በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ተጨማሪ መረጃ

ንዑሳን የደም ክፍልፋዮችና የቀዶ ሕክምና ሂደቶች

ንዑሳን የደም ክፍልፋዮችና የቀዶ ሕክምና ሂደቶች

ንዑሳን የደም ክፍልፋዮች። ንዑሳን የደም ክፍልፋዮች የሚገኙት ከአራቱ አበይት የደም ክፍልፋዮች ማለትም ከቀይ የደም ሴል፣ ከነጭ የደም ሴል፣ ከፕሌትሌትና ከፕላዝማ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ በቀይ የደም ሴል ውስጥ ሂሞግሎቢን የሚባለው ፕሮቲን ይገኛል። ከሰው ወይም ከእንስሳት ሂሞግሎቢን የሚቀመሙ መድኃኒቶች ከፍተኛ የደም ማነስ ያጋጠማቸውን ወይም በጣም ብዙ ደም የፈሰሳቸውን ሕሙማን ለማከም አገልግለዋል።

ዘጠና በመቶው ውኃ የሆነው ፕላዝማ ማዕድናትንና ስኳርን ጨምሮ በርካታ ሆርሞኖች፣ ኦርጋኒክ ያልሆኑ የጨው ዓይነቶች፣ ኤንዛይሞችና አልሚ ንጥረ ነገሮች ይገኙበታል። በተጨማሪም በፕላዝማ ውስጥ ደም እንዲረጋ የሚያደርጉ ቅመሞች፣ በሽታን ለመከላከል የሚረዱ ፀረ ተሕዋስያንና እንደ አልቡሚን ያሉ ፕሮቲኖች ይገኛሉ። አንድ ሰው ለአንድ ዓይነት በሽታ ሲጋለጥ ዶክተሮች ለዚያ በሽታ መከላከያ ካላቸው ሰዎች ፕላዝማ የተቀመመ ጋማ ግሎቡሊን የሚባል መድኃኒት እንዲወጋ ሊያዙ ይችላሉ። ከነጭ የደም ሴሎች ደግሞ አንዳንድ የቫይረስ ኢንፌክሽኖችንና የካንሰር ዓይነቶችን ለማከም የሚያገለግሉት ኢንተርፌሮንና ኢንተርሉኪን የሚባሉ ንጥረ ነገሮች ይገኛሉ።

ክርስቲያኖች ንዑሳን የደም ክፍልፋዮችን መጠቀምን የሚጠይቁ የሕክምና ዓይነቶችን ይቀበላሉ? መጽሐፍ ቅዱስ ይህን በተመለከተ ቁርጥ ያለ መመሪያ ስለማይሰጥ እያንዳንዱ ግለሰብ ሕሊናውን ተጠቅሞ በአምላክ ፊት የራሱን ውሳኔ ማድረግ አለበት። አንዳንዶች አምላክ ለእስራኤላውያን የሰጠውን፣ ደም ከአንድ ፍጡር ከወጣ “መሬት ላይ [እንዲፈስ]” የሚያዘውን ሕግ በመጥቀስ ማንኛውንም ዓይነት ንዑስ ክፍልፋይ ከመውሰድ ይቆጠባሉ። (ዘዳግም 12:22-24) ሌሎች ደግሞ ሙሉውን ደም ወይም አበይት የደም ክፍልፋዮችን የማይወስዱ መሆናቸው ግልጽ ሆኖ ሳለ፣ ንዑሳን የደም ክፍልፋዮችን መጠቀምን የሚጠይቁ ሕክምናዎችን ለመውሰድ ፈቃደኞች ሊሆኑ ይችላሉ። እነዚህ ሰዎች ከደም የተገኘው ንዑስ ክፍልፋይ በዚህ ደረጃ ላይ የፍጡሩን ሕይወት ሊወክል አይችልም የሚል አመለካከት አላቸው።

ንዑሳን የደም ክፍልፋዮችን በሚመለከት ውሳኔ በምታደርግበት ጊዜ የሚከተሉትን ጥያቄዎች አስብባቸው:- ሁሉንም የደም ንዑሳን ክፍልፋዮች ላለመውሰድ ስወስን፣ በሽታን ለመከላከል ወይም የደም መፍሰስን ለማስቆም ተብለው የሚሰጡ ደምን የሚያረጉ አንዳንድ መድኃኒቶችን ጭምር አልወስድም ማለቴ እንደሆነ ተገንዝቤያለሁ? አንዳንድ ንዑሳን ክፍልፋዮችን ለመውሰድ ፈቃደኛ የማልሆንበትን ወይም የምሆንበትን ምክንያት ለሐኪም ማስረዳት እችላለሁ?

