በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 12

‘ሌሎችን የሚያንጽ መልካም ቃል’ ተናገር

‘ሌሎችን የሚያንጽ መልካም ቃል’ ተናገር

“ሌሎችን የሚያንጽ . . . ማንኛውም መልካም ቃል እንጂ የበሰበሰ ቃል ከቶ ከአፋችሁ አይውጣ።”ኤፌሶን 4:29

1-3. (ሀ) ይሖዋ ምን ስጦታ ሰጥቶናል? ይህ ስጦታ አግባብ ባልሆነ መንገድ ጥቅም ላይ ሊውል የሚችለውስ እንዴት ነው? (ለ) ከአምላክ ፍቅር ሳንወጣ ለመኖር ከፈለግን የመናገር ችሎታችንን እንዴት ልንጠቀምበት ይገባል?

ለአንድ ለምትወደው ሰው ስጦታ ሰጠኸው እንበል፤ እሱ ግን ስጦታውን ሆን ብሎ አለአግባብ እንደተጠቀመበት ብታውቅ ምን ይሰማሃል? ስጦታው መኪና ቢሆንና በግድየለሽነት እያሽከረከረ በሌሎች ሰዎች ላይ ጉዳት እንዳደረሰ ብትሰማ ምን ይሰማሃል? በጣም አታዝንም?

2 ሌሎች ሊረዱት የሚችሉትን ሐሳብ አቀነባብረን የመናገር ችሎታ ያገኘነው ‘የመልካም ስጦታ ሁሉና የፍጹም ገጸ በረከት ሁሉ’ ምንጭ ከሆነው ከይሖዋ ነው። (ያዕቆብ 1:17) የሰው ልጆችን ከእንስሳት የሚለየው ይህ ስጦታ ሐሳባችንን ብቻ ሳይሆን ስሜታችንን ጭምር ለሌሎች እንድንገልጽ ያስችለናል። ይሁን እንጂ የንግግር ስጦታም ልክ እንደ መኪና አግባብ ባልሆነ መንገድ ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል። የመናገር ችሎታችንን በግድየለሽነት ተጠቅመን ሌሎችን ብናቆስልና ብንጎዳ ይሖዋ ምን ያህል ያዝን!

3 ከአምላክ ፍቅር ሳንወጣ ለመኖር ከፈለግን በስጦታ ያገኘነውን የንግግር ችሎታ ሰጪው እንድንጠቀምበት በሚፈልገው መንገድ መጠቀም ይኖርብናል። ይሖዋ እሱን የሚያስደስተው ምን ዓይነት ንግግር እንደሆነ በማያሻማ መንገድ ገልጾልናል። ቃሉ መጽሐፍ ቅዱስ “እንደ አስፈላጊነቱ ሌሎችን የሚያንጽና ሰሚዎቹን ሊጠቅም የሚችል ማንኛውም መልካም ቃል እንጂ የበሰበሰ ቃል ከቶ ከአፋችሁ አይውጣ” ይላል። (ኤፌሶን 4:29) ከዚህ ቀጥሎ አንደበታችንን መቆጣጠር የሚያስፈልገን ለምን እንደሆነ፣ ምን ዓይነት ነገሮችን ከመናገር መቆጠብ እንዳለብንና ‘ሌሎችን የሚያንጽ መልካም ቃል’ መናገር የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን።

አንደበታችንን መቆጣጠር የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?

4, 5. አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎች፣ ቃላት ያላቸውን ኃይል የሚገልጹት እንዴት ነው?

4 አንደበታችንን መቆጣጠር አስፈላጊ የሆነበት አንዱ ትልቅ ምክንያት ቃላት ኃይል ስላላቸው ነው። ምሳሌ 15:4 “ፈውስ የምታመጣ ምላስ የሕይወት ዛፍ ናት፤ አታላይ ምላስ ግን መንፈስን ትሰብራለች” ይላል። * ውኃ አንድን የጠወለገ ተክል ነፍስ እንደሚዘራበት ሁሉ ፈዋሽ ከሆነ አንደበት የሚወጣ ቃልም የሰሚዎቹን መንፈስ ያድሳል። በአንጻሩ ግን ከጠማማ አንደበት የሚወጣ ክፉ ቃል የሌሎችን መንፈስ ይሰብራል። በእርግጥም የምንናገራቸው ቃላት የመጉዳት ወይም የመፈወስ ኃይል አላቸው።ምሳሌ 18:21

