በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አምላክን ማስደሰት ትችላለህ

አምላክን ማስደሰት ትችላለህ

አምላክን ማስደሰት ትችላለህ

በአምላክ ስሜት ላይ ለውጥ ማምጣት እንችላለን? ደግሞስ አምላክ የደስታ ስሜት አለው? አንድ መዝገበ ቃላት “አምላክ” የሚለውን ቃል “ከሁሉ በላይ የሆነ ህላዌ” በማለት ተርጉሞታል። ይህ ህላዌ እንዲያው ኃይል ብቻ ቢሆንስ? አንድ አካል የሌለው ኃይል ሊደሰት ይችላል? እንደማይችል የታወቀ ነው። እስቲ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አምላክ ምን እንደሚል እንመልከት።

ኢየሱስ ክርስቶስ “እግዚአብሔር መንፈስ ነው” በማለት ተናግሯል። (ዮሐንስ 4:24) መንፈስ ከሰው የተለየ የሕይወት ዓይነት ነው። መንፈስ ለሰው የማይታይ ቢሆንም “መንፈሳዊ” አካል አለው። (1 ቆሮንቶስ 15:44፤ ዮሐንስ 1:18) እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌያዊ አነጋገር በመጠቀም አምላክ ዓይን፣ ጆሮ፣ እጅና እነዚህን የመሳሰሉ አካላት እንዳሉት አድርጎ ይናገራል። a በተጨማሪም አምላክ ይሖዋ የሚል ስም አለው። (መዝሙር 83:18 NW) በመሆኑም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰው አምላክ መንፈሳዊ አካል ነው ማለት ነው። (ዕብራውያን 9:24) “እርሱ ሕያው አምላክ፣ ዘላለማዊም ንጉሥ ነው።”—ኤርምያስ 10:10

ይሖዋ ሕያው አካል ያለው አምላክ እንደመሆኑ ማሰብና የተለያዩ ድርጊቶችን ማከናወን ይችላል። ባሕርያትና ስሜቶች እንዲሁም የሚወዳቸውና የሚጠላቸው ነገሮች አሉት። እንዲያውም አምላክን ስለሚያስደስቱት ወይም ስለሚያሳዝኑት ነገሮች የሚናገሩ መግለጫዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በብዛት ይገኛሉ። ሰዎች የሠሯቸው አማልክትና ጣዖታት አላቸው የሚባልላቸው ባሕርይ ወይም ጠባይ ከሠሪዎቻቸው የወረሱት ሲሆን ቀድሞውኑ እነዚህን ስሜቶች በሰዎች ላይ የቀረጸው ግን ሁሉን ቻይ የሆነው ይሖዋ አምላክ ነው።—ዘፍጥረት 1:27፤ ኢሳይያስ 44:7-11

ይሖዋ “ደስተኛ አምላክ” ለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም። (1 ጢሞቴዎስ 1:11 NW) በፈጠራቸው ነገሮች ብቻ ሳይሆን ዓላማውን ከግብ በማድረሱም ይደሰታል። ይሖዋ በነቢዩ ኢሳይያስ በኩል “ደስ የሚያሰኘኝንም ሁሉ አደርጋለሁ . . . የተናገርሁትን አደርጋለሁ፤ ያቀድሁትን እፈጽማለሁ” ብሏል። (ኢሳይያስ 46:9-11) መዝሙራዊው “እግዚአብሔር በሥራው ደስ ይበለው” ሲል ዘምሯል። (መዝሙር 104:31) ይሁን እንጂ ይሖዋን የሚያስደስተው ሌላም ነገር አለ። “ልጄ ሆይ፤ ጠቢብ ሁን፤ ልቤን ደስ አሰኘው” በማለት ተናግሯል። (ምሳሌ 27:11) ይህ ምን ማለት እንደሆነ አስብ! አምላክን ማስደሰት እንችላለን ማለት ነው።

