ሕዝቅኤል 33:1-33

  • የጠባቂው ኃላፊነቶች (1-20)

  • ኢየሩሳሌም መውደቋ ተነገረ (21, 22)

  • በፍርስራሽ ውስጥ ለሚኖሩ የተላለፈ መልእክት (23-29)

  • ሰዎች መልእክቱን ሰምተው በተግባር አያውሉትም (30-33)

    • ሕዝቅኤል “የፍቅር ዘፈን” ሆነላቸው (32)

    • “በመካከላቸው ነቢይ እንደነበረ ያውቃሉ” (33)

33  የይሖዋም ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፦  “የሰው ልጅ ሆይ፣ ለሕዝብህ ልጆች ተናገር፤+ እንዲህም በላቸው፦ “‘በአንድ አገር ላይ ሰይፍ አመጣሁ እንበል፤+ በዚህ ጊዜ የአገሪቱ ሕዝብ ሁሉ አንድ ሰው በመምረጥ ጠባቂ አድርጎ ሾመው፤  እሱም በአገሪቱ ላይ ሰይፍ ሲመጣ አይቶ ቀንደ መለከት በመንፋት ሕዝቡን አስጠነቀቀ።+  አንድ ሰው የቀንደ መለከቱን ድምፅ ሰምቶ ማስጠንቀቂያውን ተግባራዊ ሳያደርግ ቢቀር፣+ ሰይፍም መጥቶ ሕይወቱን ቢያጠፋ፣* ደሙ በገዛ ራሱ ላይ ይሆናል።+  የቀንደ መለከቱን ድምፅ ቢሰማም ማስጠንቀቂያውን ተግባራዊ አላደረገም። ደሙ በራሱ ላይ ይሆናል። ቢጠነቀቅ ኖሮ ሕይወቱ* በተረፈ ነበር።  “‘ነገር ግን ጠባቂው ሰይፍ ሲመጣ አይቶ ቀንደ መለከት ባይነፋና+ ሕዝቡን ባያስጠነቅቅ፣ ሰይፍም መጥቶ ከመካከላቸው የአንዱን ሰው ሕይወት* ቢያጠፋ፣ ይህ ሰው በገዛ በደሉ ይሞታል፤ ደሙን ግን ከጠባቂው እጅ እሻለሁ።’*+  “የሰው ልጅ ሆይ፣ አንተን ለእስራኤል ቤት ጠባቂ አድርጌ ሾሜሃለሁ፤ ከአፌ የሚወጣውንም ቃል ስትሰማ ማስጠንቀቂያዬን ንገራቸው።+  ክፉውን ሰው ‘አንተ ክፉ ሰው፣ በእርግጥ ትሞታለህ!’ ባልኩት ጊዜ፣+ ክፉውን ሰው አካሄዱን እንዲያስተካክል ባታስጠነቅቀው፣ እሱ ክፉ በመሆኑ ከሠራው በደል የተነሳ ይሞታል፤+ ደሙን ግን ከአንተ እጅ እሻዋለሁ።  ሆኖም ክፉውን ሰው ከመንገዱ እንዲመለስ አስጠንቅቀኸው አካሄዱን ለማስተካከል ፈቃደኛ ባይሆን፣ እሱ በሠራው በደል ይሞታል፤+ አንተ ግን የገዛ ሕይወትህን* በእርግጥ ታድናለህ።+ 10  “አንተም የሰው ልጅ ሆይ፣ ለእስራኤል ቤት እንዲህ በል፦ ‘እናንተ እንዲህ ብላችኋል፦ “ዓመፃችንና ኃጢአታችን እጅግ ከብዶናል፤ በዚህም የተነሳ እየመነመንን ሄደናል፤+ ታዲያ እንዴት በሕይወት መቀጠል እንችላለን?”’+ 11  እንዲህ በላቸው፦ ‘“በሕያውነቴ እምላለሁ” ይላል ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ፣ “በክፉው ሰው ሞት ደስ አልሰኝም፤+ ይልቁንም ክፉው ሰው አካሄዱን አስተካክሎ+ በሕይወት እንዲኖር እፈልጋለሁ።