በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይሖዋ በእርሱ ተስፋ የሚያደርጉትን ይጠብቃል

ይሖዋ በእርሱ ተስፋ የሚያደርጉትን ይጠብቃል

ይሖዋ በእርሱ ተስፋ የሚያደርጉትን ይጠብቃል

“ቸርነትህና [“ፍቅራዊ ደግነትህና፣” Nw] እውነትህ ዘወትር ይጠብቁኝ።”—መዝሙር 40:11

1. ንጉሥ ዳዊት ይሖዋን ምን ጠይቋል? ለጥያቄው መልስ እንደሚያገኝስ እንዴት እናውቃለን?

 የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ የነበረው ዳዊት “እግዚአብሔርን ደጅ ጠናሁት” ካለ በኋላ “እርሱም ዘንበል አለልኝ፤ ጩኸቴንም ሰማ” በማለት ተናግሯል። (መዝሙር 40:1) ይሖዋ የሚወዱትን እንዲሁም በእርሱ ተስፋ የሚያደርጉትን ሰዎች እንዴት እንደሚጠብቅ ዳዊት በራሱ ሕይወት በተደጋጋሚ አይቷል። በመሆኑም ዘወትር እንዲጠብቀው ለመጠየቅ ተገፋፍቷል። (መዝሙር 40:11) ዳዊት “የተሻለውን ትንሣኤ” እንደሚያገኙ ከተነገረላቸው ወንዶችና ሴቶች መካከል ስለተጠቀሰ ይሖዋ ይህንን ሽልማት ለመስጠት ከሚያስታውሳቸው ሰዎች መካከል አንዱ ነው። (ዕብራውያን 11:32-35) የወደፊት ተስፋው ከሁሉ በተሻለ መንገድ የተረጋገጠለት ሲሆን ስሙ በይሖዋ “የመታሰቢያ መጽሐፍ” ውስጥ ሰፍሯል።—ሚልክያስ 3:16

2. መጽሐፍ ቅዱስ የይሖዋን ጥበቃ ማግኘት ሲባል ምን ማለት እንደሆነ ለማወቅ የሚረዳን እንዴት ነው?

2 በዕብራውያን ምዕራፍ 11 ላይ የተጠቀሱት ታማኝ ሰዎች የኖሩት ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት ነበር። ይሁን እንጂ “ሕይወቱን የሚወድ ያጣታል፤ በዚህ ዓለም ሕይወቱን የሚጠላ ግን ለዘላለም ሕይወት ይጠብቃታል” በማለት ኢየሱስ ከሰጠው ትምህርት ጋር በሚስማማ መንገድ ተመላልሰዋል። (ዮሐንስ 12:25) ስለዚህ የይሖዋን ጥበቃ ማግኘት ማለት ከችግር ወይም ከስደት ነጻ መሆን ማለት እንዳልሆነ በግልጽ ማየት ይቻላል። ከዚህ ይልቅ አንድ ሰው በአምላክ ፊት ጥሩ አቋም ይዞ ለመመላለስ የሚያስችለውን መንፈሳዊ ጥበቃ ያገኛል ማለት ነው።

3. ኢየሱስ ክርስቶስ የይሖዋን ጥበቃ እንዳገኘ ምን ማረጋገጫ አለን? የተደረገለት ጥበቃ ምን ውጤት አስገኝቷል?

3 ኢየሱስ ራሱ ጭካኔ የተሞላበት ስደትና ነቀፋ ኢላማ ሆኖ የነበረ ሲሆን በመጨረሻም ጠላቶቹ ክፉኛ ተዋርዶና ተሰቃይቶ እንዲሞት አድርገዋል። ሆኖም የተከሰተው ሁኔታ አምላክ መሲሑን ለመጠበቅ ከገባው ቃል ጋር የሚጋጭ አይደለም። (ኢሳይያስ 42:1-6) ኢየሱስ ተዋርዶ ከሞተ ከሦስት ቀን በኋላ ትንሣኤ ማግኘቱ ይሖዋ ዳዊት የጠየቀውን እርዳታ እንደሰጠው ሁሉ እርሱንም እንደሰማው ያረጋግጣል። ይሖዋ ጽኑ አቋሙን እንዲጠብቅ የሚያስችለውን ኃይል በመስጠት ኢየሱስን ረድቶታል። (ማቴዎስ 26:39) ኢየሱስ በዚህ መንገድ ጥበቃ ማግኘቱ የማይጠፋ ሰማያዊ ሕይወት እንዲጨብጥ ያስቻለው ሲሆን በቤዛው ለሚያምኑ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ደግሞ የዘላለም ሕይወት ተስፋ አስገኝቶላቸዋል።

4. ለቅቡዓን ክርስቲያኖችና ‘ለሌሎች በጎች’ ምን ዋስትና ተሰጥቷል?