5 ቃላት ያላቸውን ኃይል በግልጽ የሚያሳየው ሌላው ምሳሌ ደግሞ “ግድ የለሽ ቃል እንደ ሰይፍ ይወጋል” ይላል። (ምሳሌ 12:18) ሳይታሰብበት በግድየለሽነት የሚነገር ቃል ከባድ የስሜት ቁስል የሚያስከትል ከመሆኑም በላይ ወዳጅነትን ሊያበላሽ ይችላል። አንድ ሰው በተናገረው ቃል ምክንያት ልብህ የቆሰለበት ጊዜ አለ? ይኸው ምሳሌ አንደበት ያለውን መልካም ገጽታ ሲገልጽ “የጠቢብ አንደበት ግን ፈውስን ያመጣል” ይላል። አምላካዊ ጥበብ ያለው ሰው በአሳቢነት የሚናገራቸው ቃላት የቆሰለ ልብን ሊጠግኑና ወዳጅነትን ሊያጠናክሩ ይችላሉ። ደግነት የሚንጸባረቅባቸው ቃላት ከፍተኛ የመፈወስ ኃይል እንዳላቸው በራስህ ሕይወት ያየህበት አጋጣሚ አለ? (ምሳሌ 16:24) የምንናገራቸው ቃላት ኃይል እንዳላቸው ስለምንገነዘብ አንደበታችንን ሌሎችን ለመፈወስ እንጂ ለመጉዳት ልንጠቀምበት አንፈልግም።

ፈዋሽ ከሆነ አንደበት የሚወጣ ቃል መንፈስን ያድሳል

6. አንደበትን መቆጣጠር በጣም አስቸጋሪ የሆነው ለምንድን ነው?

6 ምንም ያህል ጥረት ብናደርግ አንደበታችንን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር አንችልም። ይህ ሐቅ አንደበታችንን መቆጣጠር አስፈላጊ የሚሆንበትን ሁለተኛ ምክንያት ይጠቁመናል፤ ኃጢአተኞችና ፍጽምና የሚጎድለን መሆናችን አንደበታችንን አለአግባብ እንድንጠቀምበት ተጽዕኖ ያሳድርብናል። የምንናገራቸው ቃላት የሚወጡት ከልብ ነው፤ የሰው ልብ ደግሞ “ወደ ክፋት ያዘነበለ” ነው። (ዘፍጥረት 8:21፤ ሉቃስ 6:45) በመሆኑም አንደበታችንን መግራት በጣም አስቸጋሪ ነው። (ያዕቆብ 3:2-4) አንደበታችንን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር ባንችልም የምንጠቀምበትን መንገድ ለማሻሻል ጥረት ማድረግ እንችላለን። ወንዝ ከሚፈስበት በተቃራኒ አቅጣጫ ለመዋኘት የሚሞክር ሰው የውኃውን ግፊት ለመቋቋም እጁን ሳያሳርፍ መዋኘት እንዳለበት ሁሉ እኛም አንደበታችንን አለአግባብ እንድንጠቀምበት የሚገፋፋንን የኃጢአት ዝንባሌ ዘወትር መታገል ይኖርብናል።

7, 8. ስለምንናገረው ነገር በይሖዋ ፊት ምን ያህል ተጠያቂዎች እንሆናለን?

7 አነጋገራችንን መቆጣጠር አስፈላጊ የሚሆንበት ሦስተኛው ምክንያት ደግሞ ስለምንናገራቸው ነገሮች ይሖዋ የሚጠይቀን መሆኑ ነው። አንደበታችንን የምንጠቀምበት መንገድ ከሰዎች ጋር ብቻ ሳይሆን ከይሖዋ ጋር ያለንን ዝምድናም ይነካብናል። ያዕቆብ 1:26 “አንድ ሰው አምልኮቱን እያከናወነ እንዳለ የሚሰማው ቢሆንም እንኳ አንደበቱን የማይገታ ከሆነ ይህ ሰው የገዛ ልቡን እያታለለ ይኖራል፤ የዚህ ሰው አምልኮም ከንቱ ነው” ይላል። * ከዚህ በፊት በነበረው ምዕራፍ ላይ እንደተመለከትነው አንደበታችንን የምንጠቀምበት መንገድ ከአምልኮታችን ተነጥሎ የሚታይ አይደለም። አንደበታችን ካልተገራ ማለትም ጎጂና መርዛማ ቃላት የሚያወጣ ከሆነ ይሖዋን ለማገልገል የምንለፋው ልፋት ሁሉ በእሱ ዓይን ከንቱ ሊሆንብን ይችላል። ታዲያ ይህ በጣም አሳሳቢ ጉዳይ አይደለም?ያዕቆብ 3:8-10