+ የእስራኤል ቤት ሆይ፣ ተመለሱ፤ ከክፉ መንገዳችሁ ተመለሱ፤+ ለምን ትሞታላችሁ?”’+ 12  “አንተም የሰው ልጅ ሆይ፣ ለሕዝብህ ልጆች እንዲህ በላቸው፦ ‘ጻድቁ ሰው በሚያምፅበት ጊዜ ጽድቁ አያድነውም፤+ ክፉውም ሰው ከክፋቱ በሚመለስበት ጊዜ በክፋቱ አይሰናከልም፤+ ደግሞም ጻድቅ የሆነ ማንኛውም ሰው ኃጢአት በሚሠራበት ቀን በጽድቁ በሕይወት ሊኖር አይችልም።+ 13  ጻድቁን ሰው “በእርግጥ በሕይወት ትኖራለህ” ባልኩት ጊዜ በገዛ ጽድቁ ታምኖ መጥፎ* ነገር ቢፈጽም፣+ ከጽድቅ ሥራው መካከል አንዱም አይታሰብም፤ ይልቁንም መጥፎ ነገር በመፈጸሙ ይሞታል።+ 14  “‘እንዲሁም ክፉውን ሰው “በእርግጥ ትሞታለህ” ባልኩት ጊዜ ከኃጢአቱ ቢመለስና ፍትሐዊና ጽድቅ የሆነ ነገር ቢያደርግ፣+ 15  ደግሞም ክፉው ሰው መያዣ አድርጎ የወሰደውን ቢመልስ፣+ የሰረቀውን መልሶ ቢሰጥና+ መጥፎ ነገር ከመፈጸም ተቆጥቦ ሕይወት የሚያስገኙትን ደንቦች ቢከተል፣ በእርግጥ በሕይወት ይኖራል።+ ፈጽሞ አይሞትም። 16  ከሠራቸው ኃጢአቶች ውስጥ አንዱም አይታወስበትም።*+ ፍትሕና ጽድቅ የሆነውን ነገር ስላደረገ በእርግጥ በሕይወት ይኖራል።’+ 17  “ይሁንና ወገኖችህ ፍትሐዊ ያልሆነው የእነሱ መንገድ ሆኖ ሳለ ‘የይሖዋ መንገድ ፍትሐዊ አይደለም’ ብለዋል። 18  “ጻድቅ ሰው ጽድቅ ማድረጉን ቢተውና መጥፎ ነገር ቢፈጽም፣ በዚህ የተነሳ ይሞታል።+ 19  ሆኖም ክፉ ሰው ከክፋቱ ቢመለስና ፍትሐዊና ጽድቅ የሆነ ነገር ቢያደርግ፣ ይህን በማድረጉ በሕይወት ይኖራል።+ 20  “ይሁንና እናንተ ‘የይሖዋ መንገድ ፍትሐዊ አይደለም’ ብላችኋል።+ የእስራኤል ቤት ሆይ፣ በእያንዳንዳችሁ ላይ እንደ መንገዳችሁ እፈርድባችኋለሁ።” 21  ከረጅም ጊዜ በኋላ ይኸውም በተማረክን በ12ኛው ዓመት፣ በአሥረኛው ወር፣ ከወሩም በአምስተኛው ቀን ከኢየሩሳሌም ያመለጠ ሰው ወደ እኔ መጥቶ+ “ከተማዋ ተመታች!” አለኝ።+ 22  ያመለጠው ሰው ከመምጣቱ በፊት በነበረው ምሽት የይሖዋ እጅ በእኔ ላይ ነበረች፤ ሰውየው ጠዋት ወደ እኔ ከመምጣቱ በፊት፣ አምላክ አፌን ከፈተልኝ። እኔም አፌ ተከፍቶ በድጋሚ መናገር ቻልኩ።+ 23  ከዚያም የይሖዋ ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፦ 24  “የሰው ልጅ ሆይ፣ በእነዚህ የፈራረሱ ቦታዎች የሚኖሩ ሰዎች+ ስለ እስራኤል ምድር እንዲህ በማለት ይናገራሉ፦ ‘አብርሃም አንድ ራሱ ብቻ ነበር፤ ይሁንና ምድሪቱን ወረሰ።+ እኛ ግን ብዙ ነን፤ በእርግጥ ምድሪቱ ርስት ሆና ተሰጥታናለች።’ 