶች ነው?
9 የአምላክ አገልጋዮች አንዳቸው ለሌላው ከልብ የመነጨና ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር ያሳያሉ። ኢየሱስ “እርስ በርሳችሁ ብትዋደዱ፣ ሰዎች ሁሉ የእኔ ደቀ መዛሙርት እንደ ሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ” ሲል ተናግሯል። (ዮሐንስ 13:35) የጥንቶቹ ክርስቲያኖች እርስ በርሳቸው እንዲህ ያለ ፍቅር ነበራቸው። በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ የተመሠረተው ፍቅር ከዘር፣ ከማኅበራዊ ኑሮና ከብሔር ጋር የተያያዙ እንቅፋቶችን በመወጣት ሰዎችን በማይበጠስ የእውነተኛ ወንድማማችነት ማሰሪያ ያስተሳስራቸዋል። (ቈላስይስ 3:14) የሐሰት ሃይማኖት አባላት እንዲህ ያለ የወንድማማች ፍቅር የላቸውም። ይህን እንዴት እናውቃለን? በብሔር ወይም በጎሣ ልዩነቶች ሳቢያ እርስ በርስ ይገዳደላሉ። እውነተኛ ክርስቲያኖች ክርስቲያን ወንድሞቻቸውንም ሆነ ማንኛውንም ሰው ለመግደል የጦር መሣሪያ አያነሱም። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ሲል ይገልጻል:- “የእግዚአብሔር ልጆችና የዲያብሎስ ልጆች ተለይተው የሚታወቁት በዚህ ነው:- ጽድቅን የማያደርግ፣ ወንድሙንም የማይወድ ሁሉ ከእግዚአብሔር አይደለም። . . . እርስ በርሳችን ልንዋደድ ይገባናል . . . የክፉው ወገን ሆኖ ወንድሙን እንደ ገደለው እንደ ቃየን አትሁኑ።”—1 ዮሐንስ 3:10-12፤ 4:20, 21
10 እርግጥ ነው፣ ከልብ የመነጨ ፍቅር ማሳየት ሲባል ሌሎችን ከመግደል መቆጠብ ማለት ብቻ አይደለም። እውነተኛ ክርስቲያኖች ጊዜያቸውን፣ ጉልበታቸውንና ሀብታቸውን ምንም ሳይሰስቱ እርስ በርሳቸው ይረዳዳሉ እንዲሁም ይበረታታሉ። (ዕብራውያን 10:24, 25) በመከራ ጊዜ እርስ በርሳቸው ይደጋገፋሉ፤ በተጨማሪም ከሌሎች ጋር ባላቸው ግንኙነት ሐቀኞች ናቸው። እንዲያውም “ለሰው ሁሉ . . . መልካም እናድርግ” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር በሕይወታቸው ውስጥ ተግባራዊ ያደርጋሉ።—ገላትያ 6:10
11. አምላክ እኛን ለመታደግ ኢየሱስ ክርስቶስን አዳኝ አድርጎ እንደሚጠቀምበት አምኖ መቀበል አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
11 እውነተኛ ክርስቲያኖች አምላክ እኛን ለመታደግ ኢየሱስ ክርስቶስን አዳኝ አድርጎ እንደሚጠቀምበት ያምናሉ። መጽሐፍ ቅዱስ “ድነት በሌላ በማንም አይገኝም፤ እንድንበት ዘንድ ለሰዎች የተሰጠ ከዚህ ስም በስተቀር ሌላ ስም ከሰማይ በታች የለምና” ይላል። (የሐዋርያት ሥራ 4:12) ምዕራፍ 5 ላይ እንደተመለከትነው ኢየሱስ ታዛዥ ለሆኑ የሰው ልጆች ሕይወቱን ቤዛ አድርጎ ሰጥቷል። (ማቴዎስ 20:28) ከዚህም በተጨማሪ አምላክ ኢየሱስን መላዋን ምድር በሚገዛው ሰማያዊ መንግሥት ላይ ንጉሥ አድርጎ ሾሞታል። የዘላለም ሕይወት እናገኝ ዘንድ ኢየሱስን እንድንታዘዝና ትምህርቶቹን ተግባራዊ እንድናደርግ ይፈልጋል። መጽሐፍ ቅዱስ “በወልድ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት አለው፤ በወልድ የማያምን ግን . . . ሕይወትን አያይም” የሚለው ለዚህ ነው።—ዮሐንስ 3:36
12. የዓለም ክፍል አለመሆን ምን ነገርን ይጨምራል?