8 በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ከአምላክ የተሰጠንን የመናገር ችሎታ አለአግባብ እንዳንጠቀምበት ጥንቃቄ ማድረጋችን አስፈላጊ መሆኑን የሚያሳዩ ጠንካራ ምክንያቶች አሉ። አንደበታችንን በሚያንጽ መንገድ ልንጠቀምበት የምንችለው እንዴት እንደሆነ ከማየታችን በፊት አንድ እውነተኛ ክርስቲያን ፈጽሞ ሊጠቀምባቸው የማይገቡ የንግግር ዓይነቶችን እንመልከት።

ጎጂ ንግግር

9, 10. (ሀ) በዛሬው ጊዜ ምን ዓይነት ንግግሮችን መናገር የተለመደ ሆኗል? (ለ) ጸያፍ ንግግርን ማስወገድ የሚያስፈልገን ለምንድን ነው? (በተጨማሪም የግርጌ ማስታወሻውን ተመልከት።)

9 ጸያፍ ንግግር። በዛሬው ጊዜ ሌሎችን መዝለፍ፣ የብልግና ስድቦችን መሳደብና ጸያፍ ቃላትን መናገር በጣም የተለመደ ሆኗል። ብዙዎች ስሜታቸውን አጋንነው ለመግለጽ ሲሉ ወይም ሐሳባቸውን የሚገልጹበት ቃል ሲያጥራቸው መጥፎ ቃላት ይጠቀማሉ። ኮሜዲያኖች ብዙ ጊዜ ሰዎችን ለማሳቅ የብልግና ቀልዶችን ይናገራሉ። ይሁን እንጂ ጸያፍ ንግግር የሚሳቅበት ነገር አይደለም። ከ2,000 ዓመታት በፊት ሐዋርያው ጳውሎስ የቆላስይስ ጉባኤ ክርስቲያኖችን ‘ጸያፍ ንግግርን’ እንዲያስወግዱ መክሯቸው ነበር። (ቆላስይስ 3:8) በተጨማሪም ለኤፌሶን ጉባኤ “ጸያፍ ቀልድ” በእውነተኛ ክርስቲያኖች መካከል ‘ከቶ ሊነሱ’ ከማይገባቸው ነገሮች አንዱ እንደሆነ ተናግሯል።ኤፌሶን 5:3, 4

10 ጸያፍ ንግግር ይሖዋን በጣም ያሳዝነዋል። እሱን የሚወዱ ሰዎችም ስለዚህ ጉዳይ ተመሳሳይ ስሜት አላቸው። በእርግጥም ለይሖዋ ያለን ፍቅር ጸያፍ ንግግርን እንድናስወግድ ይገፋፋናል። ጳውሎስ ‘የሥጋ ሥራዎችን’ ሲዘረዝር በንግግር ንጹሕ አለመሆንን የሚጨምረውን ‘ርኩሰትን’ ጠቅሷል። (ገላትያ 5:19-21) ይህ በጣም ከባድ ጉዳይ ነው። አንድ ግለሰብ ተደጋጋሚ ምክር ቢሰጠውም ንስሐ ሳይገባ የሥነ ምግባር ብልግናን እንዲሁም ወራዳና ብልሹ የሆኑ ድርጊቶችን የሚያበረታቱ ሐሳቦችን የመናገር ልማድ ቢጠናወተው ከጉባኤ ሊወገድ ይችላል። *

11, 12. (ሀ) ስለ ሌሎች ማውራት ሐሜት የሚሆነው መቼ ነው? (ለ) የይሖዋ አምላኪዎች የሌሎችን ስም የሚያጠፋ ነገር ከመናገር መቆጠብ የሚኖርባቸው ለምንድን ነው?

