በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

መጽሐፍ ቅዱስ ደም መውሰድን አስመልክቶ ምን ይላል?

መጽሐፍ ቅዱስ ደም መውሰድን አስመልክቶ ምን ይላል?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 መጽሐፍ ቅዱስ ደምን ወደ ሰውነታችን ማስገባት እንደሌለብን ይናገራል። በመሆኑም ደምንም ሆነ ዋና ዋና የደም ክፍልፋዮችን በምግብ መልክ፣ በደም ሥር ወይም በሌላ በማንኛውም መንገድ መውሰድ አይኖርብንም። እስቲ የሚከተሉትን ጥቅሶች ተመልከት፦

  •   ዘፍጥረት 9:4 አምላክ፣ ከጥፋት ውኃ በኋላ ኖኅና ቤተሰቡ የእንስሳትን ሥጋ እንዲበሉ የፈቀደላቸው ሲሆን ደሙን ግን እንዳይበሉ ከልክሏቸዋል። አምላክ ኖኅን “ሕይወቱ፣ ማለት ደሙ ገና በውስጡ ያለበትን ሥጋ አትብሉ” ብሎታል። ሁላችንም የኖኅ ዘሮች ስለሆንን ይህ ትእዛዝ ከዚያን ጊዜ አንስቶ ለኖሩ የሰው ልጆች በሙሉ ይሠራል።

  •   ዘሌዋውያን 17:14 “የፍጡር ሁሉ ሕይወት ደሙ ነውና የማንኛውንም ፍጡር ደም አትብሉ፤ የበላው ሰው ሁሉ ተለይቶ ይጥፋ።” አምላክ፣ ነፍስ ወይም ሕይወት በደም ውስጥ እንዳለ እንዲሁም የእሱ ንብረት እንደሆነ ተናግሯል። ይህ ሕግ የተሰጠው ለእስራኤል ብሔር ብቻ ቢሆንም አምላክ ደም መብላትን አስመልክቶ ያለውን ጠንካራ አቋም በግልጽ ያሳያል።

  •   የሐዋርያት ሥራ 15:20 ‘ከደም ራቁ።’ አምላክ ለኖኅ ከሰጠው ሕግ ጋር የሚመሳሰል ትእዛዝ ለክርስቲያኖችም ሰጥቷቸዋል። ከታሪክ መዛግብት መረዳት እንደሚቻለው የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ደምን ለመብልም ሆነ ለሕክምና አይጠቀሙበትም ነበር።

አምላክ ከደም እንድንርቅ ያዘዘን ለምንድን ነው?

 ጉዳዩን ከጤና አንጻር ካየነው ደምን የማንወስድባቸው አጥጋቢ ምክንያቶች አሉ። አምላክ ከደም እንድንርቅ ያዘዘበት ዋነኛ ምክንያት ግን ደምን እንደ ቅዱስ ነገር አድርጎ ስለሚመለከተው ነው።​—ዘሌዋውያን 17:11፤ ቆላስይስ 1:20