ለቆላስይስ ሰዎች የተጻፈ ደብዳቤ 4:1-18

  • ለጌቶች የተሰጠ ምክር (1)

  • “በጽናት ጸልዩ” (2-4)

  • በውጭ ካሉት ጋር በጥበብ ተመላለሱ (5, 6)

  • የስንብት ቃላት (7-18)

4  ጌቶች ሆይ፣ እናንተም በሰማይ ጌታ እንዳላችሁ በመገንዘብ ባሪያዎቻችሁን በጽድቅና በፍትሕ አስተዳድሯቸው።+  በጸሎት ረገድ ዘወትር ንቁ በመሆንና ምስጋና በማቅረብ+ በጽናት ጸልዩ።+  ደግሞም ለእኔ መታሰር ምክንያት የሆነውን ስለ ክርስቶስ የሚገልጸውን ቅዱስ ሚስጥር ማወጅ እንድንችል+ አምላክ የቃሉን በር እንዲከፍትልን ለእኛም ጸልዩልን፤+  ቅዱሱን ሚስጥር የሚገባኝን ያህል በግልጽ እንዳውጅም ጸልዩልኝ።  ጊዜያችሁን በተሻለ መንገድ በመጠቀም* በውጭ ካሉት ጋር* ባላችሁ ግንኙነት በጥበብ መመላለሳችሁን ቀጥሉ።+  ለእያንዳንዱ ሰው እንዴት መልስ መስጠት እንደሚገባችሁ ታውቁ ዘንድ ንግግራችሁ ምንጊዜም በጨው+ የተቀመመ ያህል ለዛ ያለው ይሁን።+  በጌታ ታማኝ አገልጋይና አብሮኝ ባሪያ የሆነው የተወደደው ወንድሜ ቲኪቆስ+ ስለ እኔ ሁሉንም ነገር ይነግራችኋል።  እሱን ወደ እናንተ የምልከው ስላለንበት ሁኔታ እንድታውቁና ልባችሁን እንዲያጽናና ነው።  እናንተ ጋ ከነበረው ከታማኙና ከተወደደው ወንድሜ ከአናሲሞስ+ ጋር ይመጣል፤ እነሱም እዚህ እየተከናወነ ስላለው ነገር ሁሉ ያሳውቋችኋል። 10  አብሮኝ የታሰረው አርስጥሮኮስ+ ሰላምታ ያቀርብላችኋል፤ የበርናባስ ዘመድ* የሆነው ማርቆስም+ ሰላም ብሏችኋል (እሱን በተመለከተ ወደ እናንተ ከመጣ እንድትቀበሉት+ መመሪያ ደርሷችኋል)፤ 11  ኢዮስጦስ ተብሎ የሚጠራው ኢየሱስም ሰላምታ ያቀርብላችኋል፤ እነዚህ ከተገረዙት ወገን ናቸው። ለአምላክ መንግሥት አብረውኝ የሚሠሩት እነዚህ ብቻ ናቸው፤ እነሱም የብርታት ምንጭ ሆነውልኛል።* 12  ከእናንተ ጋር የነበረው የክርስቶስ ኢየሱስ ባሪያ የሆነው ኤጳፍራ+ ሰላምታ ልኮላችኋል። በአምላክ ፈቃድ ሁሉ ፍጹምና* ጽኑ እምነት ያላችሁ ሆናችሁ እስከ መጨረሻው እንድትቆሙ ዘወትር በጸሎቱ ስለ እናንተ እየተጋደለ ነው። 13  ስለ እናንተ እንዲሁም በሎዶቅያና በሂራጶሊስ ስላሉት ብዙ እንደሚደክም እኔ ራሴ እመሠክርለታለሁ። 14  የተወደደው ሐኪም ሉቃስ+ ሰላምታ ያቀርብላችኋል፤ ዴማስም+ ሰላም ብሏችኋል። 15  በሎዶቅያ ላሉት ወንድሞችና ለንምፉን እንዲሁም በቤቷ ላለው ጉባኤ+ ሰላምታዬን አቅርቡልኝ። 16  እንዲሁም ይህ ደብዳቤ እናንተ ጋ ከተነበበ በኋላ በሎዶቅያውያን ጉባኤ እንዲነበብና ከሎዶቅያ የሚደርሳችሁ ደብዳቤ ደግሞ እናንተ ጋ እንዲነበብ ዝግጅት አድርጉ።+ 17  በተጨማሪም አርክጳን+ “በጌታ የተቀበልከውን አገልግሎት ከፍጻሜ እንድታደርስ ለአገልግሎቱ ትኩረት ስጥ” በሉት። 18  እኔ ጳውሎስ በገዛ እጄ የጻፍኩላችሁ ሰላምታ ይድረሳችሁ።+ በሰንሰለት ታስሬ+ እንዳለሁ አስታውሱ። የአምላክ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “አመቺ የሆነውን ጊዜ በመግዛት።”
ወይም “የክርስቲያን ጉባኤ አባል ካልሆኑ ሰዎች ጋር።”
የበርናባስ የአጎቱ ወይም የአክስቱ ልጅ ሊሆን ይችላል።
ወይም “በእጅጉ አጽናንተውኛል።”
ወይም “ጎልማሳና።”