11 ሐሜት፣ ስም ማጥፋት። ሰዎች በአጠቃላይ ስለ ሌሎች ሰዎችና ስለ ሕይወታቸው የማውራት ዝንባሌ አላቸው። ታዲያ ስለ ሌሎች ሰዎች ማውራት ሁልጊዜ መጥፎ ነው ማለት ይቻላል? ለምሳሌ ያህል፣ ስለ ሌሎች ያወራነው ማን እንደተጠመቀ ወይም ማን ማጽናኛ እንደሚያስፈልገው በመናገር አንድ ዓይነት መረጃ ለማስተላለፍ ወይም አስደሳች ዜና ለመናገር አስበን ከሆነ መጥፎ ነው ሊባል አይችልም። የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች አንዳቸው ስለሌላው ደህንነት አጥብቀው ያስቡ ስለነበር ስለ እምነት ባልንጀሮቻቸው የሚገልጹ መረጃዎችን ይለዋወጡ ነበር። (ኤፌሶን 6:21, 22፤ ቆላስይስ 4:8, 9) ይሁን እንጂ ስለ ሌሎች የምንናገረው ነገር ሐቁን የሚያጣምም ወይም ሚስጥራቸውን የሚገልጥ ከሆነ ሐሜት ስለሚሆን ሊጎዳ ይችላል። ከዚህ የሚከፋው ደግሞ እንዲህ ያለው ሐሜት ጎጂ ወደሆነው ወደ ስም ማጥፋት ሊመራ ይችላል። ስም ማጥፋት ‘አንድን ሰው በሐሰት በመወንጀል መልካም ስሙን ማጉደፍ’ ማለት ነው። ለምሳሌ ፈሪሳውያን ኢየሱስ በሌሎች ዘንድ ተቀባይነት እንዳይኖረው ለማድረግ በተንኮል ስሙን አጥፍተዋል። (ማቴዎስ 9:32-34፤ 12:22-24) ስም ማጥፋት ብዙውን ጊዜ ጠብ እንዲፈጠር ምክንያት ይሆናል።ምሳሌ 26:20

12 ይሖዋ የመናገር ችሎታቸውን የሌሎችን መልካም ስም ለማጉደፍ ወይም መከፋፈልን ለመፍጠር የሚጠቀሙበትን ሰዎች በቸልታ አይመለከታቸውም። ይሖዋ “በወንድማማቾች መካከል ጠብን የሚጭር” ሰው ይጠላል። (ምሳሌ 6:16-19) “ስም አጥፊ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል ዲያቦሎስ ሲሆን ይኸው ቃል የሰይጣን ስም ሆኖ አገልግሏል። ሰይጣን በክፋት ተነሳስቶ የአምላክን ስም ስላጠፋ “ዲያብሎስ” ተብሏል። (ራእይ 12:9, 10) የሌሎችን ስም በማጥፋት ከዲያብሎስ ጋር እንዳንመሳሰል እንዲህ ያለውን ድርጊት ከመፈጸም መቆጠብ እንደምንፈልግ የተረጋገጠ ነው። በጉባኤ ውስጥ ‘የከረረ ጭቅጭቅንና መከፋፈልን’ የመሳሰሉ የሥጋ ሥራዎችን የሚያነሳሳ የስም ማጥፋት ወሬ ቦታ የለውም። (ገላትያ 5:19-21) ስለዚህ ስለ አንድ ሰው የሰማኸውን ወሬ ከመናገርህ በፊት ‘የሰማሁት ነገር እውነት ነው? ለሌላ ሰው ባወራው ደግነት ይሆናል? ይህን ማውራቱስ አስፈላጊ ወይም ጠቃሚ ነው?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ።1 ተሰሎንቄ 4:11

13, 14. (ሀ) ስድብ በሰዎች ላይ ምን ጉዳት ሊያስከትል ይችላል? (ለ) ሌሎችን በሚያዋርዱ ቃላት የመናገር ልማድ የተጠናወተው ተሳዳቢ ሰው የሚገኝበት ሁኔታ አደገኛ የሆነው ለምንድን ነው?

