በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ተጨማሪ ክፍል

አብን፣ ወልድንና መንፈስ ቅዱስን በተመለከተ እውነታው ምንድን ነው?

አብን፣ ወልድንና መንፈስ ቅዱስን በተመለከተ እውነታው ምንድን ነው?

በሥላሴ ትምህርት የሚያምኑ ሰዎች አምላክ የአብ፣ የወልድና የመንፈስ ቅዱስ ጥምረት ነው ይላሉ። እነዚህ ሦስቱ እያንዳንዳቸው ከሌላው ጋር እኩል ናቸው፣ ሁሉን ቻይ ናቸው እንዲሁም መጀመሪያ የላቸውም ተብሎ ይነገራል። ስለዚህ በሥላሴ መሠረተ ትምህርት መሠረት አብ እግዚአብሔር ነው፣ ወልድ እግዚአብሔር ነው እንዲሁም መንፈስ ቅዱስ እግዚአብሔር ነው፤ ሆኖም እግዚአብሔር አንድ ነው።

 በሥላሴ የሚያምኑ ብዙ ሰዎች ይህን ትምህርት በግልጽ ማስረዳት እንደማይችሉ ያምናሉ። ያም ሆኖ መጽሐፍ ቅዱስ የሥላሴን መሠረተ ትምህርት እንደሚያስተምር ይሰማቸው ይሆናል። “ሥላሴ” የሚለው ቃል ጨርሶ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደማይገኝ ሊስተዋል ይገባል። ይሁንና የሥላሴ ጽንሰ ሐሳብ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይገኛል? ለዚህ ጥያቄ መልስ ለማግኘት የዚህ ትምህርት አማኞች የሥላሴን ጽንሰ ሐሳብ ለመደገፍ ብዙውን ጊዜ የሚጠቅሱትን አንድ ጥቅስ እስቲ እንመልከት።

“ቃልም እግዚአብሔር ነበረ”

ዮሐንስ 1:1 “በመጀመሪያ ቃል ነበረ፤ ቃልም ከእግዚአብሔር ጋር ነበረ፤ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ” ይላል። ሐዋርያው ዮሐንስ “ቃል” ኢየሱስ እንደሆነ በዚሁ ምዕራፍ ላይ በግልጽ አመልክቷል። (ዮሐንስ 1:14) ይሁን እንጂ ቃል እግዚአብሔር ተብሎ ስለተጠራ አንዳንዶች ወልድና አብ የአንድ አምላክ ክፍሎች መሆን አለባቸው ብለው ያስባሉ።

ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በመጀመሪያ የተጻፈው በግሪክኛ እንደሆነ አስታውስ። ከጊዜ በኋላ ተርጓሚዎች ግሪክኛውን ጽሑፍ ወደ ሌሎች ቋንቋዎች ተረጎሙት። ይሁን እንጂ በርከት ያሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች “ቃልም እግዚአብሔር ነበረ” የሚለውን ሐረግ አልተጠቀሙም። ለምን? እነዚህ ተርጓሚዎች መጽሐፍ ቅዱስ ስለተጻፈበት የግሪክኛ ቋንቋ ባላቸው እውቀት ላይ በመመርኮዝ “ቃልም እግዚአብሔር ነበረ” የሚለው ሐረግ ለየት ባለ መንገድ መተርጎም አለበት የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል። ታዲያ መተርጎም ያለበት ምን ተብሎ ነው? ከዚህ ቀጥሎ ጥቂት ምሳሌዎች ቀርበዋል:- “ሎጎስ [ቃል] መለኮታዊ ነበር።” (ኤ ኒው ትራንስሌሽን ኦቭ ዘ ባይብል) “ቃል አምላክ (a god) ነበር።” (ዘ ኒው ቴስታመንት ኢን አን ኢምፕሩቭድ ቨርሽን) “ቃል ከእግዚአብሔር ጋር ነበር እንዲሁም ተመሳሳይ ባሕርይ ነበረው።” (ዘ ትራንስሌተርስ ኒው ቴስታመንት) ከእነዚህ ትርጉሞች መረዳት እንደምንችለው ቃል እግዚአብሔር (God) ራሱ አይደለም። * ከዚህ ይልቅ ቃል በይሖዋ ፍጥረታት መካከል ባለው ከፍተኛ ቦታ የተነሳ “አምላክ (a god)” ተብሎ ተጠርቷል። እዚህ ላይ “አምላክ” የሚለው ቃል “ኃያል” ማለት ነው።

