ዘዳግም 7:1-26

  • መጥፋት ያለባቸው ሰባት ብሔራት (1-6)

  • እስራኤላውያን የተመረጡበት ምክንያት (7-11)

  • ታዛዥነት በረከት ያስገኛል (12-26)

7  “አምላክህ ይሖዋ ርስት አድርገህ ወደምትወርሳት ምድር ሲያመጣህ+ ብዙ ሕዝብ ያላቸውን ብሔራት ይኸውም ከአንተ ይልቅ ብዙ ሕዝብ ያላቸውንና ኃያላን የሆኑትን ሰባት ብሔራት+ ማለትም ሂታውያንን፣ ገርጌሻውያንን፣ አሞራውያንን፣+ ከነአናውያንን፣ ፈሪዛውያንን፣ ሂዋውያንን እና ኢያቡሳውያንን+ ከፊትህ ያስወግድልሃል።+  አምላክህ ይሖዋ እነሱን አሳልፎ ይሰጥሃል፤ ድልም ታደርጋቸዋለህ።+ አንተም ሙሉ በሙሉ ደምስሳቸው።+ ከእነሱ ጋር ምንም ዓይነት ቃል ኪዳን አትጋባ፤ አትራራላቸውም።+  ከእነሱ ጋር በጋብቻ አትዛመድ። ሴቶች ልጆችህን ለወንዶች ልጆቻቸው አትዳር ወይም ሴቶች ልጆቻቸውን ለወንዶች ልጆችህ አትውሰድ።+  ምክንያቱም ልጆችህ ሌሎች አማልክትን ያገለግሉ ዘንድ እኔን ከመከተል ዞር እንዲሉ ያደርጓቸዋል፤+ ከዚያም የይሖዋ ቁጣ በእናንተ ላይ ይነድዳል፤ አንተንም ወዲያው ያጠፋሃል።+  “ከዚህ ይልቅ እንዲህ አድርጉባቸው፦ መሠዊያዎቻቸውን አፈራርሱ፤ የማምለኪያ ዓምዶቻቸውን ሰባብሩ፤+ የማምለኪያ ግንዶቻቸውን* ቆራርጡ፤+ የተቀረጹ ምስሎቻቸውንም በእሳት አቃጥሉ።+  ምክንያቱም አንተ ለአምላክህ ለይሖዋ ቅዱስ ሕዝብ ነህ፤ አምላክህ ይሖዋ በምድር ላይ ካሉ ሕዝቦች ሁሉ መካከል አንተን የራሱ ሕዝብ፣ ልዩ ንብረቱ* እንድትሆን መርጦሃል።+  “ይሖዋ እናንተን የወደዳችሁና የመረጣችሁ+ ከሌሎች ሕዝቦች ሁሉ ይልቅ ቁጥራችሁ ስለበዛ አይደለም፤ ቁጥራችሁማ ከሌሎች ሕዝቦች ሁሉ አነስተኛ ነበር።+  ከዚህ ይልቅ ይሖዋ እናንተን ከባርነት ቤት ይኸውም ከግብፅ ንጉሥ ከፈርዖን እጅ ይታደጋችሁ ዘንድ ይሖዋ በብርቱ እጅ ያወጣችሁ+ ስለወደዳችሁና ለአባቶቻችሁ የማለላቸውን መሐላ ስለጠበቀ ነው።+  አንተም አምላክህ ይሖዋ እውነተኛ አምላክ፣ ታማኝ አምላክ እንዲሁም ለሚወዱትና ትእዛዛቱን ለሚጠብቁ ሁሉ እስከ ሺህ ትውልድ ድረስ ቃል ኪዳኑን የሚጠብቅና ታማኝ ፍቅር የሚያሳይ መሆኑን በሚገባ ታውቃለህ።+ 10  የሚጠሉትን ግን በማጥፋት በግልጽ ይበቀላቸዋል።+ በሚጠሉት ላይ እርምጃ ለመውሰድ አይዘገይም፤ በግልጽ ይበቀላቸዋል። 11  ስለዚህ እኔ ዛሬ የማዝህን ትእዛዛት፣ ሥርዓቶችና ድንጋጌዎች በማክበር በጥንቃቄ ጠብቃቸው። 12  “እነዚህን ድንጋጌዎች ብትሰሙና ብትጠብቋቸው እንዲሁም ብትፈጽሟቸው አምላካችሁ ይሖዋ ለአባቶቻችሁ በመሐላ የገባውን ቃል ኪዳንና ታማኝ ፍቅር ይጠብቃል። 