13 ስድብ። ቀደም ሲል እንደተገለጸው ቃላት የመጉዳት ኃይል አላቸው። ፍጹማን ባለመሆናችን ምክንያት አንዳንድ ጊዜ ሁላችንም በኋላ የምንጸጸትባቸውን ነገሮች እንናገራለን። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ አንዳንድ የአነጋገር ልማዶች በአንድ ክርስቲያን ቤት ወይም በጉባኤ ውስጥ ፈጽሞ ቦታ ሊኖራቸው እንደማይገባ ይናገራል። ጳውሎስ ክርስቲያኖችን “የመረረ ጥላቻ፣ ቁጣ፣ ንዴት፣ ጩኸትና ስድብ ሁሉ ከክፋት ሁሉ ጋር ከእናንተ መካከል ይወገድ” ሲል መክሯል። (ኤፌሶን 4:31) አንዳንድ ትርጉሞች “ስድብ” የሚለውን ቃል “ክፉ ቃላት” እና “ጎጂ ንግግር” ሲሉ ተርጉመውታል። ሌሎችን በሚያንቋሽሽ ስም መጥራትና ዘወትር መንቀፍ እንዲሁም ማንኛውም ዓይነት ስድብ የአንድን ሰው ክብር የሚገፍ ከመሆኑም በላይ ግለሰቡ የማይረባ እንደሆነ እንዲሰማው ሊያደርግ ይችላል። በተለይ እንክብካቤ የሚሹትና በሌሎች ላይ እምነት የሚጥሉት ልጆች በስድብ ቃላት በቀላሉ ሊጎዱ ይችላሉ።ቆላስይስ 3:21

14 መጽሐፍ ቅዱስ ተሳዳቢነትን፣ ማለትም ሌሎችን በሚያዋርዱ ወይም በሚያቃልሉና ክብርን በሚነኩ ቃላት የመናገር ልማድን አጥብቆ ያወግዛል። እንዲህ ያለው ልማድ የተጠናወተው ግለሰብ፣ የሚሰጠውን እርዳታ ተቀብሎ ለውጥ ካላደረገ ከጉባኤ ሊወገድ ስለሚችል የሚገኝበት ሁኔታ በጣም አደገኛ ነው። ይህም ብቻ ሳይሆን በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ የመኖር አጋጣሚውን ሊያጣ ይችላል። (1 ቆሮንቶስ 5:11-13፤ 6:9, 10) ስለዚህ ጤናማ ያልሆነ፣ እውነትነት የሌለው ወይም ደግነት የጎደለው ንግግር የመናገር ልማድ ከተጠናወተን በአምላክ ፍቅር ውስጥ መኖር እንደማንችል ግልጽ ነው። እንዲህ ያለው ንግግር ጎጂ ነው።

‘ሌሎችን የሚያንጹ መልካም ቃላት’

15. ‘ሌሎችን የሚያንጽ መልካም’ ንግግር ምን ዓይነት ነው?

15 አምላክ የሰጠንን የመናገር ችሎታ እሱ በሚፈልገው መንገድ ልንጠቀምበት የምንችለው እንዴት ነው? የአምላክ ቃል ‘ሌሎችን የሚያንጽ መልካም ቃል’ እንድንናገር የሚያሳስበን መሆኑን አስታውስ። (ኤፌሶን 4:29) ይሖዋ ሌሎችን የሚያንጽ፣ የሚያበረታታና የሚያጽናና ቃል ስንናገር ደስ ይለዋል። እንዲህ ያሉ ቃላት ለመናገር አስቀድሞ ማሰብ ያስፈልጋል። መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ማድረግ የምንችልበትን መንገድ በተመለከተ ዝርዝር መመሪያ አይሰጥም፤ ወይም ደግሞ “ጤናማ ንግግር” የሚባሉት የትኞቹ እንደሆኑ አይዘረዝርም። (ቲቶ 2:8) ‘ሌሎችን የሚያንጹ መልካም’ ቃላት መናገር እንድንችል፣ እንዲህ ያለው ንግግር ተለይቶ የሚታወቅባቸውን ሦስት ቀላል ሆኖም በጣም አስፈላጊ ባሕርያት በአእምሯችን መያዝ ይኖርብናል። የሚያንጽ ንግግር ምንጊዜም ጤናማ፣ እውነት የሆነና ደግነት የሚንጸባረቅበት ነው። እነዚህን ባሕርያት በአእምሯችን ይዘን የሚያንጽ ንግግር የሚባለው ምን ዓይነት እንደሆነ የሚያሳዩ ጥቂት ምሳሌዎችን እንመልከት።—“ ከአንደበቴ የሚወጣው ሁሉ የሚያንጽ ነው?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