ተጨማሪ መረጃዎች ተመልከት

አብዛኞቹ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈበትን የግሪክኛ ቋንቋ አያውቁም። ታዲያ ሐዋርያው ዮሐንስ በእርግጥ ምን ማለቱ እንደሆነ ማወቅ የምትችለው እንዴት ነው? የሚከተለውን ምሳሌ ተመልከት:- አንድ አስተማሪ አንድን ርዕሰ ጉዳይ  ለተማሪዎቹ ያስረዳቸዋል። በኋላ ተማሪዎቹ በተማሩት ትምህርት ላይ የሐሳብ ልዩነት ፈጠሩ እንበል። ተማሪዎቹ የተፈጠረውን የሐሳብ ልዩነት መፍታት የሚችሉት እንዴት ነው? አስተማሪው ተጨማሪ መረጃዎች እንዲሰጣቸው ሊጠይቁት ይችላሉ። ተጨማሪ መረጃዎች ማግኘታቸው ርዕሰ ጉዳዩ ይበልጥ ግልጽ እንዲሆንላቸው እንደሚረዳቸው ጥርጥር የለውም። በተመሳሳይም የዮሐንስ 1:1ን ትርጉም ለመረዳት የኢየሱስን ቦታ አስመልክቶ የዮሐንስ ወንጌል የሚሰጣቸውን ተጨማሪ መረጃዎች መመልከት ትችላለህ። ከዚህ ርዕሰ ጉዳይ ጋር የተያያዙ ተጨማሪ መረጃዎች ማግኘትህ ትክክለኛ መደምደሚያ ላይ እንድትደርስ ይረዳሃል።

ለምሳሌ ያህል ሐዋርያው ዮሐንስ፣ ምዕራፍ 1 ቁጥር 18 ላይ ምን ተጨማሪ ቃል እንደጻፈ ተመልከት:- “ከቶውንም እግዚአብሔርን [ሁሉን ቻይ የሆነውን አምላክ] ያየ ማንም የለም።” ይሁን እንጂ ዮሐንስ “ቃልም [ኢየሱስ] ሥጋ ሆነ፤ በመካከላችንም አደረ፤ . . . [ክብሩንም] አየን” በማለት ስለተናገረ ሰዎች ኢየሱስን ማለትም ወልድን አይተውታል። (ዮሐንስ 1:14) ታዲያ ወልድ እንዴት ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ክፍል ሊሆን ይችላል? በተጨማሪም ዮሐንስ ቃል “ከእግዚአብሔር ጋር” ነበረ ሲል ገልጿል። ሆኖም አንድ ግለሰብ ከአንድ ሰው ጋር እያለ እንዴት ያንኑ ሰው ሊሆን ይችላል? ከዚህም በላይ ዮሐንስ 17:3 [የ1980 ትርጉም] ላይ ተመዝግቦ እንደሚገኘው ኢየሱስ ራሱንና ሰማያዊ አባቱን በግልጽ ለይቶ አስቀምጧል። አባቱን ‘ብቸኛው እውነተኛ አምላክ’ ሲል ጠርቶታል። እንዲሁም ዮሐንስ በወንጌሉ መገባደጃ አካባቢ “ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ፣ የእግዚአብሔርም ልጅ እንደሆነ ታምኑ ዘንድ . . . ይህ ተጽፎአል” ሲል ነጥቡን ጠቅለል አድርጎ ገልጾታል። (ዮሐንስ 20:31) ኢየሱስ እግዚአብሔር ሳይሆን የእግዚአብሔር ልጅ ተብሎ መጠራቱን ልብ በል። በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ የሠፈረው ይህ ተጨማሪ መረጃ ዮሐንስ 1:1 ላይ የተገለጸውን ሐሳብ እንዴት ልንረዳው እንደሚገባ ያሳያል። ኢየሱስ ማለትም ቃል “አምላክ (a god)” ነው የተባለው ካለው የላቀ ቦታ አንጻር እንጂ ሁሉን ቻይ ከሆነው አምላክ ጋር አንድ ሆኖ አይደለም።