አምላክን ማስደሰት የምንችልበት መንገድ

የቤተሰብ ራስ የነበረው ኖኅ አምላክን ደስ ያሰኘው እንዴት እንደሆነ እንመልከት። ኖኅ “በዘመኑ ከነበሩት ሰዎች ሁሉ ይልቅ ጻድቅና ከበደል የራቀ ሰው” ስለነበር “በእግዚአብሔር ዘንድ ሞገስን አገኘ።” በጊዜው ከነበሩት ሰዎች ፍጹም በተለየ ሁኔታ ኖኅ ያሳየው እምነትና ታዛዥነት አምላክን የሚያስደስት ስለነበር “አካሄዱንም ከእግዚአብሔር ጋር አደረገ” ሊባልለት ችሏል። (ዘፍጥረት 6:6, 8, 9, 22) ኖኅ “እግዚአብሔርን ፈርቶ ቤተ ሰዎቹን ለማዳን መርከብን በእምነት ሠራ።” (ዕብራውያን 11:7) ይሖዋ በኖኅ ስለተደሰተ ሁከት በነገሰበት በዚያ ዘመን እርሱና ቤተሰቡ በሕይወት እንዲተርፉ በማድረግ ባርኮታል።

የቤተሰብ ራስ የነበረው አብርሃምም የይሖዋን አስተሳሰብ ጠንቅቆ ያውቅ ነበር። ይሖዋ ሰዶምንና ገሞራን በወራዳ ድርጊታቸው ምክንያት እንደሚያጠፋቸው ሲነግረው ስለ አምላክ አስተሳሰብ የነበረው ጥልቅ እውቀት በግልጽ ታይቷል። አብርሃም ይሖዋን በሚገባ ያውቀው ስለነበር ጻድቁን ከኃጢአተኛው ጋር እንደማያጠፋ በእርግጠኝነት ለመናገር ችሎ ነበር። (ዘፍጥረት 18:17-33) ከዓመታት በኋላም አምላክ ልጁን እንዲሠዋለት በነገረው ጊዜ ‘እግዚአብሔር ከሙታን እንኳ ሊያስነሳው እንዲቻለው ስላሰበ’ ይስሐቅን መሥዋዕት አድርጎ ለማቅረብ አላመነታም። (ዕብራውያን 11:17-19 የ1954 ትርጉም፤ ዘፍጥረት 22:1-18) አብርሃም የአምላክን ስሜት ጠንቅቆ በማወቁና እንዲህ ያለ ጠንካራ እምነትና ታዛዥነት በማሳየቱ “የእግዚአብሔር ወዳጅ” ለመባል በቅቷል።—ያዕቆብ 2:23

የአምላክን ልብ ለማስደሰት ይጥር የነበረው ሌላው ሰው የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ የነበረው ዳዊት ነው። ይሖዋ እርሱን በሚመለከት “እንደ ልቤ የሆነና እኔ የምሻውን ሁሉ የሚያደርግ የእሴይን ልጅ ዳዊትን አገኘሁ” በማለት ተናግሯል። (የሐዋርያት ሥራ 13:22) ዳዊት ከጎልያድ ጋር ፍልሚያ ከመግጠሙ በፊት ሙሉ ትምክህቱን በአምላክ ላይ ያደረገ ሲሆን የእስራኤል ንጉሥ የነበረው ሳኦልን “ከአንበሳ መዳፍና ከድብ መንጋጋ ያዳነኝ እግዚአብሔር አሁንም ከዚህ ፍልስጥኤማዊ እጅ ያድነኛል” ብሎታል። ይሖዋ፣ ዳዊት በእርሱ ላይ የነበረውን ትምክህት የባረከለት ሲሆን ጎልያድን እንዲገድለው ረድቶታል። (1 ሳሙኤል 17:37, 45-54) ዳዊት ድርጊቶቹ ብቻ ሳይሆኑ ‘የአፉ ቃልና የልቡ ሐሳብ፣ [በይሖዋ] ፊት ያማረ እንዲሆን’ ይፈልግ ነበር።—መዝሙር 19:14

እኛስ ይሖዋን ማስደሰት እንችላለን? የአምላክን አስተሳሰብ ይበልጥ ባወቅን መጠን እርሱን ለማስደሰት ምን ማድረግ እንደምንችል እየተገነዘብን እንሄዳለን። እንግዲያው መጽሐፍ ቅዱስን ስናነብ ‘የፈቃዱን ዕውቀት በመንፈሳዊ ጥበብና መረዳት ሁሉ ተሞልተን ለጌታ እንደሚገባ እንድንኖርና በሁሉም ደስ እንድናሰኘው’ ስለ አምላክ አስተሳሰብ ለማወቅ ጥረት ማድረጋችን አስፈላጊ ነው። (ቆላስይስ 1:9, 10) ይህ እውቀት በተራው እምነት እንድናዳብር ይረዳናል። ‘ያለ እምነት እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት ስለማይቻል’ እምነት ማዳበራችን የግድ አስፈላጊ ነው። (ዕብራውያን 11:6) አዎን፣ ጠንካራ እምነት ለመገንባት ጥረት በማድረግና ከይሖዋ ፈቃድ ጋር ተስማምተን በመኖር ልቡን ደስ ማሰኘት እንችላለን። ከዚህ ጎን ለጎን የይሖዋን ልብ ላለማሳዘን ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብናል።