12 እውነተኛ አምላኪዎች የዓለም ክፍል አይደሉም። ኢየሱስ በሮማዊው ገዥ በጲላጦስ ፊት ለፍርድ በቀረበ ጊዜ “የእኔ መንግሥት ከዚህ ዓለም አይደለም” ሲል ተናግሯል። (ዮሐንስ 18:36) የኢየሱስ እውነተኛ ተከታዮች የትም አገር ይኑሩ የት በሰማይ የሚገኘው መንግሥቱ ተገዥዎች በመሆናቸው ከዓለም ፖለቲካዊ ጉዳዮች ሙሉ በሙሉ ገለልተኞች ናቸው። በዓለም ላይ በሚካሄዱት ግጭቶች በምንም መልኩ አይሳተፉም። ይሁን እንጂ የፖለቲካ ፓርቲ አባል ከመሆን፣ ለምርጫ ከመወዳደር ወይም ድምፅ ከመስጠት ጋር በተያያዘ ሌሎች በሚያደርጉት ውሳኔ ጣልቃ አይገቡም። የአምላክ እውነተኛ አምላኪዎች ከፖለቲካ ገለልተኞች ቢሆኑም እንኳ ሕግ አክባሪዎች ናቸው። ለምን? የአምላክ ቃል ‘በሥልጣን ላይ ላሉት ሹማምንት እንዲገዙ’ ስለሚያዛቸው ነው። (ሮሜ 13:1) አምላክ በሚፈልግባቸውና የፖለቲካው ሥርዓት በሚፈልግባቸው ነገር መካከል ግጭት ሲፈጠር “ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል” ያሉትን ሐዋርያት ምሳሌ ይከተላሉ።—የሐዋርያት ሥራ 5:29፤ ማርቆስ 12:17
13. የኢየሱስ እውነተኛ ተከታዮች የአምላክን መንግሥት በተመለከተ ምን አመለካከት አላቸው? ስለሆነም ምን ያደርጋሉ?
13 የኢየሱስ እውነተኛ ተከታዮች የሰው ዘር ብቸኛ ተስፋ የአምላክ መንግሥት እንደሆነ ይሰብካሉ። ኢየሱስ “ለሕዝብ ሁሉ ምስክር እንዲሆን፣ ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፤ ከዚያም መጨረሻው ይመጣል” ሲል ተንብዮአል። (ማቴዎስ 24:14) የኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ ተከታዮች ሰዎች ለችግሮቻቸው መፍትሔ ለማግኘት በሰብዓዊ ገዥዎች ላይ እንዲታመኑ ከማበረታታት ይልቅ ለሰው ዘር ብቸኛው ተስፋ የአምላክ ሰማያዊ መንግሥት እንደሆነ ያውጃሉ። (መዝሙር 146:3) ኢየሱስ “መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነች፣ እንዲሁ በምድር ትሁን” ብላችሁ ጸልዩ በማለት ይህ ፍጹም የሆነ መንግሥት እንዲመጣ መጸለይ እንዳለብን አስተምሮናል። (ማቴዎስ 6:10) የአምላክ ቃል ይህ ሰማያዊ መንግሥት “እነዚያን [አሁን ያሉትን] መንግሥታት ሁሉ ያደቃል፤ እስከ መጨረሻውም ያጠፋቸዋል፤ ይህ መንግሥት ራሱ ግን ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል” ሲል አስቀድሞ ተንብዮአል።—ዳንኤል 2:44
14. የእውነተኛውን አምልኮ መሥፈርቶች የሚያሟላው የትኛው ሃይማኖት ነው ብለህ ታምናለህ?