4 ይሖዋ በዳዊትና በኢየሱስ ዘመን እንዳደረገው ሁሉ ዛሬም አገልጋዮቹን የመጠበቅ ፍላጎቱም ሆነ ችሎታው እንዳለው መተማመን እንችላለን። (ያዕቆብ 1:17) በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ ጥቂት ቁጥር ያላቸው በምድር ላይ የቀሩት የኢየሱስ ቅቡዓን ወንድሞች “በሰማይ ለማይጠፋ፣ ለማይበላሽና ለማይለወጥ ርስት . . . በመጨረሻው ዘመን ሊገለጥ የተዘጋጀው ድነት እስኪመጣ ድረስ በእምነት አማካይነት በእግዚአብሔር ኀይል ተጠብቃችኋል” በሚለው ይሖዋ በገባው ቃል ላይ መተማመን ይችላሉ። (1 ጴጥሮስ 1:4, 5) በተመሳሳይም ምድራዊ ተስፋ ያላቸው “ሌሎች በጎች” በአምላክና እርሱ በመዝሙራዊው በኩል በገባው “እናንተ ቅዱሳኑ ሁሉ፣ እግዚአብሔርን ውደዱት! እግዚአብሔር ታማኞችን ይጠብቃል” በሚለው ቃል ላይ እምነት ማሳደር ይችላሉ።—ዮሐንስ 10:16፤ መዝሙር 31:23

መንፈሳዊ ጥበቃ ማግኘት

5, 6. (ሀ) በዘመናችን የአምላክ ሕዝቦች ጥበቃ ያገኙት እንዴት ነው? (ለ) ቅቡዓን ከይሖዋ ጋር ምን ዓይነት ዝምድና መሥርተዋል? ምድራዊ ተስፋ ያላቸውስ?

5 በዘመናችን ይሖዋ ሕዝቦቹ መንፈሳዊ ጥበቃ የሚያገኙባቸውን ዝግጅቶች አድርጓል። ሕዝቦቹን ከስደት ወይም ከተለመዱ ችግሮችና አሳዛኝ ሁኔታዎች ባይሰውራቸውም ከእርሱ ጋር የመሠረቱትን የቅርብ ወዳጅነት እንዲጠብቁ አስፈላጊውን እርዳታና ማበረታቻ በታማኝነት ሰጥቷቸዋል። ለዚህ ዝምድና መሠረት የሆናቸው አምላክ ባደረገው ፍቅራዊ የቤዛ ዝግጅት ላይ ያላቸው እምነት ነው። ከእነዚህ ታማኝ ክርስቲያኖች መካከል አንዳንዶቹ ከክርስቶስ ጋር በሰማይ እንዲገዙ በአምላክ መንፈስ ተቀብተዋል። የአምላክ መንፈሳዊ ልጆች በመሆናቸው ጻድቃን የተባሉ ከመሆኑም በላይ “እርሱ ከጨለማ አገዛዝ ታደገን፤ ወደሚወደው ልጁ መንግሥትም አሻገረን፤ በእርሱም መዋጀትን በደሙ አግኝተናል፤ ይህም የኀጢአት ይቅርታ ነው” የሚሉት ቃላት በእነርሱ ላይ ይሠራሉ።—ቆላስይስ 1:13, 14

6 በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሌሎች ታማኝ ክርስቲያኖችም ከአምላክ ቤዛዊ ዝግጅት መጠቀም እንደሚችሉ ዋስትና ተሰጥቷቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ላይ “የሰው ልጅ ሊያገለግልና ሕይወቱን ለብዙዎች ቤዛ አድርጎ ሊሰጥ መጣ እንጂ ሊገለገል አልመጣም” የሚል ሐሳብ እናነባለን። (ማርቆስ 10:45) እነዚህ ክርስቲያኖች “ለእግዚአብሔር ልጆች ወደ ሆነው ወደ ከበረው ነጻነት” የሚደርሱበትን ጊዜ ይጠባበቃሉ። (ሮሜ 8:21) እስከዚያው ድረስ ግን ከአምላክ ጋር ላላቸው ወዳጅነት ትልቅ ግምት የሚሰጡ ሲሆን ዝምድናቸውንም ለማጠናከር ልባዊ ጥረት ያደርጋሉ።

7. በዛሬው ጊዜ ይሖዋ የሕዝቦቹን መንፈሳዊ ደኅንነት የሚጠብቀው በምን መንገድ ነው?