የቀዶ ሕክምና ሂደቶች። ከእነዚህ መካከል ሂሞዳይሉሽንና ሴል ሳልቬጅ የሚባሉት ዘዴዎች ይገኙበታል። ሂሞዳይሉሽን በሚባለው ሂደት አማካኝነት ሕክምና በሚሰጥበት ወቅት የተወሰነ ደም አቅጣጫውን ቀይሮ ወደ ሌላ መሣሪያ እንዲገባ ከተደረገ በኋላ በምትኩ የደምን መጠን የሚጨምር ፈሳሽ ወደ ሕመምተኛው ሰውነት ውስጥ እንዲገባ ይደረጋል። በመጨረሻም የወጣው ደም ወደ ሕመምተኛው ሰውነት እንዲመለስ ይደረጋል። ሴል ሳልቬጅ የሚባለው ሂደት አገልግሎት ላይ በሚውልበት ጊዜ ደግሞ በቀዶ ሕክምናው ወቅት የፈሰሰው ደም ተጠራቅሞ ወደ ሰውነት እንዲመለስ ይደረጋል። ከተቆረጠው ወይም ከተከፈተው የሰውነት ክፍል የሚፈሰው ደም በመሣሪያ ተሰብስቦ ከታጠበ ወይም ከተጣራ በኋላ ወደ ሕመምተኛው እንዲመለስ ይደረጋል። የእነዚህ ሕክምናዎች አሰጣጥ እንደየሐኪሙ ሊለያይ ስለሚችል አንድ ክርስቲያን ዶክተሩ የሚጠቀምበትን ዘዴ ጠይቆ መረዳት ይኖርበታል።

ከእነዚህ የሕክምና ዘዴዎች ጋር በተያያዘ ውሳኔ በምታደርግበት ጊዜ ራስህን እንዲህ ብለህ ጠይቅ:- ‘የተወሰነ ደም ከሰውነቴ ወጥቶ በሌላ መስመር እንዲያልፍ የሚደረግ ምናልባትም ዝውውሩ ለጥቂት ጊዜ የሚቋረጥ ከሆነ፣ ይህን ደም የሰውነቴ ክፍል እንደሆነና “መሬት ላይ [መፍሰስ]” እንደማይገባው አድርጌ ለመመልከት ሕሊናዬ ይፈቅድልኛል? (ዘዳግም 12:23, 24) በአንዳንድ የሕክምና ሂደቶች ወቅት ከሰውነቴ ውስጥ የተወሰነ ደም ተወስዶ አንድ ዓይነት ለውጥ ከተደረገበት በኋላ እንደገና ወደ ሰውነቴ እንዲገባ ቢደረግ በመጽሐፍ ቅዱስ የሠለጠነው ሕሊናዬ ይፈቅድልኛል? የራሴን ደም በመጠቀም የሚሰጡ ሁሉንም የሕክምና ሂደቶች አልቀበልም ስል የደም ምርመራን፣ ሂሞዳያሊስስን ወይም እንደ ልብና ሳንባ ሆኖ የሚያገለግል መሣሪያን መጠቀምን ጭምር አልፈልግም ማለቴ እንደሆነ ተገንዝቤያለሁ?’

አንድ ክርስቲያን በቀዶ ሕክምና ወቅት የራሱን ደም በመጠቀም የሚሰጡትን ሕክምናዎች በተመለከተ የራሱን ውሳኔ ማድረግ ይኖርበታል። በተጨማሪም ትንሽ ደም ከሰውነት ተወስዶ ምናልባትም አንድ ዓይነት ለውጥ ወይም ማስተካከያ ተደርጎበት ወደ ሰውነት በመመለስ የሚሰጡ ሕክምናዎችን እንዲሁም የምርመራ ሂደቶችን በተመለከተም ግለሰቡ የራሱን ውሳኔ ማድረግ አለበት።