16, 17. (ሀ) ሌሎችን ማመስገን የሚኖርብን ለምንድን ነው? (ለ) በጉባኤ ውስጥ ሌሎችን ለማመስገን ምክንያት የሚሆኑ እንዴት ያሉ አጋጣሚዎች አሉ? በቤተሰብ ውስጥስ?

16 ከልብ የመነጨ ምስጋና። ይሖዋም ሆነ ኢየሱስ ለሌሎች ምስጋናንና አድናቆትን መግለጽ አስፈላጊ መሆኑን ይገነዘባሉ። (ማቴዎስ 3:17፤ 25:19-23፤ ዮሐንስ 1:47) እኛም ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ሌሎችን ከልባችን ማመስገናችን ተገቢ ነው። ለምን? ምሳሌ 15:23 ‘በወቅቱ የተሰጠ ቃል ምንኛ መልካም ነው!’ ይላል። ‘ሌሎች ከልባቸው ሲያመሰግኑኝ ምን ይሰማኛል? ደስ አይለኝም? መንፈሴስ አይታደስም?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ። እውነት ነው፣ ከልብ የመነጨ ምስጋና የሚያስተውልህና የሚያስብልህ ሰው እንዳለ፣ እንዲሁም ድካምህ ሁሉ ከንቱ እንዳልሆነ እንድትገነዘብ ያስችልሃል። ይህ ደግሞ በራስ የመተማመን ስሜትህን ከፍ የሚያደርግልህ ከመሆኑም በላይ ወደፊት ይበልጥ ጠንክረህ እንድትሠራ ያነሳሳሃል። ሌሎች ሲያመሰግኑህ ደስ የምትሰኝ ከሆነ አንተም በበኩልህ ሌሎችን ለማመስገን ጥረት ማድረግ አይኖርብህም?ማቴዎስ 7:12

17 የሰዎችን መልካም ጎን ለመመልከት ራስህን አሠልጥን፤ ከዚያም አድናቆትህን ግለጽላቸው። በጉባኤ ውስጥ ጥሩ ዝግጅት የተደረገበት ንግግር ልታዳምጥ፣ መንፈሳዊ ግቦች ላይ ለመድረስ የሚጣጣር ወጣት ልታስተውል ወይም የዕድሜ መግፋት የሚያስከትለው ጫና ቢኖርባቸውም በታማኝነት ስብሰባዎች ላይ የሚገኙ አንድ አረጋዊ ክርስቲያን ልትመለከት ትችላለህ። እነዚህ ሰዎች ለሚያደርጉት ጥረት አድናቆታችንንና ምስጋናችንን ከልባችን ብንገልጽላቸው ደስ ሊላቸውና በመንፈሳዊ ሊጠናከሩ ይችላሉ። በቤተሰብ ውስጥም ባልና ሚስቶች አንዳቸው ከሌላው ሞቅ ያለ የምስጋናና የአድናቆት ቃል መስማት ያስፈልጋቸዋል። (ምሳሌ 31:10, 28) በተለይ ልጆች ችላ እንዳልተባሉና እንደሚወደዱ ሲያውቁ ጥሩ እድገት ይኖራቸዋል። ለአንድ ተክል ፀሐይና ውኃ አስፈላጊ የሆነውን ያህል አንድ ልጅም ከወላጆቹ ምስጋናና አድናቆት ማግኘቱ አስፈላጊ ነው። ወላጆች፣ ልጆቻችሁ ለሚያደርጉት ጥረትና ለመልካም ባሕርያቸው በምታገኙት አጋጣሚ ሁሉ አመስግኗቸው። እንዲህ ያለው ምስጋና ልጆቻችሁ ድፍረትና በራስ የመተማመን መንፈስ እንዲኖራቸው ከማስቻሉም በላይ ትክክል የሆነውን ነገር ለማድረግ የበለጠ ጥረት እንዲያደርጉ ያነሳሳቸዋል።

18, 19. የእምነት ባልንጀሮቻችንን ለማጽናናት የተቻለንን ሁሉ ማድረግ የሚኖርብን ለምንድን ነው? እንዲህ ማድረግ የምንችለውስ እንዴት ነው?