አምላክን ላለማሳዘን ተጠንቀቅ

ይሖዋ ምን ያህል ቅር ሊሰኝ እንደሚችል የሚያሳይ ምሳሌ ስለ ኖኅ ዘመን በሚናገረው ታሪክ ውስጥ እናገኛለን። ዘገባው እንዲህ ይላል “ምድር . . . በዐመጽም ተሞላች። እግዚአብሔር ምድር ምን ያህል በክፉ ሥራ እንደረከሰች አየ፤ እነሆ፤ ሰው ሁሉ አካሄዱን አበላሽቶ ነበርና።” አምላክ በምድር ላይ የነበረውን ዓመጽና ወራዳ ድርጊት ሲመለከት ምን ተሰማው? መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔር ሰውን በምድር ላይ በመፍጠሩ ተጸጸተ፤ ልቡም እጅግ አዘነ” ይላል። (ዘፍጥረት 6:5, 6, 11, 12) አምላክ መጸጸቱ የሰዎች ምግባር ይበልጥ እየከፋ በመሄዱ ከጥፋት ውኃ በፊት ለነበረው ዓለም ያለውን አመለካከት መቀየሩን ያሳያል። በክፋት ድርጊታቸው በማዘኑ ምክንያት በፈጣሪነቱ ለእነርሱ የነበረው አመለካከት ተለውጦ ሊያጠፋቸው ወስኗል።

ይሖዋ ሕዝቡ የነበረው የጥንቱ የእስራኤል ብሔር ስሜቶቹንና ፍቅራዊ አመራሩን በተደጋጋሚ ቸል ባሉ ጊዜም አዝኖ ነበር። መዝሙራዊው “በምድረ በዳ ስንት ጊዜ ዐመፁበት! በበረሓስ ምን ያህል አሳዘኑት! ደግመው ደጋግመው እግዚአብሔርን ተፈታተኑት፤ የእስራኤልንም ቅዱስ አስቆጡት” በማለት ሐዘኑን ገልጿል። ቢሆንም “እርሱ ግን መሓሪ እንደ መሆኑ፣ በደላቸውን ይቅር አለ፤ አላጠፋቸውም፤ ቁጣውን ብዙ ጊዜ ገታ፤ መዓቱንም ሁሉ አላወረደም።” (መዝሙር 78:38-41) ዓመጸኞቹ እስራኤላውያን በኃጢአታቸው ምክንያት ለመከራ በተዳረጉ ጊዜም እንኳ መጽሐፍ ቅዱስ “በጭንቃቸው ሁሉ ተጨነቀ” በማለት ይናገራል።—ኢሳይያስ 63:9

ይሖዋ ለእነርሱ የነበረውን ጥልቅ አሳቢነት የሚያሳዩ በቂ ማስረጃዎችን ቢመለከቱም የእስራኤል ሕዝብ “የእግዚአብሔር ቁጣ በሕዝቡ ላይ እስኪነሣሣና ፈውስም እስከማይገኝላቸው ድረስ በእግዚአብሔር መልእክተኞች ላይ ተሳለቁ፤ ቃሉን ናቁ፤ ነቢያቱንም አቃለሉ።” (2 ዜና መዋዕል 36:16) አንገታቸውን አደንድነው በዓመጻቸው በመግፋታቸው “ቅዱስ መንፈሱንም አሳዘኑ፤” በዚህም የተነሳ ሞገሱን እስከወዲያኛው አጡ። (ኢሳይያስ 63:10) ይህ ምን አስከተለባቸው? አምላክ ያደርግላቸው የነበረውን ጥበቃ ያነሳ ሲሆን ባቢሎናውያን መጥተው ይሁዳን በማረኩና ኢየሩሳሌምን ባጠፉ ጊዜ ለከፋ ችግር ተዳረጉ። (2 ዜና መዋዕል 36:17-21) ሰዎች አምላክን የሚያስቆጣና የሚያሳዝን የኃጢአት አካሄድ ሲከተሉ ውጤቱ ምንኛ የሚያሳዝን ይሆናል!