7 ይሖዋ የሕዝቦቹን መንፈሳዊ ደኅንነት ለመጠበቅ ከሚጠቀምባቸው መንገዶች አንዱ ደረጃ በደረጃ እያደገ የሚሄደው የትምህርት ፕሮግራም ነው። ይህ ትምህርት ከምንጊዜውም በበለጠ ትክክለኛ የእውነት እውቀት እንዲያገኙ አስችሏቸዋል። በተጨማሪም ይሖዋ በቃሉ፣ በድርጅቱና በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት ቀጣይ የሆነ አመራር ይሰጣል። በምድር ዙሪያ ያሉ የአምላክ ሕዝቦች ‘የታማኝና ልባም ባሪያን’ አመራር በመከተል እንደ ዓለም አቀፍ ቤተሰብ ሆነዋል። የባሪያው ክፍል በዘር ወይም በኑሮ ደረጃ ልዩነት ሳያደርግ የዚህን ቤተሰብ መንፈሳዊ ፍላጎት የሚያሟላ ሲሆን አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ደግሞ ቁሳዊ እርዳታ የሚያገኝበትን ዝግጅት ያደርጋል።—ማቴዎስ 24:45 የ1954 ትርጉም

8. ይሖዋ በታማኝ አገልጋዮቹ ላይ ምን እምነት አለው? ምን ዋስትናስ ሰጥቷቸዋል?

8 ይሖዋ፣ ኢየሱስ ከጠላቶቹ ከባድ አካላዊ ጥቃት እንዳይደርስበት እንዳልተከላከለለት ሁሉ በዛሬው ጊዜ ላሉት ክርስቲያኖችም እንዲህ ዓይነቱን ጥበቃ አያደርግም። ይሁን እንጂ ይህ ሁኔታ ይሖዋ እንዳልተደሰተባቸው የሚያመለክት ነው? በፍጹም አይደለም! እንዲያውም ይሖዋ አገልጋዮቹ ጽንፈ ዓለማዊ ይዘት ባለው አብይ ጉዳይ ላይ ከእርሱ ጎን እንደሚቆሙ እምነት እንዳለው ያሳያል። (ኢዮብ 1:8-12፤ ምሳሌ 27:11) መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔር ፍትሕን ይወዳልና፤ ታማኞቹንም አይጥልም፤ ለዘላለምም ይጠብቃቸዋል” ስለሚል ይሖዋ በእርሱ የሚታመኑትን በፍጹም አይተዋቸውም።—መዝሙር 37:28

በፍቅራዊ ደግነትና በእውነት ጥበቃ ማግኘት

9, 10. (ሀ) የይሖዋ እውነት ሕዝቦቹን የሚጠብቀው እንዴት ነው? (ለ) ይሖዋ ታማኞቹን በፍቅራዊ ደግነቱ እንደሚጠብቅ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያሳየው እንዴት ነው?