18 ማጽናኛ። ይሖዋ ‘የተሰበረ ልብ ላለውና’ ‘በመንፈሱ ለተዋረደው’ ሰው በጥልቅ ያስባል። (ኢሳይያስ 57:15) ቃሉ መጽሐፍ ቅዱስ ‘እርስ በርሳችን መጽናናታችንን እንድንቀጥል’ እንዲሁም ‘የተጨነቁትን ነፍሳት እንድናጽናና’ ያሳስበናል። (1 ተሰሎንቄ 5:11, 14) ልባቸው በሐዘን የተደቆሰባቸውን የእምነት ባልንጀሮቻችንን ለማጽናናትና ለማበረታታት የምናደርገውን ጥረት ይሖዋ እንደሚመለከትና ይህን ማድረጋችንም እንደሚያስደስተው እርግጠኞች መሆን እንችላለን።

ሌሎችን የሚያንጽ ነገር ስንናገር ይሖዋ ይደሰታል

19 ታዲያ አንድን ተስፋ የቆረጠ ወይም በጭንቀት የተዋጠ ክርስቲያን ለማነጽ ምን መናገር ትችላለህ? ለችግሩ መፍትሔ ማስገኘት እንዳለብህ ሊሰማህ አይገባም። ብዙውን ጊዜ ጥቂት ቃላት መናገር ብቻ እንኳ ትልቅ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል። ቅስሙ ለተሰበረው ሰው እንደምታስብለት ንገረው። አብረኸው ለመጸለይ እንደምትፈልግ ግለጽለት፤ ከዚያም በጸሎትህ ውስጥ ግለሰቡ በአምላክም ሆነ በሰዎች የሚወደድ መሆኑን እንዲገነዘብ እንዲረዳው ይሖዋን ጠይቅ። (ያዕቆብ 5:14, 15) በጉባኤ ውስጥ በጣም የሚፈለግና ከፍተኛ ቦታ የሚሰጠው ሰው እንደሆነ አረጋግጥለት። (1 ቆሮንቶስ 12:12-26) ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ በእርግጥ የሚያስብለት መሆኑን እንዲያስታውስ አንድ የሚያጽናና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ አንብብለት። (መዝሙር 34:18፤ ማቴዎስ 10:29-31) ቅስሙ ለተሰበረው ሰው “መልካም ቃል” ለማካፈል ስትል ሰፋ ያለ ጊዜ አብረኸው ማሳለፍህና ከልብ በመነጨ ስሜት መናገርህ የሚወደድና የሚፈለግ ሰው እንደሆነ እንዲሰማው ሊያደርግ ይችላል።ምሳሌ 12:25

20, 21. ምክር ጥሩ ውጤት እንዲያስገኝ የሚረዱ ነገሮች ምንድን ናቸው?

20 ጥሩ ውጤት የሚያስገኝ ምክር። ፍጽምና የሚጎድለን በመሆናችን ሁላችንም ምክር የሚያስፈልገን ጊዜ ይኖራል። መጽሐፍ ቅዱስ “ምክርን ስማ፤ ተግሣጽን ተቀበል፤ በመጨረሻም ጠቢብ ትሆናለህ” ሲል ይመክረናል። (ምሳሌ 19:20) ሌሎችን የመምከር ኃላፊነት የተሰጠው ለሽማግሌዎች ብቻ አይደለም። ወላጆች ልጆቻቸውን ይመክራሉ። (ኤፌሶን 6:4) የጎለመሱ እህቶች ወጣት እህቶችን መምከር ሊያስፈልጋቸው ይችላል። (ቲቶ 2:3-5) ለሌሎች ያለን ፍቅር የምንመክረው ሰው ቅስሙ ሳይሰበር ምክሩን እንዲቀበል በሚያደርግ መንገድ እንድንመክር ያነሳሳናል። እንዲህ ያለ ምክር እንድንሰጥ ምን ሊረዳን ይችላል? ጥሩ ውጤት የሚያስገኝ ምክር ለመስጠት የሚረዱ ሦስት ነገሮችን እንመልከት፤ እነሱም መካሪው ምክሩን ለመስጠት የተነሳሳበት ምክንያትና ዝንባሌው፣ ለምክሩ መሠረት የሆነው ነገር እንዲሁም ምክሩ የተሰጠበት መንገድ ናቸው።

