በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መከራ

መከራ

ፍቺ:- አንድ ሰው ሕመም ወይም ጭንቀት በሚያጋጥመው ጊዜ የሚደርስበት ሁኔታ ነው። መከራው በአካል፣ በአእምሮ ወይም በስሜት ላይ የሚደርስ ሊሆን ይችላል። ለመከራ ምክንያት የሚሆኑት ነገሮች ብዙ ናቸው። ለምሳሌ ያህል ጦርነትና በንግድ ስግብግብነት ምክንያት የሚደርስ ጉዳት፣ በዘር የሚወረሱ ባሕርያት፣ በሽታ፣ ድንገተኛ አደጋ፣ “የተፈጥሮ አደጋዎች”፣ ሰዎች ደግነት በጎደለው ሁኔታ የሚናገሯቸው ወይም የሚያደርጓቸው ነገሮች፣ የአጋንንት ተጽዕኖዎች፣ መጥፎ ሁኔታ እንደሚመጣ በመገንዘብ ወይም በራስ ስህተት ምክንያት መከራ ሊያጋጥም ይችላል። እዚህ ላይ በእነዚህ የተለያዩ ምክንያቶች ሊመጡ የሚችሉትን መከራዎች እንመረምራለን። ይሁን እንጂ አንድ ሰው የሌሎች ሰዎችን ችግርና ኀዘን ወይም አምላካዊ ያልሆነ ጠባይ በመመልከት ሊሠቃይ ይችላል።

  አምላክ መከራ እንዲኖር የፈቀደው ለምንድን ነው?

ለዚህ በኃላፊነት የሚጠየቀው ማን ነው?

ለብዙዎቹ መከራዎች ተጠያቂዎቹ ሰዎች ራሳቸው ናቸው። ይዋጋሉ፣ ወንጀል ይፈጽማሉ፣ አካባቢአቸውን ይበክላሉ። ብዙውን ጊዜ ለሌሎች ሰዎች አሳቢነት በጎደለውና ስግብግብነት በተሞላበት መንፈስ ይነግዳሉ። አንዳንድ ጊዜም በራሳቸው ጤንነት ላይ ጉዳት እንደሚያስከትሉ የሚያውቋቸውን ልማዶች ይፈጽማሉ። የሰው ልጆች የሚያደርጓቸው ነገሮች ጉዳት ሊያስከትሉባቸው አይችሉም ብሎ ማሰብ ይቻላልን? (ገላ. 6:7፤ ምሳሌ 1:30–33) ታዲያ እነዚህ ሰዎች ራሳቸው ለሚያደርጓቸው ነገሮች አምላክን ቢያማርሩ ምክንያታዊ ይሆናልን?

ሰይጣንና አጋንንቱም ተጠያቂዎች ናቸው። ብዙ መከራ የሚደርሰው በክፉ መናፍስት ተጽዕኖ ምክንያት እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። ብዙ ሰዎች አምላክን የሚወቅሱባቸው መከራዎች አምላክ ያመጣቸው አይደሉም።—ራእይ 12:12፤ ሥራ 10:38፤ በተጨማሪም በገጽ 362, 363 ላይ “ሰይጣን ዲያብሎስ” በሚለው ርዕስ ሥር ተመልከት።