9 ዳዊት በመዝሙር 40 ላይ በሰፈረው ጸሎቱ የይሖዋ ፍቅራዊ ደግነትና እውነት እንዲጠብቁት ጠይቆ ነበር። የይሖዋ እውነተኝነትና ለጽድቅ ያለው ፍቅር፣ የአቋም ደረጃዎቹን በግልጽ እንዲያስቀምጥ ግድ ይሉታል። በእነዚህ የአቋም ደረጃዎች የሚመሩ ግለሰቦች መመሪያዎቹን ችላ የሚሉ ሰዎች ከሚገጥማቸው ጭንቀት፣ ፍርሃትና ችግር በእጅጉ ይጠበቃሉ። ለምሳሌ ያህል ከዕፅና ከአልኮል መጠጥ ሱሰኝነት፣ ልቅ ከሆነ ወሲባዊ ግንኙነትና ከመጥፎ አኗኗር ከራቅን እነዚህ ነገሮች ከሚያስከትሏቸው በርካታ አሳዛኝ ችግሮች ራሳችንንም ሆነ የምንወዳቸውን ሰዎች መጠበቅ እንችላለን። በተጨማሪም አንዳንድ ጊዜ ዳዊት አድርጎ እንደነበረው ከይሖዋ የእውነት መንገድ ወጥተው የባዘኑ ሰዎች፣ አምላክ በመጥፎ ድርጊታቸው ለሚጸጸቱ “መሸሸጊያ” እንደሆነ እርግጠኛ መሆን ይችላሉ። እንደነዚህ ያሉ ሰዎች “ከመከራ ትጠብቀኛለህ” እያሉ በደስታ መዘመር ይችላሉ። (መዝሙር 32:7) የአምላክን ፍቅራዊ ደግነት የሚያሳይ እንዴት ያለ ግሩም መግለጫ ነው!

10 የአምላክ ፍቅራዊ ደግነት ሌላው መግለጫ ደግሞ እርሱ በቅርቡ ከሚያጠፋው ክፉ ዓለም እንዲለዩ አገልጋዮቹን የሚያስጠነቅቅ መሆኑ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል:- “ዓለምን ወይም በዓለም ያለውን ማናቸውንም ነገር አትውደዱ፤ ማንም ዓለምን ቢወድ፣ የአብ ፍቅር በእርሱ ዘንድ የለም፤ ምክንያቱም በዓለም ያለው ሁሉ:- የሥጋ ምኞት፣ የዐይን አምሮትና የኑሮ ትምክሕት ከዓለም እንጂ ከአብ የሚመጣ አይደለም።” ይህን ማስጠንቀቂያ በመስማትና ከማስጠንቀቂያው ጋር በሚስማማ መንገድ በመመላለስ ቃል በቃል ሕይወታችንን ለዘላለም ጠብቀን ማቆየት እንችላለን። ምክንያቱም ጥቅሱ በመቀጠል “ዓለምና ምኞቱ ያልፋሉ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚፈጽም ግን ለዘላለም ይኖራል” ይላል።—1 ዮሐንስ 2:15-17

የመለየት ችሎታ፣ ማስተዋልና ጥበብ ይጠብቁናል

11, 12. የመለየት ችሎታ፣ ማስተዋልና ጥበብ እንዴት ጥበቃ እንደሚያደርጉልን ግለጽ።

11 የዳዊት ልጅ ሰሎሞን የአምላክን ሞገስ ለማግኘት ተስፋ ስለሚያደርጉ ሰዎች በመንፈስ አነሳሽነት “የመለየት ችሎታ ይጋርድሃል፤ ማስተዋልም ይጠብቅሃል” በማለት ጽፏል። በተጨማሪም “ጥበብን አግኛት፤ . . . ጥበብን አትተዋት፤ እርሷም ከለላ ትሆንሃለች፤ አፍቅራት፤ እርሷም ትጠብቅሃለች” ሲል ምክር ሰጥቷል።—ምሳሌ 2:11፤ 4:5, 6

12 ከአምላክ ቃል በተማርናቸው ነገሮች ላይ የምናሰላስል ከሆነ የመለየት ችሎታችንን እያሠራነው ነው ለማለት ይቻላል። እንዲህ ማድረጋችን ጥልቅ ማስተዋል እንድናዳብር ይረዳናል፤ ይህም ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገባቸውን ነገሮች እንድናስቀድም ያስችለናል። እንዲህ ማድረጋችን ደግሞ በጣም አስፈላጊ ነው፤ ምክንያቱም አብዛኞቻችን ከተሞክሮ እንደምናውቀው ሰዎች ችግር ላይ የሚወድቁት ሆን ብለውም ይሁን ባለማወቅ ጥበብ የጎደለው ምርጫ ሲያደርጉ ነው። ይሖዋ ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑ መንፈሳዊ ግቦች እንዲኖሩን ሲያበረታታን የሰይጣን ዓለም በተቃራኒው ቁሳዊ ሃብትን፣ ታዋቂነትንና ሥልጣንን እንድናሳድድ ያባብለናል። ለመንፈሳዊ ጉዳዮች ቅድሚያ በመስጠት ፈንታ የሰይጣን ዓለም የሚያቀርባቸውን ነገሮች ማሳደድ ቤተሰብ እንዲፈራርስ፣ በወዳጆች መካከል ያለው ግንኙነት እንዲዳከምና መንፈሳዊ ግቦች እንዲደበዝዙ ምክንያት ሊሆን ይችላል። ይህ አካሄድ “ሰው ዓለሙ ሁሉ የእርሱ ቢሆንና ነፍሱን ቢያጣ ምን ይጠቅመዋል?” የሚሉትን የኢየሱስ ቃላት አሳዛኝ እውነታ ወደ ማጨድ ያደርሳል። (ማርቆስ 8:36) ጥበብ “ከሁሉ አስቀድማችሁ ግን የእግዚአብሔርን መንግሥትና ጽድቁን እሹ፤ እነዚህ ሁሉ ይጨመሩላችኋል” የሚለውን የኢየሱስ ምክር እንድንከተል ያስችለናል።—ማቴዎስ 6:33