21 ምክር ጥሩ ውጤት እንዲያስገኝ በመጀመሪያ መካሪው ራሱ ሊያስብባቸው የሚገቡ ነገሮች አሉ። ‘ምክር መቀበል የሚቀለኝ መቼ ነው?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ። የሚመክርህ ሰው እንደሚያስብልህ፣ የብስጭቱ መወጫ እያደረገህ እንዳልሆነና ስውር ዓላማ እንደሌለው ስታውቅ ምክሩን መቀበል ቀላል ይሆንልሃል። አንተም ሌሎችን ስትመክር ምክሩን ለመስጠት ያነሳሳህ ምክንያትና ዝንባሌህ እንዲህ ሊሆን አይገባውም? በተጨማሪም ምክር ጥሩ ውጤት የሚያስገኘው በአምላክ ቃል ላይ የተመሠረተ ከሆነ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በቀጥታ ብንጠቅስም ባንጠቅስም፣ የምንሰጠው ማንኛውም ምክር ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረት ሊኖረው ይገባል። ስለሆነም ሽማግሌዎች ሌሎች የግል አመለካከታቸውን እንዲቀበሉ ላለመጫን፣ ወይም የግል አመለካከታቸውን መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚደግፍላቸው ለማስመሰል ጥቅሶችን ላለማጣመም ይጠነቀቃሉ። በተጨማሪም ምክር ይበልጥ ጥሩ ውጤት የሚያስገኘው በትክክለኛው መንገድ ከተሰጠ ነው። በደግነት የተቀመመ ምክር ለመቀበል የማያስቸግር ከመሆኑም በላይ ምክር የተሰጠው ሰው ክብሩ እንደተነካ ሆኖ እንዳይሰማው ያደርጋል።ቆላስይስ 4:6

22. የንግግር ችሎታህን የምትጠቀምበትን መንገድ በተመለከተ ምን ለማድረግ ቆርጠሃል?

22 በእርግጥም የንግግር ችሎታ ከአምላክ የተገኘ ውድ ስጦታ ነው። ለይሖዋ ያለን ፍቅር ይህን ውድ ስጦታ በአግባቡ እንድንጠቀምበት ሊገፋፋን ይገባል። ለሌሎች የምንናገረው ቃል የመገንባት ወይም የማፍረስ ኃይል እንዳለው እናስታውስ። እንግዲያው ይህን ስጦታ ሰጪው በሚፈልገው መንገድ ማለትም ‘ሌሎችን ለማነጽ’ ለመጠቀም እንጣር። እንዲህ ካደረግን ንግግራችን በዙሪያችን ያሉትን ሁሉ የሚያበረታታና የሚያድስ ከመሆን አልፎ እኛም ከአምላክ ፍቅር ሳንወጣ እንድንኖር ይረዳናል።

^ አን.4ምሳሌ 15:4 ላይ “አታላይ” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል “አጭበርባሪ፣ ጠማማ” ተብሎም ሊተረጎም ይችላል።

^ አን.7 “ከንቱ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል “ፍሬ ቢስ” ተብሎም ተተርጉሟል።1 ጴጥሮስ 1:18

^ አን.10 “ርኩሰት” በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ባለው አገባቡ በርካታ የኃጢአት ዓይነቶችን ሊያካትት የሚችል ሰፊ ትርጉም ያለው ቃል ነው። ሁሉም ዓይነት ርኩሰት በፍርድ ኮሚቴ ሊታይ የሚገባው ባይሆንም አንድ ግለሰብ አስነዋሪ ርኩሰት ፈጽሞ ንስሐ ባይገባ ከጉባኤ ሊወገድ ይችላል።2 ቆሮንቶስ 12:21፤ ኤፌሶን 4:19፤ በተጨማሪም ከሐምሌ 15, 2006 መጠበቂያ ግንብ ላይ “የአንባቢያን ጥያቄዎች” የሚለውን አምድ ተመልከት።