 መከራ የመጣው እንዴት ነው? የመከራን መንስዔዎች ለማወቅ የምናደርገው ምርመራ በመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን በአዳምና በሔዋን ላይ ያተኩራል። ይሖዋ አምላክ አዳምንና ሔዋንን ፍጹም አድርጎ ፈጥሮ ገነት በሆነ አካባቢ አኖራቸው። አምላክን ቢታዘዙ ኖሮ ፈጽሞ አይታመሙም ወይም አይሞቱም ነበር። ለዘላለም በሰብዓዊ ሕይወትና በፍጽምና እየተደሰቱ ይኖሩ ነበር። የሰው ልጅ እየተሠቃየ እንዲኖር የይሖዋ ዓላማ አልነበረም። ይሁን እንጂ ይሖዋ የሰው ልጆች አምላክ በሰጣቸው በረከቶች በመደሰት መቀጠላቸው በታዛዥነታቸው ላይ የተመካ መሆኑን ለአዳም በግልጽ ነግሮታል። በሕይወት ለመኖር እንዲቀጥሉ መተንፈስ፣ መብላት፣ መጠጣትና መተኛት እንደነበረባቸው ግልጽ ነው። ከሕይወት ሙሉ ደስታ ለማግኘትና ለዘላለም ለመኖር የአምላክን የሥነ ምግባር ሕግጋት መጠበቅ ነበረባቸው። እነርሱ ግን በራሳቸው መንገድ ለመሄድ፣ መልካምና ክፉ ስለሆነው ነገር የራሳቸውን የአቋም ደረጃ ለማውጣት መረጡ። ሕይወት ሰጪ ከሆነው ከይሖዋ አምላክም ራቁ። (ዘፍ. 2:16, 17፤ 3:1–6) ኃጢአት ሞት አመጣባቸው። አዳምና ሔዋን ልጅ መውለድ የጀመሩት ኃጢአተኞች ከሆኑ በኋላ ነበር። በዚህም ምክንያት ራሳቸው የሌላቸውን ነገር ለልጅ ልጆቻቸው ሊያስተላልፉ አልቻሉም። የሰው ልጆች በሙሉ ስህተት የሆነውን ነገር የማድረግ ዝንባሌ፣ ወደ በሽታ የሚመራ ድካም በመጨረሻም ሞት የሚያስከትል የኃጢአት ውርሻ ያላቸው ሆነው ተወለዱ። በዛሬው ጊዜ በምድር ላይ የሚኖር ሰው ሁሉ በኃጢአት የተወለደ ስለሆነ ሁላችንም በተለያዩ መንገዶች እንሠቃያለን።—ዘፍ. 8:21፤ ሮሜ 5:12

በተጨማሪም “ጊዜና ያልታሰበ አጋጣሚ” በሚደርስብን ነገር ላይ ተጽዕኖ እንደሚኖራቸው መክብብ 9:11 (አዓት ) ይናገራል። በዲያብሎስ ወይም በሌላ ሰው ምክንያት ሳይሆን በአጋጣሚ ብቻ አንድ ስፍራ በአጉል ጊዜ ላይ ስለተገኘን ጉዳት ሊደርስብን ይችላል።

አምላክ የሰው ልጆች ከመከራ እንዲገላገሉ ለምን አንድ ነገር አያደርግም? ሁላችንም አዳም ባጠፋው ጥፋት መሠቃየት የሚኖርብን ለምንድን ነው?

አምላክ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዴት ከብዙ ሥቃይ ልንድን እንደምንችል ይነግረናል። ስለ አኗኗር ዘዴ በጣም ጥሩ ምክር ይሰጠናል። እነዚህን ምክሮች በሥራ ላይ ስናውል ሕይወታችን ትርጉም ያለው፣ ቤተሰባችንም ደስታ የሰፈነበት ይሆናል። እርስ በርሳቸው ከልብ ከሚዋደዱ ሰዎች ጋር የተቀራረበ ኅብረት እንዲኖረን ያስችላል። አስፈላጊ ባልሆነ ምክንያት አካላዊ ሥቃይ የሚያደርስብንን ድርጊት እንዳንፈጽም ይጠብቀናል። ይህን እርዳታ ሳንቀበል ቀርተን በራሳችን ላይም ሆነ በሌሎች ላይ ለምናመጣው መከራ አምላክን መውቀስ ተገቢ ይሆናልን?—2 ጢሞ. 3:16, 17፤ መዝ. 119:97–105