ራስ ወዳድ መሆን ያለው አደጋ

13, 14. ራስ ወዳድነት ሲባል ምን ማለት ነው? ራስ ወዳድ መሆን ጥበብ ያልሆነውስ ለምንድን ነው?

13 ሰዎች በተፈጥሯቸው ራሳቸውን ይወድዳሉ። ሆኖም አንድ ሰው ለግል ምኞቶቹና ፍላጎቶቹ ትልቁን ቦታ የሚሰጥ ከሆነ ችግር ይፈጠራል። በመሆኑም ይሖዋ ከእርሱ ጋር ያለንን ወዳጅነት ለመጠበቅ እንድንችል ከራስ ወዳድነት መራቅ እንዳለብን አሳስቦናል። ራስ ወዳድነት ሲባል “ለራስ ፍላጎትና ጥቅም እንጂ ለሌሎች አለማሰብ” ማለት ነው። ይህ አባባል በዛሬው ጊዜ ያሉትን በርካታ ሰዎች በትክክል አይገልጽም? መጽሐፍ ቅዱስ በሰይጣን ክፉ ሥርዓት ‘መጨረሻ ዘመን’ ላይ “ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉ” በማለት አስቀድሞ ተንብዮአል።—2 ጢሞቴዎስ 3:1, 2

14 ክርስቲያኖች መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሌሎች ጥቅም ስለ ማሰብና ባልንጀራን እንደራስ ስለ መውደድ የሚሰጠውን ምክር መከተላቸው የጥበብ እርምጃ እንደሆነ ይገነዘባሉ። (ሉቃስ 10:27፤ ፊልጵስዩስ 2:4) በአጠቃላይ ሲታይ ሰዎች እንዲህ ማድረግ እንደማይቻል ይሰማቸው ይሆናል፤ ይሁን እንጂ የተሳካ ትዳር መመሥረት፣ አስደሳች የቤተሰብ ትስስር መፍጠርና ጥሩ ወዳጆችን ማፍራት የምንፈልግ ከሆነ ምክሩን መከተላችን በጣም አስፈላጊ ነው። ስለሆነም አንድ እውነተኛ የይሖዋ አገልጋይ ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ገሸሽ እስኪያደርግ ድረስ ለራሱ ያለው የተፈጥሮ ፍላጎት ሙሉ በሙሉ ሕይወቱን እንዲቆጣጠር በፍጹም መፍቀድ የለበትም። በሕይወቱ ዋነኛውንና ትልቁን ቦታ ሊይዝ የሚገባው የአምላኩ የይሖዋ ፍላጎት መሆን ይኖርበታል።

15, 16. (ሀ) የራስ ወዳድነት ዝንባሌ ወደ ምን ይመራል? ለዚህስ ምሳሌ የሚሆኑት እነማን ናቸው? (ለ) እንደ እውነቱ ከሆነ አንድ ሰው በሌሎች ላይ ለመፍረድ የሚቸኩል ከሆነ ምን እያደረገ ነው?

