መዝሙር 18:1-50

  • ዳዊት፣ አምላክ ስላዳነው ያቀረበው ውዳሴ

    • “ይሖዋ ቋጥኜ” ነው (2)

    • ይሖዋ ታማኝ ለሆነ ሰው ታማኝ ነው (25)

    • የአምላክ መንገድ ፍጹም ነው (30)

    • ‘ትሕትናህ ታላቅ ያደርገኛል’ (35)

ለሙዚቀኞች ቡድን መሪ። የይሖዋ አገልጋይ የሆነው ዳዊት፣ ይሖዋ ከጠላቶቹ ሁሉ እጅና ከሳኦል እጅ ባዳነው ቀን ለይሖዋ የዘመረው መዝሙር፦+ 18  ብርታቴ ይሖዋ ሆይ፣+ እወድሃለሁ።  2  ይሖዋ ቋጥኜ፣ ምሽጌና ታዳጊዬ ነው።+ አምላኬ የምሸሸግበት ዓለቴ ነው፤+ጋሻዬ፣ የመዳኔ ቀንድና* አስተማማኝ መጠጊያዬ ነው።+  3  ውዳሴ የሚገባውን ይሖዋን እጠራለሁ፤ከጠላቶቼም እድናለሁ።+  4  የሞት ገመዶች ተተበተቡብኝ፤+የማይረቡ ሰዎች የለቀቁት ድንገተኛ ጎርፍ አሸበረኝ።+  5  የመቃብር* ገመድ ተጠመጠመብኝ፤የሞት ወጥመድ ተጋረጠብኝ።+  6  በጭንቅ ውስጥ ሳለሁ ይሖዋን ጠራሁት፤እርዳታ ለማግኘት አምላኬን አጥብቄ ተማጸንኩት። በመቅደሱ ሆኖ ድምፄን ሰማ፤+እርዳታ ለማግኘት የማሰማውም ጩኸት ወደ ጆሮው ደረሰ።+  7  ምድርም ትንቀጠቀጥና ትናወጥ ጀመር፤+የተራሮች መሠረቶች ተንቀጠቀጡ፤እሱ ስለተቆጣም ራዱ።+  8  ከአፍንጫው ጭስ ወጣ፤የሚባላም እሳት ከአፉ ወጣ፤+ፍምም ከእሱ ፈለቀ።  9  ወደ ታች ሲወርድ ሰማያት እንዲያጎነብሱ አደረገ፤+ከእግሮቹም በታች ጥቅጥቅ ያለ ደመና ነበር።+ 10  በኪሩብ ላይ ተቀምጦ እየበረረ መጣ።+ በመንፈስ* ክንፎች በፍጥነት ወረደ።+ 11  ከዚያም በጨለማ ራሱን ሸፈነ፤+ጥቁር ውኃና ጥቅጥቅ ያለ ደመና+እንደ መጠለያ በዙሪያው ነበር። 12  በፊቱ ካለው ብርሃን፣ከደመናቱ መካከል በረዶና ፍም ወጣ። 13  ከዚያም ይሖዋ በሰማያት ያንጎደጉድ ጀመር፤+ልዑሉ አምላክ ድምፁን አሰማ፤+ደግሞም በረዶና ፍም ነበር። 14  ፍላጻዎቹን አስፈንጥሮ በታተናቸው፤+መብረቁን አዥጎድጉዶ ግራ አጋባቸው።+ 15  ይሖዋ ሆይ፣ ከተግሣጽህ፣ ከአፍንጫህም ከሚወጣው ኃይለኛ እስትንፋስ የተነሳ+የጅረቶች ወለል ታየ፤*+የምድር መሠረቶችም ተገለጡ። 16  ከላይ ሆኖ እጁን ሰደደ፤ከጥልቅ ውኃ ውስጥም አወጣኝ።+ 17  ከብርቱ ጠላቴ አዳነኝ፤+ከእኔ ይበልጥ ብርቱዎች ከሆኑት፣ ከሚጠሉኝ ሰዎች ታደገኝ።+ 18  ችግር ላይ በወደቅኩበት ቀን ተነሱብኝ፤+ይሖዋ ግን ድጋፍ ሆነልኝ። 19  ከዚያም ደህንነት ወደማገኝበት ስፍራ* አመጣኝ፤በእኔ ስለተደሰተ ታደገኝ።+ 20  ይሖዋ እንደ ጽድቄ ወሮታ ይከፍለኛል፤+እንደ እጄ ንጽሕና ብድራት ይመልስልኛል።+ 21  የይሖዋን መንገድ ጠብቄአለሁና፤አምላኬን በመተው ክፉ ድርጊት አልፈጸምኩም። 22  ፍርዱ ሁሉ በፊቴ ነው፤ደንቦቹን ቸል አልልም። 23  በፊቱ እንከን የለሽ ሆኜ እኖራለሁ፤+ራሴንም ከስህተት እጠብቃለሁ።+ 24  ይሖዋ እንደ ጽድቄ፣+በፊቱ ንጹሕ እንደሆኑት እጆቼ ብድራት ይመልስልኝ።+ 25  ታማኝ ለሆነ ሰው ታማኝ ትሆናለህ፤+እንከን የለሽ ለሆነ ሰው እንከን የለሽ ትሆናለህ፤+ 26  ከንጹሕ ሰው ጋር ንጹሕ ሆነህ ትገኛለህ፤+ጠማማ ለሆነ ሰው ግን ብልህ መሆንህን ታሳያለህ።+ 27  ችግረኞችን* ታድናለህና፤+ትዕቢተኛውን* ግን ታዋርዳለህ።