ይሖዋ መከራን ሁሉ ለማቆም አንድ ዝግጅት አድርጓል። አምላክ የመጀመሪያዎቹን ባልና ሚስት ፍጹም አድርጎ ፈጥሯቸዋል። በተጨማሪም ሕይወታቸው ደስታ የሞላበት እንዲሆን የሚያስችለውን ዝግጅት ሁሉ አድርጎላቸዋል። ሆን ብለው በፈቃዳቸው በአምላክ ላይ ጀርባቸውን ሲያዞሩ አምላክ ልጆቻቸውን የወላጆቻቸው ድርጊት ካስከተለባቸው ውጤት የመከላከል ግዴታ ይኖርበታልን? (ዘዳ. 32:4, 5፤ ኢዮብ 14:4) ባልና ሚስት ልጆችን መውለድ የሚያመጣውን ደስታ የማግኘት መብት ቢኖራቸውም ልጆች መውለዳቸው ኃላፊነት እንደሚያስከትልባቸው በሚገባ እናውቃለን። ወላጆች የሚኖራቸው ዝንባሌና የሚያደርጉት ድርጊት በልጆቻቸው ላይ የሚያስከትለው ውጤት ይኖራል። ይሁን እንጂ ይሖዋ አምላክ በጣም አስደናቂ በሆነና ይገባናል በማንለው ደግነቱ ተገፋፍቶ በጣም የሚወደውን ልጁን ሕይወቱን ቤዛ አድርጎ እንዲከፍልና በዚህ ዝግጅት የሚያምኑትን የአዳም ልጆች ከመከራ እንዲገላግላቸው ወደ ምድር ልኮታል። (ዮሐ. 3:16) በዚህም ምክንያት በዛሬው ዘመን ለሚኖሩ ሰዎች ሁሉ አዳም ያጣውን ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወት መከራ በሌለበት ገነታዊ ምድር የማግኘት አጋጣሚ ተከፍቷል። እንዴት ያለ ለጋስነት የሞላበት ዝግጅት ነው!

በተጨማሪም በገጽ 306–308 ላይ “ቤዛ” በሚለው ርዕስ ሥር ተመልከት።

ይሁን እንጂ የፍቅር አምላክ ይህን ለሚያህል ጊዜ መከራ እንዲቀጥል የፈቀደው ለምንድን ነው?

መከራ እስከ ዛሬ ድረስ እንዲኖር በመፍቀዱ ጥቅም አግኝተናልን? “ለአንዳንዶች የሚዘገይ እንደሚመስላቸው ጌታ ስለ ተስፋ ቃሉ አይዘገይም፣ ነገር ግን ሁሉ ወደ ንስሐ እንዲደርሱ እንጂ ማንም እንዳይጠፋ ወዶ ስለ እናንተ ይታገሣል።” (2 ጴጥ. 3:9) አምላክ አዳምና ሔዋን ወዲያው እንዳጠፉ ገድሏቸው ቢሆን ኖሮ ዛሬ ማናችንም ብንሆን በሕይወት አንገኝም ነበር። ማናችንም ብንሆን ይህ እንዲደርስብን አንፈልግም። ከዚህም በላይ አምላክ ጥቂት ቆየት ብሎ ኃጢአተኞችን በሙሉ ቢያጠፋ ኖሮ እኛ ተወልደን ለመኖር አንችልም ነበር። አምላክ ይህ ኃጢአተኛ ዓለም እስከ ዛሬ እንዲኖር መፍቀዱ በሕይወት ኖረን መንገዶቹን እንድናውቅ፣ በሕይወታችን ውስጥ አስፈላጊዎቹን ለውጦች እንድናደርግና ለዘላለም ሕይወት ካዘጋጃቸው ፍቅራዊ ዝግጅቶች እንድንጠቀም አስችሎናል። ይሖዋ ይህንን አጋጣሚ መስጠቱ ታላቅ ፍቅር እንዳለው ያሳያል። አምላክ ይህንን ክፉ ሥርዓት የሚያጠፋበት ጊዜ እንደወሰነና በቅርቡም እንደሚያጠፋ መጽሐፍ ቅዱስ ያመለክታል።—ዕን. 2:3፤ ሶፎ. 1:14

አምላክ በዚህ ሥርዓት ውስጥ በአገልጋዮቹ ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ሁሉ ለማስወገድ ይችላል፣ ያስወግዳልም። በሰው ልጆች ላይ መከራ የሚያመጣው አምላክ አይደለም። አምላክ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ሙታንን ያስነሣል፤ ታዛዥ የሆኑ ሰዎችን ከሕመማቸው ሁሉ ይፈውሳል፤ ኃጢአት ያስከተለውን ውጤት በሙሉ ያስወግዳል፤ ከዚህ በፊት አጋጥሞን የነበረውን ኀዘን እንኳ ከአእምሮአችን ፈጽሞ እንዲጠፋ ያደርጋል።—ዮሐ. 5:28, 29፤ ራእይ 21:4፤ ኢሳ. 65:17