መረጃዎቹን አረጋግጥ

ስለ አስተማሪውና ስለ ተማሪዎቹ የሚገልጸውን ምሳሌ በድጋሚ ተመልከት። አንዳንዶቹ ተማሪዎች አስተማሪው የሰጠውን ተጨማሪ ማብራሪያ ከሰሙም በኋላ ያደረባቸው ጥርጣሬ ሙሉ በሙሉ አልተወገደም እንበል። በዚህ ጊዜ ምን ሊያደርጉ ይችላሉ? ሌላ አስተማሪ በዚያው ርዕሰ ጉዳይ ላይ ተጨማሪ መረጃ እንዲሰጣቸው ሊጠይቁ ይችላሉ። ሁለተኛው አስተማሪ የመጀመሪያው አስተማሪ የሰጣቸው ማብራሪያ ትክክል መሆኑን ካረጋገጠላቸው አብዛኞቹ ተማሪዎች አድሮባቸው የነበረው ጥርጣሬ ሊወገድላቸው ይችላል። በተመሳሳይም የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የሆነው ዮሐንስ በኢየሱስና ሁሉን ቻይ በሆነው አምላክ መካከል ያለውን  ዝምድና አስመልክቶ ስለሰጠው ሐሳብ እርግጠኛ መሆን ካልቻልክ ከሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ ተጨማሪ መረጃ ልትፈልግ ትችላለህ። ለምሳሌ ያህል ማቴዎስ የጻፈውን ቃል ተመልከት። ማቴዎስ የዚህን ሥርዓት ፍጻሜ አስመልክቶ ኢየሱስ የተናገረውን በመጥቀስ እንዲህ ብሏል:- “ያን ቀንና ሰዓት ግን ከአብ በስተቀር የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ፣ ወልድም ቢሆን ማንም አያውቅም።” (ማቴዎስ 24:36) እነዚህ ቃላት ኢየሱስ ሁሉን ቻይ አምላክ እንዳልሆነ የሚያረጋግጡት እንዴት ነው?

ኢየሱስ አብ ከወልድ ይበልጥ እንደሚያውቅ ተናግሯል። ኢየሱስ ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ክፍል ቢሆን ኖሮ ግን አባቱ የሚያውቀውን ነገር ሁሉ ያውቅ ነበር። ስለዚህ ወልድና አብ እኩል ሊሆኑ አይችሉም። ይሁን እንጂ አንዳንዶች ‘ኢየሱስ ሁለት ዓይነት ባሕርይ ነበረው። እዚህ ላይ ያለውን የተናገረው ሰው ሆኖ ነው’ ይላሉ። ሆኖም እነሱ እንደሚሉት እንኳ ቢሆን ስለ መንፈስ ቅዱስስ ምን ሊባል ነው? መንፈስ ቅዱስ እንደ አብ የአንድ አምላክ ክፍል ከሆነ ኢየሱስ፣ አብ የሚያውቀውን ሁሉ መንፈስ ቅዱስም ያውቃል ለምን አላለም?

መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትህን በቀጠልክ መጠን ከዚህ ርዕሰ ጉዳይ ጋር ዝምድና ያላቸውን ሌሎች በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባቦች ታገኛለህ። እነዚህ ምንባቦች ስለ አብ፣ ስለ ወልድና ስለ መንፈስ ቅዱስ እውነታውን ያረጋግጡልሃል።—መዝሙር 90:2፤ የሐዋርያት ሥራ 7:55፤ ቈላስይስ 1:15

^ አን.3 ዮሐንስ 1:1ን በተመለከተ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን የኅዳር 1, 2008 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 24-25ን ተመልከት።