13  ይወድሃል፣ ይባርክሃል እንዲሁም ያበዛሃል። አዎ፣ ለአንተ ሊሰጥህ ለአባቶችህ በማለላቸው ምድር ላይ የሆድህን ፍሬ፣+ የመሬትህን ምርት፣ እህልህን፣ አዲሱን የወይን ጠጅህን፣ ዘይትህን፣+ የከብቶችህን ጥጆችና የመንጋህን ግልገሎች ይባርክልሃል።+ 14  አንተም ከሕዝቦች ሁሉ ይበልጥ የተባረክ ትሆናለህ፤+ በመካከልህ ልጅ የሌለው ወንድ ወይም ሴት አይገኝም፤ እንስሶችህም ግልገል የሌላቸው አይሆኑም።+ 15  ይሖዋ በሽታን ሁሉ ያስወግድልሃል፤ በግብፅ ሳለህ ታውቃቸው ከነበሩት አሰቃቂ በሽታዎች አንዱንም በአንተ ላይ አያመጣም።+ ከዚህ ይልቅ በሚጠሉህ ሁሉ ላይ ያመጣባቸዋል። 16  አምላክህ ይሖዋ አሳልፎ የሚሰጥህን ሕዝቦች ሁሉ ታጠፋለህ።+ አትዘንላቸው፤*+ አማልክታቸውንም አታገልግል፤+ ምክንያቱም እንዲህ ማድረግህ ወጥመድ ይሆንብሃል።+ 17  “ምናልባት በልብህ ‘እነዚህ ብሔራት እኮ ከእኛ ይልቅ ብዙ ናቸው። ታዲያ እንዴት ላባርራቸው እችላለሁ?’ ትል ይሆናል፤+ 18  ሆኖም አትፍራቸው።+ አምላክህ ይሖዋ በፈርዖንና በግብፅ ሁሉ ላይ ያደረገውን አስታውስ፤+ 19  ዓይኖችህ ያዩአቸውን ታላላቅ የፍርድ እርምጃዎች* እንዲሁም አምላክህ ይሖዋ አንተን ለማውጣት የተጠቀመባቸውን ድንቅ ምልክቶች፣ ተአምራት፣+ ብርቱ እጅና የተዘረጋ ክንድ አስብ።+ አምላክህ ይሖዋ በምትፈራቸው ሕዝቦች ሁሉ ላይ የሚያደርገው ይህንኑ ነው።+ 20  አምላክህ ይሖዋ በሕይወት የተረፉትና ከፊትህ የተሸሸጉት እስኪጠፉ ድረስ ጭንቀት* ይለቅባቸዋል።+ 21  ታላቅና የሚያስፈራ አምላክ+ የሆነው አምላክህ ይሖዋ ከአንተ ጋር ስለሆነ+ በእነሱ የተነሳ አትሸበር። 22  “አምላክህ ይሖዋ እነዚህን ብሔራት በጥቂት በጥቂቱ ከፊትህ ያባርራቸዋል።+ የዱር አራዊት እንዳይበዙብህ በአንድ ጊዜ ጠራርገህ እንድታጠፋቸው አይፈቀድልህም። 23  አምላክህ ይሖዋ እነሱን በእጅህ አሳልፎ ይሰጥሃል፤ እስኪጠፉም ድረስ ሙሉ በሙሉ ድል ታደርጋቸዋለህ።+ 24  እሱም ነገሥታታቸውን በእጅህ አሳልፎ ይሰጥሃል፤+ አንተም ስማቸውን ከሰማይ በታች ትደመስሳለህ።+ ድምጥማጣቸውን እስክታጠፋ+ ድረስ ማንም አይቋቋምህም።+ 25  የአማልክታቸውን የተቀረጹ ምስሎች በእሳት አቃጥሉ።+ ወጥመድ ሊሆንብህ ስለሚችል በእነሱ ላይ ያለውን ብርም ሆነ ወርቅ አትመኝ ወይም ለራስህ አትውሰድ፤+ ምክንያቱም ይህ በአምላክህ በይሖዋ ፊት አስጸያፊ ነገር ነው።+ 26  አስጸያፊ ነገር ወደ ቤትህ በማምጣት ልክ እንደ እሱ ራስህን ለጥፋት አትዳርግ። ለጥፋት የተለየ ነገር ስለሆነ ፈጽመህ ጥላው፤ ሙሉ በሙሉም ተጸየፈው።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ውድ ሀብቱ።”
ቃል በቃል “ዓይንህ አይዘንላቸው።”
ወይም “ፈተናዎች።”
“ድንጋጤ፤ ሽብር” ማለትም ሊሆን ይችላል።