እስከ አሁን ያለፈው ጊዜ በኤደን ለተነሣው ጥያቄ መልስ ለማስገኘት አገልግሏል። ዝርዝር ማብራሪያ ለማግኘት ገጽ 362, 363⁠ን እንዲሁም 428–430⁠ን ተመልከት።

በየግላችን ከአሁኑ ሥቃይ ለመገላገል እንጓጓለን። አምላክ ግን እርምጃ የሚወስደው ትክክል የሆነውን ለሚወዱ ሰዎች ሁሉ በሚጠቅም መንገድ ነው እንጂ ለጥቂቶች ብቻ ሲል አይደለም። አምላክ አያዳላም።—ሥራ 10:34

ምሳሌ:- ልጁን የሚወድ ወላጅ በኋላ የሚገኘውን ጥቅም አሻግሮ በመመልከት ልጁ ቀዶ ሕክምና እንዲደረግለትና ይህም የሚያስከትለውን ሥቃይ እንዲቀበል ይፈቅድ የለምን? በተጨማሪም የሕመም ስሜቶችን ለማስታገሥ ብቻ የሚደረጉ “የችኮላ እርምጃዎች” ዘላቂ መፍትሔ የማያስገኙ መሆናቸው የታወቀ አይደለምን? አብዛኛውን ጊዜ የበሽታውን ችግር ከሥሩ ለመንቀል ረዘም ያለ ጊዜ ያስፈልጋል።

አምላክ ለአዳም ይቅርታ አድርጎለት በሰው ልጆች ላይ የደረሰውን አሳረ መከራ እንዳይደርስ ያላደረገው ለምንድን ነው?

ይህን ማድረጉ እውነት መከራን ያስቀራል ወይስ ለሚደርሰው መከራ አምላክ ተጠያቂ እንዲሆን ያደርጋል? አንድ አባት ልጆቹ ስህተት ሲሠሩ ተመልክቶ ጠንከር ያለ የቅጣት ርምጃ ከመውሰድ ይልቅ ዝም ብሎ ቢተዋቸው ምን ይሆናሉ? ልጆቹ ከአንድ ጥፋት ወደ ሌላ ጥፋት እየተሸጋገሩ ይሄዳሉ። ለዚህም በአብዛኛው ተጠያቂ የሚሆነው አባትዬው ይሆናል።

በተመሳሳይም ይሖዋ አዳም ሆን ብሎ የሠራውን ኃጢአት ይቅር ቢል ኖሮ አምላክ የጥፋቱ ተባባሪ ይሆናል። ይህ ደግሞ በምድር ላይ የተሻለ ሁኔታ እንዲኖር አያደርግም። (ከ⁠መክብብ 8:11 ጋር አወዳድር።) ከዚህም በላይ መላእክታዊ ልጆቹ አምላክን ያቃልሉት ነበር። የተሻለ ሁኔታ ይመጣል ብሎ ለማመን የሚያስችል ምክንያት አይኖርም ነበር። ይሁን እንጂ የይሖዋ አገዛዝ በማይናወጥ ጽድቅ ላይ የተመሠረተ ስለሆነ እንዲህ ያለው ሁኔታ ሊኖር አይችልም።—መዝ. 89:14

ልጆች ከባድ የአካልና የአእምሮ ጉድለት ኖሯቸው እንዲወለዱ አምላክ የሚፈቅደው ለምንድን ነው?