አምላክ ተገቢ ያልሆነ ድርጊት ሲመለከት በጥልቅ እንደሚያዝን መጽሐፍ ቅዱስ በማያሻማ ሁኔታ ያሳያል። (መዝሙር 78:41) አምላክ ከሚያዝንባቸው እንዲያውም ከሚጠላቸው ነገሮች መካከል ኩራት፣ ውሸት፣ ነፍስ ማጥፋት፣ አስማት፣ ጥንቆላ፣ የቀድሞ አባቶችን ማምለክ፣ ልቅ ሥነ ምግባር፣ ግብረ ሰዶም፣ ለትዳር ጓደኛ ታማኝ አለመሆን፣ በቅርብ ዘመዳሞች መካከል የሚፈጸም የጾታ ግንኙነትና ድሆችን መጨቆን ይገኙበታል።—ዘሌዋውያን 18:9-29፤ 19:29፤ ዘዳግም 18:9-12፤ ምሳሌ 6:16-19፤ ኤርምያስ 7:5-7፤ ሚልክያስ 2:14-16

ይሖዋ የጣዖት አምልኮን በሚመለከት ምን ይሰማዋል? ዘፀአት 20:4, 5 እንዲህ ይላል “በላይ በሰማይ ወይም በታች በምድር ካለው ወይም በውሃ ውስጥ ከሚኖሩት ነገሮች በማናቸውም ምስል ለራስህ ጣዖትን አታብጅ። አትስገድላቸው፤ አታምልካቸውም።” ለምን? ምክንያቱም ጣዖት “በእግዚአብሔር ዘንድ አስጸያፊ ስለ ሆነ” ነው። (ዘዳግም 7:25, 26) ሐዋርያው ዮሐንስ “ልጆች ሆይ፤ ራሳችሁን ከጣዖቶች ጠብቁ” በማለት አስጠንቅቋል። (1 ዮሐንስ 5:21) ሐዋርያው ጳውሎስ ደግሞ “ወዳጆቼ ሆይ፤ ከጣዖት አምልኮ ሽሹ” ሲል ጽፏል።—1 ቆሮንቶስ 10:14

የአምላክን ሞገስ ለማግኘት ጥረት አድርግ

አምላክ ‘ወዳጅነቱ ከቅኖች ጋር ነው።’ “በመንገዳቸው ነቀፋ በሌለባቸው ሰዎች . . . ደስ ይሰኛል።” (ምሳሌ 3:32 የ1954 ትርጉም፤ 11:20) በተቃራኒው ሆነ ብለው የጽድቅ አቋሙን ችላ በሚሉ ወይም በሚጥሱ ሰዎች ላይ በቅርቡ ቁጣውን ያወርድባቸዋል። (2 ተሰሎንቄ 1:6-10) አዎን፣ በቅርቡ በጊዜያችን ተስፋፍቶ የሚገኘውን ክፋት በሙሉ ያስወግዳል።—መዝሙር 37:9-11፤ ሶፎንያስ 2:2, 3

ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ “ማንም እንዳይጠፋ . . . ፣ ሁሉ ለንስሓ እንዲበቃ” እንደሚፈልግ በግልጽ ይናገራል። (2 ጴጥሮስ 3:9) ለመለወጥ ፈቃደኛ ባልሆኑ ሰዎች ላይ ቁጣውን ከሚገልጥ ይልቅ ለሚወዱት ጻድቅ ሰዎች ፍቅሩን ቢያሳይ ይመርጣል። ይሖዋ የሚደሰተው ‘ክፉዎች ከመንገዳቸው ተመልሰው በሕይወት ሲኖሩ እንጂ ሲሞቱ’ አይደለም።—ሕዝቅኤል 33:11

ስለዚህ ይሖዋ ማንም የቁጣው ዒላማ እንዲሆን አይፈልግም። እርሱ “እጅግ ርኅሩኅና መሓሪ ነው።” (ያዕቆብ 5:11) ‘እርሱ ስለ አንተ ስለሚያስብ’ በአምላክ ስሜት ሙሉ በሙሉ በመተማመን ‘የሚያስጨንቅህን ሁሉ በእርሱ ላይ መጣል’ ትችላለህ። (1 ጴጥሮስ 5:7) የአምላክን ልብ ደስ የሚያሰኙ ሰዎች የእርሱን ሞገስና ወዳጅነት እንደሚያገኙ እርግጠኛ ሁን። እንግዲያው ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ‘ጌታን ደስ የሚያሰኘውን መፈለግ’ ያለብን አሁን ነው።—ኤፌሶን 5:10

