መክብብ 8:1-17

  • ፍጽምና የጎደለው የሰው አገዛዝ (1-17)

    • “የንጉሥን ትእዛዝ አክብር” (2-4)

    • “ሰው ሰውን የገዛው ለጉዳቱ ነው” (9)

    • አፋጣኝ ፍርድ ሳይሰጥ ሲቀር (11)

    • ብላ፣ ጠጣ ደግሞም ተደሰት (15)

8  እንደ ጥበበኛው ሰው ያለ ማን ነው? የአንድን ችግር መፍትሔ* የሚያውቅ ማን ነው? የሰው ጥበብ ፊቱ እንዲበራ እንዲሁም ኮስታራ ፊቱ እንዲፈታ ታደርጋለች።  እኔም እንዲህ እላለሁ፦ “በአምላክ ፊት በገባኸው መሐላ+ የተነሳ የንጉሥን ትእዛዝ አክብር።+  ከንጉሡ ፊት ለመውጣት አትቸኩል።+ መጥፎ የሆነውን ነገር ሁሉ አትደግፍ፤+ እሱ ደስ ያሰኘውን ሁሉ ማድረግ ይችላልና፤  ምክንያቱም የንጉሥ ቃል የማይሻር ነው፤+ ‘ምን ማድረግህ ነው?’ ሊለው የሚችል ማን ነው?”  ትእዛዛትን የሚጠብቅ ሰው ጉዳት አይደርስበትም፤+ ጥበበኛ ልብም ትክክለኛውን ጊዜና አሠራር* ያውቃል።+  የሰው ልጆች ብዙ መከራ ቢኖርባቸውም ማንኛውም ጉዳይ ትክክለኛ ጊዜና አሠራር* አለው።+  ወደፊት የሚሆነውን ነገር የሚያውቅ ሰው ስለሌለ ይህ እንዴት እንደሚሆን ሊነግረው የሚችል ማን ነው?  በመንፈስ* ላይ ሥልጣን ያለው ወይም መንፈስን መግታት የሚችል ሰው እንደሌለ ሁሉ በሞት ቀን ላይም ሥልጣን ያለው የለም።+ በጦርነት ጊዜ ከግዳጅ የሚሰናበት እንደሌለ ሁሉ ክፋትም ክፋት የመሥራት ልማድ ያላቸውን ሰዎች እንዲያመልጡ ዕድል አይሰጣቸውም።*  ይህን ሁሉ የተገነዘብኩት ከፀሐይ በታች የተሠራውን ሥራ ሁሉ በልቤ ከመረመርኩ በኋላ ነው። በዚህ ሁሉ ወቅት ሰው ሰውን የገዛው ለጉዳቱ* ነው።+ 10  ደግሞም ወደ ቅዱሱ ስፍራ ይገቡና ይወጡ የነበሩት ክፉዎች ሲቀበሩ አይቻለሁ፤ ይሁንና ይህን ባደረጉበት ከተማ ወዲያው ተረሱ።+ ይህም ቢሆን ከንቱ ነው። 11  በክፉ ሥራ ላይ በአፋጣኝ ፍርድ ስለማይሰጥ+ የሰው ልጆች ልብ ክፉ ነገር ለማድረግ ተደፋፈረ።+ 12  ኃጢአተኛ መቶ ጊዜ መጥፎ ነገር እየሠራ ረጅም ዘመን ቢኖር እንኳ እውነተኛውን አምላክ የሚፈሩ ሰዎች አምላክን በመፍራታቸው የኋላ ኋላ መልካም እንደሚሆንላቸው ተረድቻለሁ።+ 13  ክፉ ሰው ግን አምላክን ስለማይፈራ የኋላ ኋላ መልካም አይሆንለትም፤+ እንደ ጥላ የሆነውን የሕይወት ዘመኑንም ማራዘም አይችልም።+ 14  በምድር ላይ የሚፈጸም አንድ ከንቱ* ነገር አለ፦ ክፉ እንደሠሩ ተደርገው የሚታዩ ጻድቃን አሉ፤+ ጽድቅ እንደሠሩ ተደርገው የሚታዩ ክፉ ሰዎችም አሉ።+ ይህም ቢሆን ከንቱ ነው እላለሁ። 15  በመሆኑም ደስታ መልካም ነው አልኩ፤+ ምክንያቱም ለሰው ከፀሐይ በታች ከመብላትና ከመጠጣት እንዲሁም ከመደሰት የተሻለ ነገር የለም፤ ከፀሐይ በታች እውነተኛው አምላክ በሚሰጠው የሕይወት ዘመን በትጋት ሲሠራ ይህ ደስታ ሊርቀው አይገባም።+ 16  ቀንም ሆነ ሌሊት እንቅልፍ በዓይኔ ሳይዞር* ጥበብን ለማግኘትና በምድር ላይ ያለውን እንቅስቃሴ* ለማየት ከፍተኛ ጥረት አደረግኩ።+ 17  ከዚያም የእውነተኛውን አምላክ ሥራ ሁሉ አጤንኩ፤ የሰው ልጆች ከፀሐይ በታች የሚሆነውን ነገር ሁሉ መረዳት እንደማይችሉም ተገነዘብኩ።+ ሰዎች የቱንም ያህል ጥረት ቢያደርጉ ሊረዱት አይችሉም። ይህን ለማወቅ የሚያስችል ጥበብ አለን ቢሉም እንኳ ሊረዱት አይችሉም።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “የአንድን ነገር ፍቺ።”
ወይም “ፍርድ።”
ወይም “ፍርድ።”
ወይም “በእስትንፋስ፤ በነፋስ።”
“ክፉዎች ክፋታቸው ሊታደጋቸው አይችልም” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “ለሥቃይ፤ ለጉስቁልና።”
ወይም “የሚያበሳጭ።”
“ሰዎች ቀንም ሆነ ሌሊት እንቅልፍ በዓይናቸው እንደማይዞር” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “የሚከናወነውን ሥራ።”