እንደነዚህ ያሉ ጉድለቶች እንዲኖሯቸው የሚያደርገው አምላክ አይደለም። የመጀመሪያዎቹን ባልና ሚስት ፍጹም አድርጎ ከመፍጠሩም በላይ እነርሱን የሚመስሉ ፍጹማን ልጆች የማስገኘት ችሎታ እንዲኖራቸው አድርጎ ነበር።—ዘፍ. 1:27, 28

ከአዳም ኃጢአት ወርሰናል። ይህ ውርሻ የአካልና የአእምሮ ጉድለት የማስከተል ችሎታ አለው። (ሮሜ 5:12፤ ለተጨማሪ ማብራሪያ  ገጽ 392, 393⁠ን ተመልከት።) ይህ የኃጢአት ውርሻ ከተፀነስንበት ጊዜ ጀምሮ አብሮን ይኖራል። ንጉሥ ዳዊት “እናቴ በኃጢአት ፀነሰችኝ” ያለው በዚህ ምክንያት ነው። (መዝ. 51:5 አዓት ) አዳም ኃጢአት ባይሠራ ኖሮ ለዘሮቹ ጥሩ ጥሩ ባሕርያትን ብቻ ያስተላልፍ ነበር። (በ⁠ዮሐንስ 9:1, 2 ላይ ስለ ተሰጠው ሐሳብ ለመረዳት ገጽ 318⁠ን ተመልከት።)

ወላጆች ባልተወለዱ ልጆቻቸው ላይ ጉዳት ሊያስከትሉ ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል በእርግዝና ጊዜ አደንዛዥ ዕፅ መውሰድ ወይም ሲጋራ ማጨስ በፅንስ ላይ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል። እርግጥ በሕፃናት ላይ አካለ ጎዶሎነትና የጤና መቃወስ የሚደርሰው ሁልጊዜ በእናት ወይም በአባት ስህተት እንዳልሆነ የታወቀ ነው።

ይሖዋ በፍቅር ተነሣቶ ልጆች የክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ተጠቃሚዎች እንዲሆኑ አድርጓል። ትናንሽ ልጆችን እርሱን በታማኝነት በሚያገለግሉት ወላጆቻቸው ምክንያት እንደ ቅዱስ አድርጎ ይመለከታቸዋል። (1 ቆሮ. 7:14) ይህም ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ወላጆች ለልጆቻቸው ባላቸው ፍቅራዊ አሳቢነት በመነሣሣት በአምላክ ዘንድ ስላላቸው አቋም ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ይገፋፋቸዋል። በአምላክ ለማመንና የአምላክን ትእዛዛት ለመፈጸም በሚያስችል ዕድሜ ላይ ለደረሱ ልጆችም የአምላክን ሞገስ አግኝቶ አገልጋዮቹ የመሆን መብት ተከፍቶላቸዋል። (መዝ. 119:9፤ 148:12, 13፤ ሥራ 16:1–3) የአባቱ ፍጹም ነጸብራቅ የነበረው ኢየሱስ ለልጆች ደህንነት አጥብቆ ያስብ እንደነበረና እንዲያውም አንዲትን ትንሽ ልጅ ከሞት አስነሥቶ እንደነበረ ማስታወስ ተገቢ ነው። መሲሐዊ ንጉሥ በሚሆንበት ጊዜ ይህንኑ በበለጠ ሁኔታ እንደሚያደርግ የተረጋገጠ ነው።—ማቴ. 19:13–15፤ ሉቃስ 8:41, 42, 49–56

አምላክ በንብረትና በሕይወት ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትል “የተፈጥሮ አደጋ” እንዲደርስ የሚፈቅደው ለምንድን ነው?

በዛሬው ጊዜ በዜና ማሰራጫዎች አዘውትረን የምንሰማቸውን የምድር መናወጦች፣ አውሎ ነፋሶች፣ የውኃ መጥለቅለቆች፣ ድርቆችና የእሳተ ገሞራ ፍንዳታዎች የሚያመጣው አምላክ አይደለም። አንዳንድ ሕዝቦችን ለመቅጣት በእነዚህ አደጋዎች አይጠቀምም። እነዚህ የተፈጥሮ አደጋዎች አብዛኛውን ጊዜ የሚደርሱት ምድር ከተፈጠረችበት ጊዜ ጀምሮ በሥራ ላይ በሚገኙ የተፈጥሮ ኃይሎች ምክንያት ነው። በዘመናችን የምድር መናወጥና ረሀብ እንደሚበዛ መጽሐፍ ቅዱስ ተንብዮአል። ይሁን እንጂ ይህ ማለት እነዚህን ነገሮች ያመጣው አምላክ ወይም ኢየሱስ ነው ማለት አይደለም። አንድ የአየር ሁኔታን የሚተነብይ ሰው ለሚመጣው የአየር ለውጥ ኃላፊ ሊሆን አይችልም። እነዚህ ሁሉ የሥርዓቱ ፍጻሜ ምልክት እንደሚሆን ትንቢት ከተነገረለት ብዙ ነገሮችን አጣምሮ የያዘ ምልክት ክፍል ስለሆኑ የአምላክ መንግሥት የምታመጣቸው በረከቶች ቅርብ መሆናቸውን ያረጋግጣሉ።—ሉቃስ 21:11, 31