ይሖዋ ይገባናል በማንለው ደግነቱ ግሩም ባሕርያቱንና ስሜቶቹን የገለጠልን መሆኑ በጣም ያስደስታል! ደግሞም እርሱን ማስደሰት ከአቅምህ በላይ አይደለም። የአምላክን ልብ ደስ ማሰኘት የምትፈልግ ከሆነ በአቅራቢያህ ከሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች ጋር እንድትገናኝ እናበረታታሃለን። አምላክን ለማስደሰት ጠቃሚና ተግባራዊ ሆነው ያገኟቸውን መንገዶች ሊነግሩህ ፈቃደኛ ናቸው።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a “መጽሐፍ ቅዱስ አምላክን ሰብዓዊ አካል እንዳለው አድርጐ የሚገልጸው ለምንድን ነው?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

መጽሐፍ ቅዱስ አምላክን ሰብዓዊ አካል እንዳለው አድርጐ የሚገልጸው ለምንድን ነው?

“እግዚአብሔር መንፈስ ነው፤” ስለዚህ በዓይናችን ልናየው አንችልም። (ዮሐንስ 4:24) ስለሆነም መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክን ኃይልና ክብር እንዲሁም ሥራዎቹን ለመረዳት እንድንችል ተነጻጻሪና (simile) ተለዋጭ (metaphor) የሚባሉ ዘይቤዎች የሚጠቀም ሲሆን አንዳንድ ጊዜም የሰውን የአካል ክፍሎች ይጠቀማል። በመሆኑም የአምላክ መንፈሳዊ አካል ምን እንደሚመስል ባናውቅም መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ዓይን፣ ጆሮ፣ እጅ፣ ክንድ፣ ጣት፣ እግርና ልብ እንዳለው አድርጎ ይናገራል።—ዘፍጥረት 8:21፤ ዘፀአት 3:20 የ1954 ትርጉም፤ 31:18፤ ኢዮብ 40:9፤ መዝሙር 18:9፤ 34:15

እንዲህ ሲባል ግን የአምላክ መንፈሳዊ አካል ልክ ሰዎች ያላቸው ዓይነት የሰውነት ክፍል አለው ማለት አይደለም። እንዲህ ያለው ዘይቤያዊ አነጋገር ቃል በቃል የሚወሰድ ሳይሆን ሰዎች ስለ አምላክ የተሻለ ግንዛቤ እንዲያገኙ ተብሎ የሚሠራበት መግለጫ ነው። እንዲህ ዓይነቱን ዘይቤ ሳይጠቀሙ ስለ አምላክ ለሰዎች ለማስረዳት ፈጽሞ የማይቻል ባይሆንም እንኳ አስቸጋሪ ነው። ይሁን እንጂ ይህ ማለት የይሖዋ አምላክ ባሕርያት በሰዎች የተፈጠሩ ናቸው ማለት አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ እንደሚያሳየው ሰው በአምላክ አምሳል ተፈጠረ እንጂ አምላክ በሰው አምሳል አልተፈጠረም። (ዘፍጥረት 1:27) የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ቅዱሳን ጽሑፎችን የጻፉት ‘በአምላክ መንፈስ’ ተነሳስተው ስለሆነ ስለ አምላክ ባሕርያት የጻፏቸው ሐሳቦች አምላክ ስለራሱ ባሕርያት የሰጣቸው መግለጫዎች ናቸው ሊባል ይችላል። አምላክ እነዚህ ባሕርያቱ በሰብዓዊ ፍጡራኑ ላይ በተለያየ መጠን እንዲንጸባረቁ አድርጓል። (2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17) የሰዎች ባሕርይ በአምላክ ላይ እየተንጸባረቀ ሳይሆን ሰዎች የአምላክን ባሕርያት እየኮረጁ ነው።

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኖኅ በአምላክ ዘንድ ሞገስ አግኝቶ ነበር

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አብርሃም የአምላክን አስተሳሰብ ጠንቅቆ ያውቅ ነበር

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዳዊት ሙሉ በሙሉ በይሖዋ ታምኖ ነበር

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብ አምላክን እንዴት ማስደሰት እንደሚቻል መማር ትችላለህ

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

Courtesy of Anglo-Australian Observatory, photograph by David Malin