14 እስካሁን በተመለከትናቸው ነጥቦች ላይ ተመርኩዘህ ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ:- ‘ትምህርቶቹ ሁሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱና የይሖዋን ስም የሚያስታውቅ ሃይማኖት የትኛው ነው? ይሖዋ ባስተማረን መንገድ ፍቅርን የሚያንጸባርቅ፣ በኢየሱስ ላይ እምነት እንዳለው የሚያሳይ፣ የዚህ ዓለም ክፍል ያልሆነና የሰው ዘር ብቸኛ እውነተኛ ተስፋ የአምላክ መንግሥት እንደሆነ የሚያውጅ ሃይማኖት የትኛው ነው? በምድር ላይ ካሉት ሃይማኖቶች ሁሉ እነዚህን መሥፈርቶች በሙሉ የሚያሟላው ሃይማኖት የትኛው ነው?’ መረጃዎቹ በግልጽ እንደሚያሳዩት እነዚህን መሥፈርቶች የሚያሟሉት የይሖዋ ምሥክሮች ናቸው።—ኢሳይያስ 43:10-12
ምን እርምጃ ትወስዳለህ?
15. አምላክ በእሱ መኖር ከማመን በተጨማሪ ምን እንድናደርግ ይፈልጋል?
15 አምላክን ለማስደሰት በእሱ ማመን ብቻ በቂ አይደለም። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ አጋንንት እንኳ ሳይቀሩ በአምላክ መኖር እንደሚያምኑ ይናገራል። (ያዕቆብ 2:19) ሆኖም የአምላክን ፈቃድ እንደማያደርጉና በአምላክ ፊት ተቀባይነት እንደሌላቸው የታወቀ ነው። የአምላክን ሞገስ ለማግኘት አምላክ እንዳለ ማመን ብቻ ሳይሆን ፈቃዱንም ማድረግ አለብን። በተጨማሪም ከሐሰት ሃይማኖት መላቀቅና እውነተኛውን አምልኮ መቀበል አለብን።
16. በሐሰት ሃይማኖት መካፈልን በተመለከተ ምን ማድረግ ይኖርብናል?
16 ሐዋርያው ጳውሎስ በሐሰት አምልኮ መካፈል እንደሌለብን ገልጿል። “ከመካከላቸው ውጡ፤ ለእኔም የተለያችሁ ሁኑ፤ ይላል ጌታ። ርኩስ የሆነውን ነገር አትንኩ፤ እኔም እቀበላችኋለሁ” ሲል ጽፏል። (2 ቆሮንቶስ 6:17፤ ኢሳይያስ 52:11) በመሆኑም እውነተኛ ክርስቲያኖች ከሐሰት አምልኮ ጋር ንክኪ ያለውን ማንኛውንም ነገር ያስወግዳሉ።
17, 18. “ታላቂቱ ባቢሎን” ምንድን ናት? ‘ከእርሷ መውጣቱ’ አጣዳፊ የሆነውስ ለምንድን ነው?