አብዛኛውን ጊዜ ለሚደርሰው ጉዳት በኃላፊነት መጠየቅ የሚኖርባቸው ሰዎች ናቸው። በምን መንገድ? ብዙ ሰዎች በቂ ማስጠንቀቂያ ቢሰጥም እንኳ አደገኛ ከሆነው አካባቢ ለመራቅ ወይም አስፈላጊ የሆኑ ጥንቃቄዎችን ለማድረግ ፈቃደኞች አይሆኑም።—ምሳሌ 22:3፤ ከ⁠ማቴዎስ 24:37–39 ጋር አወዳድር።

እንደነዚህ ያሉትን የተፈጥሮ ኃይሎች አምላክ ሊቆጣጠራቸው ይችላል። በገሊላ ባሕር ላይ የተነሣውን የባሕር ሞገድ ጸጥ እንዲያደርግ ለኢየሱስ ክርስቶስ ኃይል ሰጥቶት ነበር። ይህም ኢየሱስ በመሲሐዊ መንግሥቱ ጊዜ ለሰው ልጆች ምን ሊያደርግ እንደሚችል ምሳሌ ይሆናል። (ማር. 4:37–41) አዳም ጀርባውን በአምላክ ላይ በማዞሩ አምላክ ለእርሱም ሆነ ለልጆቹ ሲል ጣልቃ ገብቶ እነዚህን አደጋዎች እንዲያስወግድ አለመፈለጉን አሳይቷል። በክርስቶስ መሲሐዊት ግዛት ዘመን ሕይወት የሚያገኙ ሁሉ የአምላክ ኃይል የተሰጠው መንግሥት ብቻ ሊሰጥ የሚችለውን ፍቅራዊ እንክብካቤ ያገኛሉ።—ኢሳ. 11:9

ሰዎች መከራና ሥቃይ የሚደርስባቸው አምላክ በክፋታቸው ምክንያት ሲቀጣቸው ነውን?

አምላካዊ የአኗኗር ደረጃዎችን የማይጠብቁ ሰዎች መጥፎ ነገር ይደርስባቸዋል። (ገላ. 6:7) አንዳንድ ጊዜ በአጭር ጊዜ ውስጥ መራራ ዋጋቸውን ይቀበላሉ። በሌሎች ጊዜያት ደግሞ ረዘም ላለ ጊዜ ብልጽግና ያገኙ መስለው ሊታዩ ይችላሉ። በሌላ በኩል ደግሞ እንደነዚህ ካሉት ሰዎች ፈጽሞ የተለየውና ምንም ዓይነት ስህተት ፈጽሞ የማያውቀው ኢየሱስ ክርስቶስ ብዙ መከራ ደርሶበት ተገድሏል። ስለዚህ በዚህ የነገሮች ሥርዓት ውስጥ ብልጽግና የአምላክ በረከት፣ መከራ ደግሞ የአምላክ ቁጣ ምልክት ሆኖ መታየት አይገባውም።

ኢዮብ ንብረቱን ሁሉ ያጣውና በጣም አሰቃቂ በሆነ በሽታ የተሠቃየው አምላክ ስለተከፋበት አይደለም። በኢዮብ ላይ ለደረሰው መከራ ሁሉ ኃላፊው ሰይጣን እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ይናገራል። (ኢዮብ 2:3, 7, 8) ኢዮብን ሊጠይቁት የመጡት ጓደኞቹ ግን ኢዮብ ችግር የደረሰበት አንድ የሠራው ክፉ ነገር ቢኖር ነው ብለው ተከራክረዋል። (ኢዮብ 4:7–9፤ 15:6, 20–24) ይሖዋ ግን እንደሚከተለው በማለት ገሥጿቸዋል:- “እንደ ባሪያዬ እንደ ኢዮብ ቅንን ነገር ስለ እኔ አልተናገራችሁምና ቁጣዬ በአንተና በሁለቱ ባልንጀሮችህ ላይ ነድዶአል።”—ኢዮብ 42:7