15 አንድ ሰው የራስ ወዳድነት ዝንባሌ ያለው መሆኑ ወደ ተመጻዳቂነት ይመራዋል፤ ይህ ደግሞ ጠባብ አስተሳሰብ እንዲኖረውና አጉል ድፍረት እንዲያሳይ ያደርገዋል። መጽሐፍ ቅዱስ “አንተ በሌላው ላይ የምትፈርድ፣ የምታመካኝበት የለህም፤ በሌላው ላይ በምትፈርድበት ነገር ሁሉ፣ ራስህን ትኮንናለህ፤ ፈራጅ የሆንኸው አንተ ያንኑ ታደርጋለህና” ማለቱ ተገቢ ነው። (ሮሜ 2:1፤ 14:4, 10) በኢየሱስ ዘመን የነበሩት የሃይማኖት መሪዎች ራሳቸውን ጻድቅ አድርገው ይቆጥሩ ስለነበር እርሱንና ተከታዮቹን የመገሰጽ ብቃት እንዳላቸው ተሰምቷቸዋል። በዚህ መንገድ ራሳቸውን ፈራጅ አድርገው ሾመው ነበር። ይሁን እንጂ ያሉባቸውን ድክመቶች ማስተዋል ባለመቻላቸው በራሳቸው ላይ የጥፋት ፍርድ አምጥተዋል።

16 ኢየሱስን አሳልፎ የሰጠው ይሁዳ ራሱን በሌሎች ላይ ፈራጅ አድርጎ ነበር። ኢየሱስ በቢታንያ በነበረበት ወቅት የአልዓዛር እህት ማርያም ሽቱ አምጥታ ቀባችው፤ በዚህ ጊዜ ይሁዳ ድርጊቱን ክፉኛ ተቃወመ። “ይህ ሽቱ በሦስት መቶ ዲናር ተሽጦ ገንዘቡ ለድኾች ለምን አልተሰጠም?” በማለት በንዴት ተናገረ። ይሁን እንጂ ዘገባው ሲቀጥል “ይህን የተናገረው የገንዘብ ከረጢት ያዥ በመሆኑ፣ ከሚቀመጠው ለራሱ የሚጠቀም ሌባ ስለ ነበር እንጂ ለድኾች ተቈርቊሮ አልነበረም” ይላል። (ዮሐንስ 12:1-6) እንግዲያው በሌሎች ላይ ለመፍረድ ቸኩለው በራሳቸው ላይ የቅጣት ፍርድ እንዳመጡት እንደ ይሁዳ ወይም እንደ ሃይማኖት መሪዎቹ ዓይነት ሰዎች አንሁን።

17. ትምክህተኝነት ወይም ከመጠን በላይ በራስ መተማመን የሚያስከትለውን አደጋ በምሳሌ አስረዳ።

17 የሚያሳዝነው አንዳንድ የጥንት ክርስቲያኖች እንደ ይሁዳ ሌቦች ባይሆኑም ትምክህተኞች በመሆን ለኩራት ተዳርገው ነበር። ያዕቆብ ስለ እነዚህ ሰዎች ሲጽፍ “አሁን ግን በትዕቢታችሁ ትመካላችሁ” ብሏል። አክሎም “እንዲህ ያለው ትምክህት ሁሉ ክፉ ነው” በማለት ተናግሯል። (ያዕቆብ 4:16) በይሖዋ አገልግሎት ስላገኘናቸው ስኬቶች ወይም ልዩ መብቶች የምንኩራራ ከሆነ ራሳችንን ለውድቀት እንዳርጋለን። (ምሳሌ 14:16 የ1954 ትርጉም) ሐዋርያው ጴጥሮስ ከመጠን በላይ በራሱ በመተማመን “ሌሎች በሙሉ ባንተ ምክንያት ቢሰናከሉ እንኳ እኔ በፍጹም አልሰናከልም! . . . ከአንተ ጋር መሞት ቢያስፈልግ እንኳ ከቶ አልክድህም!” በማለት ቢኩራራም ምን እንደተከሰተ እናስታውሳለን። እንደ እውነቱ ከሆነ ስለ ራሳችን የምንኩራራበት ምንም ምክንያት የለም። ያለንን ነገር በሙሉ ያገኘነው በይሖዋ ፍቅራዊ ደግነት ብቻ ነው። ይህን ማስታወሳችን ትምክህተኞች ከመሆን ይጠብቀናል።—ማቴዎስ 26:33-35, 69-75

18. ይሖዋ ስለ ትዕቢት ምን ይሰማዋል?