25  “ስለዚህ እንዲህ በላቸው፦ ‘ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “ሥጋውን ከነደሙ ትበላላችሁ፤+ ዓይኖቻችሁን አስጸያፊ ወደሆኑት ጣዖቶቻችሁ* ታነሳላችሁ፤ ደምም ታፈሳላችሁ።+ ታዲያ ምድሪቱን ልትወርሱ ይገባችኋል? 26  በሰይፋችሁ ታምናችኋል፤+ አስጸያፊ ልማዶች ትፈጽማላችሁ፤ እያንዳንዳችሁም የባልንጀራችሁን ሚስት አርክሳችኋል።+ ታዲያ ምድሪቱን ልትወርሱ ይገባችኋል?”’+ 27  “አንተም እንዲህ በላቸው፦ ‘ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “በሕያውነቴ እምላለሁ፤ በፈራረሱት ቦታዎች የሚኖሩት ሰዎች በሰይፍ ይወድቃሉ፤ አውላላ ሜዳ ላይ ያሉትንም ለዱር አራዊት መብል አድርጌ እሰጣቸዋለሁ፤ በምሽጎችና በዋሻዎች ውስጥ ያሉትም በበሽታ ይሞታሉ።+ 28  ምድሪቱን ፈጽሞ ባድማ አደርጋታለሁ፤+ ከልክ ያለፈ ኩራቷም ይጠፋል፤ የእስራኤልም ተራሮች ባድማ ይሆናሉ፤+ የሚያልፍባቸውም አይኖርም። 29  ደግሞም በፈጸሟቸው አስጸያፊ ነገሮች ሁሉ የተነሳ+ ምድሪቱን ፈጽሞ ባድማ በማደርግበት ጊዜ+ እኔ ይሖዋ እንደሆንኩ ያውቃሉ።”’ 30  “የሰው ልጅ ሆይ፣ ወገኖችህ በየግድግዳው ሥርና በየቤቱ በራፍ ላይ ሆነው እርስ በርሳቸው ስለ አንተ ይነጋገራሉ።+ አንዱ ሌላውን፣ እያንዳንዱም ወንድሙን፣ ‘ና፣ ከይሖዋ የመጣውን ቃል እንስማ’ ይለዋል። 31  እንደ ሕዝቤ በፊትህ ለመቀመጥ ተሰብስበው ወደ አንተ ይመጣሉ፤ ቃልህን ይሰማሉ፤ ሆኖም በተግባር አያውሉትም።+ በአፋቸው ይሸነግሉሃልና፤* ልባቸው ግን አግባብ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት ይስገበገባል። 32  እነሆ፣ አንተ ለእነሱ ባማረ ድምፅ እንደሚዘፈንና በባለ አውታር መሣሪያ አሳምረው እንደሚጫወቱት የፍቅር ዘፈን ሆነህላቸዋል። ቃልህን ይሰማሉ፤ ሆኖም አንዳቸውም አያደርጉትም። 33  ይህ በሚፈጸምበት ጊዜ፣ ደግሞም ይፈጸማል፣ በመካከላቸው ነቢይ እንደነበረ ያውቃሉ።”+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ቃል በቃል “እሱን ቢያስወግደው።”
ወይም “ነፍሱ።”
ወይም “ነፍስ።”
ወይም “ይሁንና ስለ ደሙ ጠባቂውን ተጠያቂ አደርገዋለሁ።”
ወይም “የገዛ ነፍስህን።”
ወይም “ፍትሕ የጎደለው።”
ወይም “አይያዝበትም።”
እዚህ ላይ የገባው የዕብራይስጥ ቃል “ፋንድያ” ከሚለው ቃል ጋር ዝምድና ሊኖረው የሚችል ሲሆን ንቀትን ለማመልከት ተሠርቶበታል።
ወይም “በጣም እንደጓጉ በሚያሳይ ሁኔታ ይናገራሉና።”