እንዲያውም ክፉ ሰዎች ለጥቂት ጊዜ ሊበለጽጉ ይችላሉ። አሳፍ እንዲህ በማለት ጽፏል:- “የኃጢአተኞችን ሰላም አይቼ በዓመፀኞች ቀንቼ ነበርና። እንደ ሰው በድካም አልሆኑም፣ ከሰው ጋርም አልተገረፉም። አስበው ክፉ ነገርን ተናገሩ፤ ከፍ ከፍ ብለውም በዓመፃ ተናገሩ። እነሆ፣ እነዚህ ኃጢአተኞች ይደሰታሉ፣ ሁልጊዜም ባለጠግነታቸውን ያበዛሉ።”—መዝ. 73:3, 5, 8, 12

አምላክ ለእያንዳንዱ እንደ ሥራው የሚከፍልበት ጊዜ ይመጣል። በዚያ ጊዜ ክፉዎችን ለዘላለም በማጥፋት ይቀጣቸዋል። ምሳሌ 2:21, 22 እንዲህ ይላል:- “ቅኖች በምድር ላይ ይቀመጣሉና፣ ፍጹማንም በእርስዋ ይኖራሉና፤ ኀጥኣን ግን ከምድር ይጠፋሉ፣ ዓመፀኞችም ከእርስዋ ይነጠቃሉ።” ብዙ መከራና ችግር ሲደርስባቸው የቆዩ ቅን ሰዎች ከዚያ በኋላ ፍጹም ጤንነት አግኝተው ከተትረፈረፈው የምድር በረከት ይካፈላሉ።

አንድ ሰው እንዲህ ቢልስ:-

‘አምላክ ይህ ሁሉ መከራ እንዲደርስ የሚፈቅደው ለምንድን ነው?’

እንዲህ በማለት ልትመልስ ትችላለህ:- ‘ይህ ሁላችንንም የሚያሳስበን ጉዳይ ነው። ግን ዛሬ ይህን ጥያቄ እንዲያነሡ ያደረገዎት ነገር ምን እንደሆነ ይነግሩኛል?’ ከዚያም ምናልባት እንዲህ በማለት ልትቀጥል ትችላለህ:- (1) ‘( ገጽ 392–395 ላይ በቀረበው ማብራሪያ ተጠቀም።)’ (2) ‘(ግለሰቡ ላይ መከራ ያስከተለበት ሁኔታ እንደሚወገድ የሚገልጹ ሌሎች ጥቅሶችን ጥቀስለት።)’

ወይም እንዲህ ማለት ትችላለህ (ግለሰቡን ያሳሰበው ነገር በዓለም ውስጥ የሚታየው የፍትሕ መጓደል ከሆነ):- ‘እንደነዚህ ያሉ ሁኔታዎች ዛሬ የኖሩት ለምን እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ያስረዳል። (መክ. 4:1፤ 8:9) አምላክ ከዚህ እንድንገላገል ምን እንደሚያደርግ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገር ያውቃሉ? (መዝ. 72:12, 14፤ ዳን. 2:44)’

ሌላ አማራጭ:- ‘በአምላክ የሚያምኑ ሰው እንደሆኑ ግልጽ ነው። አምላክ ፍቅር እንደሆነ ያምናሉ? . . . አምላክ ጥበበኛ እንደሆነና ሁሉን ማድረግ የሚችል አምላክ እንደሆነስ ያምናሉ? . . . ከሆነ መከራ እንዲኖር የፈቀደበት ጥሩ ምክንያት መኖር አለበት ብለው የሚያስቡ ይመስለኛል። እነዚህ ምክንያቶች ምን እንደሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። ( ገጽ 392–395⁠ን ተመልከት።)’