የያዕቆብ ደብዳቤ 3:1-18
3 ወንድሞቼ ሆይ፣ ከእናንተ መካከል ብዙዎች አስተማሪዎች አይሁኑ፤ ምክንያቱም እኛ የባሰ ፍርድ እንደምንቀበል* ታውቃላችሁ።+
2 ሁላችንም ብዙ ጊዜ እንሰናከላለንና።*+ በቃል የማይሰናከል ማንም ቢኖር ይህ ሰው መላ ሰውነቱንም መቆጣጠር* የሚችል ፍጹም ሰው ነው።
3 ፈረሶች እንዲታዘዙልን አፋቸው ውስጥ ልጓም ካስገባን መላ ሰውነታቸውንም መምራት እንችላለን።
4 መርከቦችንም ተመልከቱ፦ በጣም ትልቅና በኃይለኛ ነፋስ የሚነዱ ቢሆኑም የመርከቡ ነጂ በትንሽ መሪ ወደሚፈልገው አቅጣጫ ሁሉ ይመራቸዋል።
5 ልክ እንደዚሁም ምላስ ትንሽ የአካል ክፍል ሆና ሳለ ጉራዋን ትነዛለች። በጣም ሰፊ የሆነን ጫካ በእሳት ለማያያዝ ትንሽ እሳት ብቻ ይበቃል!
6 ምላስም እሳት ናት።+ ምላስ በአካል ክፍሎቻችን መካከል የክፋትን ዓለም ትወክላለች፤ መላ ሰውነትን ታረክሳለችና፤+ እንዲሁም መላውን የሕይወት ጎዳና* ታቃጥላለች፤ እሷም በገሃነም* ትቃጠላለች።
7 ማንኛውም ዓይነት የዱር እንስሳ፣ ወፍ፣ በምድር ላይ የሚሳብ ፍጥረትና በባሕር ውስጥ የሚኖር ፍጥረት በሰዎች ሊገራ ይችላል፤ ደግሞም ተገርቷል።
8 ምላስን ግን ሊገራ የሚችል አንድም ሰው የለም። ምላስ ገዳይ መርዝ የሞላባት፣ ለመቆጣጠር የምታስቸግር ጎጂ ነገር ናት።+
9 በምላሳችን አባት የሆነውን ይሖዋን* እናወድሳለን፤ ይሁንና በዚህችው ምላሳችን “በአምላክ አምሳል” የተፈጠሩትን ሰዎች+ እንረግማለን።
10 ከአንድ አፍ በረከትና እርግማን ይወጣሉ።
ወንድሞቼ፣ ይህ መሆኑ ተገቢ አይደለም።+
11 አንድ ምንጭ ከዚያው ጉድጓድ ጣፋጭና መራራ ውኃ ያፈልቃል?
12 ወንድሞቼ፣ የበለስ ዛፍ ወይራን ወይም ደግሞ የወይን ተክል በለስን ሊያፈራ ይችላል?+ ከጨዋማ ውኃም ጣፋጭ ውኃ ሊገኝ አይችልም።
13 ከእናንተ መካከል ጥበበኛና አስተዋይ ሰው ማን ነው? ሥራውን የሚያከናውነው ከጥበብ በመነጨ ገርነት* መሆኑን በመልካም ምግባሩ ያሳይ።
14 ሆኖም በልባችሁ ውስጥ መራራ ቅናትና+ ጠበኝነት*+ ካለ አትኩራሩ፤+ እንዲሁም በእውነት ላይ አትዋሹ።
15 ይህ ከሰማይ የሚመጣ ጥበብ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ምድራዊ፣+ እንስሳዊና አጋንንታዊ ነው።
16 ቅናትና ጠበኝነት* ባለበት ሁሉ ብጥብጥና መጥፎ ነገሮችም ይኖራሉ።+
17 ከሰማይ የሆነው ጥበብ ግን በመጀመሪያ ንጹሕ+ ነው፤ ከዚያም ሰላማዊ፣+ ምክንያታዊ፣+ ለመታዘዝ ዝግጁ የሆነ፣ ምሕረትና መልካም ፍሬዎች የሞሉበት+ እንዲሁም አድልዎና+ ግብዝነት የሌለበት+ ነው።
18 ከዚህም በላይ የጽድቅ ፍሬ ሰላም ፈጣሪ ለሆኑ ሰዎች*+ ሰላማዊ በሆኑ ሁኔታዎች+ ይዘራል።
የግርጌ ማስታወሻዎች
^ ወይም “ፍርዱ እኛ ላይ እንደሚጠብቅ።”
^ ወይም “እንሳሳታለንና።”
^ ወይም “ለመላ ሰውነቱ ልጓም ማስገባት።”
^ የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
^ ወይም “ተፈጥሯዊውን የሕይወት እሽክርክሪት።” ቃል በቃል “የመወለድን እሽክርክሪት።”
^ “ልዝብ፤ ለስላሳ፤ ሸካራ ያልሆነ” የሚል ትርጉም አለው።
^ “የራስ ወዳድነት ምኞት” ማለትም ሊሆን ይችላል።
^ “የራስ ወዳድነት ምኞት” ማለትም ሊሆን ይችላል።
^ “ሰላም ፈጣሪ በሆኑ ሰዎች” ማለትም ሊሆን ይችላል።