+ 28  ይሖዋ ሆይ፣ መብራቴን የምታበራው አንተ ነህና፤አምላኬ ሆይ፣ ጨለማዬን ብርሃን የምታደርገው አንተ ነህ።+ 29  በአንተ እርዳታ ወራሪውን ቡድን መጋፈጥ እችላለሁ፤+በአምላክ ኃይል ቅጥር መውጣት እችላለሁ።+ 30  የእውነተኛው አምላክ መንገድ ፍጹም ነው፤+የይሖዋ ቃል የነጠረ ነው።+ እሱ መጠጊያ ለሚያደርጉት ሁሉ ጋሻቸው ነው።+ 31  ደግሞስ ከይሖዋ ሌላ አምላክ ማን ነው?+ ከአምላካችንስ ሌላ ዓለት ማን ነው?+ 32  ብርታትን የሚያስታጥቀኝ እውነተኛው አምላክ ነው፤+መንገዴንም ፍጹም ያደርግልኛል።+ 33  እግሮቼን እንደ ዋልያ እግሮች ያደርጋል፤በከፍታ ቦታዎች ላይ ያቆመኛል።+ 34  እጆቼን ለጦርነት ያሠለጥናል፤ክንዶቼ የመዳብ ደጋን ማጠፍ ይችላሉ። 35  የመዳን ጋሻህን ትሰጠኛለህ፤+ቀኝ እጅህ ይደግፈኛል፤ትሕትናህም ታላቅ ያደርገኛል።+ 36  ለእርምጃዬ መንገዱን ታሰፋልኛለህ፤እግሮቼ* አያዳልጣቸውም።+ 37  ጠላቶቼን አሳድጄ እደርስባቸዋለሁ፤ተጠራርገው እስኪጠፉ ድረስ ወደ ኋላ አልመለስም። 38  እንዳያንሰራሩ አድርጌ አደቃቸዋለሁ፤+እግሬ ሥር ይወድቃሉ። 39  ለውጊያው ብርታት ታስታጥቀኛለህ፤ጠላቶቼ ሥሬ እንዲወድቁ ታደርጋለህ።+ 40  ጠላቶቼ ከእኔ እንዲሸሹ ታደርጋለህ፤*እኔም የሚጠሉኝን አጠፋቸዋለሁ።*+ 41  እርዳታ ለማግኘት ይጮኻሉ፤ ሆኖም የሚያድናቸው የለም፤ወደ ይሖዋም ይጮኻሉ፤ እሱ ግን አይመልስላቸውም። 42  በነፋስ ፊት እንዳለ አቧራ ፈጽሜ አደቃቸዋለሁ፤በመንገድ ላይ እንዳለ ጭቃ አውጥቼ እጥላቸዋለሁ። 43  ስህተት ከሚለቃቅሙ ሰዎች ታድነኛለህ።+ የብሔራት መሪ አድርገህ ትሾመኛለህ።+ የማላውቀው ሕዝብ ያገለግለኛል።+ 44  ስለ እኔ በሰሙት ነገር ብቻ ይታዘዙኛል፤የባዕድ አገር ሰዎችም አንገታቸውን ደፍተው ወደ ፊቴ ይቀርባሉ።+ 45  የባዕድ አገር ሰዎች ወኔ ይከዳቸዋል፤*ከምሽጎቻቸው እየተንቀጠቀጡ ይወጣሉ። 46  ይሖዋ ሕያው ነው! ዓለቴ+ ይወደስ! የመዳኔ አምላክ ከፍ ከፍ ይበል።+ 47  እውነተኛው አምላክ ይበቀልልኛል፤+ሕዝቦችንም ከበታቼ ያስገዛልኛል። 48  በቁጣ ከተሞሉ ጠላቶቼ ይታደገኛል፤ከሚያጠቁኝ ሰዎች በላይ ከፍ ከፍ ታደርገኛለህ፤+ከዓመፀኛ ሰው ታድነኛለህ። 49  ይሖዋ ሆይ፣ በብሔራት መካከል የማከብርህ ለዚህ ነው፤+ለስምህም የውዳሴ መዝሙር እዘምራለሁ።+ 50  እሱ ለንጉሡ ታላላቅ የማዳን ሥራዎች ያከናውናል፤*+ለቀባውም ታማኝ ፍቅር ያሳያል፤+ለዳዊትና ለዘሩ ለዘላለም ይህን ያደርጋል።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

^ ወይም “ኃያል አዳኜና።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
^ ወይም “የሲኦል።” የሰው ልጆችን ሁሉ መቃብር ያመለክታል። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
^ ወይም “በነፋስ።”
^ ወይም “የውኃ መውረጃ ቦዮች ታዩ።”
^ ወይም “ሰፊ ወደሆነ ስፍራ።”
^ ወይም “የተጎሳቆሉትን ሰዎች።”
^ ቃል በቃል “ትዕቢተኛውን ዓይን።”
^ ወይም “ቁርጭምጭሚቶቼ።”
^ ወይም “የጠላቶቼን ጀርባ ትሰጠኛለህ።”
^ ቃል በቃል “ጸጥ አሰኛቸዋለሁ።”
^ ወይም “ይጠወልጋሉ።”
^ ወይም “ታላላቅ ድሎችን ያጎናጽፋል።”