17 መጽሐፍ ቅዱስ ሁሉም ዓይነት የሐሰት ሃይማኖቶች ‘የታላቂቱ ባቢሎን’ ክፍል እንደሆኑ ይገልጻል። * (ራእይ 17:5) ይህ ስያሜ በኖኅ ዘመን ከደረሰው የጥፋት ውኃ በኋላ የሐሰት ሃይማኖት የተቋቋመባትን የጥንቷን የባቢሎን ከተማ ያስታውሰናል። በአሁኑ ጊዜ በሐሰት ሃይማኖት ውስጥ ያሉት ብዙዎቹ ትምህርቶችና ልማዶች የመነጩት ከጥንቷ ባቢሎን ነው። ለምሳሌ ያህል ባቢሎናውያን ሥላሴዎችን ወይም አንድም ሦስትም የሆኑ አማልክትን ያመልኩ ነበር። ዛሬ የብዙዎቹ ሃይማኖቶች ዋነኛ ትምህርት ሥላሴ ነው። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ እውነተኛው አምላክ ይሖዋ ብቻ እንደሆነና ኢየሱስ ክርስቶስ ልጁ መሆኑን በግልጽ ያስተምራል። (ዮሐንስ 17:3) በተጨማሪም ባቢሎናውያን፣ የሰው ልጆች ከሞቱ በኋላ ከሥጋ ተለይታ በሕይወት የምትቀጥል የማትሞት ነፍስ እንዳለቻቸውና ይህች ነፍስ በመሠቃያ ሥፍራ ውስጥ ልትሠቃይ እንደምትችል ያምኑ ነበር። ዛሬም አብዛኞቹ ሃይማኖቶች በእሳታማ ሲኦል ውስጥ ልትሠቃይ የምትችል የማትሞት ነፍስ ወይም መንፈስ አለች ብለው ያስተምራሉ።
18 የጥንቷ ባቢሎን አምልኮ በመላዋ ምድር ላይ ስለተስፋፋ ዘመናዊቷ ታላቂቱ ባቢሎን የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት እንደሆነች በትክክል ለይቶ ማወቅ ይቻላል። አምላክ ይህች የሐሰት ሃይማኖት ግዛት በድንገት እንደምትጠፋ ተንብዮአል። (ራእይ 18:8) ከየትኛውም የታላቂቱ ባቢሎን ክፍል መለየትህ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ አስተዋልክ? ይሖዋ አምላክ ጊዜው ሳያልፍብህ በፊት በአስቸኳይ ‘ከእርሷ እንድትወጣ’ ይፈልጋል።—ራእይ 18:4
19. ይሖዋን ማገልገልህ ምን ጥቅም ያስገኝልሃል?
19 ከሐሰት ሃይማኖት ለመውጣት በምታደርገው ውሳኔ ሳቢያ አንዳንዶች ከአንተ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ሊያቋርጡ ይችላሉ። ይሁን እንጂ ይሖዋን ከሕዝቡ ጋር ማገልገልህ ልታጣው ከምትችለው ነገር ሁሉ እጅግ የላቀ በረከት ያስገኝልሃል። ሌሎች ነገሮችን ትተው ኢየሱስን እንደተከተሉት የጥንቶቹ ደቀ መዛሙርት አንተም ብዙ መንፈሳዊ ወንድሞችና እህቶች ታገኛለህ። ከልብ የመነጨ ፍቅር የሚያሳዩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ እውነተኛ ክርስቲያኖችን የያዘው ዓለም አቀፍ የሆነ ትልቅ ቤተሰብ አባል ትሆናለህ። በተጨማሪም ‘በሚመጣው ዓለም’ አስደሳች የሆነውን የዘላለም ሕይወት ተስፋ ታገኛለህ። (ማርቆስ 10:28-30) ምናልባትም በእምነትህ ምክንያት የራቁህ ሰዎች ውለው አድረው መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረውን ትምህርት ሊመረምሩና የይሖዋ አምላኪዎች ሊሆኑ ይችላሉ።
20. እውነተኛውን ሃይማኖት የሚከተሉ ሰዎች ወደፊት ምን ተስፋ ይጠብቃቸዋል?
20 መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ በቅርቡ ይህን ክፉ ሥርዓት በማጥፋት በመንግሥቱ አገዛዝ በሚተዳደርና ጽድቅ በሚሰፍንበት አዲስ ዓለም እንደሚተካው ይናገራል። (2 ጴጥሮስ 3:9, 13) ያ ዓለም ምንኛ አስደናቂ ይሆናል! ጽድቅ በሚሰፍንበት በዚያ አዲስ ዓለም ውስጥ አንድ ሃይማኖት ወይም አንድ እውነተኛ አምልኮ ብቻ ይኖራል። አሁኑኑ ከእውነተኛ አምላኪዎች ጋር ለመቀላቀል አስፈላጊ የሆኑ እርምጃዎችን መውሰድህ ጥበብ አይሆንም?
^ አን.17 ታላቂቱ ባቢሎን የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛትን የምትወክልበትን ምክንያት በተመለከተ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በገጽ 219-220 ላይ የሚገኘውን ተጨማሪ ክፍል ተመልከት።