18 “ትዕቢት ጥፋትን፣ የእብሪት መንፈስም ውድቀትን ትቀድማለች” ተብሎ ተነግሮናል። ለምን? ይሖዋ “እኔም ትዕቢትንና እብሪትን፣ . . . እጠላለሁ” በማለት መልሱን ሰጥቷል። (ምሳሌ 8:13፤ 16:18) ይሖዋ “የአሦርን ንጉሥ ስለ ልቡ ትዕቢትና ስለ ንቀት አመለካከቱ እቀጣዋለሁ” በማለት በቁጣ መናገሩ ምንም አያስደንቅም! (ኢሳይያስ 10:12) ይህን ንጉሥ ንቀት ስለታከለበት ኩራቱ ቀጥቶታል። መላው የሰይጣን ዓለም፣ ኩሩ ከሆኑትና ራሳቸውን ከፍ አድርገው ከሚመለከቱት የሚታዩና የማይታዩ ገዢዎቹ ጋር በቅርቡ ቅጣቱን ይቀበላል። የይሖዋ ባላጋሮች የሚያሳዩትን በራስ የመመራት ዝንባሌ ፈጽሞ አናንጸባርቅ!

19. የአምላክ ሕዝቦች የሚኮሩት በምንድን ነው? ትሑት መሆን ያለባቸውስ ለምንድን ነው?

19 እውነተኛ ክርስቲያኖች የይሖዋ አገልጋይ በመሆናቸው ምክንያት ሊኮሩ ይገባቸዋል። (ኤርምያስ 9:24) ይሁን እንጂ በዚያው መጠን ትሑት መሆን ይኖርባቸዋል። ለምን? ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ “ሁሉም ኀጢአትን ሠርተዋል፤ የእግዚአብሔርም ክብር ጐድሎአቸዋል” ይላል። (ሮሜ 3:23) ስለሆነም የይሖዋ አገልጋዮች በመሆን ያገኘነውን መብት ለመጠበቅ እንድንችል “ክርስቶስ ኢየሱስ ኀጢአተኞችን ለማዳን ወደ ዓለም መጣ . . . ከኀጢአተኞችም ዋና እኔ ነኝ” በማለት የጻፈው የጳውሎስ ዓይነት አመለካከት ሊኖረን ይገባል።—1 ጢሞቴዎስ 1:15

20. ይሖዋ በአሁኑ ጊዜ ሕዝቡን የሚጠብቀው እንዴት ነው? ወደፊትስ የሚጠብቃቸው እንዴት ነው?

20 የይሖዋ ሕዝቦች መለኮታዊውን ፈቃድ ለማስቀደም ሲሉ ለራሳቸው ጥቅም ሁለተኛውን ቦታ ስለሚሰጡ ይሖዋ ለእነርሱ መንፈሳዊ ጥበቃ ማድረጉን እንደሚቀጥል እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ታላቁ መከራ በሚጀምርበት ወቅት ደግሞ ይሖዋ ለሕዝቡ መንፈሳዊ ብቻ ሳይሆን አካላዊ ጥበቃም ያደርግላቸዋል ብለን አፋችንን ሞልተን መናገር እንችላለን። እነዚህ ሰዎች ወደ አምላክ አዲስ ዓለም ሲገቡ “እነሆ፤ አምላካችን ይህ ነው፤ በእርሱ ታመንን፤ እርሱም አዳነን፤ እግዚአብሔር ይህ ነው፤ በእርሱ ታመንን፤ በማዳኑም ደስ ይበለን፤ ሐሤትም እናድርግ” በማለት በደስታ ይዘምራሉ።—ኢሳይያስ 25:9

ታስታውሳለህ?

• ንጉሥ ዳዊትና ኢየሱስ ክርስቶስ ጥበቃ ያገኙት እንዴት ነበር?

• በዛሬው ጊዜ የይሖዋ ሕዝቦች ጥበቃ የሚያገኙት እንዴት ነው?

• የራስ ወዳድነትን ዝንባሌ ማስወገድ የሚገባን ለምንድን ነው?

• የምንኮራው በምንድን ነው? ትሑት መሆን የሚገባንስ ለምንድን ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ይሖዋ ዳዊትንና ኢየሱስን የጠበቃቸው እንዴት ነበር?

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በዛሬው ጊዜ የአምላክ ሕዝቦች መንፈሳዊ ጥበቃ የሚያገኙት በምን መንገዶች ነው?

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የይሖዋ አገልጋዮች በመሆናችን ብንኮራም ምንጊዜም ቢሆን ትሑት መሆን አለብን